ጥበብ- ከማዝናናት ባለፈ ለፈውስ

13

በጥበብ የአዕምሮ ህሙማንን ማከም በዓለማችን ላይ ዘለግ ያሉ ዘመናትን ማስቆጠሩን የተለያዩ መረጃዎች እና በዘርፉ ላይ የሚገኙ ምሁራን ይጠቁማሉ። ይህን የህክምና ዘዴ ምንነት እና ትርጓሜ የብሪቲሽ የአዕምሮ ህሙማን የአርት ቴራፒስት ማህበር ‹‹ህሙማኑን የተለያዩ የጥበብ ሥራዎችን በዋናነት እና በቀዳሚነት በመጠቀም ለመፈወስ የሚሠራ ሙያ ነው›› በማለት ሲያስቀምጠው፤ በተመሳሳይ የአሜሪካ የአርት ቴራፒ ማህበር በበኩሉ ‹‹ትኩረቱን በዋናነት የአዕምሮ ህሙማን ላይ በማድረግ ግለሰቦችን፣ ቤተሰብ እንዲሁም ማህበረሰብን በተቀናጀ ጥበባዊ የፈጠራ ክህሎት የሥነ ልቦናና ተያያዠ ችግሮችን ለመፍታት የሚሠራ ነው›› ይለዋል።

እነዚህ ሁለት ታላላቅ ማህበራት በተለያየ ቋንቋ ነገር ግን በተመሳሳይ አላማ የሙያውን አስፈላጊነት አጉልተው በማሳየት የህክምና ዘርፍ ላይ ሙያው ጉልህ ድርሻ መጫወት የሚችል መሆኑን ያስገነዝባሉ። በተለይ ጥበብ ከመዝናኛ እና ነብስያን ከማስፈንጠዣነቷ በዘለለ የፈውስ እንክብል መሆኗን ይመሰክራሉ።

አርት ቴራፒ በሰለጠኑ እና ወደፊት በተራመዱት አገራት ውስጥ ትኩረት ይሰጠው እንጂ ተመሳሳይ የህክምና ትኩረት የሚሹ ዜጎች ባሉባት አህጉረ አፍሪካ እና በኢትዮጵያ ይህ ነው የሚባል አሻራ የለውም። ሙከራ በሚባል ደረጃና በግለሰቦች ጥረት ጅምር እንቅስቃሴዎችን የሚያደርጉ አካላት ግን አልጠፉም።

ከላይ በመግቢያችን ላይ ለማንሳት እንደሞከርነው ይህን ቁልፍ ጥበባዊ የህክምና ዘርፍ በዛሬው የኪነ ጥበብ አምዳችን ላይ በስፋት በማንሳት በተለይ በኢትዮጵያ ውስጥ በተገቢው ትኩረት አግኝቶ ተግባራዊ ቢደረግ የአዕምሮ ህክምና ዘርፉን በእጅጉ ሊጠቅም እንደሚችል ለማሳየት እንሞክራለን። ለሙያው ትኩረት የሰጡ ባለሙያዎችም ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ቆይታ አድርገዋል።

አርቲስት ብርሃኔ ጌታቸው የአዕምሮ ህሙማንን በኪነ ጥበብ ሥራዎች እና በአርት ቴራፒ ሙያ ለማከም በሚደረግ ጥረት ላይ ቀዳሚ ተሳታፊ ነው። ያለውን የሙዚቃ እና የፊልም የኪነ ጥበብ ሙያ መሰረት አድርጎ የስነ ልቦና ችግርና የአዕምሮ ህሙማንን ለማገዝ የሚያስችል ፕሮጀክቶችን በመንደፍ ተግባራዊ ሥራ ለመሥራት ጥረት ያደርጋል። ከህክምና ተቋማት ጋር በመቀናጀትም በርካታ ኪነ ጥበባዊ ሥራዎችን በማዘጋጀት ቀዳሚ ነው።

አርቲስት ብርሃኔ እንደሚናገረው የአዕምሮ ህሙማንን በተመለከተ በጥበብ ሥራው ትኩረት መስጠት የጀመረው ሃሬድ በሚለው የአማርኛ ፊልሙ ላይ ነበር። ይህን የፊልም ሥራ ለመሥራት የሥነ ልቦና እና የአዕምሮ ህክምና ባለሙያዎችን በሚያማክርበት ወቅት የጥበብ ሥራዎች በህክምናው ዘርፍ ላይ ትልቅ ድርሻ እንዳላቸው መረዳቱን ይናገራል። በተለይ ታማሚዎችን በፍቅር ቀርቦ ኪነ ጥበባዊ በሆኑ ሥራዎች መንከባከብ ውጤቱ ግዙፍ መሆኑን ሲረዳ ሰፊ ሥራዎችን ለመሥራት ማቀድ መጀመሩንም ይናገራል።

