ኢትዮጵያን በላቀ ክንድ እንጠብቅ!

5

 ዛሬ መስከረም 1, 2012 ዓ.ም ነው። የዓመቱ የመጀመሪያ ቀን። ሀገራዊ ሰላምና መረጋጋት የሚሰፍንበት፤ ፖለቲካዊ ውስብስብ ችግሮች በሰላማዊና በጠረጴዛ ዙሪያ እልባት የሚያገኙበት፤ ልዩነቶች በመቻቻልና በመግባባት እየተፈቱ ሀገራዊ መደማመጥና መግባባት የሚሰፍንበት የሰላም ዘመን እንዲሆንልን አጥብቀን አብዝተን ተመኘን። ዓመቱ አገራዊ ምርጫ የሚካሄድበት በመሆኑ ብጥብጥ ሁከትና ረብሻ እንዳይከሰት በዚህም አላስፈላጊ ትርምስ ውስጥ እንዳይገባ ሀገርም ሕዝብም ጉዳት ውስጥ እንዳይወድቁ ሕዝብ ነቅቶ የሚጠብቅበት ሊሆንም ይገባል።

አምናና ካቻምና የተመለከትነው ቀውስ ሀገራዊ ሰላምን ከማናጋቱ አልፎ የዜጎችን ሕይወት አስከፍሏል። ሀብትና ንብረትም ወድሟል። ታዳጊ የሆነው ኢኮኖሚያችን መቀዛቀዝ አሳይቷል። አስከፊ የኑሮ ውድነት ተከስቷል። የሀገር ልማትና እድገት የሚመጣው ኢኮኖሚያችን በተከታታይ ማደግ ሲችል ነው። ሰላም ለሀገር እድገት ወሳኝ ነው።

በአለፈው አንድ ዓመት ሁሉም ጎራ ለይቶ ፖለቲከኛ፣ ተንታኝ ጥላቻ የሚያዛምት እንቶ ፈንቶና የጎጥ ፖለቲካ አራማጅ፤ ግጭት ቀስቃሽ ሆኖ ሲያጋፍር ከረሟል። የሆኖ ሆኖ ግን ከእልቂትና ውድመት ውጪ ለሀገርም ሆነ ለሕዝብ ያስገኘው ትሩፋት የለም። በየጎራው ልዩነትን እያገዘፈ የሚሄድበት አካሄድ ሀገራዊ ጥፋትን ብቻ ነው የወለደው። ተከባብሮ፣ ተደማምጦና ተቻችሎ ከመኖር ውጪ አማራጭ የለንም።

ልዩነቱን እያሰፉ የሕዝቡን ሕብረትና አንድነት ለመሸርሸር ከዚህም አልፎ ግጭቶች እንዲቀሰቀሱ የሚደረገው የአክራሪና ጽንፈኛ ኃይሎች ስውርና ግልጽ ሴራ ሀገርን ለማጥፋት ያነጣጠረ በመሆኑ ሕዝቡ የግድ ሊያከሽፈው ይገባል። ስለፖለቲካ ስለምርጫ ውድድር ማውራት መነጋገር የሚቻለው ሰላሟ የተከበረና የተረጋገጠ ሀገር ስትኖር ነው። ሀገር ከሌለች ምንም ሆነ ማንም የለም። ይህንን ሆን ብለው እየገፉበት ያሉት አክራሪ ኃይሎች፤ በውጭ ኃይሎች የሚረዱና ለዚሁ ሀገር የመበታተን አላማ ማስፈጸሚያ ፈርጀ ብዙ በሆነ መልኩ የሚታገዙ ናቸው።

ዛሬ ደግሞ ሌላውን ዓለም በታትነውና አፈራርሰው አዛኝ ቅቤ አንጓች እንዲሉ እነሱ የለየላቸው ጸረ ዴሞክራሲና ፍጹም አምባገነኖች እንዳልሆኑ ሁሉ ለኢትዮጵያ አሳቢና ተጨናቂ በመምሰል ቅጥረኞቻቸውን አሰማርተው እያመሷት ይገኛሉ። በመሆኑም በአዲሱ ዓመት፤ መጠንቀቅና ሀገርን ከጥፋት መታደግ የሚገባው ደግሞ ሕዝብ ነው።

ጥላቻ እንዲነግስ በማድረግ መከፋፈልን የሚዘሩ ቡድኖችን እያደራጁ፤ ግጭትና የማያባራ ጦርነት እንዲነግስ ስምሪት የሚሰጡበት ይህን መሰል ታሪክ በሌሎች ሀገራትም ታይቷል። ወጣቱን የአመጽ ግንባር ቀደም ተሳታፊ በማድረግ በተለያዩ ሀገራት መጠነ ሰፊ ጥፋት፣ ውድመትና እልቂት እንዲፈጠር ሀገራቱም እንዲፈራርሱ አድርገዋል።

