አገራዊ ብድር የመክፈል አቅም እንዴት ይጎለብታል?

13

 ከአንድ ዓመት በፊት በወጣው መረጃ መሠረት ኢትዮጵያ 52 ቢሊዮን ዶላር ገደማ የውጭ እና የሀገር ውስጥ የብድር ዕዳ ነበረባት፡፡ ከዚህ ውስጥ 27 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ከውጭ ሀገር የተበደረችው ሲሆን 25 ቢሊዮኑ ከሀገር ውስጥ የብድር ምንጮች የተገኘ ነው፡፡ በ2011 ዓ.ም 1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ዕዳ ብድር መከፈሉን የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ ይናገራሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ከውጭ ንግድ ግኝት ከሚገኘው ምንዛሪ 40 እስከ 50 በመቶ የሚሆነው ለውጭ ብድር ዕዳ ክፍያ እየዋለ ነው ይላሉ፡፡

ተግባራዊ እየተደረገ ያለው ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው አንዱ ግብም በቀጣይ ሦስት ዓመታት የሀገሪቱ ኢኮኖሚ የብድር ዕዳ ለመክፈል በሚያስችል ቁመና ላይ ማድረስ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ያብራራሉ፡፡ የአንድ ሀገር ኢኮኖሚ ብድር ለመክፈል በሚያስችል ቁመና ላይ ለማድረስ በአንድ በኩል የኢኮኖሚ እድገቱን ማፋጠን በሌላ በኩል ከውጭ የሚገኘውን የብድር ዕዳ መቀነስ እንደሚገባ የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ፡፡

በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር ከአብነህ ሳሙኤል እንደሚናገሩት፤ የአንድ ሀገር ዕዳ ምን ያህል መሆን አለበት የሚለው ቁርጥ ያለ መጠን የለም፡፡ ነገር ግን የሚቀመጠው ደረጃ አለ፡፡ አንድ ሀገር መበደር ያለባት የብድር ዕዳ መክፈል የምትችልበት አቅም በላይ መሆን የለበትም፡፡ በዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) መስፈርት መሠረት የታዳጊ ሀገሮች የብድር ዕዳ ከጠቅላላ ሀገራዊ ምርት ከ40 በመቶ ባይበልጥ ይመከራል፡፡ ላደጉት ሀገራት ደግሞ ከጠቅላላ ሀገራዊ ምርት ከ60 በመቶ በላይ ባይሆን ይመረጣል፡፡ ዋናው ትኩረት መደረግ ያለበት የሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ምን ይመስላል ወይም ከሀገራዊ ሀብት አንጻር ምን ደረጃ ላይ ነው በሚለው ላይ ነው፡፡

ከአንድ ዓመት በፊት የዓለም ባንክ ባወጣው መረጃ መሠረት የኢትዮጵያ ጠቅላላ ሀገራዊ ምርት 85 ቢሊዮን ገደማ መድረሱን የሚናገሩት አቶ ከአብነህ ኢትዮጵያ አሁን ላይ ያላት ዕዳ ከጠቅላላ ሀገራዊ ምርት 60 በመቶ መድረሱን ይናገራሉ፡፡ ይህም ማለት ከጠቅላላ ሀገራዊ ምርት 60 በመቶው በዕዳ የተሸፈነ ነው፡፡ በሌላው አገላለጽ ከ570 የነፍስ ወከፍ ገቢ ውስጥ 300 ገደማ የሚሆነው በዕዳ የተሸፈነ ነው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ የዓለም ባንክ ካስቀመጠው አንጻር 20 በመቶ አልፋ ሄዳለች ማለት ይችላሉ፡፡ የሀገሪቱ የብድር ዕዳ በዓለም ባንክ በተቀመጠው ስታንዳርድ መሠረት ወደ 40 በመቶ መውረድ ይገባል ይላሉ፡፡ ለዚህም በትኩረት ሊሰራ ይገባል ሲሉ ይመክራሉ፡፡

