‹‹በርካታ ኪሎ ግራም ኮኬይን፣ ሄሮይንና ካናቢስ በቁጥጥር ሥር ውሏል››- ኮማንደር መንግስተአብ በየነ – በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ዘርፍ የአደገኛ ዕጽ ቁጥጥር ምክትል ዳይሬክተር

27

አደገኛ ዕጽ ዝውውር በይዘቱ ዓለም አቀፋዊ ባህርይ አለው።ባደጉና በማደግ ላይ በሚገኙም አገሮች የወንጀል ድርጊቱ እየተከሰተ ይገኛል።ደረጃው ይለያይ እንጂ በኢትዮጵያም የዕጽ ዝውውር ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ይታያል።አደገኛ ዕጽን መጠቀም ለብዙ የወንጀል ድርጊቶች የሚጋብዝ ሲሆን፤ በኢኮኖሚ፣ በጤና እና በፀጥታ ዙሪያም ሥጋት የደቀነ የወንጀል ድርጊት ነው።በእነዚህና ተዛማጅ ጉዳዮች ዙሪያ በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ዘርፍ የአደገኛ ዕጽ ቁጥጥር ምክትል ዳይሬክተር ኮማንደር መንግስተአብ በየነ ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።

አዲስ ዘመን፡- የአደገኛ ዕጽ ምንነትና ተጠቃሚነትን ዘርዘር አድርገው ቢነግሩን ?

ኮማንደር መንግስተአብ፡- አደገኛ ዕጽ ከስሙ እንደምንገነዘበው አደገኛነትን የሚያመላክት ነው።አደገኛነቱን የሚያመለክት ነው ስንል ምን ማለት ነው ? ከተባለ እነዚህ ዕጾች በሕግ የተከለከሉና በሕግ ያልተከለከሉ ማህበራዊ አደገኛ ዕጽ የምንላቸውን ስለሚያጠቃልሉ ነው።አደገኛነታቸው የሰውን ልጅ የማሰብ አዕምሮ ከነባራዊ ሁኔታ ውጭ በማድረግ ምናባዊ አስተሳሰብ እንዲያስብ የሚያደርጉ በመሆናቸው ነው።በተለይም ለሕገ ወጥነት ለጤና እና ለማህበራዊ ቀውስ የሚዳርግ እንዲሁም አጠቃላይ ከአወንታዊ ሁኔታዎች ባፈነገጠ መንገድ ከትክክለኛ እና ጤናማ አስተሳሰብ ውጭ የሚያደርግ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ዓለም አቀፋዊ የዘቱ ምን ይመስላል ?

ኮማንደር መንግስተአብ፡- አደገኛ ዕጽ ማንም ሰው እንደሚያውቀው ይዘቱ ዓለም አቀፋዊ ባህርይ ያለው ነው።ባደጉም ሆነ በማደግ ላይ በሚገኙ አገሮች ያለ የወንጀል ክስተት መሆኑ ግልጽ ነው።አገራችንም በዓለም ላይ ካሉ አገራት አንዷ እንደመሆኗ መጠን ከዚህ ጋር ተያይዞ ከተጽዕኖ ውጭ መሆን አትችልም።እናም በኢትዮጵያም እንደየትኛውም አገር የዕጽ ዝውውር እና ተጠቃሚነት አለ።

አደገኛ ዕጽ ሲባል ብዙ አይነት ነው።በባህሪው ይለያያል።ባህሪው ስልህ በአይነቱ ማለቴ ነው።ለምሳሌ ናይኮቲክስ ሳይኮትሮፒክስ የሚባሉ አሉ።ሳይኮትሮፒክስ ማለት ሰው ሰራሽ ለመድሃኒትነት ተቀምመው የሚሰሩ ናቸው።በተፈጥሮ የሚበቅሉ፣ የተወሰነ ደግሞ ለውጥ ተደርጎባቸው ጥቅም ላይ የሚውሉ አደገኛ ዕጾች አሉ።እነዚህ በሦስት የሚከፈሉ ናቸው።ሄሮይን፣ ኮኬይን እና ካናቢስ የሚባሉ ናቸው።የአደገኛ ዕጽ ባህርያቶችና አይነቶች ቢለያይም በተወሰነ መልኩ ክስተቱም ሆነ ምርቱ በአገራችን አለ።

አዲስ ዘመን፡- አደገኛ ዕጽን በማምረት የተለዩ አካባቢዎች የትኞቹ ናቸው?

ኮማንደር መንግስተአብ፡- በአገራችን ካናቢስ የሚባል ተክል ይበቅላል።በብዛት በምዕራብ አርሲ ሻሸመኔ አካባቢ ይታያል።እኛም ከኦሮሚያ ፖሊስ እና ከአካባቢው ፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር በየዓመቱ ሁል ጊዜ እናስወግዳለን።

አዲስ ዘመን፡- አሁን የጠቀሱት የምዕራብ አርሲ ሻሸመኔ አካባቢ ብቻ ነው በአደገኛ ዕፁ አምራችነት የተለየው ወይስ በሌሎች አካባቢዎች ይታያል?

