ቡና አምራቹን ተጠቃሚ ለማድረግ

41

የቡና መገኛ እንደሆነች የሚነገርላት ኢትዮጵያ ቡና ለማምረት ሰፊ እምቅ አቅም ቢኖራትም እስካሁን በአግባቡ መጠቀም ባለመቻሉ አርሶ አደሩም ሆነ ሀገሪቱ ተገቢውን ጥቅም እያገኙ አይደለም። ከበርካታዎቹ ችግሮች መካከለም በዘመናዊ መንገድ አለማምረት የገበያ ሰንሰለቱ ረዥም መሆንና እሴት መጨመር አለመቻል ቀዳሚዎቹ ናቸው። በቅርቡ የሀገሪቱን ቡና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በዓለም ገበያ ተገቢውን ዋጋ እንዲገያኝ ለማስቻል የአውሮፓ ሕብረት 15 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ የሚያደርግበት የኢዩ ኮፊ አክሽን ፎር ኢትዮጵያ ፕሮጀክት ይፋ ሆኗል። ፕሮጀክቱ ለአምስት ዓመት የሚዘልቅ ሲሆን ከላይ የተነሱትን መሰረታዊ የዘርፉን ማነቆዎች ለመቀነስ በር የሚከፍት ይሆናል ተብሎ እንደሚገመትም ተነግሯል።

የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ደኤታ አቶ ሳኒ ረዲ ፕሮጀክቱን አስመልክተው እንደተናገሩት፤ ፕሮጀክቱ ለአምስት ዓመት የሚቆይና ከአውሮፓ ህብረት አስራ አምስት ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ የተደረገለት ሲሆን፤ በኢትዮጵያ መንግሥትም በኩል በተጨማሪ በአይነትና በጉልበት የሚሸፈኑ ስራዎችንም ያካትታል። ፕሮግራሙ በዋናነት ትኩረት የሚያደርገው ምርታማ የሆኑና እየተከሰተ ያለውን የአየር ንብረት የሚቋቋሙ ዝርያዎችን ማፍለቅ፤ በአሁኑ ወቅት ያለው የኢትዮጵያ ቡና ግብይት ሥርዓት በጣም የተንዛዛና ብዙ ባለድርሻ አካላት ያሉት በመሆኑ ይህንን በማሳጠር ዋናውን አምራችና ሸማቹን ተጠቃሚ የሚያደርግ እንደሚሆንም ገልፀዋል። የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያን ቡና ከሚገዙ አገራት ትልቁን ድርሻ ይይዛሉ ያሉት ሚንስትር ደኤታው፤ ፕሮጀክቱ ይህንን ዘላቂ ለማድረግና ችግሮችን በጋራ ለመፍታት፤ እንዲሁም በቡናው ዘርፍ ትልቅ ለውጥ ያመጣል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።

