«ዜጎች መጪውን ጊዜመፍጠር አለባቸው»

44

ዶክተር ኤርሲዶ ለንደቦ የህክምና ዶክተር ሲሆኑ በአሁኑ ወቅት የማህበረሰብ ጤና እና ሊደርሺፕ ሳይንስ አሰልጣኝና አማካሪ ናቸው። በኤች አይቪ ኤድስ ፕሮግራሞች በኢትዮጵያና በደቡብ ሱዳን ለ12 ዓመታት አገልግለዋል። ‹‹የኑሮ ማፕ›› መጽሃፍ ደራሲም ናቸው። በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን አውታሮች ላይ በሚሰጧቸው ሙያዊና ማህበራዊ አስተያየቶችም ይታወቃሉ። በኢትዮ ኤፍ ኤም 107 ነጥብ 8 እና በዩቲዩብ የሚተላለፍ “የልጆቻችን ኢትዮጵያ” የተሰኘ የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅም ናቸው። በተጨማሪም የኢትዮ ስኳር ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማህበር የቦርድ ምክትል ፕሬዚደንትም ሲሆኑ ስለ ኢትዮጵያ ፖለቲካ እና አዲሱን ዓመት አስመልክቶ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

አዲስ ዘመን፡- ካለፈው ዓመት መጋቢት ወር ጀምሮ በኢትዮጵያ ውስጥ ሲካሄድ የነበረው ለውጥ ነው ወይስ ማሻሻያ?

ዶክተር ኤርሲዶ፡- አንድ ዓመት ተኩል የሆነው ኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ያለው ለውጥ ነው። ሪፎርምም ለውጥ ነው። አብዮተኞች የሚወዷት አንድ ቃል አለች “ስርነቀል” የሚሏት። ከመጋቢት 2010 ጀምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ያለው ስርነቀል ለውጥ ነው ወይ ሲባል ስርነቀል አይደለም፤ ነገር ግን ስርነቀል ለውጥ ሁል ጊዜ ጠቃሚ ነው ወይ የሚለውም መነሳት አለበት። ስርነቀል ለውጥ የግድ ጠቃሚ አይደለም። ምክንያቱም ስርነቀል ለውጥ አራማጆች ከዚህ በፊት የተሰራውን ሁሉንም አፍርሰው በአዲስ የመተካት መንገድ ስለሚሄዱ ችግሮችንም ይዞ ይመጣል። ስለዚህ በኢትዮጵያ የተካሄደው ለውጥ ጥሩ ለውጥ ነው የሚል እምነት አለኝ።

ጥሩ ለውጥ ነው ብዬ የምወስድበት ምክንያቶች አሉኝ። አንደኛ ለውጡ ከውጭ ተገፍቶ ከውስጥ የመጣ ነው። ለውጡ በቂ ነው ወይ ለውጡ ከየት ወዴት ነው፤ ለውጡ ምን ያህል ነው ። ለውጡ ከወሰድነው ጊዜና ካለው ጊዜ አንጻር በደንብ መታየት አለበት። ዝም ብለው እያጣጣሉ ምንም ለውጥ የለም ማለት አይቻልም። ከዚህ የበለጠ ለውጥ ማምጣት ይችል ነበር ወይ ከሆነ ጥያቄው አዎ፤ ከዚህ በጣም በተሻለ እና የበለጠ ለውጡ ሊራመድ ይችል ነበር።

አዲስ ዘመን፡- ለውጡ እየሄደበት ያለበትን ሁኔታ እንዴት ያዩታል። የሀገሪቱን ችግር ሊቀርፍ በሚችል መልኩ ነው?

ዶክተር ኤርሲዶ፡- ለውጡን በፈርጅ በፈርጁ ማየት አለብን። የመንግስት ዋናው ስራው ህግ ማስከበር፣ የህግ የበላይነትን ማስከበርና ወንጀለኞችን ማስታገስ፤ የህግ ሥርዓትን መሬት ማስነካት፤ ሰብዓዊ መብትን መጠበቅ፤ የዜጎችን በህይወት የመኖር መብት በዋነኝነት ከህይወት መብት የሚመነጨውን ነጻነት ማለትም የመንቀሳቀስ፣ የማሰብ፣ የመስራት፣ የመናገር መብቶችን ማስከበር ነው የመንግስት ዋነኛ ስራው። ስለዚህ ከዚህ አንጻር መንግስት ተግዳሮቶች አሉበት ብዬ አስባለሁ። እጥረቶችም አሉበት ብዬ አስባለሁ። እነዚህን ነገሮችን ያሻሽላል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

