በእግር ኳሱ ያየነው ፈተና በ2012 እንዳይደገም

8

አሮጌውን 2011ዓ.ም ሸኝተን አዲሱን 2012 ዓ.ም ዛሬ አንድ ብለን ተቀብለናል። ባለፉት ሦስት መቶ ስልሳ አምስት ቀናት በኢትዮጵያ ስፖርት ውስጥ መልካም ነገሮችና ተስፋዎች የታዩትን ያህል በእግር ኳሱ ዙሪያ ሊጠቀስ የሚችል አንድም መልካም ነገር አልታየም ማለት መዳፈር ሳይሆን ሀቅ ነው። ስለዚህ 2011 ዓ.ም ለኢትዮጵያ እግር ኳስ የጨለማ ዘመን ሆኖ አልፏል ቢባል ማጋነን አይሆንም። ይህን ዘመን ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ጨለማ ነው ለማለት የተለያዩ ማሳያዎችን ማስቀመጥ እና በአዲሱ ዓመት እንዳይደገሙ ሀሳብ እናቀርባለን፤ ይህ ደግሞ ተገቢ ነው።

የስቴድየም ሁከትና ግጭት

በ2009 ዓ.ም በርካታ ቁጥር ያለው የስቴዲየም ሁከት በተለይም በፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ቢከሰቱም ከብጥብጦቹ ጀርባ እግር ኳስን የሚሻገሩ ገፊ ምክንያቶች እምብዛም እንዳልነበሩ ይጠቀሳል። ከ2009 ወዲህ ግን በልዩ ልዩ ምክንያቶች የሚለኮሱ የስቴድየም ግጭቶችና ረብሻዎች ቁጥር አይሏል።

በ2010 የውድድር ዓመት ሐዋሳ፣ ድሬዳዋ፣ አዲግራት፣ ጅማና ወልዲያ ከተሞች ውስጥ የስቴድየም ሁከትና ግጭቶች ተበራክተው እንደነበር ይታወሳል። በተለይም በውድድር ዓመቱ በወልዲያ ስፖርት ክለብና በመቀሌ ከተማ መካከል ሊደረግ የነበረው የእግር ኳስ ጨዋታ ከመጀመሩ ከሰዓታት በፊት በሁለቱ ቡድኖች ደጋፊዎች መካከል በተቀሰቀሰው ግጭት ህይወት የጠፋ ሲሆን ንብረት ላይ ዘረፋና ወድመት ተከስቷል።

በዕለቱም ማገባደጃ ላይ በመቀሌ ከተማ መንገዶች ላይ ክስተቱን ለመቃወም በርካታ ሰዎች ወጥተው እንደነበር አይዘነጋም። ጨዋታው ካለመካሄዱ በተጨማሪም የግጭቱ አሻራ እስከ ቀጣይ ቀናት ሲሻገርና ከእግር ኳሳዊ ምክንያት ይልቅ ፖለቲካዊ አንደምታው ሚዛን ሲደፋ ታይቷል። የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መርሃ ግብር ከረብሻዎች ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በተለያዩ ክለቦች ላይ የጣለው ቅጣት ግማሽ ሚሊዮን ብር ገደማ መሰብሰብ መቻሉ ግጭቶች በምን ያህል ደረጃ እንደተበራከቱ ማሳያ ነው።

‹‹በእንቁላሉ ጊዜ›› ያልተቀጣው እግር ኳስ 2011 ላይ ከፖለቲካም በላይ ጦዞ ለፀጥታ አስከባሪዎች ፈተና ከመሆን አልፎ እንደ አገር ስጋት የሆነበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ሰላም በራቃቸው የስፖርት ማዘውተሪያዎች መደበኛ የውድድር መርሐ ግብሮች መተማመኛ ማግኘት እየቻሉ እንዳልሆነ ተመልክተናል። በክልል የሚካሄዱ ጨዋታዎች በፖለቲካ ትኩሳት ሳቢያ ተጨማሪ ራስ ምታት እየሆኑ መምጣታቸውን በተለይም በ2011 የውድድር ዓመት ለመታዘብ ተችሏል።