ይህ የጥፋት ፕሮጀክታቸው የሚመራው የእነሱው ቅጥረኛ በሆኑ ምሁራኖች አክቲቪስቶች ናቸው። በአዲሱ ዓመት ከዚህ ውርደትና የታሪክ ውድቀት ለመውጣት ኢትዮጵያን ነቅቶ መጠበቅ ከሴረኞች ደባ መከላከል የዜጎቿ ሁሉ ቀዳሚ አጀንዳ መሆን ይገባዋል። የአክራሪና ጽንፈኞች ከጀርባቸው ያሉት የውጭ ኃይሎች የጋራ ቅንጅትና ሴራ ግልጽ ነው። ግባቸው ሀገርን ማፈራረስ አሊያም ለእነሱ የተመቸች እንዳሻቸው የሚዘውሯት ሀገር መፍጠር ነው።

ከዚያም በኋላ ይህንን ተልዕኮ የተወጡትን ጥገኝነት ሰጥተው ወደሀገራቸው በመውሰድ እንዲኖሩ ያደርጓቸዋል። በሌሎች ሀገራት ታሪክ የታየው ይኸው ነው። አስከፊ ቀውስና ምስቅልቅል በሀገራችን እንዲከሰት ሌት ተቀን እየሰሩም ናቸው። ይህን የተቀነባበረ ሴራ ማምከን ሀገሪቱን ከጥፋት መታደግ የመንግሥትና የሕዝብ የጋራ ኃላፊነት ነው። ኢትዮጵያን ጠብቅ ያልነውም ለዚህ ነው።

ሀገራችን በተፈጥሮ ሀብት የታደለች ነች። ይህን ለመጠቀም በብዛት በተለያየ ዘርፍ የሰለጠነ በቴክኖሎጂ፤ በሳይንስና ምርምር የበቃ የሰው ኃይል ሊኖራት ግድ ይላል። ሀገርን ለማሳደግ ልጆቿ በሰላም በፍቅር በሕብረት ተጋግዘው መቆም መስራት ይጠበቅባቸዋል። ዛሬ የሚታዩት ዘርፈ ብዙ ችግሮች ከለውጡ ጋር ተያይዘው የመጡ አይደሉም። ስር ሰደው የኖሩና ተንሰራፍተው የቆዩ ናቸው። መፍትሄው ከውጭ ሀገር አይመጣም። የሚገኘው በእጃችን ነው።

ለሀገራዊ ችግር ሀገራዊ መድኃኒቱ በሰላማዊ መንገድ በቅን ልቦና ተከባብሮና ተደማምጦ ልዩነትን አቻችሎ ሀገርን መታደግ በጋራ መቆም ብቻ ነው። አክራሪና ጽንፈኛ ኃይሎች ሀገር ጠፍታ እነሱ በሰላም የሚኖሩበት ሁኔታ በምንም መልኩ እንደማይኖር ሊረዱ ይገባቸዋል። አዲሱን ዓመት በሰላም በፍቅር እንደተቀበልነው ሁሉ ሀገራችን ዳር እስከዳር ሰላም እንድትሆን መቆም የእያንዳንዱ ዜጋ ታሪካዊ ኃላፊነት መሆኑ መታወቅ አለበት። የሰላም የእድገት የተስፋ የመደማመጥና የመግባባት ዓመት እንዲሆንልን ጸንተን በጋራ እንቁም።

ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ሲሰራ የኖረው ሴራ ዘመናትን ያስቆጠረ ነው። አዲስ አይደለም። በቅርብና በሩቅ ስትራቴጂክ ጠላቶች አቀናባሪነት ሲመራ የነበረና በየጊዜው ብልጭ ድርግም ሲል የኖረ ነው። ዛሬ ደግሞ አድብተው ቀና በማለት እየተወራጩ የሚገኙበትን ሁኔታ በገሀድ ማየት ችለናል። ጥንትም በኢትዮጵያ ላይ የተሰነዘሩ ጥቃቶችና ሴራዎች በተለያየ ዘመንና ጊዜ የከሸፉት ቀደምት በነበሩት የኢትዮጵያ ትውልዶች ነው።