ሁለተኛው የኢኮኖሚ ለውጥ ነው። እኔ በጣም ትኩረት የምሰጠው አዲስቷ ኢትዮጵያ ጥሩ ትሆን ከሆነ የኢኮኖሚ ለውጥ ወሳኝ ነው። ከኢኮኖሚ ለውጥ አንጻር ለውጦቹ በጣም ዘገምተኛ ናቸው። ትላልቆችን የመንግስት ሀብቶች ወደ ግል ልናሸጋግር ነው ስለተባለ ብቻ የኢኮኖሚ ለውጥ አለ ማለት አይቻልም። እሱ ትልቅ ስህተት ነው። በእርግጥ እሱም ቀላል አይደለም። ምክንያ ቱም የቴሌን 49 በመቶ ሼር፣ ባቡርን፣ መርከብን፣ ሀይል ማመንጫዎችን ስኳር የመሳሰሉትን 100 እጅ ለመሸጥ መወሰን በራሱ ትልቅ ለውጥ ነው። ነገር ግን በቂ አይደለም። ኢትዮጵያ ውስጥ ቢዚነስ ለመስራት ነገሮችን ማቅለል ላይ መንግስት የጀመረው ነገር አለ። ጥሩ ነው።

እሱን ማበረታታት ያስፈልጋል። ነገር ግን ከዚህ በላይ መፍጠን አለበት ብዬ አስባለሁ። በማህበራዊ የሚሞከሩ ነገሮችም ጥሩ ናቸው። ነገር ግን ለውጡን በጣም የማደራጀት፤ አቅጣጫ የማስያዝ፤ ወይም ለውጡን አሰባስቦ በአንድ ማዕቀፍ የሚከት ፍኖተ ካርታ ነገር መዘጋጀት እንዳለበትም የሚናገሩ አሉ። እሱም መጥፎ ሃሳብ አይደለም፤ የሚበረታታ ነው። በአጠቃላይ ስታየው ለውጡ በደንብ አለ። ነገር ግን መሰረታዊ ነገሮች ይጎድሉታል።

 አዲስ ዘመን፡- መሰረታዊ ነገሮች ይቀሩታል ሲባል ምን ማለት ነው?

ዶክተር ኤርሲዶ፡- ለምሳሌ ያህል ህግ ከማስከበር ረገድ ሰፊ ክፍተት አለ። ከህግ ማስከበር ጋር ተያይዞ አንዳንድ የሚያስፈሩኝ ነገሮችም አሉ። በተለይም በትላልቅ ክልሎች ላይ የሚደራጀው የልዩ ሃይል የሚባለው ያሰጋኛል። የህግ የበላይነትን ከማስከበር ረገድ ለሀገር አደጋ ነው ብዬ ስለማስብ። እነዚህ ሥርዓት መያዝ አለባቸው። ልዩ ሃይል በህገ መንግስቱ ውስጥ ያለ አይመስለኝም። ስለዚህ ግልጽ የሆነው ነገር ኢትዮጵያ መከላከያ አላት ከውጭ ጠላት የሚከላከል፤ ሲቀጥል ፖሊስ ነው ያለን ወንጀል ለመከላከል ማለት ነው።

ልዩ ሃይል የፌዴራል አደረጃጀቱን አደጋ ላይ የሚጥል ነገር ነው ብዬ ነው የማምነው። ምክንያቱም አንዳንዶቹ ክልሎች ልዩ ሀይል እያደራጁ ያለው ጦር ሃይል በሚመስል መልኩ ነው። ልዩ ሃይል ወይም ወደ መከላከያው መቀላቀል አለበት ወይም ወደ ፖሊስ መቀላቀል አለበት፤ አሰራሩም መቀየር አለበት። ክልሎች የሚይዙት የጠመንጃ ልክ መታወቅ አለበት። ይህ በጣም ሊታሰብበት የሚገባ ነገር ነው።

