ኢትዮጵያን ጨምሮ 130 ሀገራትን የጎበኘው ዓይነ ስውር

20

አካል ጉዳቱ ሊደርስበት ካሰበው ሳያግደው በሰባቱ አህጉራት ከ130 በላይ ሃገራትን ተዘዋውሮ የጎበኘው እንግሊዛዊው ቶኒ ጊልስ፤ ዓይነ በሲር ሲሆን ሁለቱም ጆሮዎቹ ትንሽ ትንሽ በመሳሪያ በመታገዝ ነው የሚሰሙት። ነገር ግን ይህ አካል ጉዳቱ ወደተለያዩ ስፍራዎች ተጉዞ ጉብኝት ከማድረግ አላገደውም። በዚህም ባለፉት 20 ዓመታት ከ130 በላይ ሃገራትን ጎብኝቷል።

ትናንት ቢቢሲ ስለቶኒ በድረገጹ እንዳስነበበው፤ ቶኒ የማየት ችግር እንዳለበት የታወቀው ገና የዘጠኝ ወር ህጻን እያለ ነበር። ከዚያም አስር ዓመት ሲሆነው የዓይን ብርሃኑን ሙሉ ለሙሉ አጣ። ዓይነ ስውር ከመሆኑ በፊትም ስድስት ዓመት እንደሞላው መስማት የሚችለው በከፊል እንደሆነ ታውቆ ነበር። አሁን መስማት እንዲያስችለው ከፍተኛ ኃይል ያለው ዘመናዊ የመስሚያ መርጃ መሳሪያ ቢጠቀምም ሁሉንም ድምጾች ግን ለመስማት አይችልም።

ቶኒ ከታዳጊነቱ ጀምሮ የተለያዩ ፈተናዎች ያጋጠሙት ሲሆን፤ በ15 ዓመቱ አባቱን ከማጣቱ ባሻገር 16 ዓመት ሲሆነው ደግሞ አካል ጉዳተኛ የነበረውና የቅርብ ጓደኛው በሞት ተለየው። በገጠመው ሐዘን ሳቢያም ለስድስት ወይም ለሰባት ዓመታት የአልኮል ሱሰኛ ሆኖ ነበር። በዚህም እስከ 24 ዓመቱ የአልኮል ሱሰኛ ነበር።

አባቱ የንግድ መርከቦች ላይ ይሰሩ ስለነበረ በሚሰሩበት ወቅት ከባሕር ዳርቻ ስላዩዋቸው የተለያዩ ቦታዎች ይተርኩለት ነበር። አባቱ ይተርኩለት የነበረው ታሪክ በታዳጊው ቶኒ ልብ ውስጥ የተለያዩ ቦታዎችን የመጎብኘት ትልቅ ፍላጎትን አሳድሮበታል። በዚህም ቦታዎችን ተዘዋውሮ ለመጎብኘት ፍላጎትና ጉጉት እንዳደረበት የሚናገረው ቶኒ፤ ዓለምን ዞሮ መጎብኘት የጀመረው የዛሬ 19 ዓመት የመጀመሪያ ጉዞውን ወደ አሜሪካ ኒው ኦርሊያንስ በማድረግ ነው።

እርሱም የመጀመሪያውን ጉብኝቱን እንደተናገረው፤ “እዚያ ስደርስም የት እንደምሄድ ስላላወቅሁ ደርቄ ነበር የቀረሁት። ከዚያም ሁለት ጊዜ በጥልቁ ከተነፈስኩ በኋላ እራሴን ‘ቶኒ ካልፈለግህ ወደ ቤትህ ተመለስ’ አልኩት።” ከዚያም ጉዞውን አቋርጦ ላለመመለስ በመወሰኑ ጉዞውን ቀጥሎ፤ ሁሉንም የአሜሪካ ግዛቶችን ተዟዙሮ ለመጎብኘት ችሏል።

ቶኒ ከጎበኛቸው ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ስትሆን፤ ከ130 በላይ ሃገራትን ተዘዋውሮ የጎበኘው ተጓዡ በዓለም ላይ ያሉ ቦታዎችን በተለየ መንገድ እንደሚመለከታቸው ይናገራል። “ቀዝቃዛውን አንታርክቲካን ጨምሮ፤ ሁሉንም አህጉራት ጎብኝቻለሁ። አላማዬም በዓለም ላይ ያሉትን ሁሉንም ሃገራት ተዘዋውሬ መጎብኘት ነው” የሚለው ቶኒ፤ “አንዳንዶች ጉብኝት ለእኔ የሚታሰብ እንዳልሆነ ይናገራሉ። ነገር ግን ዓለምን በሌላ መንገድ ላያት እንደምችል እያሳየሁ ነው” ይላል የ41 ዓመቱ እንግሊዛዊ ተጓዥ።

“ሰዎች ሲናገሩ እሰማለሁ፤ ተራራዎችን እወጣለሁ፤ እወርዳለሁ፤ በቆዳዬ በኩል ሁሉንም ስሜት አገኘዋለሁ። በዚህ መንገድ ነው ሃገራትን የምጎበኘው” ሲል ስፍራዎችን እንዴት እንዴት እንደሚጎበኝ ይገልጻል።

