«ሐብቴ አባ መላ» – ጠንካራ የጦር መሪና ፍርድ አዋቂ

23

ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊሥ ዲነግዴ ከአባታቸው ከአቶ ዲነግዴ በተራ እና ከእናታቸው ወይዘሮ ኢጁ አመዲና በ1844 ዓ.ም ተወለዱ። የልጅነት ጊዜያቸውን በቤተሰቦቻቸው ቤት ያሳለፉት ሀብተ ጊዮርጊስ፣ እስከ 14 ዓመታቸው በአካባቢው ወግና ባሕል መሰረት ተኮትኩተው አደጉ።

በነሐሴ 1857 ዓ.ም የሸዋ ንጉሥ የሆኑት ምኒልክ ኃይለመለኮት (በኋላ ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ምኒልክ) የመጀመሪያ እቅዳቸው በዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ወደ መቅደላ ተወስደው በነበረበት ወቅት በቀሰሙት የአስተዳደር ልምድ መሰረት በአያታቸው በንጉሥ ሳህለሥላሴ ወሰንሰገድ ተጀምሮ የነበረውን የሸዋን ግዛት የማስፋፋት ሂደት ማጠናከር ነበር። ለዓላማቸው መሳካት ይረዳቸው ዘንድም ከሸዋ ግዛቶች በጦርነት የላቀ ውጤት ሊያስገኙ የሚችሉ የጦር አበጋዞችን በመመልመል ወደተለያዩ የሸዋ ግዛቶች መላክን ቀዳሚ ስራቸው አደረጉ።

ወደ ጅባትና ሜጫ አውራጃ ዘምተው የራስ ጎበና ዳጬ ከፊል ጦር ፈሊጦ ከተባለው ዋሻ አቅራቢያ በሚገኝ አንድ ቤት ውስጥ ተሸሽገው የነበሩትን ሀብተጊዮርጊሥን ማረከ።ኑሯቸውም አይተንፍሱ በተባለውና በማረካቸው ወታደር ቤት ሆነ። አቶ አይተንፍሱም ሀብተጊዮርጊሥን እንደልጃቸው አድርገው ለማሳደግና ለመንከባከብ ወሰኑ።ሀብተጊዮርጊሥ በየዕለቱ የሚያሳዩት የእርሻ ስራ ጥንካሬ፣ የጦር አወራወር ስልት እንዲሁም የፈረስ ግልቢያና የጋሻ ምከታ ብቃት አሳዳጊያቸውን አስደሰተ፤ በማኅበረሰቡም ዘንድ እንዲታወቁ አስቻላቸው።

የሀብተጊዮርጊሥ ጥንካሬ እየዳበረና አሳዳጊያቸውም ሀብተጊዮርጊሥን ለቁም ነገር ለማብቃትና ወራሻቸው እንዲሆን ለማድረግ እየተመኙ በነበረበት ጊዜ ንጉሥ ምኒልክ ‹‹የጨቦን ሰው ማርከህ ከቤትህ ያስቀመጥክ ሁሉ ወደ እኔ አምጣ፤ ሳታመጣ ቀርተህ በአውጫጭኝ የተገኘብህ እንደሆነ ርስትህን ትነጠቃለህ›› የሚል አዋጅ አስነገሩ።ወታደሮችም የንጉሳቸውን የአዋጅ ቃል በማክበር የማረኳቸውን ሰዎች እየወሰዱ ማስረከብ ሲጀምሩ አቶ አይተንፍሱም ወደ ንጉሱ ቀርበው ሀብተጊዮርጊሥን አስረከቡ። በወቅቱም የሀብተጊዮርጊሥ እድሜ 18 ነበር። አቶ አይተንፍሱም ስለሀብተጊዮርጊስ መልካም ጠባይና የላቀ ችሎታ ለንጉሱ ተናግረው ስለነበር ሀብተጊዮርጊሥ የንጉሱ ፈረስ ቤት አለቃ፣ የባልደራሱ ረዳት እንዲሆኑ ተደረገ። የሀብተጊዮርጊስ መልካም ጠባይና ችሎታ ባልደራሱን ስላስደሰተ አቶ አይተንፍሱ ከበሬታንና ሽልማትን አገኙ። ንጉሥ ምኒልክም ሀብተጊዮርጊስን የእልፍኝ አሽከሮች አለቃ አድርገው ሾሟቸው።

