“ባለስልጣኑን ሁሉም ሰው እንዲያውቀው በቂ ግንዛቤ ተፈጥሯል ብዬ አልወስድም” – አቶ ሚካኤል ተክሉ የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር

18

በአዋጅ ከተቋቋመባቸው ዋና ዋና አላማዎች መካከል የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማጎልበት የገበያ ግልጽነትን በማሳደግ ጸረ – ውድድር የሆኑ የንግድ አሰራሮችንና ተገቢ ያልሆኑና አሳሳች የንግድ ተግባራትን በመከላከልና ፍትሃዊ ውሳኔ በመስጠት የሸማቹንና የንግዱን ማህበረሰብ መብትና ጥቅም ማረጋገጥ ናቸው። ከዚህ አንጻር ተቋሙ ያለበት ደረጃ ምን ይመስላል? ኃላፊነቱንስ እንዴት እየተወጣ ነው በሚሉትና ሌሎችም ተጓዳኝ ጉዳዮች ዙሪያ አዲስ ዘመን ከዋና ዳይሬክተሩ አቶ ሚካኤል ተክሉ ጋር ቃለ ምልልስ አድርጋ እንደሚከተለው ይዛ ቀርባለች።

አዲስ ዘመን ፦ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በአዋጅ ተቋቁሞ ወደ ስራ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ምን ዓይነት ኃላፊነቶችን ተወጣ? በመወጣት ላይም ነው?

አቶ ሚካኤል ፦ የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን የተቋቋመው በአዋጅ ቁጥር 813 /2006 ሲሆን ከዛ በፊትም በሌላ አዋጅ ተቋቁሞ ነበር። በኋላ ግን በዚህ እንዲሻሻል ሆኖ ቀጥሏል። ባለስልጣኑ ሁለት ትልልቅ የስራ ኃላፊነቶች ያሉበት ሲሆን አንደኛው የንግድ ስርዓቱ በውድድር ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ማስቻል፣ የነጻ ገበያ መንፈሱም ውድድር የተሞላበት እንዲሆን ማድረግ ነው። ጸረ ውድድር ተግባራት እንዳይፈጸሙ ለመከላከል ህብረተሰቡን የማስተማርና ግንዛቤውን የማሳደግ ስራዎችም ይገኙበታል። እነዚህ ሁኔታዎች ተጥሰው ሲገኙ ደግሞ በህግ ተጠያቂ ማድረግ የሚቻልበትን መንገድ መዘርጋት የስራው አካል ነው።

ሁለተኛው ከሸማቾች ጥበቃ አንጻር የተዘረዘሩ መብቶች እንዴት መከበር አለባቸው የሚል ሲሆን በዚህም የሸማቾች መብቶች ተጥሰው ሲገኙ ተግባሩ ወንጀል በመሆኑ እንዲጠየቁ የማድረግ ስራ ይገኝበታልⵆ ሆኖም ከሁለት ዓመት በፊት ጀምሮ በወንጀል መጠየቅ ከእኛ የስራ ሀላፊነት ውስጥ በመነሳቱ አሁን እየሰራን ያለነው አስተዳደራዊ እርምጃን የሚጠይቁ ስራዎችን ብቻ ነው። የሸማቾችን መብት ከመጣስ አንጻር ወንጀል ሆነው የሚገኙትን ፌዴራል ፖሊስ ይመረምራል ክሱን ደግሞ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ይመሰርታል።

አዲስ ዘመን ፦ ባለስልጣኑ የንግድ ስርዓቱ በውድድር እንዲመራና የሸማቾች መብት እንዳይጣስ የሚሰራ ከሆነ በተለይ የሸማቹን መብት በማስከበር በኩል ምን ተሰራ?

አቶ ሚካኤል፦ ከሸማቾች መብት አንጻር ትኩረት አድርገን የምንሰራው ማስተማር ላይ ነው፤ አንዳንድ ጉዳዮች ላይ በማስታረቅ የምንወስዳቸው እርምጃዎች ይኖራሉ፤ ምንም እንኳን ተቋሙ የተቋቋመበት ዋና አላማ የሸማቹን መብት እንዳይጣስ ማድረግ ቢሆንም አሁን የወንጀል ምርመራ ስራው ስለቀረ በተቋሙ አስተዳደራዊ ችሎት ብቻ ጉዳዮች እየታዩ ውሳኔዎች ይሰጣሉ።

አዲስ ዘመን ፦ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በተሰጠው ስልጣንና ሀላፊነት ልክ እየሰራ ነው ማለት ይቻላል? ካልሆነስ ለምን?