ቶኒ ባለፉት 20 ዓመታት ወደ ተለያዩ ቦታዎች በመጓዝ አዳዲስ ስፍራዎችን መጎብኘቱን ተናግሮ፤ እንደ እሱው ዓይነ ስውር የሆነችውን ግሪካዊት የሴት ጓደኛውን ያገኘውም ለጉብኝት ከተጓዘባቸው በአንዱ ቦታ ነው። ባለፈው ዓመትም ከጓደኛው ጋር ወደ ሩሲያ ተጉዘው እንደነበር ጠቁሞ፤ በጉብኝታቸውም የዓለማችንን ትልቋን ሃገር በባቡር በመጓጓዝ ጎብኝተዋል። ነገር ግን በአብዛኛው የጉብኝት ጉዞው ግን ብቻውን መሆን እንደሚወድ ተናግሯል።

ቶኒ ለጉዞው የሚሆነውን ወጪ የሚሸፍነው ከአባቱ ጡረታ ላይ በሚያገኘው ገንዘብ ሲሆን፤ ጉዞውን ቀደም ብሎ በማሰብ ያቅዳል። ለመጎብኝት ወደአቀዳቸው ቦታዎች ለመሄድ ሲያስብ፤ የአብዛኞቹ አየር መንገዶች ድረ ገጽ እንደርሱ ላሉ ዓይነ ስውራን ለመጠቀም አመቺ ስላልሆኑ፤ እናቱ የአውሮፕላን ጉዞ ትኬቶቹን በመቁረጥ እንደሚረዱትም ይናገራል።

እርሱም ኢንተርኔት በመጠቀም በሚጓዝባቸው ሃገሮች ውስጥ ሊረዱት የሚችሉ ሰዎችን ፈልጎ በማግኘት ቀድሞ የሚዘጋጅ ሲሆን፤ “እንዲሁ ብድግ ብዬ ሻንጣዬን ብድግ አድርጌ እዚህ ወይም እዚያ ልሂድ ብዬ አልወስንም። ቀድሜ ስለቦታው ማወቅ ይኖርብኛል። ጥሩ የማስታወስ ችሎታ አለኝ። ለዚህም ጉዞዬን ቀድሜ አቅዳለሁ” ይላል ቶኒ።

ካሰበው ቦታ ደርሶ በማያውቀው ከተማ ውስጥ የሚፈልገውን ቦታ ለማግኘት በራሱ የሚያደርገው ጥረት የተለየ ደስታ እንደሚፈጥርበት የሚናገረው ተጓዡ፤ “አንዳንድ ጊዜ ማንን እንደማገኝና ምን ሊከሰት እንደሚችል የማውቀው ነገር የለም። ይሄ ለእኔ የተለየ ጀብድ ነው” ብሏል።

ቶኒ እንደሚለው፤ “መጓዝን እንድመርጥ ካደረጉኝ ምክንያቶች መካከል አንዱ ሽሽት ነው። በውስጤ ካለው ስሜት ለመሸሽ የማደርገው ነበር” ይላል። ወደ አዳዲስ ቦታዎች መጓዙ ለቶኒ አብዝቶ የሚፈልገውን የስሜት መነቃቃት እንዲያገኝ ያስቻለው ሲሆን፤ “የተለያዩ ሰዎችን በጉብኝቴ ወቅት ማግኘት ስጀምር፤ ዓይነ ስውር ስለሆንኩ ሳይሆን በሰብእናዬ ምክንያት አብረውኝ መሆን እንደሚፈልጉ ለማወቅ ችያለሁ” ብሏል።

ቶኒ ጉዞውን ሲያደርግ ወጪውን ቆጥቦ ነው። ለመጓጓዣም የህዝብ ትራንስፖርትን ይጠቀማል። የመኝታ ክፍልም የሚይዘው ቅንጡ ያልሆኑ፤ ነገር ግን መሰረታዊ አገልግሎት ያላቸው ቦታዎችን ይመርጣል ሲል ለቢቢሲ የተናገረው ቶኒ በቅርቡ በአዲስ አበባ ባደረገው ጉብኝት ያስተናገደው ኢትዮጵያዊ ግለሰብ ነው።

እርሱም እንደተናገረው፤ ከአካባቢው ገበያ ተገዝቶ ባመጣለት ነገር ምግብ ለማዘጋጀት እጅጉን ፈቃደኛ ነበር። “በዙሪያዬ ያለውን ነገር እሰማለሁ፣ አሸታለሁ፤ እንዲሁም እዳስሳለሁም” ይላል። ቁሶችን መንካትና መዳሰስ የሚወደው ቶኒ ከሰዎች ጋር ሲያወራና የሚሉትን ሲያዳምጥ በአዕምሮው ውስጥ ስለነገሮች ምስል ለመፍጠር እንደሚያስችለው ይናገራል።