ኮማንደር መንግስተአብ፡- አልፎ አልፎ ያጋጥማል።መጠኑ ብዙ ባይሆንም አለ።ይህ ተከስቶ ሲያጋጥምም እናስወግዳለን።

አዲስ ዘመን፡- ከዚህ በፊት በአዲስ አበባ ከተማም ለልማት ታጥረው የቆዩ ቦታዎች ላይ አደገኛ ዕፁ በቅሎ መታየቱንና እንዲወገድ መደረጉ ተገልጿል።አሁን በጠቀስኳቸውም ሆነ ሌሎች አካባቢዎች የታየበትን አጋጣሚ ይንገሩኝ?

ኮማንደር መንግስተአብ፡- በትክክል አሁንም በተጨባጭ ደርሰንበት እያስወገድን እንገኛለን።ፈርሰው ለመልሶ ግንባታና ማልማት ተብለው የተለዩ ቦታዎች መልሶ ግንባታቸው ባለመከናወኑ እንዲሁም እንደመደበቂያም ስለሚጠቀሙባቸው በእነዚህ ቦታዎች አደገኛ ዕጽ አብቅሎ ይታያል።አሁን በክረምቱ ወራት እንኳን ብዙ ቦታዎች ላይ አስወግደናል።ቂርቆስ፣ ኮልፌ እና ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አካባቢዎች እስካሁን ያስወገድንባቸው ሥፍራዎች ናቸው።በእነዚህ ቦታዎች ላይ ሁለትና ሦስት ጊዜያት አስወግደናል።

አዲስ ዘመን፡- አሁን ባነሷቸው የአዲስ አበባ ከተማ ለልማት ታጥረው የቆዩ ቦታዎች ላይ አደገኛ ዕፁን በማብቀል ተጠርጥረው ወይም ከኤግዝቢት ጋር የተያዙ ሰዎች ምን ያህል ናቸው?

ኮማንደር መንግስተአብ፡- በዚህ ምክንያት የተያዙ ሰዎች የሉም።ተክሉን ያዩ ሰዎች መረጃ ያመጣሉ።በተለይ በክረምት ወቅት ብዙ ቦታዎች ላይ እናጠናለን።የእኛ የክትትል ሰዎች በሚያደርጉት ጥናት በምንደርስበት እንዲሁም በሰዎች ጥቆማና መረጃ የምናገኘው አለ።እነዚህ ሰዎች ሲያበቅሉ ሁኔታዎችን አመቻችተው ነው የሚንቀሳቀሱት።ቦታው ለመልሶ ማልማት የተከለለ ቦታ በመሆኑና ከዕይታ ውጭ ሆነው ድርጊቱን ስለሚፈጽሙ አልተጋለጡም።ሆኖም ክትትል በማድረግ እያስወገድን እንገኛለን።የተመረቱ ምርቶች ሲያከፋፍሉ፣ ሲቸረችሩና ሲያዘዋውሩ ከእነኤግዝቢታቸው እንይዛለን።ግን ከአብቃዮቹ ጋር ተያይዞ እስካሁን ያጋጠመን ነገር የለም።

አዲስ ዘመን፡- ያስወገዳችሁት በመጠን ምን ያህል ይሆናል?

ኮማንደር መንግስተአብ፡- መጠኑ ብዙም ስፋት ያለው አይደለም።በእግር ደረጃ የሚለካ ነው።በተጠቀሱት ቦታዎች ላይ የተነቀሉትን የምንቆጥረው በእግር ደረጃ ነው።አምስት እግር፣ 10 እግር እና 20 እግር እያልን የተነቀሉትን ተክሎች ስፋት እንለካለን።ቦታውም በስፋት ለማምረት አይመችም።አብቃዮች ለዕይታ እንጋለጣለን የሚል ሥጋት ስላለባቸውም በስፋት አያመርቱትም።

ይሁን እንጂ እኛ በየጊዜው በምናደርገው ክትትል እንዲሁም ከህብረተሰቡ ጥቆማ ይደርሰናል።እነዚህን መሰረት በማድረግ ተከታትለን በመለየት እያስወገድን እንገኛለን።አብዛኛውን ጊዜ ተክሉ የሚበቅለው በክረምት ወራት ነው።በተለየ ሁኔታ ተክለው ውሃ እያጠጡ ካልተንከባከቡት በስተቀር በበጋ ወቅት ብዙም አያጋጥምም።

አዲስ ዘመን ፡- የአደገኛ ዕፆች ቁጥጥርን አስመልክቶ የሰራችሁት ሥራን በተመለከተ የ2011 ዓ.ም አፈፃፀማችሁ በተለይም ከአደገኛ ዕፆች ዝውውር ጋር በተገናኘ በቁጥጥር ሥር የዋሉ፣ የተገኘ የአደገኛ ዕጽ መጠን እና ወደ ህግ ቀርበው የተቀጡ ምን ያህል ናቸው?