ወደ አንኮበር ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ-ክርስቲያን ሄደው ፊደልና ንባብ ከተማሩ በኋላ ወደንጉሱ እልፍኝ በመመለስ በቤተ-መንግሥቱ ውስጥ በባለሟልነት ስራ ተመድበው ስራቸውን ማከናወን ቀጠሉ። እድሜያቸውም ለአቅመ አዳም ሲደርስ አልታየወርቅን አገቡ። ሀብተጊዮርጊሥ በየዕለቱ በብልህነትና በአስተዋይነት የሚያሳዩት የስራ ቅልጥፍናና ብቃት ንጉሱ ይበልጥ እያቀረቧቸው አንዳንድ ወታደራዊ ነክ ስራዎችን እንዲሰጧቸው ምክንያት ሆነ። በእምባቦው ጦርነት (የንጉስ ምኒልክና የንጉሥ ተክለሃይማት ጦር ውጊያ) ላይ ያሳዩት የውጊያ ብቃት በንጉሱ ዘንድ የበለጠ ተወዳጅ እንዲሆኑ አስቻላቸው። ንጉሱ በጦርነትም ሆነ በሰላም በቁጥጥራቸው ስር ያስገቡትን ግዛት በጥንካሬያቸው የሚተማኑባቸውን ሰዎች እንዲያስተዳድሩት ይሾሙ ስለነበር ሀብተጊዮርጊሥም የጨቦንና የበቻን ግዛት እንዲያስተዳድሩ ተሾሙ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ንጉሰ ነገሥት አፄ ዮሐንስ ፬ኛ በ1881 ዓ.ም መተማ ላይ ሲሞቱ የሸዋው ንጉሥ ምኒልክ በጥቅምት 1882 ዓ.ም ንጉሰ ነገሥትነቱን ተረከቡ። በዓድዋ ጦርነት ወቅትም በስራቸው የሚገኘውን ጦራቸውን እየመሩ አኩሪ ጀብድ ፈጸሙ።

« የሀብቴ እረኛ አጋም መቁረጥ ያውቃል፣

የምኒልክን ጠላት ልመንጥረው ይላል» ተብሎ ተገጥሞላቸዋል፡፡

የንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ምኒልክ የጦር አለቃ የነበሩት ፊታውራሪ ገበየሁ በዓድዋ ጦርነት ላይ ሲሞቱ ሀብተጊዮርጊሥ ከጦርነቱ በፊትና በጦርነቱ ላይ ባሳዩት ጀግንነትና መልካም ጠባይ የፊታውራሪነት ማዕረግ ተሰጥቷቸው የጦር አለቃነቱን ኃላፊነት ተረከቡ።የውትድርና ሥርዓት እንዲሻሻል የተቻላቸውን ጥረት አድርገዋል። የጦር አመራራቸውና ሰራዊታቸው ሥነ ሥርዓትም በንጉሱ ዘንድ ክብርን አጎናፅፏቸዋል።

በአንድ ወቅት ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ግብር ጠርተው ስለነበር መኳንንቶችና ወታደሮቻቸው ወደ ግብር አዳራሹ ገቡ። ወታደሮች ሁሉ ደክሟቸው ስለነበር ውሃ መጠጣት ፈለጉ፤ ምግብ ከመመገባቸው በፊት ለውሃ ጥም ማስታገሻ ብለው የጠጡት ጠጅ አስክሯቸው ምግብ መብላት ሳይችሉ ቀሩ። የሀብተ ጊዮርጊሥ ወታደሮች ግን የቀረበላቸውን ቁርጥ መብላት ሲጀምሩ ንጉሰ ነገሥቱ ‹‹እነዚህ የማን ወታደሮች ናቸው?›› ብለው ሲጠይቁ የፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊሥ እንደሆኑ ተነገራቸው። ንጉሰ ነገሥቱም ‹‹ጎሽ ሀብተጊዮርጊሥ! ወታደሮችህን በስነ-ሥርዓት ይዘሃል። ከምግብ በፊት ባለመጠጣታቸው ምግቡን በሚገባ በልተዋል።ይህ የሚያሳየው አንተ በየጊዜው ግብር እንደምታበላቸው ነው›› በማለት አመሰገኗቸው።ፊታውራሪም በንጉሱ ዘንድ ከመኳንንቱ ሁሉ ይበልጥ ታዋቂና ብልህ ሆነው ቀጠሉ።

