የኑሮ ውድነቱን የማረጋጋት ሥራ በአዲስ አበባ

24

 ከሚሊኒየሙ መባቻ ጀምሮ በአገሪቷ የዋጋ ንረቱና የኑሮ ውድነቱ ከዕለት ወደ ዕለት እየጦዘ ጣራ የነካ ሲሆን፤ ኑሮ ውድነቱም ልጓም አጥቶ ማህበረሰቡም በኑሮ ውድነት አለንጋ እየተገረፈ ይገኛል። በተለይ ደግሞ በተገባደደው በጀት አመት ከግንቦት ወር ጀምሮ በአገሪቱ በሸቀጦችና በግብርና ምርቶች ላይ ምክንያት የለሽ የዋጋ ንረት በመከሰቱ፣ የኑሮ ውድነቱ በተለይ ከተሜ ቀመሱን የህብረተሰብ ክፍል በህይወት የመኖር ህልውናውን እየተፈታተነው ይገኛል።

በዚህም ኑሮው ከድጡ ወደማጡ ከሆነበት የማህበረሰብ ክፍል ግንባር ቀደም ከሆኑት አንዱ የመዲናዋ ነዋሪ ሲሆን፤ በመኖርና ባለመኖር መካከል ያለውን የመዲናዋ ነዋሪን የመኖር ህልወና ለማረጋገጥ፣ በተያዘው በጀት አመት በመዲናዋ የሚስተዋለውን የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት ሰፋፊ ስራዎችን ለመስራት ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ የንግድ ኢንስፔክሽንና ሬጉላቶሪ ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ጥላዬ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።

በተለይ በ2011 ዓ.ም ከግንቦት ወር ጀምሮ በህብረተሰቡ የእለት ፍጆታ በሆኑ ምርቶችና ሸቀጦች ላይ የተከሰተው የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ምክንያት የለሽና ሆን ተብሎ ህብረተሰቡ በኑሮ ውድነቱ ተማሮ በመንግስት ላይ እንዲያጉረመርም ታቅዶ እየተከናወነ ያለ ሴራ መሆኑን የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፤ ይሄን ምክንያት የለሽ የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረት ለመከላከል እንዲሁም በአገሪቱ የተረጋጋ የገበያ ሁኔታ እንዲፈጠር ከፌዴራል መንግስት እቅድ መውረዱን ይናገራሉ።

ይሄንንም እቅድ በአገር አቀፍ ደረጃ ለማስፈጸም የተቋቋመው ግብረ ኃይል በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ሲሆን፤ በአዲስ አበባ ደረጃ ደግሞ በክቡር ምክትል ከንቲባው፣ በንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ እንዲሁም ሌሎች ቁልፍ የሆኑ ተቋማት በቅንጅት የሚመሩት ግብረኃይል በአዲስ መልኩ ተቋቁሞ ወደ ስራ መገባቱን ገልጸዋል።

በግብይት ሂደቱ ላይ ምክንያት የለሽ የዋጋ ጭማሪና ህገወጥነት መስፈኑ በማህበረሰቡ ኑሮ ጫና አሳድሯል። ስለዚህም ማህበረሰቡ እነዚህ ችግሮች ተቀርፈው የተረጋጋ የግብይት ስርዓት እንዲፈጠር ሲጠይቅና ግፊት ሲያደርግ ቆይቷል። በመሆኑም መንግስትም ችግሩን በማጤንና የህብረተሰቡን የልብ ትርታ በማድመጥ ኮንትሮባንድና ህገወጥ ንግድን ለመከላከል እንዲሁም የገበያ የማረጋጋት ስራ ለመስራት በማሰብ ይህን ግብረኃይል በማቋቋም የኑሮ ውድነቱን የማረጋጋትና ህገወጥነትን የመከላከል ስራዎችን ቀጣይነት ባለው መልኩ እየሰራ ይገኛል።

