‹‹የክልሎች ህገወጥ የፓርክ ግንባታ አሳሳቢ ሆኖብናል›› – አቶ አያልነህ አባዋ የተቀናጀ የአግሮ ኢንዱስትሪው ፓርክ ልማት ፕሮጀክት አስተባባሪ

18

ኢትዮጵያ ግብርናዋን ከኢንዱስትሪ ጋር በማስተሳሰር ከጥምረቱ ፍሬ ተጠቃሚ ለመሆን በ2009 ዓ.ም በአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ጀምራለች። ለፓርኮች ግንባታም 17 ቀጣናዎች የተለዩ ሲሆን በፓይለት ፕሮጀክት ደረጃ የጥሬ ዕቃዎች ምርት መገኛ መሆናቸውን መሠረት በማድረግ የመጀመሪያዎቹ የአራቱ ፓርኮች ግንባታ በአማራ ክልል ቡሬ፣ ትግራይ ባከር፣ በኦሮሚያ ቡልቡላ፣ በደቡብ ክልል ይርጋለም ከተማ ከተጀመረም ዓመታት ተቆጥረዋል።

አዲስ ዘመንም የፓርኮቹን ወቅታዊ ሁኔታና በኢንዱስትሪው ላይ ስለተጋረጡ ፈተናዎች የተለያዩ ጥያቄዎችን በማንሳት በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተቀናጀ የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት ፕሮጀክት አስተባባሪና የሚኒስትር ዴኤታው አማካሪ ከአቶ አያልነህ አባዋ ጋር ቆይታ አድርጓል።

አዲስ ዘመን፦ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ በታለመለት እቅድ መሠረት ምን ያህል እየሄደ ነው? አሁን ያለበት ደረጃስ ምን ይመስላል?

አቶ አያልነህ፣የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ በአጠቃላይ አራት ምዕራፍ አለው። ቀዳሚው የአዋጭነት ጥናት ነው። በዚህ ረገድ ሶስት ዓመታትን የወሰደ ጥናት ተካሂዷል። ምርጥ ቦታዎችን ለመለየት፣ በአካባቢው ምን አይነት ምርት አለ? ምን አይነት ፋብሪካ ቢቋቋም አዋጭ ይሆናል የሚለው ተቃኝቷል። ሁለተኛው የኮንስትራከሽን ምእራፍ ሲሆን በአሁን ወቅት በግንባታ ምእራፍ ላይ እንገኛለን።

ይህ ሲባል አልዘገየንም ማለት አይደለም። ኢንዱስትሪዎቹ በተለይ ከአካባቢ ብክለት ተፅእኖ ላይ የሚያሳድሩትን ጫና በሚመለከት የተደረገው ጥናት ጊዜ በመውሰዱ ግንባታዎች የተጀመሩት ዘግየት ብለው ነው። በዚህና ሌሎችም ምክንያቶች ግንባታውን በተባለው ጊዜ እናዳናስረክብ አድርጎናል።

ይሁንና አራቱን የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ስራ ለማስጀመር የሚያስችሉ መሰረታዊ የግንባታ ስራዎች የፊታችን ታህሳስ መጨረሻ ይጠናቀቃል። በተጠቀሰው ጊዜም ሁሉም ፓርኮች ተመቻችተው ክፍት ይሆናሉ፤ ለባለሀብቶችም ይሰጣሉ።

በአሁኑ ወቅትም በፓርኮቹ ላይ መሬት አግኝተው ኢንቨስት ለማድረግም በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ባለሀብቶች ተመዝግበው እየተጠባበቁ ይገኛሉ። ከመቶ በላይ ባለሀብቶች ወደ ፓርኮቹ ሊገቡ ተዘጋጅተዋል። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ ሁለትና ሶስት ፋብሪካዎችን የሚተክሉ ናቸው። በአንዳንድ አካባቢዎችም በተለይ በደቡብና በአማራ ክልል ቀድመው ወደ ስራ የገቡ ባለሀብቶች አሉ። ማምረትና ግንባታ የጀመሩም አሉ። ይህን ያደረጉትም በራሳቸው ኃላፊነቱን ወስደው ነው።

አዲስ ዘመን፦ የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ የግንባታ አፈፃፀም ከክልል ክልል ይለያያል፣ ምክንያቱ ምን ይሆን ?