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ የመንግስትን ስራ ዘመናዊ ለማድረግ በማሰብ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሚኒስትሮችን ሲሾሙ ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊሥ የጦር ሚኒስትር ሆነው ተሾሙ። በጦር ሚኒስትርነታቸውም ጦሩ በትጥቅ እንዲጠነክርና በስነ-ምግባርም የታነፀ እንዲሆን ለማድረግ ይጥሩ ነበር። በስራቸው ከሚተዳደሩ ቋሚ የመንግሥት ወታደሮች በተጨማሪ የግላቸው የሆነና በእርሳቸው ትዕዛዝ ብቻ የሚመራ 17ሺ ሰራዊት ነበራቸው።

ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊሥ ከጦር መሪነት ብቃታቸው በተጨማሪ ጎልቶ የሚጠቀስላቸው ችሎታቸው ነገር አዋቂነታቸውና ብልሃታቸው ነው።ይህ ችሎታቸውም ‹‹አባ መላ›› ተብለው እንዲጠሩ እንዳደረጋቸውና ከጦር አለቃነት ኃላፊነታቸው ባሻገር ተፅዕኖ ፈጣሪ እንዲሆኑ እንዳስቻላቸውም ታሪካቸው ያስረዳል።ከዚህ በተጨማሪም ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊሥ በአስተዳደር ስራቸው ውስጥ የችኩልነት ጠባይ አልነበራቸውም። ነገሮችን በእርጋታ ማብላላትና መመልከት ባህሪያቸው ሲሆን፤ ይህንን ያጤኑትም ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በውጭና በሀገር ውስጥ የሚነሱ የዲፕሎማሲም ሆነ ሌሎች ጥያቄዎችን ወደ ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊሥ የመላክ ልማድ ነበራቸው።

በአንድ ወቅት ሁለት እንግሊዛውያን ያለፈቃድ በኬንያ በኩል ወደ ቦረና ግዛት ገብተው ስለተገኙ ተገድለው ነበር።ተቀማጭነቱ በአዲስ አበባ የነበረው የእንግሊዝ መንግሥት ቆንሲልም ‹‹ዜጎቻችን ያለአግባብ ተገድለውብናል›› ብሎ አቤቱታውን ለንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ አቀረበ። ንጉሰ ነገሥቱም ‹‹በጉዳዩ ላይ መክረን እንነግርሃለን›› ካሉት በኋላ ፊታውራሪን አስጠርተው ‹‹እነዚህ እንግሊዞች በምን ምክንያት ነው የተገደሉት?›› ብለው ሲጠይቋቸው ‹‹ጃንሆይ … ቆንሲሉን ወደ እኔ ይላኩትና አነጋግረዋለሁ፤ መልሱንም በቶሎ አሳውቃለሁ›› ብለው መለሱ።የእንግሊዙ ቆንሲልም ወደ ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዘንድ ሄዶ ‹‹ሰዎቻችን ያለአግባብ ተገድለውብናልና ደማቸው የፈሰሰበት መሬት ይሰጠን›› ብሎ ጠየቃቸው። ፊታውራሪም ‹‹ግን በሀገራችሁ ይህን መሳይ ደንብ አለ?›› ብለው ጠየቁት። ቆንሲሉም ‹‹አዎ›› ብሎ መለሰ።ፊታውራሪም በምላሹ ‹‹እንግዲያውስ መልካም! እኛም የአፄ ቴዎድሮስ ልጅ ልዑል ዓለማየሁ ቴዎድሮስ ከዚህ ሄዶ በሀገራችሁ ሞቷልና ሎንዶንን ለእኛ ስጡን፤ እናንተም ይህንን ውሰዱ›› ብለው ቃል አርቅቀው ፈርመው ‹‹በል እዚህ ላይ ፈርም›› ሲሉት ‹‹አልፈርምም›› ብሎ ሄደ። ዳግማዊ አፄ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱም ከደስታቸው ብዛት የተነሳ የፊታውራሪን አንገት አቅፈው ሳሟቸው። የእንግሊዙ ቆንሲልም በፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊሥ የነገር አካሄድ በጣም ተቆጥቶ ሴራው በመክሸፉ ተናዶ ነገሩን ደግሞ ሳያነሳ ቀረ።