በዚህም በህገወጥ መንገድ የሚሰሩ የንግድ ተቋማትና ድርጀቶችን የማስተካከል፣ በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ ምርቶች ላይ የሚታዩ የአቅርቦት ችግሮችን ለመፍታት የሸማች ህብረት ስራ ማህበራትን ማዕከል ያደረገ የአቅርቦት ስርዓት እንዲኖር በማድረግ የማስተካከያ ስራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል።

ህገወጥነትን ከመከላከል አንጻር በዋናነት የዋጋ ንረቱ ጎልቶ በታየባቸው እንደ ዳቦ፣ አትክልት፣ ፍራፍሬ፣ ስጋ፣ እህል እንዲሁም ከኮንስትራክሽን የግብዓት ዕቃዎች ሽያጭ ጋር ተያይዞ የሚሰሩ የንግድ ድርጅቶችን የመፈተሽ ስራዎች ተሰርተዋል።

በተያዘው በጀት ዓመት አምስት ሺህ 700 የሚደርሱ የንግድ ድርጅቶች የተፈተሹ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ 609 የሚሆኑት የንግድ ድርጅቶች ህግን በመተላለፍ እና የተለያዩ ጥፋቶችን በመፈጸማቸው እንዲታሸጉ ተደርጓል። ቀሪዎቹ ሁለት ሺህ 387 የሚጠጉት ደግሞ የተለያዩ ጥፋት ቢያጠፉም ጥፋታቸው በማስጠንቀቂያ የሚታለፍ በመሆኑ፤ በማስጠንቀቂያ ታልፈዋል። አጠቃላይ ህገወጥነትን ለማስተካከልና የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት በተለያዩ የንግድ ድርጅቶች ላይ አሰራራቸውን በመፈተሽ የማስተካከል ስራ ተሰርቷል።

ከዚህ ጎን ለጎንም በዋና ዋና የአትክልትና ፍራፍሬ የግብይት ማዕከላት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ የቁጥጥርና የክትትል ስራዎች የተሰራ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሀብታሙ፤ በመዲናዋ ያለው የአትክልት ግብይት በደረቅ ሌሊት የሚፈጸም ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ግብይቱ ያለንግድ ፍቃድና ህጋዊ ደረሰኝ የሚፈጸም ከመሆኑ ባሻገር ህገወጥ ደላሎች ጣልቃ በመግባት በምርት ዋጋው ላይ ፈላጭ ቆራጭ የሚሆኑበት አሰራር አለ። እንዲሁም ግብይቱም ምርቱ መኪና ላይ እንደተጫነ አየር ባየር የሚሸጥበት ሁኔታም አለ ብለዋል።

ይሄንን ህገወጥ ግብይት ለመከላከል ግብረሀይሉ በአትክልት ተራ ለሁለት ቀን በውድቅት ሌሊት ባደረገው ቁጥጥርና ክትትል፤ በህገወጥ መንገድ አትክልትና ፍራፍሬ ጭነው ለመሸጥ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 59 መኪኖች ላይ ርምጃ ተወስዷል። ከነዚህ መኪኖች ላይም የተወረሰ አትክልትና ፍራፍሬ በህብረት ስራ ማህበራትና በኢትፍሩት ሱቆች በኩል በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ እንዲሆን በማድረግ ገበያውን የማረጋጋት ስራ ተሰርቷል። በዚህም የአትክልትና ፍራፍሬ ዋጋ ገበያው ላይ በተወሰነ መልኩ ቅናሽ ታይቷል።

በተመሳሳይ የእህል ግብይት ላይ ሰፊ የደላላ ጣልቃ ገብነትና ህገወጥ ንግድ የሚስተዋልበት መሆኑን የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፤ በህገወጥ ደላሎች ጣልቃገብነት በተለያዩ ቦታ ሲዘዋወር የነበረ 52 መኪና ጤፍና ስንዴ በቁጥጥር ስር ከማዋል ጎን ለጎን በተደረገው ርምጃና ቁጥጥር ህገወጥ ደላላዎችን በህግ ተጠያቂ የማድረግ ስራ ተሰርቷል። የተያዙትንም ምርቶች በፋይናንስ አሰራር ስርዓት መሰረት ወደ መንግስት ገቢ የማድረግ፣ የኑሮ ውድነቱንና የገበያ ዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት እነዚህን በመንግስት ቁጥጥር የተደረጉ ምርቶችን ለማህበረሰቡ ተደራሽ የማድረግ ስራ እንደተሰራም ተናግረዋል።