አቶ ሚካኤል፦ እኔ አሁን ልነግርሽ የምችለው የዚህን ዓመት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ብቻ ነውⵆ የተነገረኝም እንደዛ ስለሆነ።

አዲስ ዘመን፦ አይ እኔ ሪፖርቱን ብቻ አይደለም የምፈልገው ተቋሙ ሲቋቋም ትልቅ ሀላፊነት ተሰጥቶታል፤ ከዚህ አንጻር ባለፉት 5 ዓመታት ምን ሰራ የሚለውንም ማወቅ እፈልጋለሁ?

አቶ ሚካኤል፦ ተቋሙ የተሰጠውን የስራ ሀላፊነት እንዴት ተወጣው የሚለውን በሁለት መንገድ ማየት ይቻላል ፤ የአንድ ዓመቱን ግን በዝርዝር እገልጸዋለሁ። እስከ አሁን በወንጀል ድርጊት ውሳኔ እያሰጠ እያስቀጣ ነው የመጣው።

አዲስ ዘመን፦ ጥሩ ነው ግን ያስቀጣውን በማሳያ መናገር ከተቻለ ምን ያህል ክሶችን አደራጅቶ ፍርድ ቤት ላከ?

አቶ ሚካኤል፦ እነሱ አሁንም ያለፈው ዓመት ናቸው።

አዲስ ዘመን፦ እኮ ያለፈውንስ ዓመት ቢሆን መናገር አይቻልም?

አቶ ሚካኤል ፦ እኔ የዚህን ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት ነው ትፈልጋለች የተባልኩት።

አዲስ ዘመን፦ እርስዎ እንደ ተቋም መሪነትዎ ከዓመቱ ሪፖርት ውጪ በጠቅላላው በሰራችሁት ስራ ዙሪያ መረጃ የለዎትምን?

አቶ ሚካኤል፦ እሱ ይታወቃል እንዳይረዝምብሽ ብዬ ነው። ከውድድር ጋር የሚጻረሩ ተግባራትን የፈጸሙ ከአመታዊ ገቢያቸው ከአምስት በመቶ ጀምሮ የተቀጡ አሉ። አንዳንዶቹም እስከ አሁን በይግባኝ ሂደት ላይ በመሆናቸው ስማቸውን መጥቀሱ የፍርድ ቤት አካሄድ አይፈቅድም።

አዲስ ዘመን፦ እኔ የተቋማቱን ስም አልፈልገውም፤ ግን እናንተ ሀላፊነት እንዳለበት ተቋም ምን ያህል ክሶችን አደራጃችሁ በምን ያህሉ ላይ ውሳኔ አሰጣችሁ? በቁጥር ይግለጹልኝ ነው እያልኩ ያለሁት?

አቶ ሚካኤል፦ ባለፈው ዓመት ለምሳሌ ከ 78 ያላነሱ ድርጅቶች ተቀጥተዋል፤ ምክንያቱ ደግሞ አንድን ምርት በሚሸጡበት ጊዜ ሌላ ምርት ጨምራችሁ ካልገዛችሁ አንሸጥም። የእኔን ምርት ብቻ ነው የምታሳየው በማለታቸው የተቀጡ አሉ፤ ይህ ሂደት ደግሞ የንግድ ውድድርን ስለሚጎዳ ተከሰው እንዲቀጡ ሆነዋል። አሳሳች ማስታወቂያን በማስነገራቸው የተቀጡም አሉ። በሌላ በኩል ካምፓኒዎች ሲዋሃዱ ከባለስልጣኑ ማግኘት የሚገባቸውን ፍቃድ ካልጠየቁ ተጠያቂ ይሆናሉ።

አዲስ ዘመን፦ በአዋጅ ቁጥር 813/2006 ፤ 22/10 እና 43 /2 ላይ ነጋዴው በተለይ ለሰው ጤና ጎጂ የሆኑ ፣ ምንጫቸው ያልታወቀ፣ የጥራት ደረጃቸው የወረደ፣ የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈ፣ ከባዕድ ነገሮች ጋር የተቀላቀሉና ሌሎችንም ምርቶች ለገበያ የሚያቀርቡትን አካላት እንድትቆጣጠሩ ስልጣን ሰጥቷችኋል፤ አሁን እንደሚታየው ደግሞ ይህ ጉዳይ በአገሪቱ በሰፊው መነጋገሪያ ሆኗልና ስራችሁን ከዚህ አንጻር መዝነው ይንገሩኝ እስቲ?