አቶ አይልነህ፦ ለፓርኮች ግንባታ 17ቀጣናዎች የተለዩ ቢሆንም በፓይለት ፕሮጀክት ደረጃ የመጀመሪያዎቹ የአራቱ ፓርኮች ግንባታ የተጀመረው በአማራ፣ ትግራይ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች ነው። በአራቱም ከልሎች የፓርኮቹ ግንባታ የተጀመረው በተመሳሳይ ጊዜ ነው። ይህ እንደመሆኑም ከሞላ ጎደል ሁሉም በተመሳሳይ ደረጃ ላይ ናቸው ለማለት ይቻላል።

በትግራይ ክልል በበጀት ችግር ግንባታዎች አልተጀመሩም። በአሁኑ ወቅት ገንዘብ የማፈላለግ ስራ እየተሰራ ነው። አስቀድሞም በጀት ድልድሉ ልዩነት ነበረበት። በጀቱ የተመደበው በክልሎቹ የሚኖረው የሕዝብ ቁጥር መሰረት አድርጎ ነው። ፕሮጀክቶቹ ተመሳሳይ ሆነው በጀቱ የተለያየ እንደመሆኑም ትግራይ ክልል ወደ ኋላ መቅረት ይስተዋልበታል። በክልሉ ከተመዘገቡ ባለሀብቶች በስተቀር ወደ ስራ የገቡ የሉም።

አዲስ ዘመን፦ በፓርኮቹ የግንባታ ሂደት የፍሳሽ ማጣሪያ ስራዎች ለምን ዘገዩ?

አቶ አይልነህ ፦ በዚህ ረገድ ትልቁ ተግዳሮት፣ የትሪትመንት ፕላንት ነው። የግንባታው ትልቁ ስራም ይህ ነው። በዲዛይኑም መሰረት እያንዳንዱ ፋብሪካ የራሱ ፍሳሽ ማጣሪያ አለው። ይሁንን ከዚህ በተጓዳኝ ከየፋብሪካው የሚወጣውን ፍሳሽ በአንድ ባንክ ለማስቀመጥ ታስቧል።

በእርግጥም ይህን የመገንባት ስራ ይቀራል። የዘገየበትም ምክንያት የፋብሪካዎቹን በቦታው መገኘት ስለሚጠይቅ ነው። ዘንድሮ ለዚህ የሚሆን 50 ሚሊየን ዶላር ከኮሪያው ኤግዚም ባንክ አግኝተናል። ስለሆነም በፍጥነት ወደ ስራ እንገባለን።

አዲስ ዘመን፦ ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ የኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት የማግኘት ፈተናስ መፍትሄ አግኝቶ ይሆን?

አቶ አያልነህ፦ እውነት ነው። ዋነኛ ችግራችን የኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት ነው። የሃይል አቅርቦት ጉዳይም ረጅም ጊዜ ሲያጨቃጭቅ የዘለቀ ነው። ሃይል አቅራቢው ተቋም ለችግሩ በሚቀርበው ምክንያት ለግንባታው የሚያስፈልገው ገንዘብ የለኝም ለአራቱ ፓርኮች ከ14 ሚሊዮን ዶላር በላይ አምጡ የሚል ነው። በዚህም ምክንት በእሌክትሪክ አቅርቦት ረገድ ላለፉት አመታት ምንም ተግባር አልተከናወነም። በአሁኑ ወቅት በፓርኮቹ ውስጥ የገቡ ባለሀብቶችም ቢሆን በራሳቸው አቅም ለችግሩ መፍትሄ ለመስጠት እየተሞከረ ነው።