መኪናዎች ምርት ጭነው ከክልል ወደ መዲናዋ ከመጡ በኋላ የተለያዩ ስውር ቦታዎች ላይ ይቆማሉ። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ህገወጥ ደላሎች የምርቱን ናሙና በመያዝ በህገወጥ መንገድ ግብይት ለማካሄድ ሲደራደሩ ስምንት ህገወጥ ደላሎች ከነናሙናው በቁጥጥር ስር ውለው ለህግ እንዲቀርቡ መደረጉን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ ህገወጥ ደላሎች እንደፈለጉ ዋጋ የሚወስኑበት፣ ምርት የሚይዙበትና ሲፈልጉ የሚለቁበት አሰራር አለ። በተደረገውም ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል ይሄንን ሲፈጽሙ የተገኙ ደላሎች ላይ ርምጃ ተወስዷል። የዚህ አይነት ርምጃም በመዲናዋ የተረጋጋ የግብይት ስርዓት እስኪሰፍን ድረስ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ከቁም እንስሳትና ከስጋ ምርት አቅርቦት ጋር በተያያዘ የሚታየውን የዋጋ ግሽበት መነሻ ያደረገ ጥናት ተደርጓል። በዚህም የቁም እንስሳት ግብይት ላይ ሰፊ ህገወጥ ስራዎችና የህገወጥ ደላሎች ጣልቃገብነት መኖሩን በጥናት መረጋገጡን የተናገሩት ዳይሬክተሩ፤ በዘርፉ ላይ የሚስተዋለውን ህገወጥነት የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ ለማስተካከል እንቅስቃሴዎች መጀመሩን ገልጸዋል።

በሁሉም ዘርፎች ላይ ህግ የማስከበር ስራ ተጠናክሮ እየተሰራ ሲሆን፤ እየተወሰዱ ያሉት የቁጥጥር ስራዎችና ርምጃዎች በመዲናዋ የሚስተዋለውን የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ላይ የተወሰነ ለውጥ አምጥቷል የሚሉት አቶ ሀብታሙ፤ የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት እየተወሰደ ያለው ርምጃና ቁጥጥር ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፤ በአጠቃላይ ለዋጋ ንረት እና ለኑሮ ውድነት መንስኤ የሆኑ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት ችግሩን ከስር ከመሰረቱ ለመቅረፍ እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 07 የተስፋ ብርሃን ሸማቾች ህብረት ሰራ ማህበር የፋይናንስ ክፍል ኃላፊ አቶ አሸናፊ ሽዶ እንደተናገሩት፤ ከጳጉሜን መጀመሪያ አንስቶ መንግስት በህገወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ የወረሳቸውን የተለያዩ አይነት ሸቀጦችን በሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት በኩል ለማህበረሰቡ ተደራሽ አድርጓል። ለበዓሉም የኑሮ ውድነቱ እንዲረጋጋ የማድረግ ስራ ተሰርቷል።

በዚህም በከተማ አስተዳደሩ በኩል ለማህበሩ የተለያዩ ሸቀጣ ሸቀጦችና ምርቶች የቀረቡለት ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም እህል ይገኙበታል። ለአብነትም ቀይ ሽንኩርትን ብንወስድ በበዓሉ ዋዜማ ገበያ ላይ አንድ ኪሎ እስከ 40 ብር ገብቶ የነበረበትን ሁኔታ ለመቀየር መንግስት አንድ ኪሎ ቀይ ሽንኩርት በስድስት ብር ዋጋ ለማህበሩ ተደራሽ ያደረገ ሲሆን፤ ማህበሩ ደግሞ አንድ ኪሎ ቀይ ሽንኩርት በስምንት ብር ዋጋ ለማህበረሰቡ ተደራሽ የማድረግ ስራ ሰርቷል። በአጠቃላይ የተለያዩ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማህበረሰቡ ተደራሽ በማድረግ የዋጋ ንረቱን የማረጋጋት ስራ መስራቱን ተናግረዋል።

