“በሰራተኞቻችን ያለ አግባብ ጥቅም የተጠየቀ ሰው ካለ መረጃ ማቅረብ ይችላል” – አቶ አብዲሳ ያደታ የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር

27

ገጠርን ከከተማ በማገናኘት በገጠር የሚመረተውን ምርት ለከተሜው ከተማ ያፈራውን የኢንዱስትሪ ውጤት ለገጠሩ የህብረተሰብ ክፍል የሚያደርስ ነው የትራንስፖርት ዘርፉ። በሌላ በኩልም የወጪና ገቢ ንግድ የተሳለጠ እንዲሆንም የሚወጣው ሚና በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ይህ አገራዊ ድርሻው እንደተጠበቀ ሆኖ ግን በተለያዩ ችግሮች ውስጥም ያለ ዘርፍ ነው፡፡ መልካም አጋጣሚዎቹን በማስቀጠል ችግሮቹን ለመቅረፍ ምን እየተሰራ ነው ስንል ለፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ለአቶ አብዲሳ ያደታ ጥያቄዎችን አቅርበናል።

አዲስ ዘመን ፦ በትራንስፖርት ዘርፉ ላይ ያሉ መልካም እድሎችና ችግሮችን እንዴት ይገልጻሉ?

አቶ አብዲሳ፦ በአገራችን የመንገድ ትርንስፖርት ዘርፍ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገቱን ከማሳለጥ አኳያ ከፍተኛ ድርሻ ያለው ነው። ይህ ድርሻው እንደተጠበቀ ሆኖ ከመልካም አስተዳደር፣ ከኪራይ ሰብሳቢነት ጋር በተያያዙ እንዲሁም አሰራሩ በሚፈለገው ደረጃ በቴክኖሎጂ ያልተደገፈ ከመሆኑና ስራውም ሰፊ ኢንቨስትመንትን የሚፈልግ ስለሆነ የሚጠበቅበትን ያህል ማደግ፤ የህብረተሰቡንም ፍላጎት ማሟላት ሳይችል ቆይቷል።

በሌላ በኩልም በተለይ በዘርፉ የሚስተዋሉ ያረጁና ብልሹ የሆኑ አሰራሮች ለተደራጀ ሌብነት አጋልጠውት ቆይተዋል። እነዚህን ሁኔታዎች ለመቀየር ደግሞ ገና ብዙ መሰራት ያለባቸው ስራዎች እንዳሉም ያሳያል።

አዲስ ዘመን፦ የዘርፉ ሌላው ችግር የትራን ስፖርት ማኔጅመንት እውቀት ማነስ ነው ይባላልና በዚህ ላይ እርስዎ ያልዎች ሀሳብ ምንድን ነው?

አቶ አብዲሳ፦ ዘርፉን ለማዘመን የሚያስችል በቂ እውቀት ያለው የሰው ኃይል ካለመኖሩም በላይ ያሉትም ቢሆኑ የአገልጋይነት ባህርይን ተላብሰው የሚሰሩ አይደሉም ። ይህንን ችግር ተቋሙም ለይቶ እንዴት መፈታት አለበት የሚል የተለያዩ አካሄዶችን አስቀምጧል።

በሌላ በኩልም የትራንስፖርት ዘርፉን ለማዘመንና ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ማለትም ብቃት ማረጋገጥ፣ እድሳት፣ ከጅቡቲ መግቢያ ፍቃድ መስጠት፣ ከውጭ የሚገቡ ተሽከርካሪዎች ፍቃድ መስጠትን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ የኦን ላይን አገልግሎት በመሰጠት ላይ ነው።

ከዚህ ውጪ የፋይናንስና የሰው ኃይል አስተዳደራችንን ከገንዘብ ሚኒስቴርና ከሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ጋር በመቀናጀት እነሱ ባወጡት የኢፍሚስና የኢስሚስ ፕሮግራሞች በማሰልጠን በተቋሙ ላይ ተግባራዊ ሆኗል።

አዲስ ዘመን፦ ተቋሙ ያሉበትን ችግሮች ፈትቶ የሚፈለገው ደረጃ ላይ ለመድረስ የተጀመ ረው ስራ እንዴት ይገለጻል?