በሌላ ጊዜ ደግሞ የፈረንሳይ መንግሥት ወደ ኢትዮጵያ መልዕክተኛ ልኮ ንጉሰ ነገሥቱ መልዕክተኛውን ወደፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊሥ ላኩት። መልዕክተኛውም ፊታውራሪ ዘንድ ሲቀርብ አስተርጓሚ ባለመኖሩ ከመልዕክተኛው ጋር ተፋጠጡ።በዚህ መሐል ፈረንሳይኛ ቋንቋ የሚችል አንድ ኢትዮጵያዊ አስተርጓሚ ተፈልጎ መጣ።ሁለቱም ሰላምታ ከተለዋወጡ በኋላ መልዕክተኛው ‹‹ፈረንሳይኛ ቋንቋ ያውቃሉ?›› ብሎ ጠየቃቸው። ፊታውራሪም ‹‹አላውቅም›› በማለት መለሱለት። ‹‹እንግሊዝኛስ?›› ብሎ ደግሞ ሲጠይቃቸውም ‹‹አላውቅም›› አሉት። መልዕክተኛውም ‹‹የዓለም መንግሥታት እነዚህን ሁለት ቋንቋዎች ዓለም እንዲነጋገርባቸው ወስኗል፤ እርስዎ እነዚህን ቋንቋዎች ሳያውቁ እንዴት የጦር ሚኒስትር ሊሆኑ ቻሉ? ወደ ውጭ አገራት በተላኩ ጊዜስ በምን ይነጋገራሉ?›› አላቸው።አባ መላም ወዲያውኑ ‹‹እርስዎስ አማርኛ ቋንቋ ያውቃሉ?›› ብለው ጠየቁት።‹‹መልዕክተኛውም ‹‹አላውቅም›› አለ።‹‹ትግርኛስ? ኦሮምኛስ?›› ብለው ሌላ ጥያቄ አስከተሉ። መልዕክተኛውም ‹‹እነዚህንም አላውቅም›› ብሎ መለሰ። ፊታውራሪም ‹‹ግንኙነታችን የጋራ ከሆነ እነዚህን ቋንቋዎች ካላወቁ እንዴት መልዕክተኛ ሊሆኑ ቻሉ? ወደኛስ አገር የመጡት በምን ቋንቋ ሊነጋገሩ ኖሯል›› አሉት።መልዕክተኛውም በፊታውራሪ አነጋገር ተገርሞ፣ ብልሃታቸውን አድንቆና የመጣበትን ጉዳይ ተነጋግሮ ሄደ።

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ልጅ ኢያሱ ሚካኤል (የንጉሥ ሚካኤል አሊ እና የወይዘሮ ሸዋረጋ ምኒልክ ልጅ) አልጋ ወራሻቸው መሆኑን ካሳወቁና እርሳቸውም በፅኑ ታመው አልጋ ላይ መዋል ከጀመሩ በኋላ አልጋ ወራሹ ልጅ ኢያሱ ሚካኤል አገር ‹‹ማስተዳደር›› ሲጀምሩ ከዳግማዊ ምኒልክ መኳንንቶች ጋር ከፍተኛ አለመግባባት ውስጥ ገብተው ነበር። ይህ አለመግባባት ተባብሶ በመስከረም ወር 1909 ዓ.ም ልጅ ኢያሱ ከዙፋኑ ሲሻሩ ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊሥ ሽረቱን ካቀናበሩት መኳንንቶች መካከል ዋነኛው ነበሩ።ከዚህ በተጨማሪም ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊሥ ‹‹ልጄ ከዙፋን የተሻረው አላግባብ ነው›› ብለው በተቆጡት በልጅ ኢያሱ አባት ንጉሥ ሚካኤል አሊ እና በሸዋ መኳንንት መካከል በተደረገው የሰገሌ ጦርነት ላይ ግንባር ቀደም የጦር አዝማችና የሸዋው ጦር ባለድል እንዲሆን ዋነኛው ባለድርሻ ነበሩ።