ኮማንደር መንግስተአብ፡- ከሐምሌ አንድ 2010 ዓ.ም እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2011 ዓ.ም በነበረን የአንድ ዓመት እንቅስቃሴ ሁሉንም አይነት አደገኛ ዕጽ በቁጥጥር ሥር አውለናል።ለምሳሌ ኮኬይን ብናይ ወደ 186 ኪሎ ግራም በቁጥጥር ሥር ውሏል።ካናቢስም ወደ አንድ ሺ 104 ኪሎ ግራም አካባቢ በቁጥጥር ሥር እንዲውል ተደርጓል።ሄሮይንም ወደ ዘጠኝ ነጥብ ሁለት ኪሎ ግራም በቁጥጥር ሥር አውለናል።

ከእዚህ ጋር ተያይዞ 80 ሰዎችም በቁጥጥር ሥር ውለዋል።57 ወንዶችና 23 ሴቶች ናቸው።በቁጥጥር ሥር የዋሉት የ17 የተለያዩ አገራት ዜግነት ያላቸው ናቸው።ከእዚህ ጋር ተያይዞ በአዲስ አበባ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በአንድ ሺ ካሬ ሜትር መሬት ላይ በመልሶ ማልማት ታጥሮ የተከለለ ቦታ ላይ ተገኝቶ እንዲወገድ ተደርጓል።በሻሸመኔ አካባቢ ደግሞ በሰባት ሄክታር መሬት ላይ የበቀለ ዕፅ እንዲወገድ ተደርጓል።

አዲስ ዘመን፡- በክትትል የደረሳችሁባቸው በተደጋጋሚ ሰዎች አደገኛ ዕፁን የሚጠቀሙባቸው ቦታዎች የትኞቹ ናቸው ?

ኮማንደር መንግስተአብ፡- እንደሚታወቀው ፖሊስ ይህንን ሥራ ብቻውን አይሠራም።ብቻውን ሠርቶም ውጤታማ አይሆንም።ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት የሚተገበር ነው።ህብረተሰቡ በሚያደርሰን ጥቆማ ክትትል በማድረግ በሚመለከተው የሕግ አካል እንዲጠየቁ እናቀርባለን።ሰዎች አደገኛ ዕፁን በብዛት የሚጠቀሙባቸው ቦታዎች ሺሻ ቤቶች፣ ጫት መቃሚያ ቤቶች፣ ጭፈራ ቤቶች እና መጠጥ ቤቶች ናቸው።በየጎዳናው የሚቸረችሩና የሚጠቀሙ ሰዎችም አሉ።

በተጨማሪም የራሳችን የክትትል ክፍልም አለን።የክትትል ክፍሉ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ጥናት ያካሂዳል።በደረሰው የጥናት ውጤት መሰረትም ኦፕሬሽን ይካሄዳል።ይህ ማለት በቁጥጥር ሥር ለማዋል ሲደርስ የሚሰማራው ሃይል ሄዶ በቁጥጥር ሥር ያውላል።በዚህ ድርጊት የሚሳተፉ አከፋፋዮችን፣ ቸርቻሪዎችንና ተጠቃሚዎችን በቁጥጥር ሥር እናውላለን።

አዲስ ዘመን፡- ሽያጩ በብዛት የሚከናወንበት አካባቢና መንገድስ ምን አይነት ነው ?

ኮማንደር መንግስተአብ፡- ይህ የተለየ ቦታና ሁኔታ አለው ማለት አይቻልም።አብዛኛውን ጊዜ ጫት መቃሚያ የሚዘወተርባቸው አካባቢዎች፣ ታክሲ ተራ ስምሪት የሚደረግባቸው ቦታዎች፣ በየመጠጥ ቤት በራፍ እና በየትምህርት ቤቶች አካባቢ ሻጮቹ ያንዣብባሉ።በተለይ በብዛት የሚያጋጥመን እና በቁጥጥር የምንይዘው ካናቢስ የተባለውን ተክል ነው።በአቃቂ ቃሊቲ ኬላ አቋርጦ ሊገባ ሲል በቁጥጥር ሥር የዋለበት ሁኔታም አለ።

አዲስ ዘመን፡- በዘርፋችሁ የለያችሁት ከሆነ ይህንን አደገኛ ዕጽ የበለጠ ተጠቃሚ የሆኑት የትኞቹ የህብረተሰብ ክፍሎች ናቸው ?