በአገሪቱ የደፈረሰው ሰላም ለስፖርቱም ዋናው እርሾ እየሆነ በመታየቱ በተለይ በክልል እግር ኳስ ክለቦች መካከል የሚከናወኑ ጨዋታዎች ከእግር ኳሳዊ ትንቅንቁ ይልቅ የሥጋት ምንጭነታቸው ሲያይል ከማየት የበለጠ ለአገሪቱ እግር ኳስ የጨለማ ዘመን ማስረጃ ማቅረብ አይቻልም። በዚህም የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ መደበኛ ውድድሮች በተያዘላቸው ቀንና ጊዜ እንዳይከናወኑ ምክንያት ሆኗል። በክልል የሚካሄዱ ጨዋታዎች በፖለቲካ ትኩሳት ሳቢያ ተጨማሪ ራስ ምታት እየሆኑ መምጣታቸውን በዚሁ የውድድር ዓመት ለመታዘብ ተችሏል።

ለታኅሣሥ 17 ቀን 2011 ዓ.ም. የታሰበው የወላይታ ድቻና የሲዳማ ቡና ጨዋታ አንዱ ማሳያ ሲሆን፣ ሌላው በዚሁ የፖለቲካ ትኩሳት በይደር የቆየው መቐለ 70 እንደርታ ከፋሲል ከተማ፣ እንዲሁም ባህር ዳር ከተማ ከሽረ እንደስላሴና ሌሎችም ይጠቀሳሉ። ክለቦች በክልሉ በተዟዙሮ የሚያደርጉት ጨዋታ ከወጪውም አኳያ ቀድሞውንም ባይደግፉትም ፖለቲካው ባመጣው ጣጣ አንዳንዶቹ እየተዟዟሩ ለመጫወት ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቆይተዋል።

ቀደም ሲል የወላይታ ድቻና የሲዳማ ቡና የጨዋታ መርሐ ግብር ሲወጣ አንዳችም ተቃውሞ አልነበረም። ይሁንና የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት እንደሚካሄድ ሲጠበቅ፣ ከሲዳማ ቡና ለፌዴሬሽኑ በተላከ ደብዳቤ ጨዋታውን ወላይታ ድቻ ላይ ሄዶ መጫወት የሚያስችል ሁኔታ ባለመኖሩ ጨዋታው እንዲራዘም ተደርጓል።

የመቐለ ከተማና የፋሲል ከተማን ጨዋታ በተመለከተም ፋሲሎች ከሜዳቸው ውጪ ለሚያደርጉት ጨዋታ ዝግጅታቸውን አጠናቀው እንደነበረ፣ ሆኖም ባህር ዳር ከተማ ላይ የሚደረገው የባህር ዳርና የሽረ እንደስላሴ ጨዋታ ፀጥታውን የበለጠ አስተማማኝ ለማድረግ በሚል ከክልሉ የፀጥታ ኃላፊዎች ለፌዴሬሽኑ በቀረበ ጥያቄ መሠረት እንደሆነም በወቅቱ መነገሩ ያታወሳል። በዚሁ ሳቢያ የፋሲል ቡድን ወደ መቐለ የሚያደርገውን ጉዞ ለመሰረዝ መገደዱ ይታወቃል።

በእነዚህና በሌሎችም ተያያዥ ምክንያቶች አጣብቂኝ ውስጥ የገባው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የክልል አመራሮችን ማነጋገር የጀመረው ቀደም ሲል ጀምሮ መሆኑ ይታወሳል። ያም ሆኖ ጨዋታዎች መሰረዛቸውና የፀጥታ ስጋት መኖሩ አልቀረም። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ፌዴሬሽኑ በካፍ መርሃግብር መሰረት የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግና ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ኢትዮጵያን የሚወክሉ ክለቦችን ለማሳወቅ ምን ያህል ጥድፊያ ውስጥ እንደገባ በቅርቡ የምናስታውሰው ነው።

በስፖርቱ ዓለም የተመልካቾች ነውጠኝነት ምክንያቶች ብዙ መሆናቸውን በስፖርቱ ጥልቅ እውቀት ያላቸው ባለሙያዎች ሲናገሩ ይደመጣል። ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ ወይንም ምጣኔ ሀብታዊ ብሶቶች ስቴዲየም ላይ ሊያጠሉ እንደሚችሉም ይታመናል። በኢትዮጵያ እግር ኳስን የታከከ ግጭትና ሁከት ሲከሰት የመጀመሪያው ባይሆንም 2011 ላይ ቀይ መስመር አልፎ ታይቷል።

የቅርብ ጊዜ ክስተቶችን ስናጤን ደግሞ ከእግር ኳስ ባሻገር ከነዚህ ምክንያቶች ሁሉ ለስፖርት ጠንቅ የሆነ የፖለቲካ አጀንዳ መኖሩን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ራሳቸው አስተውለውታል። እግር ኳስ ማኅበረሰባዊ መሰረት ከሌለው በስተቀር የጠነከረ የእኔነት ስሜት ሊፈጥር አይቻለውም የሚሉ ተንታኞች ፤ ክለቦች ከማኅበረሰባዊ መሰረታቸው በዘለለ ብሔር ተኮር መልክን እየተላበሱ የመምጣታቸው አዝማሚያ አደገኛ መሆኑን አይክዱትም።

