ፍትሀዊ ተጠቃሚነትን በማክበር ጅምሩ ከፍፃሜ ይደርሳል!

14

 በቅርበት የማያውቁን የስነልቦና ጥንካሬ የሌለንና መጀመር የማንችል፣ብንጀምርም መፈጸም የሚሳነን አድርገው በንቀት የሚያዩን በርካቶች ናቸው፡፡ እኛ ግን የጀመርነውን ዳር የምናደርስ፣ የመንፈስ ጥንካሬያችን ዘመናትን የተሻገረ ጀግናና ኩሩ ሕዝቦች ለመሆናችን የቀደመውና እያከናወንን ያለው የታሪክ አሻራችን ህያው ምስክር ነው፡፡

አዎ በይቻላል መንፈስ መጋቢት 24ቀን 2003 ዓ.ም. የጀመርነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የህያው ታሪካችን አንዱ ማሳያ ሲሆን፤ ያጋጠሙትን ተግዳሮቶች ተቋቁሞ አሁን ለደረሰበት ደረጃ መብቃቱ እጅግ የሚያኮራና የጠንካራ መንፈስ ባለቤትነታችንን ማረጋገጫ ነው፡፡

አገሪቱ ከፍተኛ የልማት ሥራዎችን እንዳታከናውን የሚሹ ‹‹ኢትዮጵያ ከዓለም ባንክና የዓለም ገንዘብ ድርጅት ተቋማትና አገራት ካልተበደረች ግንባታ ልታከናውን አትችልም›› በማለት በዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ዘንድ እየተገኙ ብድር እንዳይገኝ በይፋ ቀስቅሰዋል፡፡ በህዝብና በመንግሥት አቅም እንደሚገነባ ሲነገራቸው ደግሞ ‹‹ኢፍትሃዊ በሆነ መንገድ ለራሳቸው የደለደሉት የውሃ መጠን ይቀንሳል፣ በህዳሴ ግድብ የታችኞቹ ሀገራት ላይ ጉዳት ያደርሳል፣ የግልገል ግቤ የሃይል ማመንጫ በኬኒያ የቱርካና ሃይቅ እንዲደርቅ ምክንያት ይሆናል›› ሲሉ ያላሰለሰ አፍራሽ ቅስቀሳቸውን አካሂደዋል፡፡

<<በውሃ ትጥለቀለቃለች>> ተብላ ተቃውሞ እንድታሰማ የተጋበዘችው ሱዳን እንኳ በተቃራኒው ደጋፊያችን ሆና መቆም የቻለችው በግድቡ አስተማማኝ ሆኖ መገንባትና ፍትሃዊነት ላይ እርግጠኛ ስለሆነችና ከተከዜ ግድባችንም ለራሳችን ብቻ ሳይሆን ለጎረቤት አገራትም ጭምር ሃሳቢ መሆናችንን በመረዳቷም ነበር።

የግድቡ መጠናቀቅ የሚፈጥረው በገንዘብ የማይተካ የመንፈስ ኩራት፣ከፍተኛ የኢኮኖሚና የቴክኖሎጂ አቅም ግንባታ ይገኛል ተብሎ የሚታሰበው የሥራ መስክ ልብን በሀሴት ይሞላል፡፡ የመቻላችን ማሳያ መሆኑ ደግሞ ኩራታችንን እጥፍ ድርብ ያደርገዋል። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ መቀነቱንና ኪሱን ፈትሾ የላቡን አሻራ በግድቡ ያኖረው በደጁ ከሚያልፈው ወንዝ የመብራት፣ ኃይል ሲመረትና ምርታማነት ሲያድግ ብልጽግና አገኛለሁ በሚል ተስፋ ተሞልቶ በመሆኑ የግንባታው መጠናቀቅ በጉጉት የሚጠበቅ እንጂ ፣ መልካም የማያስቡት ‹‹ቢጀምሩትም አይጨርሱትም ›› ሲሉ እንደሚያሟርቱት ከንቱ ወሬ ፍሬ ቢስ እንዲሆን አይደለም፡፡

እኒያ ከሊቅ እስከ ደቂቅ፤ ከፌደራል ፖሊስ እስከ መከላከያ በጉባ በረሀ በጥንካሬ ሥራቸውን ማከናወናቸው የተጣለባቸውን የወገን አደራ በፅናት ለመወጣት ቆርጠው በመነሳታቸው ነው፡፡ ዛሬ አብዛኛዎቹ የግድቡ ሥራዎች በመጠናቀቅ ላይ በሚገኙበት ወቅት ቀድሞውኑ በግድቡ መገንባት አይናቸው ደም የለበሱ አካላት በአልሞት ባይ ተጋዳይነት ሲፍጨርጨሩ ቢታዩም ቆራጦቹ ኢትዮጵያውያን ካለሙት ግብ ሳይደርሱ ርምጃቸውን እንደማያቆሙ ‹‹እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን!›› የሚለው መርሀቸው ብቻ ፅናታቸውን ያመለክታል፡፡

የተፈጥሮ ሀብትን ለጋራ ልማት በማዋል አገራችን የዓለም አቀፍ መርህን የምታከብርና ከጎረቤቶቿ ጋር ተደጋግፎ አብሮ በማደግ የምታምን ነች፡፡ የእስካሁኑ እርምጃዋም ይህን የሚያሳይ ነው፡፡ ይህንኑ አጠናክራ በመቀጠልም የተፋሰሱ አገራት የጋራ ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ላይ የበኩሏን አስተዋፅዎ በማድረግ ለሕዝቦቿ ተጠቃሚነት፣ ለኢኮኖሚዋ ዕድገትና ለጋራ ልማት ስትል በሕዝቦቿ የዓላማ ፅናት ጅምሩን ከፍፃሜ ታደርሳለች፡፡ አዲስ ዘመን መስከረም 7/2012