አቶ ሚካኤል፦ የወንጀል ሂደቱ ወደ ፌዴራል ፖሊስና አቃቤ ህግ ከመሄዱ ከሁለት ዓመት በፊት ይሰራ የነበረ ነው። ጠቅላይ አቃቤ ህግ ከተቋቋመ በኋላ ጉዳዩ እኛን አይመለከትም፤ ከምግብ ጋር ባዕድ ነገር መቀላቀልን በተመለከተ ፌዴራል ፖሊስ ነው የሚያጣራው፤ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ነው ውሳኔ የሚሰጥበት፤ የእኛ የስራ ሃላፊነት ማስተማር ብቻ ነው።

አዲስ ዘመን፦ የሸማቹን መብትና ደህንነት ማስጠበቅ አንዱ የስራ ሀላፊነታችሁ ከመሆኑ አንጻር ግን ከፌዴራል ፖሊስም ሆነ ከአቃቤ ህግ ጋር ተባብራችሁ መስራትስ የለባችሁም?

አቶ ሚካኤል፦ ተባብረን መስራት ይገባናል ብለን ጥቆማዎች እኛ ጋር ሲመጡ ባይመለከተንም ሰነዶቹን አደራጅተን እንልካለን።አሁን ደግሞ ለፌዴራል ፖሊስና ለአቃቤ ህግ በጋራ ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ እንድንፈራረም ደብዳቤ ጽፈናል፤ ፕሮግራም ይዘው እስከሚጠሩን ድረስም እየጠበቅን ነው። በመሆኑም ከችግሩ አሳሳቢነት አንጻር በጋራ መስራቱ ውጤት ያመጣል የሚል እምነትም አለን።

አዲስ ዘመን፦ ወደ ኋላ እንመለስና የተቋሙ አንዱ ሀላፊነት ሸማቹ ስለ መብቱ እንዲያውቅ ማስተማር ነው፤ እኔ ግን ወደ እርስዎ ጋር ስመጣ ጥቂት ሰዎችን ለማናገር ሞክሬ አንዳንዶቹ ስለ ተቋሙ አያውቁም፤ ሌሎቹ ደግሞ አለ እንዴ? ብለው ነው የጠየቁኝ ከዚህ አንጻር ተደራሽ ነን ብለው ይላሉ?

አቶ ሚካኤል፦ ባለስልጣኑን ሁሉም ሰው ያውቀዋል በቂ ግንዛቤም ተፈጥሯል ብዬ አልወስድም። ምክንያቱም ማስተማሩ ሰፊ ስራን የሚጠይቅ ነውና።በዓመት ከምንይዘው ስራ ትልቁን ቦታ የሚወስደው በየክልሉ እየዞርን የምናስተምረውና የአሰልጣኞች ስልጠና የምንሰጠው ቢሆንም ክልሎች እኛ በሰጠነው የአሰልጣኞች ስልጠና ልክ አልሰሩም፤ አብዛኞቹም እያሰለጠኑ እንዳልሆኑ ተረድተናል። ተማምነናልም፣ ከዚህ በኋላም ሰልጥነው የሚሄዱ ሰዎች ወርደው ሌላውን እንዲያሰለጥኑ እንደሚያደርጉም መግባባት ላይ ደርሰናል።

አዲስ ዘመን፦ ይህንን ተቋም ለህብረተሰቡ ለማስተዋወቅ ብሎም ሸማቹ ስለ መብትና ደህንነቱ እንዲያውቅ ለማድረግ ግን ስልጠና ብቻ ነው መንገዱ?

