የዩኒቨርሲቲዎቻችን ትውልድን በእውቀት የመገንባት ገመና

29

 ሀገር የምትገነባው፣ የምታድገውና የምትለ ማው በትምህርት ነው። መሰረቱ በጠበቀ ጥልቀት፣ ጥራትና ብቃት ባለው ትምህርት። ትምህርት ለዜጎች መኩሪያ ለሀገር አለኝታ ነው። አባቶች ‹‹ተማር ልጄ›› ሲሉ የማወርስህ ሀብት የለኝም እውቀት ነው፤ ሀብት ማለት በርትተህ ተማር ማለታቸው ነበር። እውነትም ለእውቀት የተጋ የእውቀት ጥም የነበረው ትንታግና በእውቀት ሰማይ ላይ ያረበበ ትውልድ ኢትዮጵያ ፈጥራ ነበር ዛሬም ትገነባለች።

ዛሬ ትምህርትን በተመለከተ ተዳፋቱን ጨርሰን የዘመን ቁልቁለት ላይ እንሆን አንዴ? ስል እጠይቃለሁ። በተለይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሀገርን ከድሕነትና ከኋላቀርነት ለማውጣት በሚደረገው ትግል የተለያዩ ምርምሮችን በሁሉም መስክ በማድረግ መፍትሄ ያስገኛሉ የሚል ትልቅ እምነት አለ። ለዚህም ተማሪዎች የሀገር መድኃኒት እንዲሆኑ ከፍተኛ እውቀት ልምድና ብቃት ባላቸው መምህራን መማር ከፍተኛና ብቁ የሚያደርጋቸው እውቀት ማግኘት አለባቸው።

ኮሌጅ፣ ዩኒቨርሲቲ መግባትና መመረቅ ብቻውን ብቁ አያደርግም። ዓመት ቆጥሮ ተመረቅን ከሚለውም ቃል በላይ በእውነተኛ እውቀት መገንባት በምርምር መታገዝ መብቃ ትንም ይጠይቃል። ጥያቄው ሰርተፊኬት ዲፕሎማ ዲግሪ ከዚያም በላይ ማግኘቱ ላይ አይደለም። እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ምሩቃን በየተማሩበት የሙያ መስክ ሲፈተኑ በአስደንጋጭ ቁጥር መውደቃቸው እንደ ሀገር ያስደነግጣል። ወዴት እየሄድን ነው ያሰኛል።

በተሰማሩበት ሥራ ላይ ውጤት የሚጨበጥ ለውጥ ማምጣትና ማስመዝገብ ካልቻሉ ዲግሪ መያዙ የደመወዝ ደረጃን ለማሳደግ ብቻ ካልሆነ በስተቀር ለድሀ ሀገር ፋይዳ የለውም። በብዙ የሙያ መስኮች ሲመዘን ብዙ ችግር እንዳለ በትምህርት መስክ ለፍኖተ ካርታው መዘጋጀት ምክንያቶች ያሳብቃሉ። በየቦታው የሆነውም ይኸው ነው።

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ተግተውና በርትተው እንዲማሩ እንዲያጠኑ በፈተናም ላይ ተገቢ ውጤት እንዲያስመዘግቡ መስራት አለባቸው። የእስከዛሬው በሀገር ላይ የመቀለድ ያህል ነበር። በይድረስ ይድረስና በምንቸገረኝ ተማሪን በበቂ ሁኔታ ሳያስተምሩና ሳይፈትኑ ማሳለፍ አደጋው የሚተርፈው ለሀገርና ለሕዝብ ነው። በሚሰማሩበት መስክ ከእውቀት እጦት ብዙ ስህተቶች ጉድለቶች ጥፋትም ያደርሳሉ።

ዛሬ በየመስኩ በኮንስትራክሽን (በቤቶች ግንባታ) በመንገድ ሥራ፤ በአስተዳደር (በየቀበ ሌው በዞን ከዚያም በላይ)፤በመምህርነት፤ በህክም ናውና በሌሎችም መስኮች የሚታዩት የገዘፉ ችግሮች የበቂ እውቀትና ችሎታ ማጣት ግን ደግሞ ተምረዋል፤ ተመርቀዋል በሚል የመጀመሪያና የሁለተኛ ዲግሪ ባለቤት የመሆናቸው ሁኔታ ተቃር ኖውን ያመለክታል። ለዚህም ብዙ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል።