እንደ ከአብነህ ማብራሪያ፤ የሀገሪቱ የብድር ዕዳ ከፍ እንዲል ያደረጉት ሁለት ዋና ዋና ችግሮች አሉ፡፡ አንዱ የበጀት ጉድለት ነው፡፡ በየዓመቱ በጀት ሲበጀት ወደ 3 ነጥብ 2 በመቶ የበጀት ጉድለት ያጋጥማል፡፡ ስለዚህ ይህን ለማሟላት ተጨማሪ ብድር እያስፈለገ ነው፡፡ ገቢና ወጪ ንግድ መካከል ያለው ልዩነት እየሰፋ መሄድ ነው፡፡ በመሆኑም በአንድ በኩል የበጀት ጉድለት ለመቀነስ የመንግሥትን ገቢ ከፍ ማድረግ ያስፈልጋል። የመንግሥትን ገቢ ከፍ ለማድረግ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በጥንቃቄ ሊከናወኑ ይገባል።

ወደ ውጭ በሚላከውና ወደ ሀገር ውስጥ በሚገባው መካከል ያለው ልዩነት በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ ከውጭ የሚገባው ወደ ውጭ ከሚላከው በብዙ ዕጥፍ ይበልጣል፡፡ ይህን ክፍተት ለማጥበብ በትኩረት መስራት ዋነኛው ተግባር ሊሆን ይገባል፡፡ ወደ ውጭ የሚላከውን ከመጨመር ጎን ለጎን ወደ ውስጥ የሚገባውን መጠን ለመቀነስ በሀገር ውስጥ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል፡፡ የኤክስፖርት እድገት ብድር የመክፈል አቅም ስለሚጨምር የብድር ብድር እየቀነሰ እንዲሄድ እንደሚያደርግ ይናገራሉ፡፡

ሀገራዊ ኢንቨስትመንት ወይም ሀገራዊ ቁጠባ በማሳደግ በመንግሥትና በግል የሚቆጠበውን ቁጠባ ማሳደግ ኢንቨስትመንትን የበለጠ ለማሳደግ እንደሚያስችል የሚያብራሩት መምህር ከአብነህ፤ ኢንቨስትመንት እየጨመረ ሲሄድ የሚገኘው ገቢ ስለሚጨምር ከምናገኘው ገቢ በመቀነስ ብድር ለመክፈል እንደሚቻል አብራርተዋል፡፡

የመክፈል አቅምን ለማጎልበት ኢኮኖሚ ለማሳደግ ሁለት ፖሊሲዎች ጎን ለጎን ሥራ ላይ መዋል አለባቸው። ፊስካልና ሞኒተሪ ፖሊሲ፡፡ ጥቁር ገበያውን፣ ዶላሩን ለመቆጣጠር የተጀመሩ ተግባራት በበጎ የሚታዩ ናቸው፡፡ የኢኮኖሚ አቅም ለማሳደግም ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት ነው፡፡ ይህ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ችግርን ለመቅረፍ እገዛው ላቅ ያለ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ይላሉ፡፡

እንደ ከአብነህ ማብራሪያ በጥቁር ገበያ ከሚደረገው የቁጥጥር ሥራ ጎን ለጎን ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት የተጀመሩ ማሻሻያዎች ሊጠናከሩ ይገባል፡፡ የውጭ ባለሀብቶችን ቁጥር እና ኢንቨስትመንት መጠን ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት ሊጠናከሩ ይገባል። በሌላ በኩል የወለድ መጠን ፖሊሲ ላይ ማሻሻያ ሊደረግ ይገባል፡፡ ይህም አጋዥ ይሆናል። የወለድ መጠን ፖሊስ ለኢንቨስትመንትና ቁጠባ የራሱ አስተዋጽኦ ስለሚኖረው ይህ ፖሊሲ ለረጅም ዘመን የቆየ በመሆኑ ተገቢው ጥናት ተደርጎ ማሻሻያ ሊደረግበት ይገባል፡፡

አሁን የሚደረገው ሪፎርም ጠቅላላ ሀገራዊ ምርት እየጨመረ ብድሩ እንዳይጨምር የማድረግ ስትራቴጂ ላይ ትኩረት አድርጎ ሊሆን እንደሚገባ የሚያነሱት ከአብነህ፤ ያንን ሀገራዊ ምርት እንዲጨምር ከማድረግ ጎን ጎን ብድር እንዳይጨምር ማድረግ ከባድ እና ፈታኝ ቢሆንም መንግሥት ይህንን ከባድ የቤት ሥራ ለመወጣት መዘጋጀት አለበት ይላሉ፡፡ ያላላቁ ፕሮጀክቶችን ቶሎ ጨርሶ ወደ ሥራ እንዲገቡ ማድረግ እና በብድር ከተገኘው ገንዘብ ውስጥ በአግባቡ ሥራ ላይ ያልዋሉ ካሉ ተከታትሎ ወደ ሥራ እንዲገቡ የማድረግ ሥራ ቢሰራ ኢኮኖሚውን ማሳደግ ይቻላል ይላሉ፡፡