አቶ ሚካኤል፦ ስልጠናው አንዱ ቢሆንም የመጨረሻው ግን አይደለም። በተለያዩ የመገናኛ ብዙሀን በአዝናኝ ድራማዎች ለማስተማር እንሞክራለን። ቃለ ምልልሶችን በማድረግ እንሰራለን፤ ሆኖም እንደ ከዚህ ቀደሙ በራሪ ወረቀቶችና ሌሎችን በማዘጋጀት ማስታወቂያዎችን በማስነገር የሚሰራ ስራ ግን በመንግስት

ስለተከለከለ ማድረግ አልቻልንም። የመንግስት በጀትና አሰራሩ በሚፈቅደው ልክ ግን በሚቀጥለው ዓመትም የግንዛቤ ፈጠራ ስራውን የምንቀጥልበት ይሆናል።

አዲስ ዘመን፦ ተቋሙ ከበጀትና ከሰው ሃይል አንጻር ያለበት ደረጃ ስራውን የሚሸከም ነው ማለት ይቻላል? ካልሆነስ ለሚመለከተው አካል ማስተካከያ እንዲደረግ አቅርባችኋል?

አቶ ሚካኤል፦ ስራው እኮ በገንዘብ ብቻ አይደለም የሚሰራው፤ የበጀት ችግርም ያዘን እያልኩ አይደለም ግን እራሳችንን ለማስተዋወቅ የምንጠቀምበት አንዱ ስፖንሰር ማድረግ ተከልክለናል ነው፤ ይህም እንዲፈቀድልን በተደጋጋሚ ጠይቀናል ግን ወጥ የሆነና ለሁሉም ተቋማት የተላለፈ መመሪያ ስለሆነ ሊስተካከል አልቻለም።

አዲስ ዘመን፦ ይህ ማለት እኮ ገንዘብ ስለሌላችሁ እራሳችሁን በሚፈለገው ልክ ማስተዋወቅና ለሸማቹ ህብረተሰብ መቆም አልቻላችሁም ማለት አይደለም?

አቶ ሚካኤል፦ አንዱ እንቅፋት የሆነብን ነገር ከክልል የምንጠራቸውን ሰዎች ባለው የአበል አሰራር እዚህ ድረስ መጥተው መሳተፍ አለመቻላቸው ነው። በዚህ ምክንያት ሲጠሩም የሚቀሩ አሉ። መንግስት በቀጣይ ያየዋል ብለን እናስባለን።እኛ በዚህ ልክ እነሱን ማስተናገድ አልቻልንም ብለን ቁጭ አላልንም እራሳችንን ክልል ላይ በመሄድ እያሰለጠንን ነው።

ከማሰልጠን ባለፈ ቀጣይ የሆኑ ስራዎችን የሚጠይቅ በመሆኑ ተማሪዎች ገና ከአንደኛ ደረጃ ጀምረው እንዲማሩት ትምህርት ሚኒስቴር በሚያዘጋጀት የትምህርት ስርዓት (ካሪኩለም) ውስጥ እንዲካተት ለማድረግ እየተነጋገርን ነው። ይህ ደግሞ ህብረተሰቡ ለዘለቄታው በተገቢው ሁኔታ ግንዛቤው እንዲያድግ ልጆችም ገና ከጅማሬው በስርዓት ታንጸው እንዲያድጉ ያደርጋል።

አዲስ ዘመን፦ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ሲቋቋም በመንግስትም በህዝብም ዘንድ ትልቅ እምነት የተጣለበት ተቋም ነበር፤ ይህንን ሀላፊነቱን ተወጥቷል ይላሉ?

አቶ ሚካኤል፦ ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው፤ ግን መለኪያው ምንድን ነው? ይህ ተቋምስ በአንድ ጊዜ የንግድ ውድድር ስርዓቱን ጤናማ እንዲያደርግ፣ የሸማቹን መብት እንዲያስከብር ታስቦ ነው እንዴ የተቋቋመው ? እንደዛ ቢሆን ኖሮ ለአንድ አመት ሰርቶና ውጤቱ ተገምግሞ እንዲዘጋ ነበር የሚሆነው፣ ስራው ሂደት ነው፣ ስርዓት ነው። በየወቅቱ እየተከታተልን የምንሰራበትና በየወቅቱ የሚያጋጥሙ ችግሮች የሚፈቱበት ነው፤ ተቋሙ ባለው የሰው ሃይል ደግም እየሰራ ነው። ዘንድሮ ተገቢ ያልሆነ ድርጊት ፈጽመዋል ባልናቸው ላይ የተጠያቂነትን እርምጃ ወሰድን ስንል የዘንድሮው የአምናና ካቻምናው ተደማምረው ያመጡት ውጤት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።ከዚህ አንጻር ተቋሙ ሁኔታዎችን በአንድ ጊዜ እንዲለውጥ ተብሎ የተቋቋመ ባለመሆኑ ለውጡንም ቶሎ መጠበቅ አይቻልም።

