የማህበሩ ቅሬታ ከመግለጫ እስከ ፍርድ ቤት

10

የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን «በኢትዮጵያ አሁን ያለው የሊግ አደረጃጀት በፋይናንስ ረገድ ክለቦች ላይ ያለው ተጽዕኖ ምንድነው?» በሚል ርዕስ አንድ ጥናት አስጠንቶ ነበር። የፌዴሬሽኑ ጥናት እንዳመለከተው፤ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሚገኙት አጠቃላይ ክለቦች በየዓመቱ ሁለት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር ወጪ ያደርጋሉ። ክለቦቹ ይህንን ገንዘብም ለተጫዋቾች ወርሃዊ ደመወዝ፣ ለምግብ፣ ለመኝታ፣ ተዟዙሮ ለመጫወትና ለትራንስፖርት ወጪ እንደሚያወጡም ገልጿል።

ከህዝብ፣ ከግብር ከተሰበሰበ ገንዘብ፣ ከክልል መስተዳድሮች በሚሰጥ በጀት ያለ ተጠያቂና ውጤት ተኮር ዓላማ ለተጫዋቾች የሚወጣው በሚሊየኖች የሚቆጠር ገንዘብ እጅጉን ያስደነግጣል። የክለቦቹ ገደብ አልባ ወጪ በብዙ መልኩ አነጋጋሪ በመሆን ለዓመታት የተሻገረ ሲሆን፤ ብሄራዊ ፌዴሬሽኑ ለዚህ ጉዳይ ልጓም ይሆናል ያለውን መፍትሄ አመላክቷል።

ባሳለፍነው ነሐሴ 3 ቀን 2011 ዓ.ም የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ የክልል ስፖርት ቢሮ ኃላፊዎችና የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች አመራሮች በተገኙበት ቢሾፍቱ በተደረገው ጉባዔ ለዚሁ ችግር መፍትሄ የሚያመጣ ውሳኔ መተላለፉ ይታወሳል።

ፌዴሬሽኑ በዚህ ውሳኔው የተጫዋቾች ደመወዝ ከ50 ሺህ ብር በላይ እንዳይሆን ህግ አውጥቷል። ይህ መመሪያ ጸድቆ ተግባር ላይ ቢውልም ከወዲሁ የተቃውሞ ድምጾች እየተሰሙበት ይገኛሉ። የኢትዮጵያ ፕሮፌሽናል ፉት ቦለር አሶሴሽን በውሳኔው ተገቢነት ላይ ጥያቄን ካነሱት አካላት መካከል ይጠቀሳል። ማህበሩ ብሄራዊ ፌዴሬሽኑ ውሳኔውን ባስተላለፈ ማግስት ውሳኔው ተገቢነት እንደሌለው በመግለጽ ቅሬታውን ሲያሰማ ቆይቷል። ከሰሞኑ መመሪያው የተጫዋቾችን ሰብአዊ መብት የሚነካ በመሆኑ ብሄራዊ ፌዴሬሽኑን ፍርድ ቤት ለማቆም መሰናዶ መጀመሩን አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ፕሮፌሽናል ፉት ቦለር አሶሴሽን ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ እንደነገሩን ፤ ማህበሩ ለዚህ ውሳኔ የበቃው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በተደጋጋሚ ደብዳቤዎች ቢላኩለትም ምላሽ ባለመስጠቱ ነው።

የኢትዮጵያ ፕሮፌሽናል ፉት ቦለር አሶሴሽን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በጉዳዩ ላይ ብሄራዊ ፌዴሬሽኑ ምን መሰረት ይዞ ውሳኔ እንዳሳለፈ አቶ ግርማ አስረድተዋል። «ብሄራዊ ፌዴሬሽኑ በመጀመሪያ ደረጃ የተጫዋቾች የደመወዝ ጣሪያ መመሪያ ሲያወጣ የራሱን መመሪያና የፊፋን መተዳደሪያ ደንብ የጣሰ እንደሆነ ያምናል ። መስከረም 27 ቀን 2004 ዓ.ም. በወጣው የፌዴሬሽኑ መተዳደሪያ ደንብ በአንቀጽ አምስት የአባላት የጋራ ጥቅም እንዲሁም በአንቀጽ 11፣ 46 እና 47 የአባላት መብቶችና የዓለም አቀፍ የስፖርት ግልግል ፍርድ ቤት ከሚከተሉት ሕጋዊ አሠራር ያፈነገጠ ነው» ብለዋል።

