የኢሬቻ ኤግዚቢሽን – የኦሮሞ ባህል ተምሳሌት

26

ይህ ወቅት የኦሮሞ ህዝቦች፣ የክረምቱን ጨለማ ወቅት በሰላም አሳልፎ ለብርሃናማው የጸደይ ጊዜ ላሸጋገራቸው አምላክ ምስጋናን የሚያቀርቡበት፣ እርጥብ ሳርና አደይ አበባን በእጃቸው ይዘው በዛፎች ጥላና በወንዝ ዳርቻ ፈጣሪያቸውን የሚያከብሩበት፣ እንደ ክረምቱ ሁሉ የበጋውን ጊዜም በሰላም ጠብቆ እንዲያሳልፋቸው የሚማጸኑበት የገዳ ስርዓት አንዱ መገለጫ የሆነው የኢሬቻ በዓል ማክበሪያ ነው። ይሄን መሰል በዓል ሲታሰብ ደግሞ የህዝቡ ባህል ጎልቶ የሚወጣበት እድል ሰፊ ነው።

የኦሮሞ ህዝብ የበርካታ ቱባ ባህሎች ባለቤት ቢሆንም፤ ይሄን ቱባ ባህሉን በሚፈለገው ልክ አውጥቶ ከመጠቀም ብሎም ከማስተዋወቅና የሌሎችም የጋራ ሀብት እንዲሆን ከማድረግ አኳያ ችግሮች ነበሩ። ዛሬ ላይ ይሄን ታሪክ መቀየር የሚያስችሉና የኦሮሞ ህዝብ ቱባ ባህሉን አውጥቶ እንዲጠቀምና እንዲያስተዋውቅ የሚያግዙ ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ። ከእነዚህ መካከል አንዱ የሆነውን የኢሬቻ በዓል በአዲስ አበባ በደመቀ መልኩ ለማክበር የሚያስችሉ ቅድመ ዝግጅቶች እየተከናወኑ ነው።

በዓልና ባህል ተቀናጅተው ከሚታዩባቸው ምክንያቶች አንዱ ደግሞ የህዝቦች የባህል አልባሳት አንዱ ነው። የኢሬቻ በዓልን ምክንያት በማድረግም እየተከናወኑ ካሉ ተግባራት መካከል ትናንት በኦሮሞ ባህል ማዕከል የተከፈተው የባህል ኤግዚቢሽን አንዱ ሲሆን፤ ይህ ኤግዚቢሽንም የኦሮሞን ቱባ ባህል በጥቂቱ ከማስተዋወቅ ባለፈ ኢሬቻን በድምቀት ለማክበርና የቱሪዝም መስህብ ለማድረግ የሚያስችል ስለመሆኑም ተነግሯል።

የሜጫና ቱለማ ቦርድ አባል እንደሆኑ የነገሩን አቶ ሚልኬሳ ገለልቻ፣ የኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ እና የመሰረት ዳባ የማስታወቂያ ድርጅት በጋራ ባዘጋጁት ኤግዚቢሽን ላይ ተገኝተው ሲጎበኙ ካገኘናቸው መካከል አንዱ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ የኦሮሞ ህዝብ ሰፊ የባህል ሃብት ቢኖረውም በሚፈለገው መልኩ መጠቀምም ሆነ አውጥቶ ማስተዋወቅ አልቻለም። ለዚህም ሜጫና ቱለማ ከንጉስ ሃይለስላሴ ዘመን ጀምሮ ለኦሮሞ ህዝብ ባህል እድገት ሲታገልና ሲሰራ ቆይቷል። አሁን ላይ በዚህ መልኩ ባህሉ እንዲተዋወቅ፤ በዓሉም በአዲስ አበባ እንዲከበር መደረጉ እጅጉን አስደሳች ነው።

የኦሮሞ ህዝብም የኢሬቻን በዓል የሚያከብረውም ከጨለማ ወደ ብርሃን ያሸጋገረውን አምላክ በማመስገንና ቀጣዩንም ጊዜ በሰላም እንዲያሳልፈው ፈጣሪውን በመጠየቅ ነው። በዚህ መልኩ የሚከበር በዓል ደግሞ ሊደምቅና የበለጠ ባህሉን ሊያስተዋውቅ በሚችል መልኩ ሊሆን ያስፈልጋል። በዓሉን ምክንያት በማድረግ ይሄን አይነት ኤግዚቢሽን መካሄዱም የገበያ ትስስርን ከመፍጠሩ ባለፈ ህዝቡ ባህሉን እንዲያውቅ፣ እንዲጠቀምና እንዲያስተዋውቅ እድል ይፈጥርለታል።

ወይዘሮ ሚስራ አብዱራህማን፣ ከሐረር ከተማ የምስራቅ ሐረርጌን የአፍረን ቀሎ የባህል አልባሳት፣ መገልገያ ቁሳቁስ፣ ጌጣጌጥ ይዘው በባዛሩ ላይ ተሳትፈዋል። እርሳቸው እንደሚሉት፤ ለ18 ዓመታት ያክል የኦሮሞን የባህል አልባሳትና ቁሳቁስ ይዞ በማስተዋወቅ ስራ ላይ ቆይተዋል። የዕለቱ ኤግዚቢሽን ግን ከዛ ሁሉ ለየት የሚል ሲሆን፤ ታሪካዊ በሆነው የኢሬቻ በዓል መዳረሻ ላይ መሆኑ ለበዓሉ ድምቀት የሚሆኑ አልባሳትና ጌጣጌጦች ህዝቡ በቀላሉ እንዲያገኝ የሚያስችለው ነው። ኤግዚቢሽኑም ሰፊ የሆነውን የኦሮሞ ህዝብ ባህል ለማስተዋወቅ፣ የኦሮሞ ህዝብ በራሱ በውስጡ ያሉትን ባህሎች እንዲያውቅ፣ ተተኪው ወጣትም ባህሉን እንዲረዳና አውቆም እንዲያስቀጥል የሚችልበትን እድል የሚፈጥር ነው።