ለዚህ ነው የሀገራችን የትምህርት ስርዓት እጅግ ጥብቅና የማያወላዳ የጠራ እውቀት ባለቤቶችን ለማፍራት መትጋት አለበት የሚባለው። አብዛኛው ጉድለት አለበት ለማለት እንጂ ከፍተኛ እውቀት ያላቸው በርትተው ለእውቀት ያጠኑ የሰሩ ሀገርና ሕዝብን የሚያኮሩ በርካታ ወጣት ምሁራንንም አይተናል።

ዲግሪና ማስትሬት ለስሙ የተሸከሙ ማፈሪያዎችንም በስፋት ተመልክተናል። በመሰረቱ እውቀት ሁለገብ በመሆኑ በወረቀትና በኪሎ አይመዘንም። የአንድ ሀገር የትምህርት ስርዓት የሀገሪቱ የወደፊት እጣ ፈንታ የሚወሰንበት ሀገር ተረካቢ ትውልድና መሪዎች የሚወጡበት ስለሆነ የላቀ ጥንቃቄ ያሻዋል። በሌሎች ሀገራት ያለው ጥብቅ የፈተና ስርዓት ተማሪው በኮሌጅም ሆነ በዩኒቨርሲቲ ተምሮ ከጨረሰ በኋላ ፈተናው የሚሰጠው ለፈተናው በተሰየመ የመንግሥት ኮሚሽን ነው።

በተምሬአለሁ ስም ለሚግበሰበሰው ማጣሪያ ወንፊት ማበጀት ግድ ይላቸዋል።ዛሬ በየቦታው ዲግሪና ማስትሬት አለኝ ባዩ ሁሉ ዳግም ይፈተን ቢባል ምድር ቀውጢ ትሆናለች። ትምህርት ሚኒስቴርና ከፍተኛ ትምሕርት ኮሚሽን እጅግ በላቀ ጥንቃቄ መስራት ይጠበቅባቸዋል። ሀገር በዚህ መልኩ አታድግም። አትለማም። እልፍ አትልም። ባለፉት ሀያ ሰባት ዓመታት የሀገራችን የትምህርት ስርዓት ወርዶ ተፍገምግሟል። በሀገር ደረጃ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ደረጃም አሳፋሪ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ድሮ ምርጥና የተከበረ የነበረው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአፍሪካ ምርጥ ከሚባሉት ምሁራንን ከሚያወጡ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ነበር። ዛሬ ያንን ደረጃ አጥቷል። ዲግሪና ማስትሬት በኮታ አይሰጥም። በእውቀት ጥራትና ብቃት ብቻ ነው የሚገኘው።

በሌሎችም መስኮች የሚታየውም ችግር በምንም ተአምር የእወቀት የምጥቀት የልሂቅነት ማረጋጋጫ አይደለም። መማርም ሆነ እውቀት ከራስ አልፎ ለማሕበረሰብ ለሀገር ችግር መፍትሄ ካላስገኘ ፋይዳ የለውም። መማር መመራመር ማወቅ ለውጥ ካላመጣ ትምህርት እውቀት ሊሆን አይችልም።

ታላላቅ ሀገራት የእድገታቸው ምስጢር በከፍተኛም ሆነ በመለስተኛ ደረጃ ብቁ ትምህርትና ምርምር እንዲያገኙ አድርገው ወጣቶቻቸውን ማስተማራቸው ነው። ለሀገራቸው መሰረታዊ ችግሮች መፍትሄ ማስገኘትና ማመንጨት የቻሉት። በእውቀት የታነጸ፤ የበቃ ተመራማሪ፤ ሀሳብ አፍላቂና አመንጪ መፍትሄ ፈላጊ ትውልድ መፍጠር በመቻላቸው ከጨለማ ወደ ብርሀን ተሸጋግረዋል።

ከድህነት የወጣች ሀገር ለመገንባት በቅተዋል። ዲግሪና ማስትሬት እያመረቱ በመቶ ሺዎች አድለዋል፤ በፎርጅድ። ገንዘብ የያዘ ስሙን በቅጡ መጻፍ የማይችለው ሁሉ የዲግሪ ባለቤት እንዲሆን የማድረግ ሀገራዊ ወንጀል አልፈጸሙም፤ ያደጉ አገራት፤ እነሱም አያደርጉትም። ሀገርን መግደል መሆኑን ያውቁታል።