ለምሳሌ የንግድ ውድድርና የሸማች መብቶች የሚመለከቱ ስራዎች ምንጫቸው ግለሰቦች ናቸው በእያንዳንዱ ቤትና ሱቅ ፖሊስ ማስቀመጥ ደግሞ አይቻልም። ቢቀመጥም እንኳን አስተሳሰባችን ካልተስተካከለ ወደ ስርዓት መምጣቱ በጣም አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፣ በመሆኑን እያንዳንዱ ሰው ለሰዎች ጤና ጎጂ የሆነ ባዕድ ነገር ፈጸምኩ ብሎ ሲያስብ ከዚህ ነገር ምንድን ነው የምጠቀመው ተመልሶስ ማንን ነው የሚጎዳው ማለት መቻል አለበት።

በውድድሩም በኩል ጸረ -ውድድር ተግባር ከፈጸመ እነዚህ ጉዳዮችም ተመልሰው እኔኑ ነው የሚጎዱኝ ብሎ ማሰብ ሲጀምር ነው ሰርዓት እየያዘ የሚመጣው፣ ይህ ተቋም ወጣ ብለው የሚታዩ ጥቂት ነገሮች ላይ እርምጃ በመውሰድ ሊከላከል ይችል ይሆናል እንጂ በየጓዳው የሚሰሩ ህገወጥ ተግባራትን ሁሉ ያስቆማል ማለት አይደለም። ይህ ማለት ደግሞ ህገ ወጥነት እንዳይንሰራፋ ያደርግ ይሆናል እንጂ ችግሩን ሙሉ በሙሉ አይቀርም እንደማለት ነው።

አዲስ ዘመን፦ ግን ባለፉት አምስት ዓመታት የተለየ ተዓምር መስራት ባይቻል እንኳን በመሰረታዊ ችግሮች ላይ ስርዓት ማስቀመጥ አይቻልም ነበር?

አቶ ሚካኤል፦ ወደ ስርዓት የተገቡ ነገሮች አሉ፤ ለምሳሌ ይህንን ካልገዛህ ሌላ ምርት አታገኝም በማለት ልክ እንደ መብት ይታዩ የነበሩ ነገሮች ላይ እርምት ተወስዷል። ምናልባት እነዚህ ሁኔታዎች ሲስተካከሉ ስለማይታዩ ነው። አሁንም እንደዚህ የሚሉ ካሉ ለመያዝ እየፈለገን ነው። ሌላው የማይሰራ እቃ ሸጦ መልስ ሲባል እንደ ቀድሞ አልመልስም የሚል ነጋዴ ቀንሷል። በዚህ መልክ መጥተው በድርድር የተጠናቀቁ ከ 50 ያላነሱ ጉዳዮችም አሉን።

ይህም ቢሆን ግን በሁሉም የገበያ አካባቢዎች ላይ ያሉ ችግሮች ተፈተዋል ስርዓት ይዘዋል ማለት አይደለም ገና ብዙ ይቀራል። ግን መሻሻሎች እንዳሉና ህብረተሰቡም መብቱን እያወቀ ያለበት ሁኔታ እንዳለ ግን መረዳት ይቻላል።

ይህ ተቋም ከመቋቋሙ በፊት አንዳንድ ምርቶችን ጥቂት ነጋዴዎች እያከማቹና በገበያው ላይ እጥረት እየፈጠሩ መልሰው ዋጋ በመጨመር የሚሸጡበት ሁኔታ ነበር ፤ አሁን ግን ሁኔታው ከስርዓት በወጣ መልኩና በጥጋብ የሚኬድበት አካሄድ ቀርቷል። ሆኖም አሁንም በድብቅ አይሰራም ለማለት ግን አይቻልም። ጎልተው የማይታዩት ግን ተጠራቅመው የቆዩት ችግሮች መፍትሔ ካገኙት በላይ በመሆናቸው ነው።

አዲስ ዘመን፦ በተለይ አሁን እንዳለንበት ሁኔታ ኑሮ ሲወደድ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የከተማው ንግድ ቢሮም እንዲሁም ሌሎች ይመለከተናል የሚሉ አካላት ገበያውን እያረጋጋን ነው ህገ ወጦችን እየያዝን የንግድ ቤታቸውንም እያሸግን ነው፤ የሚሉ መረጃዎችን ይለቃሉና የተቋሙ ተሳትፎ ምንድን ነው?

