ከወራሽነት መንቀል እና ሕጋዊ ውጤቱ

4

ጥቂት ስለውርስና ኑዛዜ

በአገራችን ሕግ ውርስ በሁለት ዓይነት ሥርዓቶች ይፈጸማል – በኑዛዜ እና ያለኑዛዜ፡፡ ከስያሜያቸው መረዳት እንደሚቻለው በኑዛዜ የተደረገ ውርስ የሚፈጸመው በኑዛዜው መሰረት ነው፡፡ ያለኑዛዜ ውርስ የሚባለው ደግሞ ሟች ከመሞቱ በፊት ንብረቱን በተመለከተ ምንም ዓይነት ኑዛዜ ሳይተው የቀረ እንደሆነ ውርሱ በሕጉ በተቀመጠው መሰረት ያለኑዛዜ (ለሕጋዊ) ወራሾቹ የሚተላለፍበት ሂደት ነው፡፡

አንድ ሰው ኑዛዜ ሳይተው ቢሞት ንብረቱን ማንና እንዴት ይወርሰዋል ለሚለው ጥያቄ ሕጉ ዝርዝር መልሶችን አስቀምጧል፡፡ በፍትሐብሔር ሕጉ አንቀጽ 842 እና ተከታታዮቹ ድንጋጌዎች በግልጽ ሰፍሮ እንደምናነበው ሳይናዘዝ የሞተ ሰው የመጀመሪያ ደረጃ ወራሾች ልጆቹ ናቸው፤ ለሰው እንደትዳር አጋሩ ሁሉ ከልጆቹ የሚቀርበው ሌላ ዘመድ የለውምና፡፡ የሟቹ ልጆች ወይም ከልጆቹ አንዱ ሞተው እንደሆነና ወደታች የሚቆጠሩ ተወላጆች ያሏቸው ከሆነ ልጆቻቸውም በእነሱ ምትክ ሆነው ይወርሳሉ፡፡

ሟቹ ወደታች የሚቆጠሩ ተወላጆች የሌሉት እንደሆነ ደግሞ አባትና እናቱ ሁለተኛ ደረጃ ወራሾች ተብለው ንብረቱን ይከፋፈላሉ፡፡ አባት ወይም እናት ከሟቹ አስቀድመው ሞተው ከሆነ ልጆቻቸው (የሟች እህትና ወንድሞች) ወይም የእነርሱ ልጆች ተተክተው ይወርሳሉ፡፡ የሟች አባትና እናት ወይም የነሱ ልጆች ወይም ተወላጆቻቸው ከሌሉ ደግሞ አያቶች ሶስተኛ ደረጃ ወራሾች ይሆናሉ፡፡ እነዚህም የሌሉ ከሆነ ቅድመ አያቶቹ አራተኛ ደረጃ ወራሾች ሆነው ሟችን ይወርሱታል፡፡ እነዚህ ሁሉ ከሌሉ ደግሞ መንግስት ንብረቱን ይወርሰዋል፡፡

የኑዛዜ ውርስ ሁለተኛው የውርስ ዓይነት ነው፡፡ በአግባቡ የተጠናቀረ መረጃ ማቅረብ ባይቻልም የኢትዮጵያ ሕዝብ በአብዛኛው ውርስን በኑዛዜ የማስተላለፍ ልማድ እንደሌለው በተለያዩ ጽሁፎች ላይ ሰፍሮ እናነባለን፡፡ በዚሁ መነሻ ውርስ የሚከናወነው ከላይ በተገለጸው የወራሽነት ደረጃ አማካኝነት በተወላጆችና በወላጆች እንዲሁም ወደጎን ባለ ዝምድና (እህትና ወንድም) መካከል ነው፡፡

ያም ሆኖ በፍርድ ቤቶች ከውርስ ጋር ተያይዘው ከሚደረጉት ክርክሮች ውስጥ አያሌዎቹ ኑዛዜን የተመለከቱ ናቸው፡፡ ከኑዛዜ ለሚመነጭ ክርክር ዋነኛው ምክንያት ደግሞ ተናዛዦች ሕግን ተከትለው ኑዛዜ አለማድረጋቸው ነው፡፡ የኑዛዜ ተጠቃሚዎችም ሆኑ ያለኑዛዜ (የህግ) ወራሾች ከኑዛዜው ጋር በተያያዘ ሕጋዊ መብትና ግዴታቸውን ጠንቅቀው አለማወቃቸውም ለሙግቶች መብዛት ዓይነተኛ መነሾ መሆኑም አልቀረም፡፡ ለኑዛዜ አድራጊውም ሆነ ለወራሾች እንዲህ ወደ ክርክር መግባት መሰረታዊው አመክንዮ ታዲያ የንቃተ ሕግ አለመዳበር ስለመሆኑ መናገር ጉንጭ ማልፋት ይሆናል፡፡