ክለቦች ሲቋቋሙ ወይንም ሲዋቀሩ አካባቢያዊ መገለጫ ወይንም ከተማዊ ስያሜ ሊኖራቸው ቢችልም ከብሔር፣ ከዘር ወይንም ከኃይማኖት ጋር በተቆራኘ መልኩ መደራጀት ክልክል መሆኑን የስፖርት ኮሚሽን የስፖርት ማኅበራት ማደራጃ መመሪያ አንቀፅ 50 ቁጥር 2 ይገልፃል። ነገር ግን ባለፉት ዓመታት ብቻ ፌዴሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው ሊጎች የብሔር ስም የተቀጠላላቸው በርካታ ክለቦች ውድድር እያደረጉ ይገኛሉ።

እግር ኳሱ ከአንዳንድ ሁከቶች አልፎ እጅግ ወደተደራጀ ነውጠኛነት እያመራ ስለመሆኑ የ2011 ዓ.ም መርሃግብሮች ቁልጭ አድርገው አሳይተውናል። ቀስ በቀስም ወደመቧደን እየተሄደ ራሳችንን መከላከልና ማዘጋጀት አለብን በሚል ደጋፊዎች ራሳቸውን ማደራጀት ከጀመሩ የሚያሰጋ ዓይነት እውነታ ሊፈጠር እንደሚችል በ2011 የውድድር ዓመት ተመልክተናል።

በደጋፊዎች መካከል የእኔነቱ መንፈስ ከሮ ከኳስ ወዳጅነት አፈንግጦ በብሔርተኝነት ጎዳና መጓዝ ተጀምሯል። ከዚህ ቀደም ብጥብጡ ተጀምሮ የሚያልቀው ስቴዲየም ነው፤ ከዚያ አያልፍም። አሁን አሁን እየታየ ያለውን ግን ማብራሪያ የማይፈልግ የአደባባይ ሃቅ ነው። ክለቦች የማንነት ማግነኛና የራስ ኩራት መገለጫ መድረኮች እየሆኑ የመምጣታቸውን ሃቅ በየአካባቢው እየጎመራ ከመጣው የዘውግ ብሔርተኛነት ጋር የሚያስተሳስሩትም ጥቂት አይደሉም።

ክለቦች መጠሪያው ባይኖራቸውም ከሚመጡበት ክልል ጋር ተያይዞ የእገሌ ብሔር ነው የሚል እምነት አሳድረዋል። ከዚህም በተጨማሪ ክለቦች የተለያዩ የአገሪቱን ክልሎች እንደሚወክሉ መታሰቡ፤ ክልሎች ብሔርን መሰረት አድርገው እንደመዋቀራቸው ብሄርን እንደሚወክሉ ወደመታሰብ አድጓል። ፌዴሬሽኑ ከውይይት የዘለለ ፋይዳ ያለው ነገር እየሰራ እንዳልሆነ የሚጠቁሙ የስፖርት ቤተሰቦች ከዚህም በኋላ ችግሩን ይቀርፋል የሚል እምነት ማሳደር ተቸግረውበታል። ይህንንም በውድድር ዓመቱ በጉልህ ተመልክተነዋል።

ሳይጠናቀቅ የተጠናቀቀው ፕሪሚየር ሊግ

አሁን አሁን በአዲስ አበባም ሆነ የክልል ስታደዬሞች ገብቶ ኳስ መታደም የራስን ደህንነት አደጋ ላይ ከመጣል ጋር ይነፃፀር ጀምሯል። ጨዋነት የጎደላቸው ደጋፊዎች፣ ከዳኛ ጋር ቡጢ የሚገጥሙ ተጫዋቾችና የቡድን አባላት፣ እንዲሁም ኢ-ፍትሐዊ የሆኑ ውሳኔዎች የሊጉ መገለጫ ከሆኑ ሰነባብተዋል። የ2011 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከስቴድየም ግጭትና ከፌዴሬሽኑ አወዛጋቢ ውሳኔዎች ጋር ተያይዞ ክለቦች የውድድር ዘመኑን ሳይቋጩ ራሳቸውን ከውድድር ያገለሉበት ሆኖም ይታወሳል።

