ኤጀንሲው የድርጅቱን መልካም ሥም እንዳያነሳ እግድ ተጣለበት

234

አዲስ አበባ፡- የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ የኤ ቢ ኤች (ጥምረት ለተሻለ ጤና) ሰርቪስስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል አማካሪ ድርጅትን መልካም ሥም ከማንሳት እንዲቆጠብ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እግድ እንደጣለበት የመዝገብ ግልባጩ አስነብቧል፡፡

በመዝገብ ቁጥር 241863 በ 02/01/2012 ዓ.ም የወጣው መዝገብ ግልባጭ እንደሚያመላክተው፤ ኤጀንሲው የአማካሪ ድርጅቱን መልካም ሥምና ዝናን በማንሳት ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ጋር አያይዞ ለመገናኛ ብዙሃን ሲሰጥ የነበረው መረጃ አግባብነት የለውም።ድርጊቱም በድርጅቱ ላይ ጉዳት ሊያደርስ ስለሚችል ኤጀንሲው የዚህ ዓይነት መሠል ተግባር እንዳይፈጽም ወይም የድርጅቱን መልካም ሥም ማንሳት እንዲያቆሙ የእግድ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ከሳሽ አማካሪ ድርጅቱ እንዲሁም ተከሳሾች ኤጀንሲውና አምስት የሥራ ኃላፊዎቹ የሆኑበት ይህ መዝገብ የግራ ቀኙን አቤቱታና ምላሽ እንደተስተናገደ አብራርቷል።አማካሪ ድርጅቱ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ላይ የተሰማራ የንግድ ማህበር መሆኑን በመጥቀስ ከዓለምና አገር አቀፍ ተቋማት ጋር የትብብር ስምነቶችን በማድረግ ትልልቅ የአገር ውስጥ ፕሮጀክቶችን በውል ስምምነት በመውሰድ አገራዊ ፋይዳ ያላቸውን አገልግሎቶች እንደሚሰጥ በአቤቱታው አቅርቧል።

በዚህም ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ጋር ባደረገው የትብብር ስምምነት ላለፉት ስድስት ዓመታትና ለቀጣይ ስምንት ዓመታት የውል ግዴታ ገብቶ ሲሠራ ቢቆይም ተከሳሹ ግን በመገናኛ ብዙሃንና የተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች የሐሰት መግለጫዎችን ሲሰጡ መቆየታቸውን አስፍሯል።ይህም የተከሳሾች ድርጊት የድርጅቱን መልካም ሥምና ዝና በማጥፋት ተግባር በመፈፀም፣ ከዩኒቨርሲቲው ጋር የገባውን የውል ግዴታ እንዳይወጣና ከሐምሌ ወር 2011 ዓ.ም ጀምሮ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ሁከት በመፈፀም በድርጅቱ ላይ ከፍተኛ የገንዘብ ኪሳራ እያደረሱ መሆኑን አቅርቧል።በዚህም ደንበኞቻቸው እየቀነሱና ዕምነት እንዲያጡ እያደረጉ መሆናቸውን በአቤቱታቸው አሰምተዋል፡፡

አንደኛ ተከሳሽ የሆነው ኤጀንሲው በሰጠው አስተያየት፤ ድርጅቱ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በትብብር ለማስተማር ፍቃድ እንዳልተሰጠው፣ የጥራት መለኪዎቹ በኤጀንሲው ተገምግሞ እንደማያውቅ፣ በአዋጅ ቁጥር 1076/2018 መሠረት በትብብር ለመሥራት ፍቃድ እንዳላገኘ፣ በትብብር የሚሰጥ ትምህርት እንዲቆምና ለ2012 የትምህርት ዘመን ምዝገባ እንዳይከናወን ጅማ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ አራት ዩኒቨርሲቲዎች ላይ ክልከላ የተደረገ ሆኖ ሳለ ድርጅቱ ግን አዲስ ተማሪዎችን ለመቀበል በመገናኛ ብዙሃን እያስነገረ በመሆኑ ሕብረተሰቡ እንዳይታለልና እንዲጠነቀቅ ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠቱን አቅርቧል።ይህም ሥም ማጥፋትም ሆነ ሁከት መፈፀም ስላልሆነ ከሳሽ የጠየቀው የእግድ ጥያቄ ተቀባይነት የለውም ብሏል፡፡

የኤጀንሲው አምስት የሥራ ኃላፊዎች በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት፤ በኤጀንሲው ውስጥ በተለያየ ኃላፊነት ላይ የሚያገለግሉ ሠራተኞች በመሆናቸው የሥራ ግዴታቸውን ስለተወጡ የፈፀሙት ሕገወጥ ተግባር አለመኖሩን አብራርተዋል። ከዩኒቨርሲቲው ጋር በትብብር ለመሥራት ፈቃድ በኤጀንሲው በኩል ያልተሰጣቸው ስለሆነ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የፈፀሙት ሁከትም ሆነ በድርጅቱ ላይ የሚደርስ ሁከት ባለመኖሩ አቤቱታው ውድቅ እንዲሆን ጠይቀዋል፡፡

በግራ ቀኙ የቀረበው የጽሁፍ ክርክር በመመልከትና ጉዳዩን በመመርመር ኤጀንሲው የአማካሪ ድርጅቱን መልካም ሥምና ዝናን በማንሳት ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ጋር አያይዞ ለመገናኛ ብዙሃን ሲሰጥ የነበረው መረጃ አግባብነት የለውም በማለት በቀጣይ ከዚህ መሠል ተግባር እንዲታቀብ የእግድ ትዕዛዝ አስተላልፎ ተለዋጭ መደበኛ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ኤጀንሲው ‹‹የትብብር ሥልጠና ትክክል ባለመሆኑ እንዲያቆሙ›› በሚል የሣይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በደብዳቤ ማሳወቁን በመግለጽ፤ በዚህ መልኩ ሲሠሩ የነበሩ የጅማ፣ የደብረ ማርቆስ፣ የባህር ዳር እና የሐረማያ ዩኒቨርሲቲዎች እንደታገዱ ማሳወቁ ይታወሳል።አማካሪ ድርጅቱም ኤጀንሲው ይቅርታ እንዲጠይቅ ያቀረበውን ጥያቄ ስላልተቀበለው ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት እንደወሰደው መግለጹ ይታወቃል።

በዚህም የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ እንዲሁም አምስት የሥራ ኃላፊዎቹ በድርጅቱ ላይ ላደረሱትና ለሚደርሰው ጉዳት የ174 ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ብር ክስ በኤ ቢ ኤች (ጥምረት ለተሻለ ጤና) ሰርቪስስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል አማካሪ ድርጅት እንደቀረበባቸው መዘገባችን ይታወሳል።

አዲስ ዘመን መስከረም 7/2012

 ፍዮሪ ተወልደ