ልዩ ሃይል ሲደራጅ ዓላማው ምንድን ነው? የሚለውን ማየት ያስፈልጋል። ክልሎችን የሚወር የውጭ ጠላት የለም። የማንም ካድሬ አንዱን ህዝብ ከአንዱ ህዝብ ጋር ለማጋጨት ነው ልዩ ሃይል ያደራጀው። ሌላ ምንም ትርጉም የለም። ስለዚህ የፌዴራል መንግስቱ እዚህ ላይ ኮስተር ያለ መስመር መከተል አለበት። ልዩ ሀይል የሚባለው አካል በህጋዊ ፖሊስ ስር መግባት አለበት።

ፖሊስ ደግሞ የሚታጠቀው የመሳሪያ መጠን ህግ አለው። ሀገሪቱ የፌዴራል ስርዓት የምትከተል ሀገር ስለሆነች ክልሎች ሰብዓዊ መብት የሚጥስ ፖሊስ ማደራጀት አይችሉም። ስለዚህ በሰብዓዊ መብት ማዕቀፍ ስር ከፌዴራሉ ጋር በተወሰነ ደረጃ ፌዴራሉ ክልሎች ላይ የተወሰነ ሃይል ሊኖረው ይገባል። ይህ ማለት የክልሎች ራሳቸውን በራስ የማስተዳደር መብት መጣስ ማለት አይደለም። ራስን በራስ ማስተዳደር ሌሎች ነገሮች ግባቸው የ100 ሚሊዮን ዜጎችን ነጻነት መጠበቅ ነው። የ100 ሚሊዮን ዜጎችን በህይወት የመኖር መብት ማስከበር ነው።

አሁን እየተሄደ ያለበት ሁናቴ ግን የ100 ሚሊዮን ዜጎች መብት አደጋ ላይ የመጣል ስለሆነ ፌዴራል መንግስቱና ክልሎች ውይይት ማድረግ አለባቸው። ስለዚህ እኔ ለውጡን ወደ ባሰ ችግር ሊመራ የሚችል ነገር ብዬ የምፈራ ነገር ልዩ ሃይል ማደራጀትና ጥግ የወጣ ብሄርተኝነት ጋር ያለው ችግር ነው። ምክንያቱም አሁን የክልሎች የመንግስት አካላት ናቸው ብሄርተኝነትን በጣም እያርገበገቡ ያሉት። ስለዚህ እነሱ ሥርዓት መያዝ አለባቸው። እዛ ጋር ህግ መከበር መቻል አለበት። ለውጥ ውስጥ የማየው አንዱ ተግዳሮት እሱ ነው። እዛ ላይ የፌዴራል መንግስቱ አቋሙን ግልጽ ማድረግ አለበት።

አዲስ ዘመን፡- በርሶ ተደርሶ በቅርቡ በገበያ የዋለው ኑሮ Map መጽሃፍ ዋነው ጭብጡ ምንድን ነው?

 ዶክተር ኤርሲዶ፡- ኑሮ Map ርዕሱ ነው። በየጊዜው የሚበለፀግ አስደሳች ህይወት ሳይንስ የሚለው ንፁስ ጽንሰ ሃሳብ ነው። መጽሃፉ ያካተታቸው ነገሮች በመጽሃፉ መግቢያ ላይ በቀላሉ ለማስቀመጥ ተሞክሯል። መጽሃፉ በዋነኝነት የሚያወራው የህይወትን ብቃት፣ እውቀትና ክህሎትን አመራር እንዴት ማሳደግ እንደሚቻል። የትምህርትና እውቀት አስፈላጊነት፤ ውጤታማና ምርታማ ገቢ ፈጠራ፤ ከድህነት ወጥቶ የመበልጸግ የኑሮ መንገድ፤ ስለስነምግባርና ሲቪክስ አስተሳሰቦች፤ ስለ ሰለጠነ ግጭት መከላከልና አብሮ የመኖር ሳይንስ፤ ከዚያ በተጨማሪ የኤች አይ ቪ ኤድስ፤ የጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እና ሌሎችም የጤና ችግሮች፤ በሁሉም ዘርፎች የሚያጋጥሙ ዋነኛ የውድቀት መንስኤዎች ምንድን ናቸው? እነዚህን እንዴት ተከላክሎ መኖር ይቻላል፤ ይሄ አንዱ ነው።