ኮማንደር መንግስተአብ፡- ይህንን አደገኛ ዕጽ ተጠቃሚነትን ጠቅለል ባለ መልኩ ስንመለከት ዕድሜ፣ ፆታና ዘር የማይለይ ሆኖ እናገኘዋለን። በአብዛኛው የተጠቃሚነት ደረጃን ስናይ ሰፊ ቁጥር የሚሸፍነው የዕድሜ ክልል ግን ወጣቶች ናቸው።

አዲስ ዘመን፡- አብዛኛዎቹ በሱስ የተያዙ ሰዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ የገፋፋቸው ወይም መነሻ ምክንያቶቻቸው ምንድን ነው?

ኮማንደር መንግስተአብ፡- ብዙ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ።ከምክንያቶቹ የተወሰኑትን መጥቀስ ይቻላል።አንዳንዶች ሐሳብን እና ጭንቀትን ያቀላል የሚል የተሳሳተ አመለካከት በመያዝ ነው።ከዚህ በላይ ግን ዋናው ለበርካቶች መጠቀም ምክንያት የሚሆነው የጓደኝነት ግፊት ነው።ከጓደኛሞች መካከል አንድ ተጠቃሚ ካለ ለመሞከር ወይም ለመመሳሰል ሲሉ ይገቡበትና ሱሰኝነት ስለሚጠናወታቸው በዚያው ተስበው ይቀራሉ።

አላስፈላጊ ቦታ ወይም ሕገ ወጥና ሥራ ፈት የሆኑ ሰዎች የሚሰበሰቡበት ስፍራ መገኘትም ለብዙዎች መጠቀም እንደ ሰበብ የሚሆንበት አጋጣሚ ሰፊ ነው።ሥራ ከመፍጠር ይልቅ ያልተለመዱ ሁኔታዎችን ለመለማመድ ይዳርጋል።በመሆኑም በእንዲህ አይነት ሁኔታዎች መከሰት በሱስ ለመያዝ ምክንያት ሊሆን ይችላል።

አዲስ ዘመን፡- ሕገ ወጥ የሚባሉ ስፍራዎች ምን አይነቶች ናቸው ?

ኮማንደር መንግስተአብ፡- ሕገ ወጥ ከሚባሉት መካከል ጫት መቃሚያ ቤቶች፣ ሺሻ ማጨሻ፣ ቁማር ቤቶች ይጠቀሳሉ።እነዚህ ቦታዎች ሕግም የሚደግፋቸው አይደሉም።በመሆኑም ሱስ የሌለበት ሰው በእነዚህ ቦታዎች መገኘቱ በእራሱ ወደ ሱሰኝነት ይጋብዘዋል።

አዲስ ዘመን፡- አደገኛ ዕፆቹን በመጠቀም የሚፈፀሙ የወንጀል ድርጊት ምን አይነቶች ናቸው ?

 ኮማንደር መንግስተአብ፤ አደገኛ ዕጽን በመጠቀም የማይፈፀም የወንጀል ድርጊት የለም።‹‹እንዴት ይፈፀማል?›› የሚለውን ብናነሳ የተሻለ ይሆናል።አደገኛ ዕጽ በሁለት አይነት መንገድ ወንጀል ይፈፀምበታል።አደገኛ ዕፁን ተጠቅመው ወንጀል የሚፈፅሙ አሉ።ዕፁን የሚጠቀሙ ሰዎች የግድ ገንዘብ ያስፈልጋቸዋል።እነዚህ ሰዎች ሠርተው ገንዘብ ማግኘት የሚችሉ አይደሉም።

ስለዚህ ሱሳቸውን ለማርካት ሲሉ ገንዘብ የሚያገኙበትን የወንጀል መንገድ ይቀይሳሉ።ይዘርፋሉ፣ ይቀማሉ፣ ከውጭ ብቻ ሳይሆን ከቤተሰቦቻቸውም ጭምር ይዘርፋሉ።ተጠቃሚዎቹ ከባድ ወንጀሎችን ጭምር ለመፈፀም ወደ ኋላ አይሉም።አደገኛ ዕጽ ተጠቃሚዎች ማናቸውንም የወንጀል ድርጊቶችን አይፀየፉም።

አዲስ ዘመን፡- የአደገኛ ዕጽ ዝውውር እና ተጠቃሚነት በኢትዮጵያ ምን ይመስላል? በዕጽ ማዘዋወር በይበልጥ ተሳታፊ የሆኑትስ የየት አገር ዜጎች ናቸው?

ኮማንደር መንግስተአብ፡- አገራችን በትክክል የጂኦግራፊ አቀማመጧና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተደራሽነት ለዚህ አደገኛ ዕጽ ዝውውር ምክንያት እየሆነ ነው።ከዚህ ጋር ተያይዞም የብዙ አገር ዜጎች ሲሳተፉ በቁጥጥር ሥር ይውላሉ።የአንድ ወይም የሁለት አገር ብቻ ሳይሆን ብዛት ያላቸው የተለያዩ አገራት ዜጎች በዚህ ወንጀል ላይ ተሳትፈው ይገኛሉ። የመጠን እና የብዛት ልዩነት ሊሆን ይችላል እንጂ የብዙ አገር ዜግነት በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

አዲስ ዘመን፡- በደረጃ ብናስቀምጥ ከያዛችኋቸው መካከል የበለጠ የወንጀል ድርጊቱ ተሳታፊ ናቸው ብላችሁ የምታስቀምጡት የየትኞቹን አገራት ዜጎች ነው ?