ሚንስትሩ ጨምረው እንደተናገሩት፤ በተመሳሳይ ከዚህ ቀደም ይህንን ዘላቂ ለማድረግ ችግሮችን በጋራ መፍታት ይገባል በሚል የአውሮፓ ህብረት ‘ሲፕ’ የተሰኝ ፕሮጀክት ቀርፆ በየአምስት ዓመቱ አስራ አምስት ሚሊዮን ዩሮ እየደገፈ ሲሰራ ቆይቷል። በቡና ምርታማነትና ጥራት እንዲሁም የቡና በሽታ በተስፋፋበት ወቅት ደግሞ የቡና በሽታዎችን የሚቋቋሙ ዝርያዎችን በማምጣት ምርምሮችን ሲደገፍ የቆየ ቢሆንም የቡና ባለስልጣን ሲፈርስ ውጤት ሊያመጣ አልቻለም በሚል ፕሮጀክቱ ተቋርጦ ነበር። በ2008 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን እንደገና ሲቋቋም ፕሮጀክቱ እንደገና እንዲጀምር ጥያቄ ቀርባል። የአውሮፓ ህብረትም የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን እንደገና ከተቋቋመና መዋቅሩንም አምራቹ ድረስ ከዘረጋ፤ እንዲሁም ከምርምር ጋር ያለውን ግንኙነት ወደነበረበት ከመለሰ የጋራ ተጠቃሚ እንሆናለን በሚል ፈቃደኛ ሆኖ ይህንን ለአምስት ዓመት የሚቆይና አስራ አምስት ሚሊዮን ዩሮ የሚጠይቅ ፕሮጀክት ለመጀመር በቅቷል ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዱኛ ደበላ በበኩላቸው፤ ፕሮግራሙ ባለስልጣኑ ለይቶ ያቀረባቸውን ችግሮች መሰረት አድርጎ የተዘጋጀ ሲሆን፤ በሀገሪቱ ያለውን የቡና ምርትና ምርታማነት፤ እንዲሁም ጥራት በማሳደግ አርሶ አደሩንና በዘርፉ የተሰማሩትን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ይላሉ። እንደ ዶክተር አዱኛ ማብራሪያ፤ ፕሮግራሙ የሚተገበረውም የተሻሉ ቡና አምራች ተብለው በተለዩ በኦሮሚያ 16፤ በደቡብ 10፤ እንዲሁም በአማራ ሁለት ወረዳዎች ይሆናል። ፕሮጀክቱ ለአምስት ዓመት የሚቆይ ሲሆን ከተጠናቀቀ በኋላ እንዳይቋረጥ ከግሉ ዘርፍ ጋር እስከ ወረዳ ድረስ የማተሳሰር ሥራ የሚሰራ መሆኑንና በጠቅላለው አምስት ሚሊዮን የሚደርሱ አርሶ አደሮችን ተደራሽ እንደሚያደርግም ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ቡና ከሌላ ቡና ጋር ተቀላቅሎ እንዳይቀርብ ‘ብራንድ’ ላይ የማስተዋወቅ ሥራ በሌላ ፕሮጀክት እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ የገጠር ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ቡድን መሪ ሚስተር ዶሚኒክ ዶቮክስ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ከምትልከው ቡና 42 በመቶ ወደ አውሮፓ መሆኑን በማስታወስ፤ “ፕሮጀክቱ የጋራ ተጠቃሚ የሚያደርግ እንደሆነ ገልፀዋል። የቡድን መሪው ጨምረው እንደተናገሩት፤ የቡና ምርት በኢትዮጵያ አራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን የሚደርሱ አርሶ አደሮችን የያዘ ሲሆን እሴት በመጨመርና በሌሎች እንቅስቃሴዎችም አስራ አምስት ሚሊዮን ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጥር በመሆኑ ፕሮጀክቱ በርካቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው” ይላሉ። በሌላ በኩል፤ “የኢትዮጵያ ቡና በተፈጥሮ የበለፀገ ቢሆንም በዓለም አቀፍ ገበያ ተገቢውን ዋጋ እያገኘ አይደለም” ያሉት አስተባባሪው ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያ ቡና እውቅና ኖሮት ተገቢውን ዋጋ አግኝቶ አርሶ አደሩንም ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚረዳ አስረድተዋል።

“ረጅሙን እሴት የማይጨምር የንግድ ሰንሰለት በመበጣጠስ በቡና ንግድ ጉዞ አርሶ አደሩንና ላኪውን ብቻ ማስቀረት ይጠበቃል። ለዚህ ደግሞ በቀጥታ ላኪውና አርሶ አደሩ እንዲገናኙ ይደረጋል።” የሚሉት ደግሞ በኦሮሚያ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ምክትል ቢሮ ሃላፊና የቡናና ፍራፍሬ ዘርፍ ሃላፊ አቶ መሐመድ ሳኒ አሚን ናቸው። እንደ አቶ መሐመድ ማብራሪያ፤ እስካሁን ትኩረት ተሰጥቶ ሲሰራ የነበረው በምርት ወቅት አርሶ አደሩን ዘመናዊ መንገድ እንዲከተል በማድረግ የተሻለ ምርት ለማግኘት ነበር።