ውዝግቦችና አለመግባባቶች በኢትዮጵያ እግር ኳስ ነግሰዋል። መሬት ያልነኩ፣ በእውቀት ያልተዋጁ ውሳኔዎች ሰላማዊውን መድረክ የብጥብጥ ቀጠና አድርገውታል። ሊጉ የሚቀጥልበት አቅም ባለማግኘቱም በተደጋጋሚ ለመቋረጥ ተገዷል። ለዚህም የአገሪቱ ታላላቅ ክለቦች የሆኑት ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና በውድድር ዓመቱ መጨረሻ ላይ ከፌዴሬሽኑ ጋር የገቡበት ውዝግብ የአዲስ አበባ ክለቦች የራሳቸውን ሊግ ለማቋቋም ውሳኔ ላይ እስከመድረስ ገፍተው እንዲሄዱ አድርጓቸዋል። ያም ሆኖ የአዲስ አበባ ክለቦች የራሳቸውን ሊግ በማቋቋም የጀመርነውን አዲስ ዓመት ይገፉበታል ወይም በተለመደው ፕሪሚየር ሊግ ይቀጥላሉ የሚለው ሃሳብ ጥርት ያለ ድምዳሜ ላይ ሳይደረስበት ወደ አዲሱ የውድድር ዓመት ተሸጋግረናል።

ብሔራዊ ቡድኑ (ዋልያዎቹ)

2011 ዓም የአንድ አገር ሊግ ድክመትና ጥንካሬ የብሔራዊ ቡድኑ መገለጫ እንደሚሆን አሳይቶን አልፏል ማለት ይቻላል። የአገሪቱ ሊግ በግጭትና ፍትሃዊ ባልሆኑ ውሳኔዎች እየታመሰ አይደለም ለወትሮውም ጥሩ ስም የለውም። የሊጉ ደካማነት ብሔራዊ ቡድኑ (ዋልያዎቹ) ላይ ተንፀባርቆ ያለፈበት ዓመት ለመሆኑ ጥቂት ውድድሮችን ለአብነት ማንሳት ይቻላል። ከሁለትና ሦስት ዓመታት በፊት እንደ ጅቡቲ ያሉ የእግር ኳስ ደረጃቸው ከኢትዮጵያ ያልተሻሉ አገራትን በቀላሉ ግማሽ ደርዘን ግብ አስቆጥረን ማሸነፍ እንችል ነበር። አሁን አሁን ይሄም እየከበደን ከአንድ ግብ በላይ ማስቆጠር እየተሳነን እንደመጣ በውድድር ዓመቱ ተመልክተናል።

ቀደም ሲል በቻን የምናደርገውን ተሳትፎ አሁን ማድረግ አልቻልንም፣ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ አገራት ከአስራ ስድስት ወደ ሃያ አራት ከፍ ብሎ እንኳን ተሳታፊ መሆን አልቻልንም። ለኳታሩ የዓለም ዋንጫ ቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ እንኳን ሌሴቶን ባህር ዳር ላይ ገጥመን ግብ ማስቆጠር አልቻልንም፣ የመልሱም ጨዋታ ቢሆን አንድ ለአንድ ተለያይተን ወደ ምድብ ድልድል የገባንበት አጋጣሚ ደረት የሚያስነፋ አይደለም።

በመጨረሻም

እግር ኳሱ በ2011 የውድድር ዓመት በዚህ ደረጃ ዘቅጦ ፌዴሬሽኑ አዲሱን ዓመት በምን መልኩ መጀመር እንዳለበት በግልፅ ያስቀመጠው ስትራቴጂክ እቅድ የለም። ፕሪሚየር ሊጉ እንዳለፈው ዓመት ተዟዙሮ የመጫወት መንገድ ይቀጥል አይቀጥል ማንም አያውቅም። ከፌዴሬሽኑ ዝምታ ተነስቶ ግን ሊጉ በነበረበት እንዲቀጥል ፍላጎት መኖሩን መገመት ከባድ አይደለም። ይህ ደግሞ ካለፈው ስህተት አለመማር ብቻም ሳይሆን የአገር ንብረትና የዜጎች ሕይወት የሚጠፋበትን መንገድ መፍቀድ ጭምር ነው። ፌዴሬሽኑ ከዚህ ጉዳይ ይልቅ የተጫዋቾች የደመወዝ ጣሪያ ጉዳይ አስጨንቆት ከርሟል። ለዚህም አበጀሁለት ያለው መላ መልካም ጎን እንዳለው ሁሉ በርካቶችን ያስማማና ከትችት ያመለጠ አልሆነም።

አዲስ ዘመን   መስከረም 1 /2012

 ቦጋለ አበበ