የአምቦ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ጉቱ ቴሶ እንደተናገሩት፤ የሀገሪቱ ብድር የመክፈል አቅሟ እንዲዳከም ያደረጉት በርካታ ምክንያቶች አሉ፡፡ በሀገሪቱ በነበረው ግጭቶች ምክንያት ወደ ውጭ ይላክ የነበሩት ማዕድናትና የግብርና ምርቶች መጠን እያሽቆለቆለ መምጣቱ አንዱ ነው፡፡ እነዚህ ምርቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ ዳግም ወደ ዓለም ገበያ የሚገቡበትን ሁኔታ ማመቻቸት የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርሙ ዋነኛው ተግባር ሊሆን ይገባል፡፡

ሀገሪቱ በኢንዱስትሪ ልማት በርካታ ተግባራትን የጀመረች ቢሆንም ዘርፉ በተለያዩ ችግሮች የተተበተበ በመሆኑ የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት አልተቻለም የሚሉት ዶክተር ጉቱ፤ በዘርፉ የሚስተዋሉ ሳንካዎች እንዲቀረፉ ማድረግ ለነገ የማይባል ተግባር ነው ይላሉ፡፡ ኢንዱስትሪዎች በሚፈለገው ልክ ማምረት ደረጃ ላይ ከደረሱ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ብድር ለመክፈል በሚያስችል ቁመና ላይ ማድረስ እንደሚቻልም ያብራራሉ፡፡

እንደ ዶክተር ጉቱ ማብራሪያ፤ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በጥሩ ቁመና ላይ እንዳይሆን እያደረገ ያለው ዋነኛው ገቢና ወጪ ንግድ መካከል ያለው ሰፊ ልዩነት ነው፡፡ ገቢና ወጪ ንግድ መካከል ያለውን ልዩነት የማጥበብ ሥራ በትኩረት ሊሰራ ይገባል፡፡

የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ብድር ለመክፈል በሚያስችል ቁመና ላይ ለማድረስ በትንሹ አምስት ዓመታት ሊፈጅ ይችላል የሚሉት ዶክተር ጉቱ፤ ማዕድን ማኑፋክቸሪንግና ሌሎች ዘርፎች ላይ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን መቅረፍ ላይ መንግሥት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አንስተዋል፡፡ ኢኮኖሚ አቅም ለማጎልበት የፖለቲካ ሹክቻን በመተው ወደ ኢኮኖሚ ማዘንበል ያስፈልጋል፡፡

እንደምሁራኑ ማብራሪያ በቀጣይ ዓመታት የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ብድር ለመክፈል በሚያስችል ቁመና ላይ የማይደርስ ከሆነ ብዙ አደጋዎችን ይዞ ሊመጣ ይችላል፡፡ አንደኛው የሀገሪቷን የመበደር ዕድሎችን ያሳጣል፡፡ ሁለተኛው ለፖለቲካ ቀውስም ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ ብድር ከፍ እያለ ሲሄድ በተለይም የውጭ ብድር ከሆነ መንግሥት ጫና ውስጥ ስለሚወድቅ መንግሥት ግብር ከፍ ያደርጋል፡ ፡

ገቢ መሰብሰቢያ መንገዶችን ከፍ ያደርጋል፡፡ ይህ ደግሞ ከሕዝብ ጋር ያጋጫል፡፡ ይህ ደግሞ መረጋጋት እንዳይኖር የማድረግ ዕድል አለው፡፡ ብድሩ እየጨመረ በሄደ ቁጥር ወለዱ እየጨመረ ስለሚሄድ ሀገራዊ ኢኮኖሚ ላይ ጫና እየፈጠረ ይሄዳል፡፡ በመሆኑም በአጭር ዓመታት ውስጥ ኢኮኖሚውን በዚያ ደረጃ ላይ ማድረስ ያስፈልጋል፡፡

አዲስ ዘመን  መስከረም 15/2012

መላኩ ኤሮሴ