እውቀትና ትምህርት በጎጥ በጎሳ በዘር አይወከ ልም። እውቀት ዓለም አቀፍ ነው። ዘር፤ ጎጥ፤ መንደር፤ ቀለም የለውም። በአንድ የትምህርት መስክ ኢትዮጵያ ውስጥ የተማረ የተመረቀ ሰው በሌላ ሀገርም ሄዶ መስራት ብቁ ተወዳዳሪ መሆን ነው የሚጠበቅበት። ዛሬ ግን እየሆነ ያለው በፊት ከነበረው በእጅጉ የተለየ ነው። ተማሪን ብቁ ለማድረግ በእውቀት ልቀው የተገነቡ ምሁራን መኖር ግድ ይላል።

ብርቱ የቀለም ቀንዶች በእውቀት በስነምግባር የታነጹ የተከበሩ መምህራን መኖር ነው ትውልድን የሚቀርጸው። ብርቱ የእውቀት ማማ የሆኑ መምህራን በነበሩበት ዘመን ተምሮ ተመረቀ ማለት ተማረ አወቀ ተመራመረ አረዳዱ ሰፋ ግንዛቤው መጠቀ ማለት ነበረ። ዛሬ የኮሌጅና የዩኒቨርሲቲ የምርቃት ገዋን ያደረጉና ስም ገላጭ ወረቀት የተሸከሙ አእላፋት በየዓመቱ ማየት ካልሆነ በስተቀር በቂ እውቀት ይዘው ወጥተዋል፤ ብቃቱ ችሎታውስ አላቸው ወይ የሚለው ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ከወደቀ ዓመታት ተቆጥረዋል። አከራካሪ ብቻ ሳይሆን አሳፋሪ ደረጃ ላይም ደርሷል።

በአሁኑ ተጨባጭ ሁኔታ ዲግሪም ሆነ ማስትሬት የእውቀት መለኪያ መሆን አይችልም። በተቀመጠው የሲቪል ሰርቪስ መስፈርት መሰረት ለደመወዝና ለእድገት ይጠቅማል። ለሀገር ግን በምንም መልኩ ጠቃሚነት የለውም። ብዙዎቹ ሰዎች ወረቀት እንጂ እውቀት የተሸከሙ አይደሉም። ሀገር ራሷን እያታለለች በራስዋ እየቀለደች መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል። የትምህርት ጥራት በኢትዮጵያ ውስጥ በእጅጉ ወድቋል። ክርክር የለውም።

ከማን አንሼ የሚለው ፉክክር ያመጣው የፖለቲካ ውስብስብ ችግር ዳፋው ለትምህርቱም መስክ ተርፏል።የተማሩ ያወቁ የበቁ ሰዎችን ማግኘት የማይቻልበት አሳፋሪ ዘመን ላይ ተደርሷል። የሀሰት የትምህርት ማስረጃ ዲግሪ ማስትሬት ከዚያም በላይ በስውር በሚቸበቸብበት ፤ስሙን በቅጡ የማይጽፈው ሁሉ ባለዲግሪ በሆነበት ሀገር የትምህርት ጥራቱ ምን ያህል ተፍገምግሞ እንደወደቀ የውጭ ጥናት አጥኚዎችም በተደጋጋሚ አጥንተው መስክረዋል። ብሔራዊ ውርደት ነው። በየሰፈሩ የተቋቋሙ የሸቀጥ ንግድ ይመስል ለመጣና ገንዘብ ለከፈለ ሁሉ ወረቀት እያተሙ የሚሸጡ ኮሌጅና ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪው እየከፈለ እስከተማረ ድረስ ገቢያቸው ነውና አይጥሉትም። የሞቀ ቢዝነስ ነው። እነሱን ምን ቸገራቸው ሀገር ይጭነቃት እንጂ።