አቶ አብዲሳ፦ ችግሮቹን ለመፍታት የመጀመሪያ ያደረግነው የተቋሙን የማስፈጸም አቅም መገንባት ነው። በዚህም ተቋሙ ከላይ የተዘረዘሩትን ጨምሮ ከዛም የባሱ ችግሮች ተለይተዋል። በዚህም ችግሮቹን ሊፈቱ የሚችሉ የጥናት ስራዎችም ሲሰሩ ቆይተዋል። በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ ሊፈቱ የሚችሉ ተብለውም ተለይተዋል።

በአጭር ጊዜ የሚፈቱ ችግሮችን ከማቃለል አኳያ የመስሪያ ቤቱን አደረጃጀት ሊለውጥ የሚችል ጥናት የማድረግና ለሚኒስትር መስሪያ ቤቱ የማቅረብ ስራ ተከናውኗል፤ ሌላው መስሪያ ቤቱ የተቋቋመበትን አዋጅ ለማሻሻል ጥናት በማድረግ ለሚመለከተው አካል የማቅረብ ተግባርም ተከናውኗል፤ አዋጁን ተከትሎ ሌሎች ደንቦችም አዘጋጅተናል፡፡ በጠቅላላው በእኛ በኩል መሰራት ያለበትን የአደረጃጀትና የአሰራር ማሻሻያ በማድረግ የመስሪያ ቤቱን የመፈጸም አቅም ሊለውጡ የሚችሉ አሰራሮችን በመዘርጋት በትኩረት እየሰራን ነው።

በሌላ በኩልም ችግሮቹ ውጤት ተኮር በሆኑ እቅዶች መፈታት እንዲችሉ የማድረግና ሁሉም ሰራተኛ የራሱን እቅድ ቆርሶ በመውሰድ ለተግባራዊነቱ እንዲተጋ የማድረግ አካሄድም ተከትለናል። ብልሹ አሰራሮችን ለመዋጋት በመስሪያ ቤቱ የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የውስጥና የውጭ ብለን ለይተናል።

ለምሳሌ ከአሽከርካሪ፣ ከተሽከርካሪ፣ ከጭነትና ከህዝብ ትራንስፖርት ጋር ያሉ ችግሮች ምንድን ናቸው? እንዴትስ ነው በአጠረ ጊዜ የሚፈቱት ብለን ለይተናል።

አዲስ ዘመን፦ በተለይም በእናንተ ተቋም ላይ የሚነሳው ችግር አብዛኛውን ጊዜ የባለሙያዎች የስነ ምግባር ግድፈት ነውና ከዚህ አንጻር ያያችሁት ወይም ለመፍታት የሞከራችሁት ነገር የለም?

አቶ አብዲሳ፦ ከፌዴራል ጸረ ሙስናና ስነ ምግባር ኮሚሽን ጋር በመተባበር የስነ ምግባር ምክር ቤት በማቋቋምና በመስሪያ ቤቱ ያሉ ብልሹ አሰራሮችን እንዲለይና እንዲያቅድ በማድረግ ተግባራዊነቱን እየተከታተልን ነው። እንደዚሁም ዘርፉ ሰፊ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ተገልጋዩ በየቀኑ በአገልግሎት አሰጣጣችን ላይ የሚያነሳውን ቅሬታ የመቀበያ አግባብ የመፍጠርና እሱንም ተከታትለን እንዲፈቱ የማድረግ ስራም እያከናወንን ነው።

የእነዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ተቋማዊ አቅማችንን እያሻሻለን የሄድንበት በተቋሙ ላይ የሚነሱ ቅሬታዎች የቀነሱበት ለቅሬታ መንስኤ የሆኑ ችግሮች እንዲፈቱና ወደፊት እንዳይከሰቱ የመከላከል ስራ የሰራንበት ሁኔታ ነው ያለው።

አዲስ ዘመን፦ በተለይ የእናንተ ተቋም አደጋን ለመቀነስ ሰፊ ሚና ያለውን የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛን ይመለከተዋልና ማሰልጠኛ ጣቢያ ዎቹን ምን ያህል ታውቋቸዋላችሁ ወይም ትከታተሏቸዋላችሁ?