ለዚህም ነው እጅግ ሰፊ ከሆነው የኑዛዜ ጉዳይ ውስጥ ከወራሽነት ስለመንቀል የሚለውን ጉዳይ ብቻ እንደ ሰበዝ በመምዘዝ ግንዛቤ ለማስጨበጥ የወደድኩት፡፡

ከወራሽነት መንቀል

ኑዛዜ የሟቹ ጥብቅ የሆነ ራሱ የሚፈጽመው ሕጋዊ ድርጊት ነው፡፡ ይህ ማለት ሟቹ አንድን ሌላ ሰው በእሱ ቦታ ሆኖ ወይም በስሙ ኑዛዜ እንዲያደርግ፣ እንዲለውጥ ወይም እንዲሽር ስልጣን (ውክልና) ሊሰጠው አይችልም ማለት ነው፡፡ በሕጋችን ኑዛዜ ሶስት ዓይነት ነው። አንደኛው በግልጽ የሚደረግ ኑዛዜ ሲሆን ይኸውም ተናዛዡ እየተናገረ ማናቸውም ሌላ ሰው ወይም ራሱ ተናዛዡ በምስክሮች ፊት የሚጽፈው ነው፡፡ ሁለተኛው ተናዛዡ ራሱ ኑዛዜ መሆኑን በግልጽ በማስፈር ሙሉ በሙሉ ብቻውን የሚጽፈው የኑዛዜ ዓይነት ነው፡፡

ሶስተኛው የቃል ኑዛዜ ሲሆን አንድ ሰው የሞቱ መቃረብ ተሰምቶት የመጨረሻ የፈቃድ ቃሎቹን ለሁለት ምስክሮች የሚሰጥበት ነው፡፡ የቃል ኑዛዜን በርካታ አገራት ከሕጋቸው ያስወገዱት ሲሆን (ለምሳሌ ፈረንሳይ ከ1735 ዓ.ም. በኋላ) በኢትዮጵያ ሕግ ደግሞ በውስን ሁኔታዎች ማለትም የቀብሩን ሥነ ሥርዓት አፈጻጸምን በተመለከተ፣ እያንዳንዳቸው ከ500 ብር የማይበልጡ ግምት ያላቸው ኑዛዜዎችን ለመስጠት እና አካለ መጠን ላልደረሱ ልጆች አሳዳሪ ወይም ሞግዚትን የሚመለከቱ ትዕዛዞችን ለመስጠት ብቻ የቃል ኑዛዜ ይፈቀዳል፡፡

በየትኛውም የኑዛዜ ዓይነት ተናዛዡ በኑዛዜው ውስጥ የሚያሰፍራቸው ቃሎች በጣም ወሳኝና ሕግን የተከተሉ መሆን አለባቸው፡፡ ተናዛዡ በኑዛዜው ውስጥ አንድ ወይም ብዙ የጠቅላላ ሀብቱን ወራሾቹን መግለጽ፣ ልዩ የኑዛዜ ስጦታ ማድረግ፣ የቀብሩን ሥነ ሥርዓት የሚመለከቱ ትዕዛዞችን መናገር ወይም መጻፍ እንዲሁም አንድ የበጎ አድራት ድርጅት ወይም የንብረት አደራ ጠባቂ ማድረግ ወይም አንድ ወይም ብዙ ወራሾቹን ከወራሽነት መንቀልን የተመለከቱ ቃሎችን ሊያስቀምጥ ይችላል፡፡

ተናዛዡ በኑዛዜው ውስጥ ከሚያስቀ ምጣቸው ቃላት ውስጥ ታዲያ ቀላል ለማይባሉ ሙግቶች ምክንያት የሚሆነው ወራሾቹን ከወራሽነት መንቀልን የተመለከተው ነው፡፡ ከወራሽነት የመንቀልን ስልጣን ሕጉ ለተናዛዡ የሰጠበት ዓይነተኛው ምክንያት አንድም አውራሹ በህይወት ሳለ ጥሮ ግሮ በላቡ ጠብታ ወይም በሌላ ሕጋዊ መንገድ ያፈራው ሐብት ከሞቱ በኋላ በእነማን እጅ ይሁን የሚለውን የመወሰን ሙሉ መብት ያለው መሆኑን እውቅና ከመስጠት መነሻ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ልጆቹም ቢሆኑ ከታች በዝርዝር እንደምናየው የሱን ንብረት ለመውረስ የማያበቃ ክፉ ነገር አድርገውበት ከሆነ ምክንያቶቹን ጠቅሶ እነዚህን ልጆቹን የሚቀጣውም ከድካሙ ፍሬ እንዳይቋደሱ በመንቀል ስለመሆኑ መናገር ይቻላል፡፡