ኮማንደር መንግስተአብ፡- እንደሁኔታው ነው የሚለያየው።ለምሳሌ የአንድ አገር ሰዎች በተደጋጋሚ በርከት ያሉ ሊሆኑ ይችላሉ።በሌላ ጊዜ ደግሞ የሌላ አገር ዜጎች ይያዛሉ።በመሆኑም የእዚህኛው አገር ዜጎች ብዙ ናቸው ብሎ ማስቀመጥና መወሰን አይቻልም።በአንድ ወቅት የድግግሞሽ እና የብዛት ጉዳይ አለ።

አዲስ ዘመን፡- ቀደም ሲል እንደጠቀሱልኝ አየር መንገድ በብዙ አገሮች ተደራሽ መሆኑ ለእዚህ ወንጀል መስፋፋት እንደ አንድ ምክንያት መሆኑን ጠቅሰውልኝ ነበር።እንደ ዚያ ከሆነ ወንጀሉን ለመቆጣጠር የፍተሻና የቁጥጥር ሥራችሁ በሰለጠነ የሰው ሃይልና በአስፈላጊ መሣሪያዎች የመታገዝ አቅሙ ምን ይመስላል?

ኮማንደር መንግስተአብ፡- ይህ ዘርፍ በፌዴራል ፖሊስ ሥር አንድ ክፍል ሆኖ ተደራጅቷል።ለዚህ ክፍል የተመደበለት የሰው ኃይል አለ።አስፈላጊ ትጥቅና መጓጓዣዎችም አሉን።ተደራሽ ለመሆን ፈታኝ ነው።ዓለም አቀፍ ዝውውር እና ዓለም አቀፍ ባህሪ ያለው በመሆኑ፣ የአደባበቅ ስልቱም የረቀቀ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የሰው ሃይሉ ሙሉ ለሙሉ ይሸፍናል ባይባልም አሁን ባለው የሰው ሃይል ቁጥጥር እያደረግን እንገኛለን።የሰው ሃይሉ ግን በቂ ነው ማለት አይቻልም።

አዲስ ዘመን፡- ይህንን ዘርፍ የበለጠ ለማጠናከር ምን ቢደረግ የተሻለ ነው ይላሉ?

ኮማንደር መንግስተአብ፡- ይህ የወንጀል ድርጊት ከጊዜ ወደ ጊዜ ባህሪውን እየቀያየረና እየረቀቀ ይገኛል።የመዳረሻ ቦታዎቹም እየሰፉ መጥተዋል።ባህሪያቸውን፣ ስልታቸውን እና መዳረሻዎቻቸውን ይቀያይራሉ።ስለሆነም ተመጣጣኝ አቅም ማጎልበት ይጠበቅብናል።ለዚህ ደግሞ በሰው ሃይል፣ በስልጠና እና በአስፈላጊ ግብአቶች ጊዜው የሚጠይቀውን ሁሉ አሟልተን መራመድ አለብን። ይህ የማይቋረጥ ሂደት መሆን አለበት።አሰራራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ እና እየዘመነ መሄድ ይኖርበታል።

አዲስ ዘመን፡- አደገኛ ዕፆቹን የሚያሳልፉበት የአደባበቅ ስልቱ ምን አይነት ነው ?

ኮማንደር መንግስተአብ፡- አደገኛ ዕጽን ደብቆ ማዘዋወር የወንጀል ተግባር እንደመሆኑ በወንጀል ድርጊቱ ተሳታፊ የሆኑ አካላት በጣም በርካታ የወንጀል አፈፃፀም ስልቶችን ይጠቀማሉ።አደገኛ ዕፁ በጠጣር እና በፈሳሽ መልክ ይዘዋወራል።በሆዳቸው ውስጥ ውጠው የሚመጡ አሉ።በሻንጣ ሽፋን ደብቀው ሊያልፉ ሲሞክሩም ያጋጥሙናል።በመጠጥ አይነቶች፣ በሻምፖ መልክ፣ ውድ የመጠጥ አይነቶች በማስመሰል፣ በጫማቸው ሶል፣ ድሬድ የሆኑት በጸጉራቸው ውስጥ ተሰርተውት ደብቀው የሚመጡ እና ለማሳለፍ ጥረት የሚያደርጉ ያጋጥሙናል።