ፕሬዚዳንቱ ብሄራዊ ፌዴሬሽኑ ውሳኔውን ያስተላለፈው ከስፖርት ኮሚሽን ጋራ በአብሮነት መሆኑን አንስተዋል። ስፖርት ኮሚሽን በብሄራዊ ፌዴሬሽኑ መተዳደሪያ ደንብ መሰረት የፌዴሬሽኑ አባል አለመሆኑ፣ በፌዴሬሽኑ ደንብ ላይ የተገለጸው የተጫዋቾች መብት አለመጠበቁ፣ አንቀጽ 47 ላይ የተደነገገው የስፖርት ግልግል ጉባኤ አለመተግበሩ ህጋዊ መሰረት የሚያሳጠው መሆኑን በመግለጽ ሞግተዋል። ብሄራዊ ፌዴሬሽኑ በተጫዋቾች የደመወዝ ጣሪያ መመሪያ ሃገር አቀፍና አለም ዓቀፍን መተዳደሪያ ደንብ ከመጣስ ባሻገር፤ የኢትዮጵያን የፍትሐብሄር ህግ የጣሰ ድርጊት እንደሆነም አመልክተዋል።

የፌዴሬሽኑ ውሳኔ ላይ ተቃውሞ እንዳለው የተናገረው የማህበሩ ስራ አስፈጻሚ አባል አቶ ዳዊት እስጢፋኖስ ፤ ፌዴሬሽኑ በግለሰብ ላይ እንዲህ ዓይነት ውሳኔ የማሳለፍ መብት እንደሌለው ገልጿል፡፡ ብሄራዊ ፌዴሬሽኑ የፈፀመው ድርጊት ህጋዊ መሰረት እንደሌለውና መተዳደሪያ ደንቡን የሚጥስ እንደሆነ በተደጋጋሚ በደብዳቤም ጥያቄ አቅርበው በአፋጣኝ መልስ ሊሰጥ እንዳልቻለ ያስታውሳል። ማህበሩ ብሄራዊ ፌዴሬሽኑ ለጥያቄያቸው እስከ መስከረም አንድ ቀን 2012 ድረስ መልስ ካልሰጠ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድ ከውሳኔ ላይ መድረሱን አስታውቋል።

ዳዊት እስጢፋኖስ፤ ለብሄራዊ ፌዴሬሽኑ ጥያቄያቸውን አስገብተው ምላሽ እየጠበቁ እንደሚገኙ፣ ከፌዴሬሽኑ ጋር አብሮ ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸውና አብሮ መስራት ሲባል ግን በዚህ መልኩ አለመሆኑን ጠቅሷል። የፌዴሬሽኑ ዋናው ክፍሎች ተጫዋቾች በመሆናቸውም የተጫዋቾች መብት ማስጠበቅ ይኖርበታል። የተጫዋቾችን መብት ባላከበረና ባልጠበቀ ሁኔታ፣ ሳያማክርና መግለጫ ሳይሰጥ ውሳኔ ማሳለፍ አግባብነት የሌለውና ትክክል እንደሆነ በመግለጽ የብሄራዊ ፌዴሬሽኑን ድርጊት ኮንኗል።

የማህበሩ ስራ አስፈጻሚ ሌላው አባል አቶ ኤፍሬም ወንድወሰን በበኩሉ‹‹ማህበሩ አላማው የተጫዋቾችን መብት ማስከበር ነው ፤ በተጫዋቾች ላይ ቀደም ሲል ሲደርሱ የነበሩ የተለያዩ የመብት ጥሰቶች ነበሩ ፤ አሁን ግን ከመንግስት የተሰጠን ፍቃድ በመጠቀም በተጫዋቾች ላይ የሚደርሱ የመብት ጥሰቶችን ለመከላከል እንሰራለን›› ካሉ በኋላ፤ ማህበሩ ፍቃድ ካገኘ በኋላ እርሱን ያላማከለ ውሳኔ ተወስኖ የሞራል ጉዳት መድረሱን አብራርተዋል።

አቶ ኤፍሬም «በተደጋጋሚ ለፌዴሬሽኑ ጥያቄዎች ቢቀርቡለትም ከዝምታ ውጪ ምላሽ አልሰጠም። ማህበሩ ካሉት የህግ ሰዎች ጋር ተመካክሮ ቀጣይ መንገዶችን መጓዝ እንዳለበት ከውሳኔ ደርሷል። በመሆኑም ሁላችንም ወደምንዳኝበት ፍርድ ቤት ጉዳዩን ይዘን የምንሄድ ይሆናል። ብሄራዊ ፌዴሬሽኑ ለመነጋገር በሩ ክፍት ነው። እስከ መስከረም አንድ ቀን 2012 ዓ.ም በዚሁ ፍላጎቱ የሚፀና መሆኑንና ምላሽ ከሌለ ወደ ህግ የሚጓዝ ይሆናል» ሲል ሃሳቡን ቋጭቷል።

ብሄራዊ ፌዴሬሽኑ መመሪያውን ተግባራዊ ለማድረግ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ከመግለጽ በስቀር የማህበሩን እንቅስቃሴ በተመለከተ ምንም አይነት ማብራሪያም ሆነ መግለጫ ሲሰጥ አልተደመጠም።

አዲስ ዘመን  ረቡዕ ጳጉሜ 6/2011

ዳንኤል ዘነበ