ቅንጭብ ታሪክ

26

 ወረህ አቡል፡ በገነቴ ዘዬ የምርቃት መክፈቻ ነው። ብዙውን ጊዜ አክስቴ ቤት ስሄድ ቡና ሲፈላ እደርሳለሁ። ታድያ ይሄ በሂና የቀላ ጢማቸው የእሳት ፏፏቴ መስሎ ከአገጫቸው የሚወርደው፤ ዘወትር መፋቂያ ሰክተው የማያቸው ሰውዬ፤ በቡና ጠጪ ጎረቤቶቻቸውና በሚጣፍጥ የቆላ እጣን መካከል ሆነው ‹‹ ውረህ አቡል!›› ብለው ይጀምሩና ወደ አስቂኝነት የተጠጋ ግጥም የመሰለ ረጅም ምርቃት ይቀጥላሉ።

‹‹ አሜን በል፤ ተቀበል /የማታውቅ ፈቀቅ በል/ ከጎረቤት ምቀኛ/ ከአሮጊት ነገረኛ/ ከጅል ግልምጫ/ ከአህያ እርግጫ/ … ይሰውርህ ‹‹አቦ›› ታድያ ‹‹አቦ›› ሲሉ ‹‹ቦ›› ን ጠበቅ አድርገው ነው። አንዴ ጨብ የሚያደርጓት ደማቅ ጭብጨባቸው የምታጅበው ይህቺ ‹‹አቦ›› ሲናገሯት የምታረካ፤ እገጭ አድርጋ የምትዘጋ ቤት መምቻ ነበረች። ‹‹አቦ››ን ማንም እንደሳቸው ሲላት ሰምቼ አላውቅም።

#############

ኤህ! የእርግማን መክፈቻ። ልክ ‹‹ወረህ አቡል›› የምርቃት መጀመሪያ እንደሆነው ሁሉ። ‹‹ኤህ›› አንዳንዴም በራሷ እርግማን ልትሆን ትችላለች። ብዙ ጊዜ ሁለተኛዋ ድምፅ ‹‹ህ›› ላላ ስለምትል ቃሉ ‹‹ኤ›› ብቻ ይመስላል። ታድያ የጓደኛዬ የመሰረት ወንድም፤ ተረጋሚው ሀብታሙ ‹‹ኤህ!›› ሲሉት አንቱታቸውንም ትቶ ጭራሽ ያሾፍባቸው ጀመረ፡ ‹‹ አይሻልሽም ቢ?›› አሮጊቷ ወደ ሰማይ አንጋጠው፤ የእንባ ግት በቋጠሩ ትናንሽ ዐይኖቻቸው ወደ አርአያም እያዩ፤ አመልካች አውራ ጣታቸውን አጋጥመው በሌሎቹ ሶስት ጣቶቻቸው ወደ ሰባተኛው ሰማይ

 እየጠቆሙ፤ ብቸኝነት በቀጠነው የተራጋሚ አሮጊት ድምፅ፡ ‹‹የእናት አባቴ ውቃቢ በአጭር ያስቀርህ፤ በአጭር ቅር እቴ!››

እርግማናቸው መሬት ጠብ አትልም የሚባሉትና በዚህም ብዙው የመንደር ሴት የሚፈራቸው ይህቺ መካን ሴት በሌላም ጊዜ ይህቺን እታለም ሉሉ የተባለች ታታሪ ወላድ ሲረግሟት የሰማሁት ከዚህ ይብሳል፡ ‹‹እመቤቴ በሽፍን ትውሰድሽ፤ ማህፀነ ጃርት ያድርግሽ››። እታለም ያኔ ስድስተኛ ልጇን አርግዛ ነበር። በሽፍን አልወሰደቻትም፤ ማህፀነ ጃርት አለመሆንዋን ግን አላውቅም።

ምንጭ፡- ( በደራሲ ሙሉጌታ አለባቸው ከተፃፈው ማህረቤን ያያችሁ መፅሀፍ ከገፅ 118 እና 122 የተወሰደ)

አዲስ ዘመን  መስከረም 19/2012