በሕጋችን ከወራሽነት መንቀል በሁለት መልኩ ይከናወናል – በግልጽ እና በዝምታ ከውርስ መንቀል፡፡ በግልጽ ቃል ከወራሽነት ስለመንቀል የሚደነግገው የፍትሐብሔር ህግ ቁጥር 937 እንደሚያመለክተው ተናዛዡ በኑዛዜው ውስጥ ጠቅላላ የውርስ ስጦታ የሚደረግለትን ሰው ሳይጠቅስ ያለኑዛዜ (በሕግ) የሚወርሱትን ወይም ከእነዚሁ አንዱን ግልጽ በሆነ ቃል ከወራሽነት መንቀል ይችላል፡፡ ይህ ሲሆን ታዲያ የተነቀሉት ወራሾች ከተናዛዡ በፊት እንደሞቱ ተቆጥረው የውርሱ ሥርዓት ይፈጸማል ማለት ነው፡፡

እዚህ ላይ ሁለት መሰረታዊ ነጥቦችን ነጣጥሎ ማየት ያስፈልጋል፡፡ የመጀመሪያው “ጠቅላላ የውርስ ስጦታ” የሚለው ነው፡፡ ጠቅላላ የውርስ ስጦታ ማለት ተናዛዡ ሀብቱን በጠቅላላ ወይም ከመላ ንብረቱ አንዱን በሙሉ ሀብትነት ለአንድ ወይም ለብዙ ሰዎች የሚያወርስበት የኑዛዜ ቃል ነው፡፡ ከዚህ የተለየ ማናቸውም ሌላ የኑዛዜ ቃል ደግሞ ልዩ የኑዛዜ ስጦታ ተደርጎ እንደሚቆጠር ከህጉ ቁጥር 912 (2) መረዳት ይቻላል፡፡ አንድ ኑዛዜ ልዩ የኑዛዜ ስጦታ መሆኑ ከተረጋገጠ ደግሞ እንደ ውርስ እዳ ተቆጥሮ የውርስ ሐብት ከመከፋፈሉ በፊት በሕጉ ቁጥር 1104 (ሠ) መሰረት የሚወራረድ እዳ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

ሁለተኛው ጉዳይ ደግሞ “ግልጽ በሆነ ቃል” የሚለው ሲሆን፤ ይኸውም ተናዛዡ ከወራሾቹ ውስጥ አንዱን ወይም ብዙ የሆኑትን በግልጽ አነጋገር ከንብረቱ የውርስ ድርሻ ሊኖራቸው እንደማይገባ አድርጎ የሚያስቀምጠው የኑዛዜ ቃል ነው፡፡

ከላይ እንደተብራራው አንድ ሰው ከኑዛዜ የሚነቀለው በግልጽ በሰፈረ ቃል አማካኝነት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ወደታች ለሚቆጠሩ ተወላጆች ከውርስ የመነቀል ሥነሥርዓት ደግሞ ሕጉ ልዩ ድንጋጌ አስቀምጧል፡፡ ይኸውም ተናዛዡ ከውርስ ለመንቀል የደረሰበትን ምክንያት በኑዛዜው ውስጥ ካልገለጸ በቀር ልጁን ወይም ወደታች የሚቆጠር ተወላጁን (የመጀመሪያ ደረጃ ወራሾቹን) ከውርስ ቢነቅል እንደማይጸና ሕጉ አስቀምጧል፡፡ ስለዚህ ለመንቀል ያበቃውን ምክንያት በግልጽ ማስቀመጥ ይገባዋል ማለት ነው፡፡ ሕጉ ይህንን ግዴታ በተናዛዡ ላይ በማስቀመጥ የተወላጆችን መብት የጠበቀላቸው መሆኑን እንገነዘባለን፡፡