ገንዘቡ ተገኝቶ ወደ ስራ እንግባ ቢባል እንኳን የኃይል አቅርቦት ግንባታው 18 ወራትን ይፈጃል። ይህ ደግሞ ባለሀብቶች ወደ ፓርኮቹ ለመግባት ዳተኛ እንዲሆኑ እንዳያደርጋቸው ያሰጋል። በእርግጥ በአሁኑ ወቅት ችግሩን ፈር ለማስያዝ ድርድር እየተካሄደ ነው። ችግሮቹም ፈር እየያዙ መጥተዋል። ከአንድ የቻይና ካምፓኒ ጋር በጋራ የመስራት ጅምሮችም ተከናውነዋል። ሆኖም ግን የሃይል አቅርቦቱ ጉዳይ አፋጣኝ ትኩረትን የሚሻ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል።

አዲስ ዘመን ፦ ከሃይል አቅርቦቱ በተጓዳኝ አሁን ላይ በጣም ያሳስበናል የምትሉት ስጋት አለ?

አቶ አያልነህ ፦ ቀደም ሲል እንደነገርኩህ ለፓርኮች ግንባታ ከተለዩት 17 ቀጣናዎች መካከል አራቱ ክልሎች ላይ በፓይለት ደረጃ የተጀመረው በምክንያት ነው። ይህም በአራቱ ፕሮጀክቶች ትግበራ ከሚያጋጥሙ ችግሮችና ስኬቶች በአግባቡ በመማር በቀጣይ ውጤታማ መሆን ስለሚቻል ነው።

ይህ በሆነበት ሁኔታ አሁን ላይ በጣም የሚያሳስበን ከፌዴራል መንግስት እውቅና ውጪ አንዳንድ ክልሎች የፓርኮች ግንባታ እያከናወኑ መሆናቸው ነው። አንዳንዶቹ ክልሎችም ተጨማሪ ፓርክ ለመገንባት ቦታውን ከመምረጥ ባለፈ በልማቱ ለሚነሱ አርሶ አደሮች ካሳ ሁሉ ከፍለው ጨርሰዋል። ጉዳዩንም የፖለቲካ ጥያቄና የፍትሃነት አጀንዳ አድርገውታል። ይህን አይነት አካሄድም በኦሮሚያ ፣ በአማራና በደቡብ ክልል አስተውለናል።

በእርግጥ ይህን የሚያደርጉት ለማልማት ካላቸው ፍላጎትና የስራ እድል መፍጠርን ታሳቢ አድርገውም ሊሆን ይቻላል። የእኛ ስጋትና ቅሬታም ክልሎቹ ለምን ፓርኮቹን ይገነባሉ አይደለም። ይሁንና ግንባታውን ከማካሄዳቸው አስቀድሞ ነገሮችን ሰከን ብለው በማየት መከተል የሚገባቸውን አካሄድና ጥናትን መሰረት አድርገው አለመጓዛቸውና በስሜታዊነት መራመዳቸው ነው የሚያሳስበን።

በአግባቡ መገንዘብ የሚያስፈልግ አንድ ጉዳይ ቢኖር የአግሮ ኢንዱሰትሪ ፓርኮች ግንባታ እጅግ ከፍተኛ ወጪና አያሌ ጥናቶችን የሚጠይቅ መሆኑ ነው። ፓርክ መገንባት ማለት ትልቅ ከተማ እንደመገንባት ነው።ጥናቱ ብቻ ሶስት አመት ሊፈጅ ይቻላል። ክልሎቹ እንደሚያስቡት ሕንፃ መገንባት አይደለም። ከዚህ ቀደም አሊያም በአንዱ አካባቢ የተሰሩ ጥናቶች ለሌላው ይሆናሉ ብሎ ታሳቢ ማድረግም አግባብ አይደለም። ይህ ማለት ለአንድ ሰው የተሰጠን የሕክምና ትዕዛዝ ለራስ እንደማድረግ ነው።

ይህ እንደመሆኑ እኛ የክልሎች በራሳቸው የመጓዝ ሂደት ቢቆም ደስ ይለናል። ከመጀመሪያዎቹ የፓይለት ፕሮጀክት አፈፃፀሞች በአግባቡ በመማር አስፈላጊውን ልምድና ውጤት ወስዶ መቀጠሉ ይበጃል። ለዚህ ደግሞ ክልሎቹ ትእግስት ቢኖራቸው ጥሩ ነው።

አዲስ ዘመን ፦ የክልሎቹ ተግባር ህገ ወጥ ከሆነ ለምን ማስቆም አልቻላችሁም?