ልጅ ኢያሱ ተሽረው ዘውዲቱ ምኒልክ ‹‹ንግስተ ነገሥታት›› ተፈሪ መኮንን (በኋላ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ) ደግሞ ‹‹አልጋ ወራሽ›› ሆነው ከተሾሙም በኋላ የፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊሥ ተፅዕኖ ከፍ ያለ ነበር። መሐል ሰፋሪዎች በሚኒስትሮች ላይ አምፀው አድማ ሲያደርጉና ስልጣናቸውን እንዲለቁ ሲጠይቁ አባ መላን ግን ‹‹ከስልጣናቸው ይውረዱ›› ያላቸው አልነበረም።ይሁን እንጂ አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን ስልጣኑን ጠቅልለው ለመውሰድ ባደረጉት ጥረት ፊታውራሪ ከንግሥቲቱ ጎን መሰለፍን ምርጫቸው አደረጉ። ይህም በሕይወታቸው የመጨረሻ ዓመታት በፊታውራሪና በአልጋ ወራሹ መካከል ልዩነት እንዲፈጠር ስለማድረጉ ይነገራል።

ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊሥ መንግሥታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ከሚሰጧቸው ብያኔዎች በተጨማሪ በሌሎች ጉዳዮች ላይም የሰጧቸው ውሳኔዎች እጅግ አስገራሚና የእርሳቸውን ብልሃት የሚያሳዩ ነበሩ። ለአብነት ያህል ይህን እንመልከት። አንድ ሰው አንዲት ሴተኛ አዳሪን ‹‹ለአንድ ሌሊት ሁለት ብር እሰጣለሁ›› ብሎ ተዋውሎ ወስዶ ከቤቱ አሳደራት።ከዚያም በኋላ ስለተዋደዱ ያለጋብቻ በቤቱ ያኖራት ጀመር። ሰውየውም እርስዋ ከገባች በኋላ እድሉ ተቃንቶ ብዙ ሀብት አገኘ። ለአምስት ዓመታት ያህል አብረው ከኖሩ በኋላ ሌላ ሚስት ለማግባት ፈልጎ ሴትዮዋን ‹‹ከቤቴ ውጪ›› ይላታል።እርሷም ‹‹አብረን ለፍተን ያገኘነውን ሀብት አካፍለኝና ልሂድ›› ብትለው ‹‹በፈቃድሽ ኖርሽ እንጂ ምን የጋብቻ ውል አለሽ? አላካፍልሽም›› አላት።ሰዎቹም ተካሰው ከፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊሥ ችሎት ደረሱ።ሁለቱም ጉዳያቸውን ለችሎት አቅርበው ከተከራከሩ በኋላ ፍርድ መስጠት ተጀመረ። ፈራጆቹም ሁሉ ‹‹የጋብቻ ውል ከሌላት ንብረት መካፈል የለባትም›› ብለው ፈረዱባት።ፊታውራሪ ግን ‹‹ለስንት ዓመት አብራችሁ ኖራችሁ?›› ብለው ሰውየውን ጠየቁት።‹ ‹አምስት ዓመት ኖረናል›› ብሎ መለሰ። ‹‹ለመጀመሪያ ሌሊት የወሰድካት ጊዜ ምን ልትሰጣት ነበር የተዋዋልከው?›› አሉት። ‹‹ሁለት ብር ልሰጣት ነበር፤ እርሱንም ሰጥቻታለሁ›› አለ።ፊታውራሪም ሁኔታውን ከተመለከቱ በኋላ ‹‹አዬ ጉድ! የጋብቻ ውል ሳይኖራት ‹ንብረት አካፍለኝ› ማለቷ ተገቢ አይደለም። ነገር ግን አምስት ዓመት አኑረሃታልና ለአንድ ሌሊት ሁለት ብር በታሰበ ትከፍላለህ›› ብለው ፈረዱ።ለአንድ ሌሊት ሁለት ብር ሲታሰብ የአምስት ዓመቱ ሂሳብ ካለው ንብረት በላይ ሆነበትና ሰውየው ተቸገረ።ስለሆነም ሴትዮዋን ተለማምጦ ታረቀና የጋብቻ ውል ሰጥቶ ባልና ሚስት ሆነው መኖር ቀጠሉ።