ልክ በመስሪያ ቤት ውስጥ ቢዚነስ ፕሮሰስ ሪ ኢንጂነርንግ (ቢፕ አር) እንደሚባለው ይሄ ደግሞ በግለሰብ ደረጃ ላይፍ ፕሮሰስ ሪ ኢንጂነርንግ (ኤል ፕ አር) ነው። ማለትም ሰዎች መሰረታዊ የህይወት አሰራር ለውጥ እንዲያመጡ ማለት ነው። በአጭሩ አዕምሯችንን በዝባዚንኬ ካጨቅነው ውጤቱም ያው ነው። ውጤቱም ዝባዚንኬ ነው የሚሆነው። ስለዚህ ወደ አዕምሯችን የሚገባውን በመፈተሽ ከአዕምሯችን የሚወጣውም ትክክለኛ እንዲሆን ማድረግ ይቻላል። ከዚህ አንጻር የብሄር ፖለቲካ፣ ጭፍን ሃይማኖተኝነት፣ በእኛ ሀገር የሚታየው መንግስት ነው ሁሉንም ነገር የሚፈታው የሚለው መንግስት ላይ የተንጠለጠለ አባዜ፤ መንግስትን ዜጋና ግለሰብ ሁል ጊዜ ደካማ ነው፤ የግሉ ዘርፍ ሁል ጊዜ ጠላት ነው፣ በዝባዥ ነው የሚሉ የሶሻሊዝምና የኮሚዩኒዝም አባዜዎች ልክ እንዳይደሉ በሳይንሳዊ መንገድ ተተንትኖ በደንብ የተጻፈ ነው።

አጭር ነው፤ ስታነበው ግን ጭንቅላትህን ለመፈተሽ መድፈር አለብህ። የተለመደውንና ለብዙ ዓመታት የሰማነውን ነገር መጠየቅ እንዳለብን ነው ኑሮ ማፕ የሚነግረን። ያንን ለመጠየቅና ማሰብ ለሚደፍሩ ሰዎች የተጻፈ መጽሃፍ ነው። የተለመደውን ለመስማት ለተዘጋጁ ሰዎች ላይጠቅማቸው ይችላል። ነገር ግን እነሱም ቢሆኑ ማንበብ ከጀመሩ በኋላ አንጎል ሁሌም ጨዋ ስለሆነ ብቻቸውን ሲሆኑ ቢያንስ ያውቋታል፣ ይወቅሳቸዋል፣ ይነግራቸዋል። ምክንያቱም አንጎል ጨዋነት አለው። በዚህ ምክንያት በጣም ብዙ ሰው እየወደደው ያለ መጽሃፍ ነው። አሁን 10 ሺህ ታትሞ አልቆ ሶስተኛው እትም አምስት ሺህ እትም ወደ ገበያ እየገባ ነው። ጋዜጠኞች ከተለመደው አስተሳሰብ ወጥተው በአጽንኦት እንዲያስቡ የሚረዳ መፅሀፍ ነው።

አዲስ ዘመን፡- መጽሃፉ ውስጥ የሰፈሩ ሃሳቦች በአሁኗ ኢትዮጵያ ምን ያህል ገቢራዊ ሊሆኑ ይችላሉ?

ዶክተር ኤርሲዶ፡- እነዚህ ነገሮች በእኛ ሀገር በጣም ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ናቸው። በመሰረቱ በዚህ ውስጥ የሰፈሩ ነገሮች ስለእኛ ሀገር አይደለም። ስለ ሰው ማንነት ነው። ስለንጹህ አዕምሮ ነው። ስለ ምክንያታዊነት ነው። ስለእውነት ነው። እውነት ድንበር የለውም። በእኛ ሀገር በሌላ ሀገር የሚባል ነገር የለውም። እውነት በማንም ሀገር ይሰራል፤ ሳይንስ በማንም ሀገር ይሰራል፤ የግለሰብ ነጻነትና በህይወት የመኖር መብት የፈረንጆች አይደለም። የጥቁሮችም አይደለም። የሰው ልጅ ነው። ሉዓላዊ ግለሰብ የፈረንጅ ወይም የአሜሪካ አይደለም። ሉዓላዊ ግለሰብ እንዳለ የሰው ልጅ ነው።