በባዛሩ አልባሳትና ጌጣጌጦችን ሲሸምቱ ከነበሩ ተሳታፊዎች መካከል ወጣት ለማ ተሬሳ እንደሚለው፤ የኢሬቻ በዓል በአዲስ አበባ ከረዥም ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲከበር በዓሉ የበለጠ ደምቆ እንዲታይ የባህል አልባሳት ትልቅ ድርሻ አላቸው። ይሄን ታሳቢ በማድረግ ባዛሩ መዘጋጀቱም የሚበረታታ ሲሆን፤ ህብረተሰቡም በቀላሉ የሚፈልጋቸውን ነገሮች በአንድ ቦታ አግኝቶ እንዲገበያይ ያስችለዋል። በተለይ ወጣቱ ለባህሉ ያለው ግንዛቤ እንዲያድግና በቅርበት እያገኘም እንዲጠቀም የሚያስችለው ነው። ይሄ ተግባርም ቀጣይነት ባለው መልኩ ሊከናወን ይገባል።

ዶክተር ወንድሙ ተገኔ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ መምህር ሲሆኑ፤ በኤግዚቢሽኑም ከገዳ ጋር ተያያዥ የሆኑ መገለጫዎች የታተመባቸውን ቲሸርቶች ይዘው ቀርበዋል። እርሳቸው እንደሚሉት፤ ኤግዚቢሽኑ በቀላሉ የኦሮሞን ህዝብ ባህል፣ ቋንቋ፣ ምግብና ማንነቱን ለማስተዋወቅ፣ የኢሬቻ በዓል በባህላዊ አልባሳት ደምቆ እንዲከበር ለማድረግ፣ እንዲሁም ከኢሬቻ በዓል ጋር ተያይዘው የሚከናወኑ ተግባራት ወደ ሀብትነት እንዲቀየሩ የሚያስችል ነው።

የመሰረት ዳባ የማስታወቂያ ድርጅት ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ መሰረት ዳባ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ የኤግዚቢሽኑ ዓላማ የኦሮሞን ቱባ ባህል ማስተዋወቅና ተደራሽ ማድረግ ነው። በዚህም የኦሮሞ ህዝብ የባህል አልባሳት፣ ምግቦች፣ መገልገያ ቁሳቁሶች፣ ጌጣጌጦችና የጽሑፍ ውጤቶች እንዲቀርቡ ሆኗል። ይህ ደግሞ ባህሉ እንዲተዋወቅ፣ የገበያ ትስስር እንዲፈጠር፣ በዓሉንም ለማድመቅና የቱሪዝም መስህብ በማድረግ በአገር ግንባታ ውስጥ የድርሻውን እንዲወጣ ማድረግን ታሳቢ ያደረገ ነው።

የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ከበደ ዴሲሳ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ በዓሉ በአዲስ አበባ መከበሩን ተከትሎ በዚህ መልኩ የሚከናወን ኤግዚቢሽን ህብረተሰቡ ሁሉንም የባህል ውጤቶች በአንድ ቦታ እንዲያገኝ፣ ባህሉን እንዲያውቅና እንዲያስተዋውቅ፣ ለበዓሉ ድምቀት ደምቆ የሚወጣበትን አልባሳትና ጌጣጌጦች በቀላሉ በአንድ ቦታ እንዲያገኝ ያስችለዋል። ይሄን መሰል ኤግዚቢሽኖችም በክልሉ ባለው የዞንና የከተማ አስተዳደር መዋቅሮች የሚካሄድ ሲሆን፤ በቀጣይም የኦሮሞን ህዝብ ቱባ ባህል ከማስተዋወቅና ለቱሪዝም መስህብ ሆነው ለአገር ልማት የሚጠበቅባቸውን እንዲያበረክቱ ከማድረግ አኳያ ቢሮው የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።

የኢሬቻን በዓል ለማድመቅ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ነው፤ ህዝቡም በባህል አልባሳትና ጌጣጌጦች ደምቆ ለማክበር በሰፊው እየተዘጋጀ ነው። ይሁን እንጂ በዓልን ደምቆ ለማክበር ከመዘጋጀት በተጓዳኝ፤ በዓሉ በራሱ ደምቆ እንዲጠናቀቅ መስራትና ለዛም ራስን ማዘጋጀት ያስፈልጋል። በመሆኑም ኢሬቻ የሰላም፣ የአንድነትና የፍቅር በዓልነቱን መገንዘብ፣ የኢሬቻ የሰላም በዓልነትን ብቻም ሳይሆን የዚህ በዓል ባለቤት የሆነው የኦሮሞ ህዝብ ሰላማዊነትን በመገንዘብ በዓሉ ያለምንም ችግር በድምቀት ተከናውኖ በሰላም እንዲጠናቀቅ ሁሉም በአንድነት መንፈስ ሊተጋ ይገባዋል የሚለው የሁሉም አስተያየት ሰጪዎች መልዕክት ነው።

አዲስ ዘመን  መስከረም 14/2012 ዓ.ም

ወንድወሰን ሽመልስ