ስንትና ስንት ሺህ ባለዲግሪ ተምሮ ተመርቆ ሥራ የለውም የሚባልበት ምስጢርም ያለው እዚሁ ጋር ነው። ትምህርት ሚኒስቴርም ሆነ ከፍተኛ ትምህርት ኮሚሽን አዲስ ዘዴና መንገድ መቀየስ እስካልቻለ ድረስ በትምህርት መስክ ያለው አደጋ ዘመን ይሻገራል። በትውልድ ላይ የሚያደርሰው ኪሳራ ግዙፍ ነው። ማግበስበስ ነው የተያዘው። የድሮ አባቶቻችን እንደ ዛሬ ሀገር ምድሩ በዲግሪና በማስትሬት ሳይሞላ በፊት በሰርተፍኬት በዲፕሎማ ለሀገራቸው በታማኝነት ብዙ ሰርተዋል።

እንደ ፖለቲካው ሁሉ በብሔረሰብ ፉክክር የራስን ሰው ዲግሪና ማስትሬት ለማሸከም ሲሰራ የኖረው የዘቀጠ ወራዳ ተግባር ሀገር ገድሏል። አሳፋሪ ዘመን ላይ ደርሰናል። ሁሉም ነገር ረክሷል። የግል ኮሌጆች ዩኒቨርሲቲዎች የጅምላ ዲግሪና ማስትሬት ማምረቻ ፋብሪካዎች የመሆናቸውን እውነት ሕብረተሰቡ ከተረዳው ውሎ አድሯል። የትምህርት ስርዓቱ መሰረታዊ ብልሽት መገለጫ ነው።

ሀገር በቂና ተገቢ ትምህርት ተምሮ ተፈትኖ ለሥራ ዝግጁ የሆነ የበቃ የሰው ኃይል ማግኘት የተቸገረችበት ዘመን ላይ ተደርሷል። መቸም ሁሉም ተሞክሯል።መንግሥት ነቅቷል እንጂ፤አሁን የቀረን አይን ባወጣ መንገድ በየሱቁ በግላጭ ለጥፎ እዚህ ሱቅ ዲግሪና ማስትሬት ይሸጣል፤ ሁለት ጉርድ ፎቶግራፋችሁን፤ የምት ፈል ጉትን የትምህርት መስክ ብቻ ግለጡልን፤ ዋጋ እንደራደራለን የሚል ማስታ ወቂያ መለጠፍ ብቻ ነው። እንዴት ነሽ ኢትዮጵያ ?

የተማሪዎችን የመመረቂያ ጽሁፍ ሌሎች ሰዎች በክፍያ የሚጽፉላቸው መሆኑ እየታወቀ ሀገር ምን አይነት ምሁር እንዲኖራት እንጠብቃለን፡ ይህ ብቻ አይደ ለም። እነዚሁ ሰዎች ናቸው ተመልሰው ወደ መምህርነት የሚገቡት ።ምን አይነት ተማሪስ እንጠብቃለን። ይህ ሁሉ እጅግ አሳፋሪ በትውልድና በሀገር ላይ የተፈጸመ ታላቅ ወንጀል ነው ሲሰራ የኖረው። በተለያዩ የትምህርት መስኮች ተመርቀው ዲግሪና ማስትሬት የያዙ በየተመረቁበት የሙያ መስክ ለውድድር ቀርበው ከመቶው አስርና አስራ አምስት ሰው ብቻ የሚያልፉባት ሌሎቹ ፈተናውን የሚወድቁባት ሀገር ናት ኢትዮጵያ።

ስለነገው ተተኪ ትውልድ ብቃትና የጠለቀ እውቀት መጨነቅና መጠበብ ከቀረ ዓመታት አልፈዋል። ዲግሪ ያለው መሀንዲስ፤ ሀኪም፤ የአስተዳደር ሰው ፤በቂ እውቀት የሌለው በተሰማ ራበት መስክ ብቁና አጥጋቢ አገልግሎት መስጠት የማይችል መብዛቱ ነው ሀገርን ገደል የከተታት። የሀገር ውድቀት ከዚህ ሌላ ምን አለ? ምንስ ይኖራል? በእውቀት የታነጸና የተገነባ ትውልድ መፍጠር ካልተቻለ ሀገር አታድግም። ልታድግም አትችልም። ዛሬ የሀገራችን ትልቁ ፈተና ፖለቲካውና ትምህርቱ ነው። ከዚህ ዝቅጠት ለመውጣት መሰራት አለበት።

አዲስ ዘመን  መስከረም 8 / 2012

 ወንድወሰን መኮንን