ሴቶች በውስጥ ሱሪያቸውና በጡት መያዣቸው ደብቀው ሊያሳልፉ ሲሞክሩ የያዝናቸው አሉ።በእንዲህ እና በመሳሰሉት በርካታ መንገዶች በወንጀል ድርጊቱ ፈፃሚዎች አስተሳሰብ ለመፈተሽ ያስቸግራቸዋል ብለው በሚያስቡበት መንገድ ደብቀው ለማሳለፍ የሚሞክሩበት መንገድ አለ።ይሁን እንጂ በተመሳሳይ ፆታ በምናደርገው ፍተሻ ይጋለጣሉ።በተጨማሪም የድርጊቱ ተሳታፊዎች የመደበቂያ ስልት እንደሚጠቀሙ ሁሉ እኛም በእዛው ልክ የቁጥጥር ሥርዓታችንን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሳደግን እንገኛለን።

አዲስ ዘመን፡- አደገኛ ዕጽን በሚጠቀሙ ሰዎች ላይ የሚደርሱ ጉዳቶች ምን አይነት ናቸው?

ኮማንደር መንግስተአብ፡- በኢኮኖሚ፣ በጤናና በሥነ ልቦና ላይ የሚያደርሰው ጉዳት አለ።አደገኛ ዕጽ በኢኮኖሚ ላይ ጉዳት ያደርሳል።ቀደም ብለን እንዳነሳነው ዕፁን በብዛት የሚጠቀሙት ወጣቶች ናቸው።ሱሰኝነቱ ደግሞ ለሥራ ፈጣሪነት አያነሳሳም።ሱሰኛ የሆነ ሰው ደግሞ ሥራ ለመሥራትም ተነሳሽ አይሆንም።ሌላው አደገኛ ዕጽን ለመጠቀም ገንዘብ ያስፈልጋል።ተጠቃሚ የሆነው ሰው ካልሠራ ገንዘብ አያገኝም።በመሆኑም ገንዘብ ለማግኘት ወደ ሌብነት፣ ሥርቆት እና አላስፈላጊ ተግባራት ይሰማራል።

ከጤና ጋር ተያይዞም ተጠቃሚ የሆኑ ሰዎች ጤናማ አስተሳሰብ አይኖራቸውም።አስበው ሥራ ለመፍጠርና ሠርተው ገንዘብን ለማግኘት ያላቸው ተሞክሮ ዝቅተኛ ነው።እነዚህ ተደማምረው በኢኮኖሚው ላይም ተጽዕኖ ያሳድራሉ።ሱሰኞች ጤናማ አስተሳሰብ አይኖራቸውም።ጤናማ አስተሳሰብ ያለው አይነት ሐሳብ አያስቡም፣ አመጋገባቸውም ሊለይ ስለሚችል ጤና ላይ ተጽዕኖ ያሳድርባቸዋል።

አዲስ ዘመን፡- አደገኛ ዕፆችን የሚጠቀሙ ሰዎች በሴቶች፣ በወንድ ህጻናት እና ወጣቶች ላይ ጥቃት ያደርሳሉ እየተባለ ይወራል።በእንዲህ አይነት ወንጀል ተሳታፊ ሆነው በተጠርጣሪነት የያዛችሁት ወይም ያስቀጣችሁትን ቢነግሩኝ?

ኮማንደር መንግስተአብ፡- አደገኛ ዕጽን መጠቀም ለብዙ የወንጀል ድርጊት እንደሚጋብዝ ይታወቃል።አደገኛ ዕጽ ተጠቃሚዎችን ክትትል በማድረግ በቁጥጥር ሥር እናውላለን።ይህ የዕለት ተዕለት ተግባራችን ነው።ከእዚህ ጋር ተያይዞ ግን በተጨባጭ አደገኛ ዕጽን ተጠቅመው እንዲህ አይነት ወንጀል ፈፅመዋል በሚል ጥርጣሬ ወይም በተጨባጭ ማስረጃ በቁጥጥር ሥር ያዋልናቸው ሰዎች የሉም።እንደሚባለው ግን ሁላችንም እንሰማለን ።ዓለም አቀፍ የወንጀል ባህሪ ያለው እንደመሆኑ እኛ አገር ባይፈፀምም ሌሎች አገሮች ይፈፀማል።በተጨባጭ እነዚህ አደገኛ ዕፆችን ተጠቅሞ ወንጀል ፈፅሟል በሚል በወንጀል ድርጊት ላይ የተመዘገበም የለም።

አዲስ ዘመን፡- የተለያዩ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በአደገኛ ዕፆች ዝውውር ሰንሰለት ውስጥ ባለሀብቶች፣ ፀጥታ አስከባሪዎች እና የመንግሥት ባለሥልጣናት ጭምር ይገኙበታል ይባላልና በዚህ ላይ ምላሽዎ ምንድን ነው?