የዛሬው ትውልድ ሀገሩን ከተለያዩ የጥፋት ኃይሎች የመታደግ ትውልዳዊና ሀገራዊ ብሎም ታሪካዊ ኃላፊነት አለበት። ሀገር ሰላም ስታጣ በተረጋጋ ሁኔታ ኢኮኖሚዋን ማሳደግ አይሆንላትም። ገበሬው በሰላም ማረስ ነጋዴው በሰላም መነገድ የገዛውንም ከሩቅ ቦታ ጭኖ በሰላም ለሕዝብ ማድረስ አይችልም። ሰላም ከሌለ ፋብሪካዎች መሠረታዊ አቅርቦት ስለማያገኙ በአግባቡ መስራት ማምረት ቢያመርቱም ማከፋፈል ማዳረስ አይችሉም። ሰላም ከሌለ ትርምስ ከነገሰ መሰረታዊ የሆኑ የሸቀጥ አቅርቦቶች ለሕዝብ ማድረስ አይሞከርም። ሰላምና መረጋጋት ከሌለ ሀገርና ሕዝብ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ይወድቃሉ። ይህን መሰሉ ተግባር በአዲሱ ዓመት መታየት የለበትም።

ይህ ዓይነቱ ችግር እንዳይፈጠር በተለይ በአዲሱ ዓመት የለውጡ ጉዞ እንዳይደናቀፍ የሀገር ሰላምና መረጋጋት ተጠብቆ እንዲቀጥል ለማድረግ ሕዝብ ነቅቶ መጠበቅና መከላከል ይገባዋል። ኢትዮጵያን ትርምስና ምስቅልቅል ውስጥ ለመክተት የማያባራ የጦርነት ቀጣና ለማድረግ፤ ሕዝቡ እንዲከፋፈል ጎራ ለይቶ እንዲጋጭ ብሎም እንድትበታተን የሀገር ውስጥ ጽንፈኛና አክራሪ ኃይሎች ከውጭ ኃይሎች ጋር በመቀናጀት ያወጁት ጦርነት በሕልውና ላይ ያነጣጠረ አደገኛ ሀገር አፍራሽ ድርጊት መሆኑን ጠንቅቆ መረዳት ተገቢ ነው።

መንግሥት በግልጽ ቁርጠኛ አቋም መውሰድ ይጠበቅበታል። ይህ ሲሆን ነው የሕግ የበላይነት የሚከበረው። በሕግና በሥርዓት የማይመራ ልቅ ዴሞክራሲ የሚባል ነገር በዓለም ላይ የለም። ሀገርን ለማፍረስ የሚሰሩ ኃይሎችን መታገስም ሆነ በዝምታ ማለፍ አይቻልም። የሀገራችን መሰረታዊ ችግር ድህነትና ኋላቀርነት ነው። ከድህነት ለመውጣት በርትቶና ጠንክሮ ኢኮኖሚያችንን ማሳደግ ብቁ የሰው ኃይል ማፍራት፤ ግብርናውን ማዘመን፤ ኢንዱስትሪዎችን ማስፋፋት በዚህም የሥራ አጥነት ችግርን በተቻለ መጠን ማቃለልን ይጠይቃል።

ሀገራዊ ችግሮቻችን ትናንት የተወለዱ የተፈጠሩ አይደሉም። በአንድ ጊዜ አይፈቱም። ሊፈቱም አይችሉም። ሁኔታዎችን አጣጥሞ ችግሮችን ለመፍታት በጋራ መምከር መወያየት መቻቻልን ይጠይቃል። ረዥም ጊዜም ይወስዳል። በሂደት ደረጃ በደረጃ ነው መፍትሄ እያገኙ ሊሄዱ የሚችሉት። ሀገራችን አንጸባራቂ ገድልና ታሪክ ያላት ነች። ይሄን ጠብቆ ወደተሻለ ምዕራፍ መሸጋገር ሲገባ ዛሬ የተከሰተው ሀገርን የማፍረስ በሽታ ከወዲሁ ካልተቀለበሰ አደጋው ለሁሉም ይተርፋል።

ኢትዮጵያ በዓለማችን ላይ እጅግ ጥንታዊ ከሆኑ መንግሥታት ውስጥ አንዷ ነች። የመጀመሪያው የሰው ዘር መገኛ ምድር፤ የዓለማችን ረዥሙ ወንዝ ምንጭና ማህጸን የቀደምት ስልጣኔ ባለቤት፤ እጅግ የተመቸ የአየር ንብረት ቆላ፣ ደጋ፣ ወይና ደጋ ያላት፤ የበርካታ ወንዞች ኃይቆች ባለቤት፤ የብርቅ አዕዋፋትና የዱር እንስሳት መገኛ ናት። በዓለም የተመዘገቡ በሌላውም ዓለም የሌሉ የማይገኙ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች ባለቤት፤ለመላው የዓለም ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ተጋድሎ ቀዳሚ ምሳሌና አርአያ በመሆን ወራሪ ቅኝ ገዢ የነበረውን የፋሽስት ሠራዊት ጦርነት ገጥማ አድዋ ላይ ድል ያደረገች በዚህም መላውን ዓለም ያስደመመች ሀገር ነች። ኢትዮጵያን ነቅተህ ጠብቅ።