እዚሁ ልጆችን ከወራሽነት ስለመንቀል ላይ ግንዛቤ ሊያዝበት የሚገባው ጉዳይ ምናልባት ክርክር ተነስቶ እንዲመለከተው የቀረበለት ዳኛ ተናዛዡ በኑዛዜው ያስታወቀው ከውርስ የመንቀያ ምክንያት ትክክል ወይም እውነት መሆን ያለመሆኑን መመርመር የማይችል መሆኑን ነው፡፡ ከውርስ የተነቀለው ሰውም የተነቀለበት ምክንያት ትክክል (እውነት) አይደለም ብሎ ክርክር ሊያደርግበት ተቃራኒ ማስረጃም ሊያቀርብበት አይችልም፤ የማይስተባበል የህግ ግምት ነውና፡፡

ሕጉ ይህንን ያስቀመጠበት ዋና መነሻ ደግሞ ክርክር በሚደረግበት ወቅት ተናዛዡ በህይወት የሌለ በመሆኑ ከውርስ ለመንቀል በኑዛዜው ውስጥ ያስቀመጠው ምክንያት ትክክል መሆን ያለመሆኑን የሚያውቀው እና ሊያስረዳም የሚችለው እሱ በመሆኑ ከውርስ ተነቅያለሁ የሚለውን ሰው ክርክር ብቻ አድምጦ ውሳኔ መስጠት ስለማይቻል ነው፡፡ ስለዚህ ተናዛዡ ከውርስ ለመንቀል የሰጠው ምክንያት ትክክል (እውነት) እንደሆነ ተቆጥሮ ዳኛው ግን ይህ ምክንያት ከውርስ ለመንቀል የሚያበቃ መሆን ያለመሆኑን የመመርመርና የመወሰን ስልጣን በሕግ ተሰጥቶታል ማለት ነው፡፡

እዚህ ላይ ታዲያ ከውርስ ለመንቀል የሚያበቃ ምክንያት የትኛው ነው? ለመንቀል የማያበቃ የሚባለውስ ምን ዓይነት ምክንያት ነው የሚለው ጉዳይ አከራካሪ ነው፡፡ ምክንያቱም ሕጉ በግልጽ ይሄ ይሄ ከውርስ ለመንቀል ምክንያት ይሆናል ስለማይል፡፡ በዚህ መነሻ ዳኞች በሕሊና ሚዛናቸው ምክንያቱን መርምረው ከውርስ ለመንቀል ምክንያት ይሆናል ወይስ አይሆንም በሚለው ላይ ውሳኔ ይሰጣሉ፡፡ ምክንያቱን የሚመዝኑበት መለኪያ ደግሞ ሕጋዊነቱ፣ በቂና አሳማኝነቱ ስለመሆኑ መናገር ይቻላል። “በሕይወቴ ላይ ከፍተኛ ችግር ስላደረሱብኝ ከውርስ ነቅያቸዋለሁ” የሚል የኑዛዜ ቃል በቂና አሳማኝ አይደለም፡፡

ከወራሽነት መነቀልን በተመለከተ ግንዛቤ ሊያዝበት የሚገባ ሌላ መሰረታዊ ጉዳይም በሕጉ ሰፍሮ እናገኛለን፡፡ ይኸውም አውራሹ ኑዛዜውን እያደረገ ባለበት ወቅት ኑዛዜውን ወይም በኑዛዜው ውስጥ የሰፈረን አንድን ቃል ኑዛዜ አድራጊው እንዳያጸድቀው የተቃወመውን አንድ ወይም ብዙ ወራሾች በዚህ ድርጊታቸው ምክንያት በሙሉ ወይም በከፊል ከወራሽነታቸው ነቅያለሁ ብሎ ተናዛዡ የሚያስታውቅበት የኑዛዜ ቃል ሁሉ ፈራሽ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