ኮማንደር መንግስተአብ፡- በዚህ ዙሪያ እኛ እስካሁን ያጋጠመን ነገር የለም።በተጨባጭ ዕገሌ የሚባል ባለሀብት ወይም ባለሥልጣን በእዚህ ድርጊት ተሳታፊ ነው ወይንም ሲሳተፍ ተገኘ ተብሎ የደረስንበት ሁኔታ የለም።ነገር ግን ዕጽ አዘዋዋሪዎችን፣ አከፋፋዮችንና ቸርቻሪዎችን እንይዛለን።ግን በተጨባጭ ፀጥታ አስከባሪዎች ዕገሌ የሚባል ባለሀብት ወይም ባለሥልጣን በግልጽ እጃቸው አለበት ተብሎ የተጠቆምንበትም በምርመራ ደረጃም የደረስንበት የለም።

አዲስ ዘመን፡- አደገኛ ዕጽ ወደፊት በአገር ላይ የሚያስከትለውን ተጽዕኖ ቢገልፁልኝ? ሂደቱ ወዴት ሊያመራ ይችላል የሚል ሥጋት አለዎት?

ኮማንደር መንግስተአብ፡- አደገኛ ዕጽ በአገር ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ሥጋት ነው።አደጉ የሚባሉት የምዕራብ አገራት ከእኛ ጋር በመረጃ ልውውጥም ሆነ በስልጠና ቅርብ ግንኙነት አለን።እንደምንገነዘበው ችግሩ አጠቃላይ ሥጋት የጋረጠ ነው።በኢኮኖሚ፣ በጤና እና በፀጥታ ዙሪያ መለስ ሥጋት ያለው የወንጀል ድርጊት ነው።ስለዚህ በአገራችን ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ በሥጋት የተቀመጠ ተግባር ነው።እኛም ከየትኛውም አገር የተለየን ስላልሆን ሥጋቱን እንጋራዋለን።በተለይ ደግሞ የአፍሪካ አገራት ገና በማደግ ላይ የምንገኝ እንደመሆናችን የችግሩ መጠን በኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል።በመሆኑም ትልቅ ሥጋት አድርገን ልንጠቅሰው እንችላለን።

አዲስ ዘመን፡- በተጠቀሰው ደረጃ ሥጋት የጋረጠ ከሆነ ምን መደረግ ይገባዋል ይላሉ? ህብረተሰቡ፣ የፀጥታ አካላት፣ መንግሥት እና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የወንጀል ድርጊቱን ከወዲሁ በመከላከል እና በመቆጣጠር ረገድ ምን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ?

ኮማንደር መንግስተአብ፡- ባለድርሻ አካላት የጤና ባለሙያዎች፣ የወጣት ማህበራት እና ሌሎች አካላትም ድርጊቱን በመከላከል ረገድ ከጊዜ ወደ ጊዜ ብዙ ተነሳሽነት እያሳዩ ነው።በጋራ እየሠራንም እንገኛለን።በዚህ ረገድ ህብረተሰቡ በተናጠል የሚያደርጋቸው ድጋፎች አሉ።ይህ ወደ መደበኛ ሁኔታ ቢመጣ፣ ማዕቀፍ ተበጅቶለት የጋራ እንቅስቃሴ ቢደረግ ትልቅ ውጤት ሊያስገኝ ይችላል።ከዚህ ድርጊት በሕገ ወጥ መንገድ ገንዘብ ማካበት የሚፈልጉ ግለሰቦች አሉ።

እነዚህ አካላት ከህብረተሰቡ አብራክ የወጡ ናቸው።ስለዚህ ህብረተሰቡ ከፀጥታ አካላት ጋር በቅርበት የሚሠራ ከሆነ ችግሩ የትም ሊደርስ አይችልም።ችግሩ እየቀነሰ እንዲሄድ ማድረግ ግን ይቻላል።ከጊዜ ወደ ጊዜም የተፈለገው ውጤት እንዲመዘገብ ማድረግ ይቻላል።ድርጊቱ እንዲቆም በጋራ መሥራት እንፈልጋለን ብለው የሚቀርቡ ብዙ የህብረተሰብ ክፍሎች አሉ።

ይሄንን የህዝቡን ፍላጎት አደረጃጀት ፈጥሮ ማጠናከር ይገባል።የሃይማኖት ተቋማት፣ እድሮች፣ ትምህርት ቤቶች ጭምር ተቀናጅተው ከሕግ አስከባሪ ጎን ተሰልፈው ተባብረው ቢሠሩ መልክ ማስያዝም ይቻላል።ጠንካራ ቅንጅት ከተፈጠረ የወንጀል ድርጊቱ ተሳታፊዎች ቦታ ያጣሉ።አደገኛ ዕጽ አዘዋዋሪዎቹ እንደልባቸው የሚጋልቡበት ሜዳ ይጠብባቸዋል።ስለዚህ ህብረተሰቡ ይህንን ነገር አውቆ ከሥጋት ነፃ ሆኖ ከፀጥታ አካላት ጋር በጋራ መሥራት ቢችል ዘለቄታዊ መፍትሄ ሊገኝበት ይችላል።

አዲስ ዘመን፡- በብዛት ወደ ኢትዮጵያ የሚገባው ከየትኞቹ አገራት ነው?

