የከተማዋ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን

57

. ከተማዋ ከሚጠበቀው በላይ የኢንቨስትመንት ፍሰት እየመጣላት ነው

. የ11 ባለኮከብ ሆቴሎች ግንባታ ወደ ትግበራ ይገባል

. በኪራይ ቤት የኢንቨስትመንት ስራ እየሰሩ ለሚገኙ ባለሀብቶች ቦታ ያቀርባል አለ

 አዲስ አበባ፡- አዲስ አበባ ከእቅድ በላይ የኢንቨስትመንት ፍስት እየታየባት መሆኗን እና በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ያስቀመጣቸውን ግቦች ማሳካት መቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢንቨስትመንት ከሚሽን አስታወቀ። የ 11 ባለኮከብ ሆቴሎች ግንባታ ወደ ትግበራ እንዲገባ የከተማዋ ካቢኔ ውሳኔ ማሳለፉንም ገልጿል።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አቶ አብዱልፈታ የሱፍ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፣ ከተማዋ የሀገሪቱ መዲና፣ የአፍሪካ ህብረት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ መሆኗ እንዲሁም ባለፉት ዓመታት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተው አለመረጋጋት ያልታየባት እንደመሆኗ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲታይባት አድርገዋል።

ባለፈው ዓመት ብቻ ከ2ሺ 500 በላይ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ መውሰዳቸውን ኮሚሽነሩ ጠቅሰው፣ወደ 40 ሺ ኢንቨስተሮች በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ እየሰሩ መሆናቸውንም አስታውቀዋል። ‹‹በአጠቃላይ ሲታይ የኢንቨስትመንት ፍሰቱ ካቀድነው በላይ እየሄደ ነው ›› ብለዋል።

ኮሚሽኑ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የኢንቨስተሮችን ቁጥር ከነበረበት 40 ሺ ወደ 50 ሺ ለማድረስ ማቀዱን ተናግረው፣‹‹በየዓመቱ የታየውን ፍሰት ስንመለከት ኢንቨስትመንቱ ከአንድ ነጥብ አምስት በመቶ በላይ እየጨመረ መጥቷል›› ሲሉም አብራርተዋል። ይህም ኮሚሽኑ ሁለተኛውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱን በከፍተኛ ደረጃ እያሳካ ስለመሆኑ አንድ ማሳያ መሆኑን አስታውቀዋል።

የመሬት አቅርቦት ለኮሚሽኑ ተግዳሮት እንደሆነበት ገልጸዋል። ይህን ችግር ለመፍታት ውስን መሬት በሚፈልጉ፣ የኢንቨስትመንት ተልእኮውን ሊያሳኩ በሚችሉ፣ የሀገሪቱን መሰረታዊ ችግር በሚፈቱና ገበያውን በሚያረጋጉ ምርቶችና አገልግሎቶች እንደዚሁም የውጭ ምንዛሪ በሚያስገኙ ዘርፎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል። ሰፊ መሬት የሚፈልጉ ኢንቨስትመንቶች ወደ ክልሎች እንዲሄዱ ከሚመለከታቸው ጋር እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

‹‹የመሬት እጥረትን ለመፍታት በአንድ በኩል ያሉትን ቦታዎች በቁጠባ እና አዋጭ በሆነ መስክ ላይ በማዋል ለመስራት እየተንቀሳቀስን ነው።›› ያሉት ኮሚሽነር አብዱልፈታ ፣ሰፊ የሥራ እድል በሚፈጥሩና የውጭ ምንዛሪ በሚያስገኙ እንደ ሆቴልና ቱሪዝም እንዲሁም የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂን በሚጠቀሙ ኢንቨስትመንቶች ላይ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

እንደ ኮሚሽነር አብዱልፈታ ማብራሪያ፤ ከተማዋ በጣም ብዙ ህዝብ ይኖርባታል። ስለዚህ ብክለት የሚያስከትሉ የኢንቨስትመንት መስኮች ወደሌላ አካባቢ እንዲሄዱ ለማድረግ ከባለሀብቶች በጋራ ይሰራል። ይህን የማመቻቸት ሥራም ወደፊት የሚከናወን ይሆናል።

በሥራ ላይ ያሉ ግን በኪራይ እየተሰቃዩ ያሉ ባለሀብቶች በቅድሚያ መሬት እንዲያገኙ ለማድረግ እንደሚሰራ ጠቅሰው፣ እነዚህ ሥራዎች የሥራ እድል ፈጠራውን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያበረታቱም ጠቁመዋል።

ኮሚሽነሩ ብዙ ቦታ በማይጠይቁ እንደ ሆቴል፣የኢንፎርሜሸን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂን በሚጠቀሙ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ጠቅሰው በተጨማሪም በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ኢንቨስትመንት ላይም በትኩረት እንደሚሰራም ተናግረዋል::

የሆቴል ኢንቨስትመንት ሲስፋፋ ቱሪዝሙም እንደሚያደግ እና የውጭ ምንዛሪ ግኝቱ እንደሚጨምር ጠቅሰው፣‹‹ለዚህም እኛ በተቻለ መጠን ባለኮከብ ሆቴሎችን የሚገነቡትን ለማበረታታት እንሰራለን። በዚህም ከአምስትና ከዚያ በላይ በሆኑት ሆቴሎች ላይ እናተኩራለን›› ብለዋል።

በቅርቡም ባለኮከብ ደረጃ ያላቸው ወደ 11 ሆቴሎች ቦታ ቀርቦላቸው ወደ ትግበራ እንዲገቡ ውሳኔ መተላለፉን ጠቅሰው፣ ሆቴሎቹን የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ከውጭ ባለሀብቶች ጋር በሽርክና የሚገነቧቸው መሆናቸውንም አመልክተዋል።

የእነዚህ ሆቴሎች ግንባታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ትግበራ እንዲገባም ካቢኔው ውሳኔ ማሳለፉንና የካፒታል መጠናቸውም በጣም ብዙ መሆኑን አመልክተዋል። ለአንድ ሆቴል ብቻ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ የካፒታል መጠን የቀረበበት ሁኔታ እንዳለም ጠቅሰዋል። ይህም የሆቴል ኢንዱስትሪውን በከፍተኛ ደረጃ ያሳድገዋል›› ሲሉም ገልጸዋል።

‹‹አሁንም እየቀረቡ ያሉ የሆቴል ልማት ጥያቄዎች አሉ። ለእነዚህ የሆቴል ልማት ጥያቄዎች የሚያስፈልገው ቦታ እንደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ካሉ ኢንቨስትመንቶች አኳያ ሲታይ በጣም ውስን ሲሆን የሚፈጥረው የኢኮኖሚ ፋይዳ ግን በጣም ብዙ ነው።›› ብለዋል።

 አዲስ ዘመን መስከረም 6/2012

 ኃይሉ ሣህለድንግል