ከበርካታ ክርክሮች፣ የፍርድ ቤት ውሳኔዎችና ከአንዳንድ የህግ ባለሙያዎች አስተያየቶች ሳይቀር ለመረዳት እንደሚቻለው ከወራሽነት መነቀልን “ሟችን ለመውረስ ያልተገባ መሆን” (Unworthiness) ከሚባለው ጉዳይ ጋር የማምታታትና የማቀላቀል ሁኔታ ይስተዋላል፡፡ ሟችን ለመውረስ ያልተገባ መሆን ራሱን የቻለ ሰፊ የውርስ ሕግ ጽንሰ ሃሳብ ነው። በፍትሐብሔር ሕጉ ቁጥር 838 በግልጽ እንደተደነገገው አንድ ሰው ሟችን ለመውረስ የማይገባ ነው ተብሎ የወራሽነትን መብት የሚያጣው ሟቹን ወይም የሟቹን ተወላጆች ወይም ወላጆች አንዱን ወይም የሟችን ባል ወይም ሚስት አስቦ በመግደል የተፈረደበት ወይም ለመግደል በመሞከሩ የተቀጣ ከሆነ ወይም በሐሰት በመወንጀል ወይም በሐሰት ምስክርነት ከእነዚሁ ሰዎች መካከል በአንደኛው ላይ የሞት ፍርድ ወይም ከአስር ዓመት የበለጠ የጽኑ እስራት ቅጣትን ለማስከተል የሚያሰጋ ሆኖ በዚሁ የሐሰት ስራው የተቀጣ ሰው ከሆነ ነው፡፡

ከዚህ ድንጋጌ ለመረዳት እንደሚቻለው ጥፋተኛ የተባለው ሰው ሟችን እንዳይወርስ ክልከላው የተቀመጠበት በሕግ ነው፤ በሕግ በተቀመጡት ምክንያቶች አማካኝነት ማለት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሰው አውራሹ በጽሁፍ ይቅርታውን ሰጥቶት ካልሆነ በስተቀር ከውርሱ ሀብት ተቋዳሽ እንዳይሆን ነው ሕጉ ራሱ ክልከላውን ያስቀመጠበት፡፡ ከውርስ መንቀል ግን በሕግ የሚደረግ ክልከላ ሳይሆን ማቹ ራሱ የሚያደርግው ክልከላ ነው፡፡

በአጭርና ግልጽ ምሳሌ ነገሩን ላስቀም ጠው፡፡ የሟች ወይዘሮ ዝናሽብዙ የልጅ ልጅ የሆነችውና ባለቤታቸውን በቢላዋ ወግታ በመግደሏ ምክንያት የእስራት ቅጣቷን ጨርሳ የወጣችው ሰናይት ወይዘሮ ዝናሽብዙን ለመውረስ የማትገባ ሰው ናት፡፡ ምክንያቱም እሳቸውን እንዳትወርስ ሕጉ ራሱ የፍትሐብሔር ክልከላና ቅጣት (Civil Sanction) ጥሎባታልና።

በተመሳሳይ ወይዘሮ ዝናሽብዙ እርጅና ተጫጭኗቸው አልጋ ላይ ከዋሉ በኋላ በአንድ ወቅት ልጃቸው አሸብር በትራስ አፍኖ ሊገድላቸው ሲሞክር ጎረቤት ደርሶ አድኗቸዋል፡፡ አሸብር ግን በዚህ አድራጎቱ ማንም የከሰሰው ሰው አልነበረም፡፡ እናትም በኑዛዜያቸው ያደረገባቸውን ምክንያት ጠቅሰው ከውርስ ሀብቱ ቤሳቤስቲን እንዳያገኝ ብለው በኑዛዜያቸው

አሰፈሩ፡፡ ይህ ከውርስ መንቀል ነው፡፡ ምንም እንኳን የመግደል ሙከራ ቢያደርግም አሸብር ተከሶ ስላልተቀጣበት በሕግ መውረስ የማይገባው ሰው ነው አይባልም፡፡ ይልቁንም በግልጽ ምክንያት ከውርስ የተነቀለ ሰው ነው ማለት ነው፡፡

ሁለተኛው ከወራሽነት የመንቀል ዓይነት በዝምታ መንቀል ነው፡፡ በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 939 እንደተመለከተው ዘመዶቹ የሁለተኛ ደረጃ (አባት፣ እናት ወንድም እህት ወይም የእነሱ ተወላጆች)፤ የሶስተኛ ደረጃ (አያቶች) ወይም የአራተኛ ደረጃ (ቅድመ አያቶች) ወራሾች ሆነው ተቃራኒ የኑዛዜ ቃል ከሌለ በቀር የጠቅላላ የኑዛዜ ስጦታ ማድረግ የእነዚህን የሟችን ዘመዶች ወራሽነት መንቀሉን ያስከትላል፡፡ ይህ ማለት አንድ ተናዛዥ ሀብቱን በጠቅላላ ወይም ከመላ ንብረቱ አንዱን በሙሉ ሀብትነት ለአንድ ወይም ለብዙ ሰዎች በመስጠት የተናዘዘ እንደሆነ ሁለተኛ፣ ሶስተኛ እና አራተኛ ደረጃ ወራሾቹን ከወራሽነት በዝምታ ነቅሏቸዋል ማለት ነው፡፡