ይህም ቢሆን አብዛኛዎቹ አርሶ አደሮች ያልተማሩና እድሚያቸውም የገፋ በመሆኑ አዳዲስ አሰራርና ቴክኖሎጂ መቀበሉ ላይ ተግዳሮት አለ። አንዳንዴ ያረጀውን ቆርጦ አዲስ ለመተካት ‘ድሮ አባቴ የተከለውን አልቆርጥም’ እስከ ማለት የሚገዳደሩ ነበሩ። ለዚህም በሰርቶ ማሳያ በባለሙያ ተደጋጋሚ ክትትል እየተደረገ ሲሆን ለውጥም እየተገኘ ነው። ለአርሶ አደሩ የምርት ብዛት ሳይጨምር ጥራቱን በመጠበቁ ብቻ ገቢውን ማሳደግ እንደሚችል እንዲያውቅ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እየሰጠን ነው። ‘ኢዩ ካፌ’ በክልሉ የሚተገበርባቸው ወረዳዎች እስካሁን ምንም ፕሮጀክት ያልተያዘባቸው፤ ነገር ግን ከፍተኛ ቡና ለማምረት አቅም ያላቸው ናቸው። ግብይቱን የተስተካከለ በማድረግ ምርቱ ለሀገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ገበያ ሲቀርብ የነበረውን የተንዛዛና አርሶ አደሩንና ተጠቃሚውን ሳይሆን ደላላውን ተጠቃሚ ያደርግ የነበረውን አካሄድ ለማስቀረት ብዙ አልተሰራም። አሁን ግን በፕሮግራሙ ይኸ ዋናው የትኩረት አቅጣጫ ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል፤ “በክልሉ አዲስ መሬት ላይ በተለይ አሲዳማ አፈር ባለባቸውም ቢሆን ቡና አሲዳማ አፈር መቋቋም የሚችል መሆኑን ከግምት በማስገባት መንግሥት ድጋፍ የሚያደርግበት በአስር ዞኖች ውስጥ ባሉ 75 ወረዳዎች ተግባራዊ የሚሆን ፕሮጀክት ፀድቆ ወደ ሥራ እየተገባ ነው” ያሉት ሃላፊው፤ ባጠቃለይም በክልሉ በ2011 ዓ.ም 996 ሺ 586 ሄክታር መሬት በቡና ተሸፍኖ የነበረ ሲሆን፤ በ2012 ይህንን ቀጥር አንድ ሚሊዮን 46 ሺ 412 ሄክታር በማድረስ ሰባት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል የቡና ምርት ለማግኘት ዕቅድ መያዙንም ጠቁመዋል።

የደቡብ ክልል ቡና፤ ሻይና ቅመማ ቅመም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፍን ቃሮ በበኩላቸው፤ “የንግድ እንቅስቃሴውን በተመለከተ እንደ ሀገርም፤ እንደ ክልልም ያለው የተንዛዛ ሂደት ሥር የሰደደ ችግር በመሆኑ ይህንን የማስወገዱ ተልዕኮ በፕሮግራሙ ሊታቀፍ ችሏል” ይላሉ። እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፤ እስካሁን ባለው አካሄድ በአርሶ አደሩና በአቅራቢው መካከል ደላላ አለ። በአቅራቢውና በላኪውም መካከል ደላላ አለ። እነዚህ ደላሎች ደግሞ ዋጋ እስከመወሰን የሚደርሱ ከመሆናቸው ባሻገር ሌሎች አሻጥሮችንም ይሰራሉ። ችግሩ አሳሳቢ በመሆኑ ከሁለት ዓመት በፊት መንግሥት አዋጅ ቁጥር 1051/2009ኝ ያወጣ ሲሆን፤ ዘንድሮም አዋጁን ለማስፈፀም የሚረዳ መመሪያ አዘጋጅቶ ወደተግባር ገብቷል።

በዚህም መሰረት በደቡብ ክልል መመሪያውን ተግባራዊ በማድረግም በአሁኑ ወቅት በአቅራቢና በአርሶ አደር መካከል ያለውን ደላላ ለማስወገድ እያንዳንዱ ሳይት ቡና እንዲሸጥ አቅጣጫ ተቀምጧል። በተጨማሪም፤ ከዚህ በፊት በምርት ገበያ ባለስልጣን በኩል ብቻ የሚከናወነው ግብይት ቀርቶ አርሶ አደሩ ራሱ ቡናውን ወደ ውጭ እንዲልክ ከፈለገ ለምርት ገበያ እንዲያስረክብ እየተደረገ ነው። በዚህም አሁን ላይ አቅራቢው በቀጥታ ከላኪው ጋር መገናኘት ችሏል። እስካሁንም ከ350 በላይ አርሶ አደሮች የላኪነት ፈቃድ እንዲወስዱ ተደርጓል።

በሌላ በኩል፤ በክልሉ የሰለጠነ የልማት ሠራተኛ እጥረት እንዳለ በማስታወስ ቡናን ብቻ ስፔሻላይዝድ ያደርጉ ባለሙያዎች በከፍተኛና በመካከለኛ ቡና አብቃይ አካባቢዎች እንዲኖሩ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። በአሁኑ ወቅት በክልሉ 870 ሺ ሄክታር መሬት በቡና ተሸፍናል። ከዚህ ውስጥ ደግሞ ምርት የሚሰጠው እናት ቡና 574 ሺ ሄክታር አካባቢ እንደሆነ ይገመታል። በቀጣዩ 2012 በጀት ዓመትም 560 ሺ ቶን ቡና ይገኛል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፤ ከሀገር ውስጥ ፍጆታና በምርትና ድህረ ምርት ወቅት የሚባክነውም ተቀንሶ ከክልሉ ለማዕከላዊ ገበያ 128 ሺ ቶን ቡና ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል ሲሉ ተናግረዋል።

አዲስ ዘመን መስከረም 2/2011

 ራስወርቅ ሙሉጌታ