ወጣቶች ስለ አዲሱ ዓመት ምን ይናገራሉ?

4

 ወጣት ሰዴ አሻግሬ ነዋሪነቱ በሽሮ ሜዳ አካባቢ ሲሆን ቀን ቀን ጫማ የማስዋብ ሥራ እየሰራ የማታ ትምህርት ይከታተላል። የቤተሰብ አስተዳዳሪና የልጅ አባትም ነው። ያለፈው ዓመት በርካታ መልካምና መጥፎ ነገሮች የነበሩበት ነው። መጥፎ ነገሮች በፈጣሪ እገዛ አልፏል። አዲሱ ዓመት መልካም ነገር ከፈጣሪ ዘንድ ይመጣል። አዲሱ ዓመት ለራሱም ሆነ ለሀገር ካለፈው ዓመት እጅግ የተሻለ ዓመት እንደሚሆን ተስፋ ሰንቋል። ለቀጣይ ዓመት እቅዶችንም ነድፏል።

 የማታ ትምህርቱን ከመግፋት ጎን ለጎን ልጁንም ለማስተማር አስቧል።

በአዲሱ ዓመት የተከፋ ሰው ባላይ ደስ ይለኛል የሚለው ሰዴ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ደስተኛ ሆነው ማየት እመኛለሁ ይላል።

የተከፋ ፊት ማየት እጅግ ያሳዝነዋል። ሁሌም ደስተኛ የሆነ ፊት ማየት እንደሚያስደስተው ይናገራል። ሰው ሰርቶ ደስተኛ የሚሆንበት፤ ጸብ የሌለበት ዓመት እንዲሆን ምኞቱ ነው። በአዲስ ዓመት የተሻለች ኢትዮጵያን ለማየት የበኩሉን ለማበርከት እቅድ እንዳለው ያነሳል። ከመጥፎ ነገሮች ራሱን ለማራቅና መልካም የሆኑትን ነገሮች ለማከናወን አስቧል። ለሀገር የማይጠቅሙ ነገሮችን ከጭንቅላቱ ለማስወገድ ከወዲሁ ተዘጋጅቷል።

በጎ በጎውን ብቻ ለማሰብና ለመከወን ነው የተዘጋጀው። መጥፎ የሚያደርጉትን ከመጥፎ ተግባራቸው ለመመለስ ጥረት እንደሚያደርግ፤ መጥፎ አድራጊዎች ከመጥፎ ተግባራቸው የማይታቀቡ ከሆነ ደግሞ ከነሱ ለመራቅ ማሰቡን ያነሳል። በአቅሙ ከሚያከናውናቸው ተግባራት በተጨማሪ ኢትዮጵያን ሰላም እንዲያደርጋት ፈጣሪውን ለመማጸን እቅድ አለው።

አዲስ ዘመን   መስከረም 1 /2012

 መላኩ ኤሮሴ