አርቲስት ብርሃኔ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከአማኑኤል የአዕምሮ ህሙማን ሆስፒታል ጋር በጋራ በመሆን የአርት ቴራፒ በጥበብ ታካሚዎችን የመንከባከብ ሥራዎችን ማከናወን ጀመረ። በፊልሙ ላይ ሳይገደብም የሙዚቃ ኮንሰርቶችን በማሰናዳት አንጋፋና ወጣት ሙዚቀኞችን ከታካሚዎች ጋር በማገናኘት ውጤታማ የሆኑ ሥራዎችን ማከናወኑን ተያያዘው። ያገኘው የመጀመሪያ ውጤትም አበረታቶት ሥራውን ይበልጥ እንዲያጠናክረውም አገዘው።

‹‹የሥነ ልቦና እና የአዕምሮ ህሙማን አብዛኛውን ጊዜ መገለል ይደርስባቸዋል›› የሚለው አርቲስት ብርሃኔ ይህ ሂደት ከህመሙ በላይ እንደሚጎዳቸው ይገልፃል። በተለይ በቶሎ ፈውስ እንዳያገኙ ምክንያት እንደሚሆንም ያነሳል። ይህን ችግር ለመቅረፍም ኪነ ጥበባዊ ይዘት ያላቸው የህክምና ዘዴዎች ቁልፍ መሆናቸውን ይናገራል። አርቲስቶች ሥራዎቻቸውን ከነዚህ ህሙማን ጋር ቢያቀርቡ እና የአርት ቴራፒ ሙያ ቢስፋፋም ችግሩን ለማቃለል ሁነኛ መፍትሄ መሆኑን ይጠቁማል።

በዘርፉ ላይ እንደ ጅምር ያስገኘለትን ስኬት ተጠቅሞ ሙያውን ማሳደግ እንደሚፈልግ የሚናገረው አርቲስት ብርሃኔ በሙዚቃው እና በፊልሙ ላይ ብቻ ሳይገደብ ሁሉንም የጥበብ ዘርፎች በማካተት ወጥ ሥራ ለመሥራት ዝግጅቱን እንዳጠናቀቀ ይናገራል። በተለይ በርካታ ሚሊዮኖች የሚያዩት የበዓላት ፕሮግራም ላይ የቴሌቪዥን ሾው ከማቅረብ ባለፈ ተከታታይ ሥራዎችን ለመሠራት በሂደት ላይ ይገኛል።

ይህ ጥረቱ አርት ቴራፒ ሙያን በኢትዮጵያ እንዲያድግ በር ይከፍታል የሚል እምነትም አለው። በህክምናው ሙያ ላይ የሚገኙ ሳይካቲርስቶች እና ሃላፊዎች በሙሉ ድጋፍ እና ቀናነት በትብብር ከእርሱ ጋር በመሥራት ላይ መሆናቸውም ደግሞ ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግለት ነው የገለፀው።

ዶክተር ዳዊት አሰፋ ይባላሉ። በየካ ኮተቤ ሆስፒታል የአእምሮ ህክምና ስፔሻሊስት ከመሆናቸው ባለፈ የኢትዮጵያ የአዕምሮ ህክምና ማህበር ፕሬዚዳንት ናቸው። አርት ቴራፒ በኪነ ጥበብ ሥራዎች የአዕምሮ ህሙማንን ማከም እንደሆነ በማንሳት የትኛውንም የኪነ ጥበብ መንገድ ለዚህ መሰል አላማ መጠቀም እንደሚቻል ይናገራሉ። በተለይ ሙዚቃ፣ ድራማ እንዲሁም ስዕልን የመሳሰሉ የጥበብ ሥራዎች ታማሚዎችን ለመፈወስ ግብአት ናቸው።

በተለይ ታካሚዎች ስሜታቸውን በኪነ ጥበባዊ ሥራዎች ሲገልፁ አንዱ የመተንፈሻ መንገድ እንደሚሆናቸው ይናገራሉ። የጥበብ ክህሎት ተሰጦ ያላቸው ህሙማንም አሳታፊ ለማድረግ እና ወደ ቀድሞ ጤንነታቸው እንዲመለሱ ለማገዝ እንደሚረዳም ያስረዳሉ።

‹‹በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሰለጠኑት የዓለማችን ክፍላተ አገራት የአርት ቴራፒ አጥጋቢ በሆነ መንገድ አልተስፋፋም። በስፋት መተግበር ቢችል ግን ውጤታማ እንደሚሆን በሳይንሱ የተረጋገጠ ነው›› የሚሉት ዶክተር ዳዊት፤ ይህን ለማሳካት የህክምናውን እና የጥበብ ተሰጦን ያማከለ አርት ቴራፒስት ባለሙያ አስፈላጊ መሆኑን ያነሳሉ። ጥበባዊ ሥራዎች ለታማሚዎች ብቻ ሳይሆን ለመላው ማህበረሰብም ግዙፍ ሥነ ልቦናዊ ፋይዳ እንዳላቸው ነው በምክረ ሐሳባቸውን የሚያስቀምጡት።

በምንኩስናው ዓለም የሚያውቋቸውን አንድ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ አባት እንደ ምሳሌ በማንሳትም የጥበብ ፋይዳው አለማዊም ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊም መሆኑን ያነሳሉ። ይህን ትልቅ የአዕምሮ ውጤት በህክምናውም ሆነ በየዕለት ኑረታችን ውስጥ አንዱ አካል ማድረግ ከቻልን ከጥልቅ ድብርትም ሆነ ውጥረት የሚያላቅቀን ፈውስ መሆኑን ይመሰክራሉ።