ይህ ግን አሁንም ለመጀመሪያ ደረጃ ወራሾቹ (ልጆችና ተወላጆቻቸው) ተፈጻሚነት እንደማይኖረው መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ወራሾችን በዝምታ ከውርስ መንቀል አይቻልም፡፡ ይልቁንም ተናዛዡ ልጁን ከውርስ መንቀሉንም ሆነ ከወራሽነት ለመንቀል ያበቃውን ምክንያት በግልጽ ማስቀመጥ የግድ ይለዋል ማለት ነው፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ግን ሟቹ ወደታች የሚቆጠሩ ተወላጆቹን ከወራሽነት በግልጽ ያልነቀላቸው እንደሆነ በኑዛዜው የጠቅላላ ስጦታ የተደረገለት ሰው እንደሟች ልጅ ተቆጥሮ ከእነዚሁ ወደታች ከሚቆጠሩ የሟቹ ተወላጆች ጋር በውርሱ ተካፋይ እንደሚሆን ህጉ ደንግጓል፡፡

እዚህ ላይ አንድ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት እልባት ያገኘ ክርክርን በምሳሌነት እናንሳው፡፡ ተናዛዧ ወይዘሮ በአዲስ አበባ ከተማ ያላቸውን ቤት ለእህታቸው የልጅ ልጅ በኑዛዜ ከሰጡ በኋላ፤ የማህጸናቸው ፍሬ ለሆነው ልጃቸው ደግሞ 100 ብር ብቻ እንዲሰጠው ተናዝዘው በሞት ይሰናበታሉ፡፡ ልጅ ታዲያ እናቴ ያለአግባብ ከውርስ ነቅላኛለችና ኑዛዜው ፈራሽ ሆኖ የሚገባኝን ላግኝ በሚል ለከተማዋ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ክስ ያቀርባል፡፡ ፍርድ ቤቱም ኑዛዜው በሕጉ አግባብ የተደረገና ተናዛዥም ለልጃቸው 100 ብር የተናዘዙ በመሆናቸው ከውርስ ነቅለውታል አያሰኛቸውም በማለት መዝገቡን ዘግቶ አሰናበተው፡፡ ጉዳዩን በቅደም ተከተል ለከተማዋ ይግባኝ ሰሚና ሰበር ችሎት በይግባኝ ቢያቀርብም የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ ጸናበት፡፡

በፍጻሜው ታዲያ ልጁ ዶሴውን ሸክፎ ለፌዴራሉ ሰበር ችሎት ጉዳዩን አቀረበው። ችሎቱም በውሳኔው ሟች ተወላጅን ከኑዛዜ ለመንቀል የሚችለው በኑዛዜው ውስጥ በግልጽ በሰፈረ ቃል አማካኝነት ከውርስ ለመንቀል የደረሰበትን ምክንያት በመግለጽ መሆን እንደሚገባው፤ ይሁንና ሟች ልጃቸውን በግልጽ በምክንያት ከውርስ አለመንቀላቸውን፤ ይልቁንም ሟች መኖሪያ ቤታቸውን ለእህታቸው የልጅ ልጅ መናዘዛቸውና ለልጃቸው 100 ብር ብቻ መስጠታቸው ልጃቸውን ከውርሱ በተዘዋዋሪ በዝምታ የነቀሉት መሆናቸውን እንደሚያሳይ፤ ልጅ ደግሞ በዝምታ ከውርስ ሊነቀል የማይገባው መሆኑን በመጥቀስ በሕጉ መሰረት በኑዛዜ ጠቅላላ ስጦታ ከተደረገለት የሟች የእህት የልጅ ልጅ ከሆነው ጋር እኩል ቤቱን እንዲካፈል በማለት ወስኗል፡፡

ከዚህ የምንረዳው መሰረታዊ ቁም ነገር ታዲያ የመጀመሪያ ደረጃ ወራሾችን በዝምታ ከውርስ መንቀል እንደማይቻልና ይልቁንም ተናዛዡ ልጁን ከውርስ መንቀሉንም ሆነ ከወራሽነት ለመንቀል ያበቃውን ምክንያት በግልጽ ማስቀመጥ እንደሚገባው ነው፡፡

በደህና እንሰንብት!

አዲስ ዘመን  ረቡዕ ጳጉሜ 6/2011

ከገብረክርስቶስ