መገናኛ ብዙሃን የአሳታፊነትና ሚዛናዊነት ችግር ይታይባቸዋል ተባለ

37

አዲስ አበባ፡- ባለፈው ዓመት በአገሪቱ ዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሳተፉና ሃሳባቸውን እንዲገልፁ እድሉን በማመቻቸትና በሚዛናዊነት ረገድ መገናኛ ብዙሃን ውስንነቶች እንደተስተዋለባቸው የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና ምሁራን ተናገሩ፡፡

የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስና የመድረክ ሰብስብ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፣ ለጋዜጣው ሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ባለፈው ዓመት መገናኛ ብዙሃን ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሳተፉና ሃሳባቸውን እንዲገልፁ እድሉን በማመቻቸትና ከወገንተኝነት በፀዳ መልኩ በሚዛናዊነት ሥራቸው ለመስራት ሲቸገሩ አስተውለዋል፡፡

‹‹መገናኛ ብዙሃን አንዳንድ ጊዜ እኔ በጠበኩት ሳይሆን ባልጠበኩት መልኩ መረጃን በማስተላለፍ ነገሮች የማራገብ የማንጫጫትና ለተወሰኑት ኃይሎች የመወገን ዝንባሌ አይቼባቸዋለሁ›› ያሉት ፕሮፌሰር መረራ፣ውይይት ብለው የሚያዘጋጇቸው መድረኮችም የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋትና ለማጎልበት በሚረዳና አቅጣጫ በሚያሳይ መልኩ የሚቃኝ አለመሆኑን አብራርተዋል፡፡ ይህ ጉዳይ በአዲሱ ዓመት ሊስተካከል እንደሚገባውም አፅንዖት ሰጥተውታል፡፡

የኢትዮጵያ አንድነት ዴሞክራሲ ድርጅት ፕሬዚዳንት አቶ አድማሱ ሃይሉ በበኩላቸው፣መገናኛ ብዙሃን ባለፈው ዓመት ለተወሰኑ ፓርቲዎች ብቻ እድል ሲሰጡ መቆታቸውን ተናግረዋል፡፡ በትውውቅና በዝምድና ሲሰራ እንደነበርም ጠቁመዋል፡፡

መገናኛ ብዙሃኑ በአገሪቱ ዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ላይ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሳተፉና ሃሳባቸውን እንዲገልፁ በማመቻቸት ረገድ ውስንነቶች እንደነበሩባቸው ያስታወሱት አቶ አድማሱ፣ ነገን የተሻለ ለማድረግ ይህ መስተካከል አለበት ብለዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰብዓዊ መብትና ፌዴራሊዝም ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ መንግስቴም፣ሀሳብን በነፃነት ከማራመድ አንፃር መገናኛ ብዙሃኑ አማራጭ በመሆን ማገልገላቸውን አስታውሰዋል።

እንደ ረዳት ፕሮፌሰሩ ገለፃም‹ ባለፈው ዓመት ለውጦችን ቀጣይ ለማድረግ የሚታትሩና ለጉዳዩ ትኩረት የሚሰጡ መገናኛ ብዙሃንን መመልከት የተቻለ ቢሆንም ከዚህ በተቃርኖ ሙሉ በሙሉ ለውጦችን በመቃወም ብቻ የተጠመዱና በለውጡ የታዩ ተስፋዎችን የሚያጨልሙም ነበሩ።

ከዚህ ባሻገር አንዳንዶቹ ጥላቻን የማስፋትና ለግጭት ትኩረት የመስጠት አዝማሚያ እንደተስተዋለባቸው የጠቆሙት ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ በአዲሱ አመት ለውጥ እንዲመጣ ከተፈለገ ይህ አይነቱ አካሄድ ሳይውል ሳያድር መስተካከል እንዳለበት አፅንኦት ሰጥተውታል። ‹‹‹ሚዛናዊ ለሆነ ዘገባ ትኩረት መስጠት፣አሉታዊ ነገሮችን በስፋት ከማራገብ ይልቅ አንድነታችንን ማጉላት፣ መተሳሰባችንን ይበልጥ ማሳየትና መልካም ነገሮች ላይ ተጨማሪ ትኩረቶችን መስጠት ይገባቸዋልም›› ብለዋል።

አዲስ ዘመን መስከረም 6/2012

 ታምራት ተስፋዬ