እየተወሰደ ያለው ርምጃ የሚበረታታ ቢሆንም አሁንም የዋጋ ንረቱና የኑሮ ውድነቱ እንዲባባስ የሚያደርጉ ህገወጥ ነጋዴዎችና ደላሎች አልተያዙም የሚሉት አቶ አሸናፊ፤ የዋጋ ንረቱና የኑሮ ውድነት በዘላቂነት እንዲቀረፍ በቀጣይነት በህብረት ስራ ማህበራቱ በኩል እነዚህ ምርቶች ለህብረተሰቡ ተደራሽ ቢደረግ በአትክልት ተራና በአንዳንድ ትልልቅ የገበያ ቦታዎች ላይ የሚስተዋለውን የዋጋ ንረት እና የደላሎች ጣልቃ ገብነትን ማስቀረት ይቻላል።

እንዲሁም ከገበሬው ማሳ ጀምሮ እስከ ምርት መዳረሻው ድረስ ባለው ሂደት መካከል ያሉትን ህገወጥነቶች ለማክሰም፤ ከምርቱ መነሻ ጀምሮ የአሰራር ስርዓት ዘርግቶ ቁጥጥር በማድረግ ገበሬውና ሸማቹ በቀጥታ የሚገናኙበትን ተቋማት በማስፋት የዋጋ ንረቱንና የኑሮ ውድነቱን ለመቅረፍ መሰራት አለበት።

ለአብነት በግብጽ በአንድ ወቅት ከኢትዮጵያ የገዘፈ የዋጋ ግሽበት ነበረ። የዋጋ ንረቱ እንዲቀረፍ በተቀናጀ መልኩ ቀጣይነት ያለው ስራ በመስራታቸው አሁን ላይ በግብጽ የዋጋ ንረቱ ወርዷል። በኢትዮጵያም ይህ እንዲመጣ የተቀናጀና ቀጣይነት ያለው ስራ መሰራት እንዳለበት ተናግረዋል።

በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 07 በሚገኘው ተስፋ ብርሃን ሸማቾች ማህበር የተለያዩ ምርቶችን ሲሸምቱ ያገኘናቸውን አቶ ጌታቸው ጸጋየና ወይዘሮ ሶፊያ ሸሪፍን እንደሚከተለው አነጋግረናቸዋል። በወረዳ 07 ቀበሌ 08 ነዋሪ የሆኑት አቶ ጌታቸው እንደሚናገሩት፤ ከህብረት ስራ ማህበሩ አትክልት ፍራፍሬ እንዲሁም እህል ገዝተዋል። ለአብነትም ከበዓሉ በፊት አንድ ኪሎ ቀይ ሽንኩርት 28 ብር ነበር። የአዲስ አመት አውዳመቱን ተከትሎ በበዓሉ ዋዜማ እስከ40 ብር ደርሶ ነበር። አሁን ላይ መንግስት እየወሰደ ባለው እርምጃ ደግሞ ወደ 15 ብር ወርዷል።

በህገወጥ መንገድ ሲዘዋወር በነበረ የአትክልትና የፍራፍሬ እንዲሁም እህል ምርት ላይ መንግስት የወሰደው ርምጃ የሚበረታታና እንደግለሰብም ያስደስታቸው መሆኑን የተናገሩት አቶ ጌታቸው፤ በህብረት ስራ ማህበሩ በኩል የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም እህል በመቅረቡ ለበዓል አንድ ኪሎ ቀይ ሽንኩርት በስምንት ብር፣ አንድ ኪሎ ጤፍ በ24 ብር፣ ሶስት ኪሎ ጥቅል ጎመን በአምስት ብር ዋጋ በመግዛት አመት በዓሉን ከልጆቻቸው ጋር ተደስተው እንደዋሉ ተናግረዋል።