አቶ አያልነህ፦ እኛ ይህን አይነቱ አካሄድ የተሳሳተ መሆኑን ለማስረዳትና አቁሙ ለማለት አቅሙ አንሶናል። ከዚህ ይልቅ በአማራጭነት የአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ምን ያህል ፈታኝ እንደሆነ ለማስገንዘብ ስልጠና ለመስጠት ዝግጅት በማድረግ ላይ እንገኛለን።

አዲስ ዘመን ፦ ብቃት ያላቸው ባለሀብቶች በመመልመል ረገድስ ምን እየተከናወነ ነው?

አቶ አያልነህ፦ ይህን ጥያቄ በመመለስ ረገድ ጠንካራ ተግባር እየተከናወነ ነው። ብቃት ያላቸው ባለሀብቶች በመመልመል ረገድ ሌሎች አገራት በምን መስፈርት ሰሩ የሚለውን የመቃኘት ስራ እየተሰራ ነው። እዚህ ላይ የሚፈፀሙ ስህተቶች አደጋቸው ከፍተኛ ነው። እኛ ከዚህ ቀደም የነበሩ ችግሮች ዳግም ተከስተው መመልከት አንፈልግም።ይህ እንዳይሆንም ጥናት ላይ መሰረት አድርገን እየሰራን ነው።

ፓርኮቹን የሚያለሙት 80 በመቶ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ሲሆኑ ቀሪዎቹ የውጭ ሀገር ኢንቨስተሮች ናቸው። በአሁኑ ወቅትም ብቃት ያላቸው ባለሀብቶች መመልመል ተግባር እየተከናወነ ነው። ተመዝግበው የእኛን ውሳኔ እየተጠባበቁም ይገኛሉ።

ከዚህ ባሻገር የተለያዩ ዓለምና አህጉር አቀፍ ባዛሮችን በማዘጋጀት የአገር ውስጥ ሀብቶችንና ባለሃብቶችን ቁመና የማስተዋወቅ ስራ እየሠራን እንገኛለን። ታላላቅ ባለሃብቶችን ለመሳብና ለማምጣትም ግዙፍ የመረጃ መረቦችን እየተጠቀምን ነው።፡

አዲስ ዘመን፦ ከፓርኮቹ ግንባታው በተጓዳኝ የምርት ግብዓቶች አቅርቦት በበቂ መጠን ማዘጋጀት ምን ያህል ታስቦበታል?

አቶ አያልነህ፦ የእኛ ፍርሃትም ይህ ነው። በርካታ ፋብሪካዎች ቢመጡ በቂ ምርት አለን ወይ የሚለው ሁሌም ያሳስበኛል። በአገሪቱ የሚመረቱትም ቢኖሩ በፓርኮቹ ውስጥ የሚገቡ ፋብሪካዎች ከሚፈልጓቸው ምርቶች አንፃር ተመጣጣኝ አይደሉም።

ይህን ለማስተካካል ይበልጥ መሰራት ይኖርበታል። ግብርና ሚኒስቴር አብሮን መሮጥ ይኖርበታል። በዚህ ረገድ ግብርና ብቻም ሳይሆን ሌሎች የተለያዩ ባለሙያዎችን አቅም ለማጎልበት የትምህርት ተቋማት ከኢንዱስትሪው ዘርፍ ጋር በቅርበት መስራት ይኖርባቸዋል። በቅርቡ አንድ ትልቅ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ተጀምሯል። የመስኖ ፕሮግራሙም በቅርቡ ይጀመራል። ለዚህም ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች የገንዘብ ድጋፍ ተገኝቷል።

አዲስ ዘመን፦ ስለነበረን ቆይታ ከልብ አመሰግናለሁ።

አቶ አያልነህ፦ እኔም አመሰግናለሁ።

አዲስ ዘመን  መስከረም 13/2012

ታምራት ተስፋዬ