በምክር አዋቂነታቸው፣ በፍርድ ችሎታቸውና በጦር መሪነታቸው ዝነኛ የነበሩት ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊሥ፣ ታኅሣሥ ሶስት ቀን 1919 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።የእረፍታቸው ቀን ከዳግማዊ አፄ ምኒልክ የእረፍት ቀን ጋር ተገጣጠመ (አፄ ምኒልክ ያረፉት ታኅሳሥ ሦስት ቀን 1906 ዓ.ም ነበር)፤ በዚህም ሕዝቡ ሁሉ በጣም ተገረመ።ለክብራቸውም መድፍ ተተኩሶ፣ ነጋሪት ተጎስሞ፣ አልጋ ወራሹና መኳንንቱ በተገኙበት ስርዓተ-ቀብራቸው በመናገሻ ገነተ-ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ-ክርስቲያን (አራዳ ጊዮርጊስ) በድምቀት ተፈፀመ።

ነጋድራስ ተሰማ እሸቴም የፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴን ሞትና ስርዓተ ቀብር እንዲህ በማለት በግጥም ገልጸውታል፡፡

«ከምኒልክ ይዞ እስካሁን ድረስ፣

ያልታዬ ሞት ሆነ የሀብተጊዮርጊስ» ፊታውራሪ ተክለሃዋርያት ተክለማርያም ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊሥን ‹‹… ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊሥ በሕ ዝብ ዐይን የንጉሥ አካል ናቸው። ብይናቸውን አፈ ንጉሥ አይገለብጠውም።በአጭሩ የማይነቃነቁ ተራራ ናቸው …›› በማለት ገልፀዋቸዋል።

ብላታ መርስዔሃዘን ወልደቂርቆስ በበኩላቸው ‹‹ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊሥ በዳኝነት አቃዊነታቸውና በዘመኑ የአስተዳደር ፈሊጥ እጅግ የተመሰገኑ ነበሩ›› በማለት ስለጠንካራው የጦር መሪና ፍርድ አዋቂ ሰው ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

የእንግሊዙ ቆንሲልም ወደ ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዘንድ ሄዶ «ሰዎቻችን ያለአግባብ ተገድለውብናልና ደማቸው የፈሰሰበት መሬት ይሰጠን» ብሎ ጠየቃቸው፡፡ ፊታውራሪም» «ግን በሀገራችሁ ይህን መሳይ ደንብ አለ?» ብለው ጠየቁት፡፡ ቆንሲሉም «አዎ» ብሎ መለሰ፡፡ ፊታውራሪም በምላሹ «እንግዲያውስ መልካም! እኛም የአፄ ቴዎድሮስ ልጅ ልዑል ዓለማየሁ ቴዎድሮስ ከዚህ ሄዶ በሀገራችሁ ሞቷልና ሎንዶንን ለእኛ ስጡን፤ እናንተም ይህንን ውሰዱ» ብለው ቃል አርቅቀው ፈርመው «በል እዚህ ላይ ፈርም» ሲሉት«አልፈርምም» ብሎ ሄደ፡፡ ዳግማዊ አፄ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱም ከደስታቸው ብዛት የተነሳ የፊታውራሪን አንገት አቅፈው ሳሟቸው፡፡

አዲስ ዘመን  ረቡዕ ጳጉሜ 6/2011

አንተነህ ቸሬ