ህዝቡ በኑሮ ውድነቱ ተማሮ መንግስትና ህዝብ ሆድና ጀርባ እንዲሆኑ የሚሰሩ ህገወጥ ነጋዴዎችንና ደላሎችን ለሚመለከተው የመንግስት አካል በመጠቆም የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ የተናገሩት አቶ ጌታቸው፤ ወፍጮ ቤት ላይ በእህል ንግድ የተሰማሩ አያሌ ህገወጥ ነጋዴዎችና ደላሎች ስላሉ መንግስት ፊቱን ወደዚህ ዘርፍ አዙሮ መሰል ርምጃ እንዲወስድ ጠቁመዋል። እየተወሰደ ያለው ርምጃ ትክክለኛና የህብረተሰቡን እንባ ያበሰ ሲሆን፤ በቀጣይም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለመንግስት አሳስበዋል።

ሁሌም ፒያሳ አትክልት ተራ ሂደው የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬ ሲገዙ ከአምስት ኪሎ ላይ አንድ ኪሎ ተኩል በእያንዳንዱ ምርት ላይ እንደሚቀሸቡ የሚናገሩት በወረዳ 07 ቀበሌ 15 ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ሶፊያ፤ የአስር ቤተሰብ አስተዳዳሪ ናቸው። በኑሮ ውድነቱ ጫና ልጆቼን ምን ላቅርብላቸው እያልሁ በመብሰልሰል መንገድ ስጓዝ ብቻዬን እያወራሁ እጓዛለሁ።

ቤት ውስጥም የሌለብኝን አመል ጸባዬ ንጭንጭ ይላል የሚሉት ወይዘሮ ሶፊያ፤ ጤፍ በኪሎ ከ36 እስከ 40 ብር ገበያ መግባቱን ጠቁመው፤ ይሄንን ያህል ዋጋ አውጥተው የመግዛት አቅም ባይኖራቸውም፤ መንግስት በህብረት ስራ ማህበራት በኩል በተመጣጣኝ ዋጋ ማኛ ጤፍ በኪሎ 24 ብር እየገዙ ልጆቻቸው ሳይራቡ ቤተሰቦቻቸውን እየመሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በቅርቡ የበዓል ዋዜማ ጎረቤታቸው ሁለት ኪሎ ሽንኩርት 40 ብር ገዝተው በዓሉን ለመዋል ሲሰናዱ፤ እርሳቸው ግን በዚህ ዋጋ ገዝተው በዓሉን ለማሳለፍ አቅሙ አልነበራቸውም ነበር። በዓሉንም እንዴት ብለው እንደሚያሳልፉ ግራ እየተጋቡ ባለበት ወቅት፤ መንግስት በህገወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ በነበሩ ምርቶች ላይ በወሰደው ርምጃ በማህበራቱ በኩል የተለያዩ አትክልቶችንና ፍራፍሬዎችን ለማህበረሰቡ ተደራሽ በማድረጉ፤ በስምንት ብር ዋጋ አስር ኪሎ ቀይ ሽንኩርት 80 ብር በመግዛት ዘመን መለወጫን ከቤተሰቦቻቸው ጋር ስቀው ማሳለፋቸውን ተናግረዋል።

መንግስት እንደ ስኳርና ዘይት ሌሎች ህብረተሰቡ ለዕለት ፍጆታ የሚያውላቸውን ምርትና ሸቀጦች በህብረት ስራ ማህበራቱ በኩል በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ ቢያደርግ ህብረተሰቡን ከገባበት የኑሮ ውድነት ማላቀቅ እንደሚችል የሚናገሩት የመዲናዋ ነዋሪ፤ መንግስት አሁን ላይ እየወሰደ ያለው ርምጃና ቁጥጥር የሚበረታታ ቢሆንም፤ እንደ አሁን ቀደሙ ተጀምሮ እንዳይቆም ስጋት እንዳደረባቸውም ተናግረዋል።

አዲስ ዘመን  መስከረም 16/2012

ሶሎሞን በየነ