ስለዚህ እኛ እንደፈረንጆች፣ እንደምዕራቦቹ፣ እንደጃፓኖች እውነት ሰው ነን፣ እውነት እኩል ነን ብለን የምናምን ከሆነ ኑሮ ማፕ ውስጥ የተጻፉ ነገሮች ለእኛ ሀገርም ይሰራሉ። አይ ለነሱ ነው የሚሰራው ለእኛ አይሰራም ካልን እነሱ ሰው ናቸው፤ እኛ ደግሞ ከሰው በታች ነን ብለን እንደማሰብ ነው። ሰው ነን ብለን ካመንን፣ እንደሌሎቹ እኩል አዕምሮ ተሰጥቶናል ብለን ካመንን እዚህ ውስጥ ያሉት ምክንያታዊና ሳይንሳዊ አስተሳሰቦች ለሁሉም ሰው እኩል ናቸው። ብዙ ሰዎች እኛ ሀገር ይሰራል ወይ የሚል ጥያቄ ያነሳሉ። ይህን ከተጠራጠርንና ለነሱ ነው የሚሰራው ካልንና ሳይንስ በእኛ ሀገር አይሰራም ካልክ ከሰው ታንሳለህ ማለት ነው። አሜሪካን ሀገር የሚሰራ ሳይንስ ኢትዮጵያ ውስጥ ካልሰራ ኢትዮጵያውያን ከአሜሪካውያን ያንሳሉ እንደማለት ነው።

ሌላኛው ብዙ ሰው እዚህ ሀገር ውስጥ የማያውቀው በዓለም ገበያ ላይ አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር አይደለም የሚወዳደረው። ዶክተር ኤርሲዶ ከጆን ጋር ነው የሚወዳደረው። ግለሰቦችና ኩባንያዎች ናቸው በዓለም ላይ የሚወዳደሩት እንጂ ሀገሮች አይደሉም የሚወዳደሩት። ብዙ ጊዜ እኛ ምንሰራው ስህተት ይህ ነው። ስለዚህ አንድ ቻይናዊ ከአንድ ኢትዮጵያዊ በምንም አይበልጥም። እኩል ሰው ናቸው።

ያ ቻይናዊ ስላሰበና ስለሰራ ነው የሆነ ለውጥ እያመጣ ያለው። ኢትዮጵያዊውም ማሰብና መስራት ከቻለ ያንን ለውጥ ማምጣት ይችላል። ሀገሮችን ከሀገሮች ማወዳደር የለብንም። ኢትዮጵያን ከእንግሊዝ ጋር ካወዳደርን ለዘልዓለም እኛ ታች ፣ እንግሊዝ ደግሞ አንደኛ እያልን ነው የምንኖረው። እንደሱ አይደለም። በቃ ጆን የሚባለውን እንግሊዛዊ አበበ ከሚባለው ኢትዮጵያዊ ጋር ነው ማወዳደር ያለብን። አበበና ጆን እኩል አንጎልና ሴል ነው ያላቸው።

እኩል ናቸው እንደሰው ልጅ። ስለዚህ ያኛው አንጎሉን ተጠቅሞ ብዙ ነገር ከሰራ ይህኛውም አንጎሉን ተጠቅሞ ብዙ ነገር እንደሚሰራ ነው ማወቅ ያለበት።

ሀይሌ ገብረ ስላሴ ብዙ ምዕራባውያን አትሌቶችን መዘረር ከቻለ፤ አንድ ከበደ የሚባል ኢንቨስተር ከምዕራባውያን ኢንቨስተሮች ጋር መወዳደርና መዘረር ይችላል ማለት ነው። ሀገር ከሀገር ከማወዳደር አባዜ በመውጣት 100 ሚሊዮን ዜጎችን ሉዓላዊ ለማድረግ ማሰብ አለብን። ይህ ከአንድ ሰው ነው የሚጀምረው። እኔ ከራሴ ጀምሬለሁ። ሌላውም ሰው መጀመር አለበት። እንዲህ እያለ ኋላ ላይ አንድ ላይ ይመጣል ማለት ነው።

በጣም ትልቁ መልዕክት በኑሮ ማፕ ውስጥ ያለው እውነት በድምጽ ብልጫ አይወሰንም። ሚሊዮኖች ተደራጅተው ድንጋይን ዳቦ ማድረግ አይችሉም። ብዙ ሰው ስላመነው አንድ ነገር እውነት ነው ማለት አይደለም። ጥሩ ምሳሌ የብሄር ፖለቲካ ነው። አንድ ነገር ብዙ ስለቆየ፤ ያረጀ ውሸትም እውነት አይሆንም። ስለዚህ ሰዎች ብድግ ብለው መጠየቅ አለባቸው። እና ከዚህ የብሄር ቅዠት መውጣት አለባቸው።

አዲስ ዘመን፡- 2012 ዓ.ም ምን አይነት ዓመት ይሆናል ብለው ይጠብቃሉ?