አቶ ሚካኤል ፦ እዚህ ላይ በተለይ የዋጋ ማረጋገት ስራን በተመለከተ ተከታታይ ስራዎችን ስንሰራ ነበር፤ በዚሁ አጋጣሚ መግለጽ የምፈልገው እኛን ዋጋ ንረትን ተቆጣጣሪ አርድጎ የመረዳት ክፍተት አለ። የእኛ ተቋም ዋጋ ተቆጣጣሪ አይደለም። ለምሳሌ አዋጁ ላይ እንደተቀመጠው በስምምነት ዋጋ መጨመርን በተመለከተ እኛን ይመለከተናል። ስለዚህ ትልልቅ ድርጅቶችና ካምፓኒዎች ተስማምተው ዋጋ ሲገድቡ፣ ምርት ቀንሰው ወይም ሰብስበው በገበያው ላይ መጨናነቅ በሚፈጥሩበት ጊዜ ይመለከተናል። ሆኖም እከሌ በዚህ ምርት ላይ በአላስፈላጊ ሁኔታ ይህንን ያህል ገንዘብ ጨምረሃል ብለን ለመከታተል ህጉ አይፈቅድልንም።

አሁን ላይ ግን ይህንን ህግ እንዲቀየር አንደገና እያዘጋጀነው ነው። በዚህ አዋጅ ላይ በተለይም መንግስት ቢያጸድቀው ይጠቀማል ብዬ የማስበው ለምሳሌ” ያለምንም በቂ ምክንያት ዋጋ ከጨመረ የሚል አለ ” ነጋዴው ደግሞ ይህን ይህንን ምክንያት አድርጌ ጨመርኩ ነው የሚለው። በዚህ ምንያትም ሲከሰስ ነጻ ይወጣል። ስለዚህ ክፍተት አለው ማለት ነው። በዚህ በኩል ያለው የህግ ክፍተት እንኳን መስተካከል ከቻለ ለውጦች ይመጣሉ።

ሌላው ሊሻሻል ይገባዋል የምለው መሰረታዊ በሆኑና ህብረተሰቡን በጣም በሚጎዱ ምርቶች ላይ የትርፍ ህዳግ መንግስት ያስቀምጥ የሚል ነው። በዚህ መሰረት እንዲያተርፍ ከተቀመጠለት በላይ የሄደ አካል በህግም ተጠያቂ ለማድረግ ቀላል ይሆናል። ሆኖም ይህንን ህግ ደግሞ በሁሉም ምርቶች ላይ ማድረግ አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የገበያ ሰንሰለቱን በተመለከተና ሌሎችንም ጥናቶች ያጠናል ይህ ደግሞ ግብዓት የሚሆነው የተለዩዩ ክፍተቶችን ለመሙላት ነው። በቀጣይ ግን እንዲሻሻል የምንፈልገው አዋጅ ደንብም ይኖረዋል ፤ አዋጁ መሻሻሉ ደግሞ መንግስት ከተቋሙ ከሚጠብቀው ውጤት አንጻር አላሰራ ያሉ ሁኔታዎችን ይቀርፋል። እነሱ ተቀረፉ ማለት ደግሞ ተቋሙም ሀላፊነቱን በአግባቡ ተወጣ እንደማለት ነው።

በአጠቃላይ ስራችንን ለመስራት ህጉ ክፍተት ቢኖረውም ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር ተባብረን እየሰራን ነው። ጎን ለጎንም ካምፓኒዎችን ድርጅቶችን ነጋዴዎችን የማወያየት ስራም እንሰራለን። ለምሳሌ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች ዘንድሮ በምርቶቻቸው ላይ የዋጋ ጭማሪ ለማድረግ አስበው ነበር ፤ነገር ግን እኛ ስናነጋግራቸው ባለበት እንዲቀጥል አደርገዋል፣ ብረትም በተመሳሳይ ነው።

አዲስ ዘመን፦ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ግን መንግስትንና ሸማቹን ህብረተሰብ እያገዘ ነው ብለው ያስባሉ?

አቶ ሚካኤል፦ እነዚህ ስራዎች እንግዲህ ያው መንግስትን ማገዝ ናቸው። በተሰጠው የስራ ድርሻ ልክም ሸማቹን እየረዳ ነው ብዬ ነው የምወስደው።

አዲስ ዘመን፦ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ባይኖር ኖሮ እነዚህ ችግሮች ይፈጠሩ ነበር ብለው የሚሉት ነገር ይኖር ይሆን?