የኢትዮጵያ ድል ለፓን አፍሪካ መመስረት ለመላው ዓለም ጥቁሮች ከባርነትና ከቅኝ ግዛት ከአፓርታይድ ነፃ ለመውጣት ለሚያደርጉት ትግል መነሳሳት አርአያ በመሆን ብዙ ሀገራት ታግለው ነፃነታቸውን ተቀዳጅተዋል። ደቡብ አፍሪካ ከአፓርታይድ ቅኝ አገዛዝ ነፃ እንድትወጣ እነ ኔልሰን ማንዴላን ሀገር ውስጥ አምጥታ ወታደራዊ ትምህርት ያስተማረች ያሰለጠነች መሣሪያም ያስታጠቀች ታላቅ ሀገር ናት ኢትዮጵያ።

የታሪክ ውርዴዎች ይህችን ሀገር ለማጥፋትና ለማፈራረስ ነው እየተክለፈለፉ ያሉት። እነሱ ይፈርሳሉ። ኢትዮጵያ ግን አትፈርስም። የዚምባቡዌን ዛኑ ፒኤፍና ሰሞኑን ያለፉት መሪውን ሮበርት ሙጋቤን ተቀብላ ያስተናገደች ሠራዊቱን ያሰለጠነች፤ የደቡብ ሱዳንን መሪ ኮ/ል ጆንጋራንግ በነፃነት ትግላቸው ውስጥ ያስጠለለች ፤40 ሺህ ሠራዊት ያሠለጠነች ያስታጠቀች ከራሷ አልፋ ለአፍሪካ ነፃነት ቀንዲል ሆና የኖረች ሀገር ናት ኢትዮጵያ። ይችን ድንቅ ሀገር ነው በሕልውናዋ ላይ የዘመቱት። ነገሩ እሳት ቢያንቀላፋ ገለባ ጎበኘው ዓይነት መሆኑ ነው። ክብርህ ኩራትህ መመኪያ ናት። ኢትዮጵያን ጠብቅ።

በዓለም ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሊግ ኦፍ ኔሽንስ ሲቋቋም የነበረች በኋላም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሲመሰረት ቀደምት መስራች የሆነች ሀገር ናት ኢትዮጵያ። ለመጀመሪያ ጊዜ በተባበሩት መንግሥታት ጥያቄ ለደቡብ ኮርያ ነፃነት የቃኘው ሻለቃን ሠራዊት አዝምታ የኢትዮጵያ ሠራዊት በተሰለፈበት የውጊያ መስመር ሁሉ የተሰዋም ሆነ የቆሰለ አንድም ወታደር ያላስማረከች በዚህም በጦርነቱ ማብቂያ ከተሳተፉ 121 ሀገሮች ውስጥ ባንዲራዋን ከፍ አድርጋ በብቸኝነት ያውለበለበች የጀግኖች ሀገር ናት ኢትዮጵያ።

ተከብረው ሀገራቸውን የሚያስከብሩ የሚያኮሩ እልፍ ጀግኖች የነበሯት፤ ዛሬም ያሏት ሀገር ነች። ማንም እንዳሻው እየተነሳ የሚያቀረሽባት ሀገር አይደለችም። ኢትዮጵያን ጠብቅ። ሌላ ብዙ መጥቀስ ይቻላል። ይህችን ሀገር ልጆቿ በጋራ ሆነው ማልማት ማሳደግ ወደ ታላቅነት ምዕራፍ ማሸጋገር ሲገባቸው እርስ በእርስ እንዲባሉ ለማድረግ የተሰራውና የሚሰራው ደባ የኢትዮጵያ ቀንደኛ ጠላቶች ሴራ መሆኑን ሁሉም ዜጋ በውል ሊረዳው ይገባል። ለሀገሩ ሰላምና ደህንነት ፀንቶ መቆም ይጠበቅበታል። ለኢትዮጵያ ጠላቶች የሚከፈት በር አይኖርም። አዲሱ ዓመት የሰላም የፍቅር የመግባባት የመደማመጥ ይሁንልን !!

አዲስ ዘመን   መስከረም 1 /2012

 ወንድወሰን መኮንን