ኮማንደር መንግስተአብ፡- ኮኬይን የሚባለው አደገኛ ዕጽ ብቅለቱ ወደ ላቲን አሜሪካ ነው። ወደ ምርትነት የሚቀየረውም እዛው አካባቢ ነው።ሲጓጓዝም መነሻውን የሚያደርገው ያንን አካባቢ ነው።በብዛት እኛ የሚያጋጥመን እና በቁጥጥር ሥር የምናውለው ከብራዚል ሳኦፖሎ ከተማ መነሻ አድርጎ የሚመጣውን ነው።

ሄሮይን የሚባለው አደገኛ ዕጽ የሚበቅለው በእስያ አካባቢ ነው።በአፍጋኒስታን፣ ኢራንና ፓኪስታን አካባቢ ስለሚበቅል በህንድ ወይንም ደግሞ በዱባይ አቋርጦ ነው የሚዘዋወረው።እነዚህ ሁለት አደገኛ የዕጽ አይነቶች እነዚህን አቅጣጫዎች አልፈው ሲመጡ ነው በቁጥጥር ሥር የምናውለው።

አዲስ ዘመን፡- ከአየር መንገድ ባሻገር በድንበር የሚገባውን ለመቆጣጠር የተሠራ ሥራ ካለ ቢነግሩኝ?

ኮማንደር መንግስተአብ፡- እነዚህ አደገኛ ዕፆች አብዛኛውን ጊዜ ለመዘዋወር የሚጠቀሙት ትራንስፖርት አውሮፕላን ነው።ካናቢስ የሚባለው አደገኛ ዕጽ ግን ብዙ ጊዜ ከአገር ሊወጣ ሲል ነው የሚያጋጥመን።ምክንያቱም ቀደም ሲል እንደገለጽኩት በተወሰነ ደረጃ ብቅለቱ እኛ አገርም በአርሲ ሻሸመኔ አካባቢ በመኖሩ ነው።በመሆኑም በሞያሌ በኩል ወደ ኬኒያ እንዲሁም በመተማ በኩል ወደ ሱዳን ሊወጣ ሲል በአካባቢው ካሉ የፀጥታ ሃይሎች ጋር ባለን የመረጃ ልውውጥ እና የሥራ ግንኙነት በቁጥጥር ሥር ይውላል።

አዲስ ዘመን፡- መጨመር የሚፈልጉት ሐሳብ እና የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ?

ኮማንደር መንግስተአብ፡- ህብረተሰቡ በተደራጀ መልኩ ከፀጥታ ሃይሉ ጋር ቢሳተፍ ጥሩ ነው።ይህ ተግባር የፖሊስ የሥራ ድርሻ ተደርጎ ይቆጠራል።ግን አደገኛ ዕጽን መከላከልና መቆጣጠር የሁሉም ህብረተሰብ ሥራና ሃላፊነት መሆን አለበት።በመሆኑም ሁሉም በየድርሻው የሚችለውን ጥረት ቢያደርግ ይመከራል።የሃይማኖት አባቶች በእምነት ቦታዎች ጎጂነቱን እና ለአገር ጥፋት መሆኑን ቢያስተምሩ ይጠቅማል።

ወጣቱ ከዚህ ጥፋት እንጂ የሚያተርፈው ነገር አለመኖሩን ይገነዘባል።ዕድሮችም በተመሳሳይ ሃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው።ወጣቶች ከአደገኛ ዕጽ የራቁ ሊሆኑ ይገባቸዋል።ጎጂ እና አጥፊ እንጂ ጠቀሜታ የሌለው መሆኑን መገንዘብ ይገባል።

አደገኛ ዕፁን በማዘዋወር ተጠቃሚ ነን ብለው የሚንቀሳቀሱ የህብረተሰብ ክፍሎች ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ይገባል። በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የሚፈፀም ማናቸውም የወንጀል ድርጊት ከተጠያቂነት አያድንም።ስለዚህ በእዚህ አደገኛ ዕጽ ጉዳይ እጃቸው ያለበት የህብረተሰብ ክፍሎች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ እመክራለሁ።ብዙሃን መገናኛ ግንዛቤ በማስጨበጥ ረገድ ጉልህ ሚና አለው።በመሆኑም ለጉዳዩ ተገቢ ትኩረት በመስጠት ለህብረተሰቡ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ መሥራት ይጠበቅበታል።

አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ !

ኮማንደር መንግስተአብ፡- እኔም አመሰግናለሁ !

አዲስ ዘመን ረቡዕ  መስከረም 14/2012

 ዘላለም ግዛው