አቶ ሚካኤል፦ አዎ ባይኖር ኖሮ በንግድ ላይ ያለው ስርዓት አልበኝነት ስርዓት ወይም ሲስተም ይሆን ነበር። ሌላው ሁሉንም ዘርፍ ጠቅለው መያዝ የሚፈልጉ ካምፓኒዎች ስላሉ ባለስልጣኑ ባይኖር ኖሮ ብዙ ምርቶች በአንድ ሀብታም ቁጥጥር ስር ይወድቁ ነበር። ከዚህ አንጻርም በርከት ያሉ ህገወጥ ድርጊቶች ስርዓት ሆነው ይቀጥሉ ነበር ።

ሌላው አሁን ላይ ስርዓት አልበኝነት ቢኖርም በድብቅ የሚሰራ ነው ያ የድብቅ ስራ ደግሞ ግማሾቹን እረፍት ስለሚነሳቸው ሳይወዱ በግድ ወደ ህጋዊው መስመር እየገቡም ነው።

አዲስ ዘመን ፦ የ2012 ዓም የተቋሙ እቅድ ምንድን ነው?

አቶ ሚካኤል፦ በቀጣዩ ዓመት ያቀድነው ባለን የሰው ሃይልና የገንዘብ ሀብት ልክ ነው፤ በመሆኑም ትልቁ ትኩረታችን ሸማቹ ስለ መብቶቹ ጠንቅቆ እንደረዳ ማስተማር ነው። ጎን ለጎንም ህግ የማስከበር ስራው የሚቀጥል ይሆናል።

በሌላ በኩልም ተቋሙ እንደሌላው ባለመሆኑ ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋርም መተማመን ላይ ለመድረስ እንሰራለን ከዚህ አንጻርም ያለበትን የበጀት ማነስና የሰው ሃይል ችግር ለመፍታት ይሰራል ፤ ሸማቹም ሆነ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ሲቸገሩ ብቻ የት አለ? ብለው ሊያውቁን ስለማይገባ ይህንን አስተሳሰብ ለመቀየር ስራዎች የሚሰሩበት ዓመት ይሆናል።

በቀጣይ ከአፍሪካ አገራት ጋር ከሚኖረን የንግድ ትስስር አንጻር ባለን አቅም እንዘጋጅ የሚል እቅድ ይዘናል፤ ምክንያቱም አንዱ ነጋዴ ሌላውን እንዳይውጠውና ውድድሩን እንዳይገድበው በማድረግ የተሻለ ውጤት ለማምጣት ስለሚያስፈልግ።

አዲስ ዘመን ፦ ምናልባት የዛሬ ስድስት ወር ወይም ከዛ በፊት ምን ሰራችሁ ብዬ ተመልሼ እመጣለሁና ያን ግዜ ይህንን ስራ ከግብ አድርሰን እንጠብቅሻለን ብለው ቃል የሚገቡት እኔም ለህብረተሰቡ የማደርስልዎት ነገር ካለ?

አቶ ሚካኤል፦ የእኛ ስራ ውጤቱ በአንዴ አይመጣም። 1ሺ ሰው ስናስተምር እነሱ ደግሞ ሌሎች 4ሺ ያስተምራሉ ብለን ነው የምናስበው፣ 4 ሺዎቹ ለውጥ ቢያመጡም ይህንን መለካት ደግሞ የሚታይ አይሆንም። ግን በቀጣዩ ስድስት ወር በአንዱ እቅድ ብቻ እንኳን ብንነጋገር ሰፋፊ የህዝብ ንቅናቄ መድረኮች አካሂደን እንጠብቅሻለን እላለሁ። ውጤቱ ግን ልክ አምስተኛ ክፍል ላይ ደረስኩ ብሎ ትምህርት እንደማያቆም ተማሪ ሁሉ በየጊዜው መስራት የሚጠይቅና በተሰራው ልክም ውጤቱ የሚታይ ነው።

አዲስ ዘመን ፦ አመሰግናለሁ።

አቶ ሚካኤል፦ እኔም አመሰግናለሁ።

አዲስ ዘመን  ረቡዕ ጳጉሜ 6/2011

እፀገነት አክሊሉ