የኪነጥበብ ዜናዎች

16

ብዝሀ ህይወትን መሰረት ያደረገ የኪነ ጥበብ ምሽት ተዘጋጀ

 ‹‹አገራችንን በጥይት በተሸነቆረ የዝሆን ጆሮ አጮልቀን ስናያት›› በሚል መሪ ሀሳብ የብዝሀ ህይወት እና ተፈጥሮ ላይ የሚያተኩር ልዩ የኪነ ጥበብ ምሽት ነገ ሰኞ በብሄራዊ ቲያትር መዘጋጀቱ ታወቀ። መሰናዶውን ተስፋ ፊልም ፕሮዳክሽንና የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለስልጣን በትብብር እንዳዘጋጁት ሰምተናል።

የዝግጅቱ አስተባባሪ አቶ ገዛኸኝ ሀብቴ ለአዲስ ዘመን የኪነ ጥበብ ዜና ዝግጅት ክፍል እንዳስታወቁት ኪነ ጥበብ እና ስነ ምህዳር ያላቸውን ቁርኝት አጉልቶ የሚያሳይ የኪነ ጥበብ ምሽት ተዘጋጅቷል። በእለቱ ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ ፣ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሴ እንዲሁም ፕሮፌሰር ታደለ ደሴ ልዩ ተሞክሯቸውን እና ጥናታዊ ስራዎችን ያቀርባሉ። ፕሮፌሰር ሽብሩ በዱር እንስሳት ዙሪያ እንዲሁም በእፅዋቱ ላይ ፕሮፌሰር ሰብስቤ ፅሁፎቻቸውን ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በዚህ ልዩ የኪነ ጥበብ ምሽት ላይ ደራሲ አለማየሁ ገላጋይ የሚገኝ ሲሆን የስነ ፅሁፍ እና ተፈጥሮ ምንነት ላይ ምልከታውን ለታዳሚዎች የሚያቀርብ ይሆናል። ሌላኛው የዝግጅቱ ተጋባዥ ሰርፀፍሬ ስብሀት ሲሆን ሙዚቃና ተፈጥሮ ያላቸውን መስተጋብር መሰረት በማድረግ ዳሰሳ ያቀርባል። ዶክተር አለማየሁ ዋሴ በቤተ ክህነት ዙሪያ ያለውን ምልከታ እና በሰሯቸው መፅሀፎች ዙሪያ ዝርዝር ትንተናዎችን ያቀርባሉ። በባህል ህክምና ላይ ሀኪም አበበ ሽፈራው ከእፅዋት ጋር ያለውን ቁርኝት አንስተው ታዳሚውን እውቀት እንደሚያስጨብጡም ይጠበቃል ሲሉ አዘጋጆቹ ነግረውናል።

 ‹‹መስቀልና ባህላዊ አከባበር›› የመዝናኛ ዝግጅት ይደረጋል

 ‹መስቀል እና ባህላዊ አከባበር›› በሚል መሪ ሀሳብ በአገር ውስጥ እና በውጪ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን መዘጋጀቱን አብርሀም ግዛው ኢንተርቴይመንት እና ፕሬስ ስራዎች ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መልክዕት አስታወቀ። ዝግጅቱ ዛሬ የሚካሄድ ሲሆን ሙሉ መሰናዶው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች በልዩ ሁኔታ በሚያከብሩት የመስቀል በዓል እለት በጄ ቲቪ ኢትዮጵያ ለእይታ እንደሚቀርብ ታውቋል።

የመዝናኛ መሰናዶው ዋና አዘጋጅ አብርሀም ግዛው ለዝግጅት ክፍላችን በገለፀው መሰረት የሁነቱ ዋና አላማ የመስቀል ባህላዊ ጨዋታ ባህላዊ እሴቱን በጠበቀ ሁኔታ ወደ ቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፍ ማድረግ ነው። በዚህም በእለቱ የአገር ሽማግሌዎች ተገኝተው ባህላዊ ምርቃት የሚያቀርቡ ሲሆን በዓሉን በማስመልከት የኮሜዲያን ስራዎች ይቀርባሉ። ታላላቅ አባቶችም በዓሉን በማስመልከት መልክቶችን ያስተላልፋሉ።

አዘጋጁ መዝናኛ መሰናዶውን በማስመልከት ባስተላለፈው መልዕክት መስቀል እና ባህላዊ አከባበር ማዕከል በማድረግ የበ,ዓል ማድመቂያ ከመሆናቸው ባሻገር ባህልን ጠብቆ ከነትውፊቱ ለማቆየት ህብረተሰቡን ተሳታፊ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ተናግሯል። ይህን እሴት ለማስቀጠልም መሰናዶውን ለህብረተሰቡ ማቅረብ ማስፈለጉንም አስታውቋል።

 ጀግናው የቃኘው ሻለቃ በኮሪያ›› መፅሃፍ ተመረቀ

 በዶክተር ጌታቸው ተድላ የተፃፈው ‹‹ጀግናው የቃኘው ሻለቃ በኮሪያ›› የተሰኘው የታሪክ መፅሃፍ ትናንት በእለተ ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ አምስት ኪሎ በሚገኘው ቅርስ እና ጥበቃ ባለስልጣን አዳራሽ በይፋ ተመርቋል።

መፅሀፉ በአማርኛ እና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች ተፅፎ ለንባብ መብቃቱን ደራሲው ለዝግጅት ክፍላችን ገልፀውልናል። 295 የገፅ ብዛት የያዘው የታሪክ መፅሀፍ በኮሪያ የኢትዮጵያ ጀግና ወታደሮች ያደረጉትን ተጋድሎ የሚተርክ ነው። በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ የኮሪያ ዘማቾች እና ቤተሰቦቻቸውን ጨምሮ በርካታ እንግዶች ተገኝተው በጊዜው የነበረውን የጀግና አርበኞች ታሪክ የሚያወሳ መፅሀፍ መመረቅ ችለዋል። በመፅሃፉ እና በዘመቻው ዙሪያም የተለያዩ ውይይቶች እና መሰናዶዎች ለታዳሚዎች ቀርበዋል።

የመፅሃፉ ደራሲ ዶክተር ጌታቸው ይህን ታሪክ ለመፃፍ ያነሳሳቸውን ጉዳይ ሲገልፁ ፤ “በአንድ ስብሰባ ላይ በመገኘት ስለኮሪያ ዘማቾች ምን ያህሎቹ እንደሚያውቁ ሲጠየቁ ከመቶዎቹ ውስጥ ከሁለት ሰዎች በስተቀር ምንም ግንዛቤው እንደሌላቸው ተረዳሁ” ብለዋል።በዚያ ቁጭት ተነሳስተው ወጣቱ ታሪኩን እንዳይረሳ እና ጀግና አባቶቹን የከፈሉትን ተጋድሎ እንዳይዘነጋ በማለት መፅሃፉን ፅፈው ለንባብ ማብቃታቸውን ተናግረዋል።

ዶክተር ጌታቸው ከዚህ ቀደም ከ12 በላይ የሚሆኑ መፅሃፍ በማዘጋጀት ለንባብ ማብቃታቸው የሚታወስ ሲሆን የአክሊሉ ማስታወሻ፣የዘመናዊ እርሻ ፋና ወጊ፣እንደወጡ የቀሩት ኢትዮጵያዊ፣ከትዝታ ጓዳ እንዲሁም ሌሎች መፅሃፍትን ለንባብ ያበቁ አንጋፋ የስነ ፅሁፍ ሰው ናቸው።

አዲስ ዘመን መስከረም 11 ቀን 2012 ዓ ም