አዲስ አበባ ውስጥም የጥበብ ኤግዚቢሽን ወደ ሚታይበት ቦታ ሄዶ የቀረቡትን ስዕሎች በእጁ እንዲዳስስ ተፈቅዶለት ነበር። በዚህም ከሌሎቹ ሙዚየሞች በተለየ ለእሱ ፍላጎት ምላሽ በማግኘቱ ከሌሎቹ እኩል ቦታ እንደተሰጠው እንደተሰማው ተናግሯል።

እርሱም ተጓዡን እንደገለጸው፤ ብዙ ጊዜ ሌሎች ከሄዱበት መንገድ ውጪ ለመጓዝ ይደፍራል። ኢትዮጵያ ውስጥ በጉብኝት በነበረበት ወቅት ቱሪስቶች ብዙም ወደ ማይወዱት አንድ ሐይቅ በመሄድ በውሃው ላይ ላሉት አእዋፋት አሳ እየወረወረ ሲመግብ እንደነበርም ተናግሯል።

ቶኒ በጉዞው ላይ አንዳንድ ጊዜ የሚመራው ሰው የሚቀጥር ሲሆን፤ በአብዛኛው ግን ጉዞውን የሚያደርገው ብቻውን ነው። በዚህም በጉዞው ላይ የመጥፋት አጋጣሚዎች እንደነበር የጠቆመው ቶኒ፤ ነገር ግን በመንገድ ላይ ሲጠፋ ብዙም አይሸበርም። በእርጋታ በመንገዱ የሚያልፉ ሰዎችን ጠብቆ እንዲረዱት እንደሚጠይቅ ይናገራል።

“አስር አልፈው የሚሄዱ ሰዎችን ልታገኝ ትችላለህ፤ ከመካከላቸውም አንዱ ቆም ብሎ ‘መንገድ ጠፍቶህ ነው? እርዳታ ትፈልጋለህ?’ ብሎ ይጠይቅሃል የሚለው ቶኒ፤ በጉዞው ላይ ያገኛቸው የማያውቃቸው ሰዎች ወደ ቤታቸው ወስደው ምግብ እንደጋበዙትና በመንገዱም ላይ እንደረዱት ይናገራል።

ወደ ተለያዩ ሃገራት ባደረገው ጉዞ ወቅት ገንዘብ ከማሽኖች ማውጣትና የተለያዩ የገንዘብ ኖቶችን መለየትና በአግባቡ ማውጣት ትልቁ ፈተና መሆኑን የሚናገረው ተጓዡ፤ “ለዚህ አንድ የማምነው ሰው ማግኘት አለብኝ። ለዚህ ደግሞ ስለሰዎቹ ማጣራት ነበረብኝ። ታሪካቸውንም እጠይቃለሁ” ይላል።

ስለሰዎቹ የሰማው ነገር እምነት እንዲጥልባቸው ካደረገው ከማያውቀው ሰው ጋር ወደ ገንዘብ ማውጫ ማሽኖች በመሄድ ገንዘብ እንደሚያወጣ ገልጾ፤ “ገንዘቡን ካወጣሁ በኋላም አብረውኝ ያሉትን ሰዎች ገንዘቦቹ ምን ምን ያህል መጠን እንዳላቸው እጠይቃቸዋለሁ” ይላል። ከዛም የገንዘብ ኖቶቹን ለይቶ በመያዝ ለሚጠቀማቸውና ለሚገዛቸው ነገሮች ክፍያ ሳይቸገር እንደሚከፍል ተናግሯል።

ቶኒ በሚያደርጋቸው ጉዞዎቹ ሁሉ የተለያዩ የሙዚቃ መሳሪያዎችን ለመጫወት ሙከራ የሚያደርግ ሲሆን፤ “ከማፈቅራቸው ነገሮች መካከል አንዱ ሙዚቃ ነው። እራሴን ከሙዚቃ ጋር ማጣጣም እችላለሁ። ምቶቹን በደንብ እረዳቸዋለሁ። ሙዚቃ ሁሉንም ድንበር ይሻገራል” ይላል ቶኒ።

ቶኒ ባደረጋቸው ጉዞዎች ውስጥ በርካታ ድንቅ ገጽታ ያላቸውን ቦታዎች ጎብኝቷል፤ ፎቶግራፎችንም አንስቷል። ፎቶዎቹን አይቶ ሊደሰትባቸው ባይችልም በእራሱ ድረ ገጽ ላይ እንዲወጡ በማድረግ ሌሎች አይተውት እንዲደሰቱበት ያደርጋል።

ቶኒ አንዳንድ ጊዜ እርሱ ለጉብኝት ባለው ጥልቅ ፍቅር ግራ የሚጋቡ ሰዎች ያጋጥሙታል። “ዓይነ ስውር ሰው ስለምን ዓለምን ለመጎብኘት ይፈልጋል?” ሲሉ ይጠይቁታል። እርሱም ለነዚህ ሰዎች ቀላል ምላሽ ያለው ሲሆን “መልሱም፤ ለምን አይፈልግም?” ሲል ጠያቂዎቹን አፋቸውን ያስይዛል።

አዲስ ዘመን  መስከረም 16/2012

ሶሎሞን በየነ