ዶክተር ኤርሲዶ ፡- 2010 በጣም አሪፍ ዓመት ነበር። በሬዲዮ ፕሮግራሜ 2010 አንድ ዓመት አይደለም፤ ምን አልባትም አስር ዓመት ነው ብዬ ነበር። 2011 ከተግዳሮቶች አንጻር ስታየው አንድ ዓመት አይደለም። በጣም ብዙ ዓመት ነው። ከባድ ዓመት ነው። ነገር ግን እኔ 2012 በራሱ ጥሩ ዓመት ይሆናል ብዬ አልወስድም። በራሱም መጥፎ ዓመት ይሆናል ብዬ አልወስድም። 2012 ዜጎች በሚወስዱት ጥሩ እርምጃ ጥሩ ሊሆን ይችላል። ዜጎች በሚወስዱት መጥፎ እርምጃ መጥፎ ሊሆን ይችላል። ከዚህ አንጻር የአንድ ትልቅ ሰው አንድ አባባል አለ። ስለመጪው ጊዜ እርግጠኛ መሆኛው ብቸኛ መንገድ መጪውን ጊዜ መፍጠር ብቻ ነው እንጂ መጪውን ጊዜ መተንበይ አይደለም። ስለዚህ ዜጎች መጪውን ጊዜ መፍጠር አለባቸው የሚል እምነት አለኝ።

ልክ የሆነውን ነገር መስራት አለባቸው። እያንዳንዱ ሰው የራሱን ስራ መስራት አለበት። እያንዳንዱ ሰው የሚናገረው ንግግር በስልጡን ስነምግባር፣ በምክንያታዊነትና ሳይንስ ማሰብ አለበት። በግለሰብ በህይወት መብትና በህግ የበላይነት ስር መተግበር አለበት። ስለዚህ በዚህ ሁናቴ ከተራመድን መጪው 2012 በጣም ቆንጆ ይሆናል ብዬ አስባለሁ። መጪው 2012 ትልቅ ተግዳሮትም ያለው ዓመት ነው።

ምክንያቱም ምርጫም ስላለ ማለት ነው። ስለዚህ ይህ ምርጫ ይካሄድ አይካሄድ የሚለውን ኢትዮጵያውያን ዜጎች ስልጣን ላይ ያለው ገዢ ፓርቲ እና ሊፎካከሩ የሚፈልጉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ቁጭ ብለው እጅግ በሰለጠነ ስነምግባር፣ በምክንያታዊነትና ሳይንስ የምርጫ ትርጉም ምንድን ነው። ለምንድን ነው ምርጫ የሚያስፈልገው የሚለውን በደንብ አውቀው በግለሰብ ነጻነትና የህግ የበላይነት ስር ሆነው ለመስራት ተስማምተው በሥነ ሥርዓት መፈጸም አለባቸው ብዬ አስባለሁ። በዚያ ሁናቴ የሚካሄድ ከሆነ ጥሩ ይሆናል ብዬ አስባለሁ።

አዲስ ዘመን፡- በአዲሱ ዓመት ምኞትዎ ምንድን ነው?

 ዶክተር፡- የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሃይሎች ቁጭ ብለው ተስማምተው አሁን ያለውን የኢህአዴግ ገዥ መንግስት ማዕከል አድርገው፤ ማለትም እንደመሸጋገሪያ አድርገው እነሱም ገብተውበት ኢትዮጵያ ከአምስት እስከ ስድስት የሽግግር ዓመታት ቢኖራት ደስ ይለኛል። እነዚህ ዓመታት ውጥንቅጦችን በሙሉ ጥርግ አድርገን የምንጨርስበት ማለት ነው። ነገር ግን ሁሉን አንድ ላይ የስልጣን አካል መሆን አለባቸው።

ተፎካካሪዎችንም ስልጣን ላይ ያለውንም አካል መሆን አለባቸው። ሰው የሽግግር መንግስትም ይበለው ምንም ይበለው ነገር ግን ሁሉንም ያቀፈ መሆን አለበት። ነገር ግን የሽግግር መንግስት ከተባለ ያለውን አቁመህ አዲስ ተደራጅተህ ምናምን ነው መሆን ያለበት የሚሉ አሉ።