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከቅርብ ጊዜ በፊት ባወጣው ዳሰሳዊ ጥናት እስከ 27 በመቶ የሚሆነው የማህበረሰብ ክፍል በየደረጃው የአዕምሮ ህመም ተጠቂ ሊሆን እንደሚችል አስቀምጧል። የአዕምሮ ጤና ችግር የሚባለው እብደት ብቻ አይደለም። ከ360 በላይ የህመም አይነቶች መኖራቸውንም ዓለም አቀፍ ጥናቶች ይጠቁማሉ። ዶክተር ዳዊት የአዕምሮ ህመም ያለባቸው ዜጎች በርካታ ቢሆኑም ወደ ህክምናው የሚመጡት ግን ከ10 በመቶ የሚበልጡት እንዳልሆኑ ጠቁመው በተገቢው መንገድ ክትትል የሚያደርጉትም ከሁለት በመቶ እንደማይዘሉ ያነሳሉ።

ከዚህ መነሻ ዋናውን የህክምና መንገድ በአግባቡ መድረስ ሳይቻል አርት ቴራፒው ላይም በተገቢው መንገድ መሄድ አስቸጋሪ እንደሚሆን እንደምክንያት ይጠቅሳሉ። ነገር ግን አንዳንድ ጅምሮች መኖራቸው ይበል የሚያሰኙ መሆናቸውን ይናገራሉ።

‹‹ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የኪነ ጥበብ ሙያቸውን ተጠቅመው በአርት ቴራፒ ህሙማንን ለማገዝ በጎ ምግባር የሚያከናውኑ አካላት እየተፈጠሩ ነው›› የሚሉት ዶክተር ዳዊት፤ ከነዚህ ውስጥ ብሬ ማን የፊልም ፕሮዳክሽን አንዱ እንደሆነ ይገልፃሉ። ከዓመታት በፊት በተጀመረው በዚህ ጥረት ላይ በርካታ ኪነጥበባዊ ሥራዎችን በማዘጋጀት ህሙማኑን ለመርዳት መቻሉንም በማንሳት ይህን አመርቂ ጅማሮ ላደረገው የፊልም ባለሙያ አርቲስት ብርሃኔ ምስጋናቸውን ያቀርባሉ። በተለይ ሳይንሳዊ መንገድ ተከትሎ ውጤቱን ለጊዜው ይፋ ማድረግ ባይቻልም አመርቂ ለውጦች እየተመዘገቡ መሆኑን ይገልፃሉ።

እንደ ህክምና ስፔሻሊስቱ እሳቤ በጅምር የተጠነሰሰው የአርት ቴራፒ ሃሳብ ሰፊ የማህበረሰብ ንቅናቄ ለመፍጠር ድርሻው ላቅ ያለ ነው። ይሄን በጎ ምግባር ፊት ላይ ሆኖ እየመራው ያለው አርቲስት ብርሃኔን እና ሌሎች መሰል አካላትን መደገፍ ደግሞ ሙያው ወደፊት እንዲራመድ ዕድል ይሰጠዋል የሚል እምነት አላቸው። ከዚህ ቀደም እርሳቸው በዋና ዳይሬክተርነት የሚመሩት የአማኑኤል ሆስፒታል ውስጥም በስዕል ሥራዎች ተመሳሳይ ሙከራዎች ሲደረጉ መቆየታቸውን አንስተው አሁንም ይሄን መሰል ሂደት ለማስቀጠል የሚተገበሩ ሥራዎች ስለመኖራቸው መረጃ እንዳላቸው ገልፀዋል። ከዚህ በተጨማሪ ከአለ ፈለገሰላም የስዕል ትምህርት ቤት ጋር በመቀናጀት ይህ ሙያ እንደ ዋና የትምህርት አይነት በቋሚነት ለመስጠት ሙከራዎች እየተደረጉ እንደሆነም ተናግረዋል።

ዶክተር ዳዊት የአዕምሮ ህክምና ማህበሩ እና ሆስፒታሎቹ ከኪነ ጥበብ እና የጥበብ ተሰጦ ካላቸው ማናቸውም አካላት ጋር በመተባበር ሙያውን ለማሳደግ ፍላጎት እንዳላቸው ያነሳሉ። በተለይ ሙያው መሰረት እንዲይዝ የጥበብ ቤተሰቡ በበጎ ፍቃድ አብሯቸው እንዲሠራ ጠይቀዋል። በፊልሙና በሙዚቃው ዘርፍ አርቲስት ብርሃኔ ጌታቸው፤ በቲያትሩ ዘርፍ ደግሞ እንደነ አርቲስት ፋሲል ግርማ አይነት ተነሳሽነት እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፤ መንግሥት ጥበብ ከማዝናናት ያለፈ የፈውስ ምክንያት መሆኑን ተረድቶ ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው ጥሪ አቅርበዋል።

አዲስ ዘመን  መስከረም 4/2012

 ዳግም ከበደ