እኔ የማስበው ግን እንደሱ አይነት አይደለም።

መንግስት እንዳለ ሆኖ ነገር ግን ተፎካካሪ ፓርቲዎች ውክልና ኖሯቸው ገብተው ፓርላማውም ማሻሻያ ተደርጎበት እነሱም ገብተው አንድ አምስት ዓመት ቁጭ ብለን ፖሊሲያችንን ፍርድ ቤታችንን፤ የብሄር አስተሳሰባችንን፤ ኢኮኖሚውን ነጻ አድርገን ዜጎች በደንብ እየተንቀሳቀሱ የሚሰሩበትን፤ መንገድ ማመቻቸት ነው።

ጦራችንን፤ ምርጫ ቦርዳችንን፤ አስተዳ ደራችንን እስከ ታች ድረስ አሻሽለን፤ ህጎቻችንን እስከታች ድረስ አይተን፤ የሰዎች መንግስት የሆነውን የኢትዮጵያ መንግስት የህግ መንግስት አድርገን እንዲሆን የሚያደርግ በጣም የተረጋጋ የሚያደርግ የአንድ የአምስት፣ ስድስት ወይም ሰባት ዓመት የሽግግር ጊዜ ቢኖረን፤ በዚያው መካከል ኢኮኖሚው እያደገ፤ ኢንቨስትመንቱ እያደገ፤ ግን ዜጎች ሁሉ የተስማሙበት አንድ መንግስት፤ ማንም ገዥ ማንም ተገዥ ያልሆነበት ሂደት አድርገን በዚህ ጊዜ ውስጥ ተከራክረን፣ ተነጋግረን፣ ህዝበ ውሳኔ የሚያስፈልጋቸው ነገሮች ላይ ህዝበ ውሳኔ አካሂደን፤ የህገ መንግስት ማሻሻያ ተደርጎ እንደዚያ አይነት ሽግግር ብናደርግ ደስ ይለኛል።

አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ አካላት አሁን ያለው መንግስት በህዝብ የተመረጠ አይደለም ሲሉ ይደመጣሉ። እነዚህ አካላት ምርጫ ተካሂዶ አዲስ መንግስት ሳይመሰረት እንዲህ አይነት ማሻሻያዎች ሊደረጉ አይገባም ሲሉ ይከራከራሉ። እንዲህ አይነት አስተሳሰቦች ባሉበት ሁኔታ አሁን ያለው መንግስት ይህን አይነት ተግባራትን መፈጸም ይችላል ወይ?

ዶክተር ኤርሲዶ፡- ገዥው ፓርቲና ተቃዋሚ ዎች ተነጋግረው ይህንን ማድረግ ይችላሉ። እነሱ ከተስማሙበት ምንም የሚከብድ ነገር አይደለም። በዚያ ውስጥ ምሁራንም ሽማግሌዎችም፤ ህዝቡን የሚመራቸው ሰዎችም ተወክለውበት ማድረግ ይችላሉ። ልዩ ሸንጎ አይነት ነገር ፈጥረው መራመድ አለባቸው ብዬ ነው የማስበው። እርግጠኛ ከሆኑና ተስማምተናል፤ የህግ የበላይነቱም ተረጋግጧል የሚሉ ከሆነ ምርጫ ያድርጉ፤ ጥሩ ነው። የምርጫ ቅድመ ሁኔታ ግን መታወቅ አለበት።

ከምርጫው የምናገኘው ውጤት መታወቅ አለበት። የህግ የበላይነት መጀመሪያ ሥርዓት መያዝ አለበት። በየሰፈሩ ያለው ሚሊሻ ሥርዓት መያዝ አለበት። ይህ ሁሉ ሚሊሻ ባለበት ግን ምርጫ አካሂዶ በቀላል መላቀቅ ይቻላል ብሎ አሳንሶ ማየት ስህተት ነው ብዬ አስባለሁ። ስለዚህ መታሰብ አለበት። መነጋገርና መወያየት ያስፈልጋል ባይ ነኝ። ገዥው ፓርቲም መጠንቀቅ አለበት። አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ። ዶክተር ኤርሲዶ፡- እኔም አመሰግናለሁ።

አዲስ ዘመን   መስከረም 1 /2012

መላኩ ኤሮሴ