አቶ አብዲሳ፦ ከተቋሙ ወጣ ብለን አገልግሎት በምንሰጥባቸው ቦታዎች ላይ ቡድኖችን በማቋቋም በአገሪቱ ያሉ 536 የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት ውስጥ በ440ዎቹ ላይ የአንድ ወር የሱፐርቪዝን ስራዎችን በመስራት በ13 ላይ የመዝጋት እርምጃ የወሰድንበት በተቀሩት ላይም ከመጀመሪያ ደረጃ ማስጠንቀቂያ ጀምሮ በተለያየ ደረጃ የሚመዘን እርምጃ የወሰድንበት ሁኔታ እንዳለ ማየት ይቻላል። 29 በሚደርሱ የማሽነሪ ማሰልጠኛ ተቋማት ላይም ቁጥጥር በማድረግ 3ቱን ዘግተናል።

አዲስ ዘመን፦ ከተቋማቱ ባሻገር ግን በተለይም አሰልጣኞችና ፈታኞች ባልተገባ የጥቅም ግንኙነት የሚተሳሰሩበት አካሄድ ይደ መጣልና ባለሙያዎቹን በምን መልኩ ነው የምትከታተሏቸው?

አቶ አብዲሳ፦ ይህንን እንደ ማንኛውም ሰው እንሰማለን፤ ግን እስከ አሁን እጅ ከፍንጅ የተያዙ ሰዎች የሉም። በ 2007 ና በ 2008 ዓ.ም ገደማ በፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የታዩ ጉዳዮች ነበሩ፤ እኛም የማጣራት ስራ ሰርተን 40 ያህል ሰዎች ለሕግ አቅርበናል፤ ሆኖም እስከ አሁን በመረጃ ተደግፎ የቀረበልን ነገር የለም።

ስራው በድብቅና በሁለት ሰዎች ስምምነት የሚሰራ ወንጀልና ሕገ ወጥ ተግባር ነው፤ ይህንን ችግር ህዝቡ መታገል መቻል አለበት፤ ከተቋሙ ጎን መሆን አለበት፤ ተባብረንም ችግሩን እየቀነስን በሂደትም እያጠፋን መሄድ አለብን የሚል ጽኑ እምነት አለኝ። ህዝቡ በጉዳዩ ላይ የጸና አቋም ይዞ ከሄደ ሌቦቹ እየቀነሱ የማይሄዱበት ምክንያት አይኖረም።

አዲስ ዘመን፦ ህዝቡ በዚህ ልክ ንቃተ ህሊናው እንዲዳብርና አይሆንም ማለትን ልምድ እንዲያደርግ የሚያስችል የማነቃቃት ስራ ሰርተናል ብላችሁ ታስባላችሁ?

አቶ አብዲሳ፦ ይህ ትክክል ነው፤ የተለያዩ

 የመገናኛ ብዙሀንና ሌሎች ህዝብ የሚገኝባቸውን መንገዶች በመጠቀም ህብረተሰቡ ስለ መብትና ግዴታው እንዲያውቅ የማድረግ ስራ በመሰራት ላይ ነን።

በተጨማሪም ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በትምህርት ቤቶች ስለ መንገድ ትራንስፖርት ሰፋ ያሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶች እንዲሰጡ፣ የተለያዩ ክለቦች እንዲቋቋሙ በማድረግ ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ ነው።

አዲስ ዘመን፦ የተሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጥ የእናንተ ተቋም ኃላፊነት ቢሆንም ስራውን ለውጭ አካላት ሰጥታችኋል፤ ከዚህ አንጻር ደግም አንዳንድ ተሽከርካሪዎች እንዴት ምርመራውን አለፉ የሚያስብሉ ናቸው፤ ይህንን ችግር እንዴት ያዩታል?

አቶ አብዲሳ፦ 58 በሚሆኑ የተሽከርካሪ ብቃት መመርመሪያ ተቋማት ላይ የሱፐርቪዥን ስራ በማከናወንና ግምገማ በማድረግ 22 በሚሆኑት ላይ ከማስጠንቀቂያ እስከ እገዳ የሚደርስ እርምጃ በመውሰድ አሰራራቸውን በሚፈለገው ደረጃ እንዲያስተካክሉ ያደረግንበት ሁኔታ አለ።

ሌላው በመናኸሪያዎች ላይ በመገኘት 6 ሺ በሚጠጉ መኪኖች ላይ የቅድመ ስምሪት የተሽከርካሪ ምርመራ በማድረግ የቴክኒክ ብቃታቸው ያልተረጋገጡ 4 ሺ 414 የሚሆኑት ተሽከርካሪዎች ተገኝተዋል፤ እነዚህም ራሳቸውን እንዲያስተካክሉና ስምሪት እንዳያገኙ ሆኗል። ከዚህ ውጪ በመላው አገሪቱ በመንገድ ላይ ድንገተኛ የተሽከርካሪ የቴክኒክ ምርመራ በማድረግ 120 ሺ ተሽከርካሪዎች በድግግሞሽ የቴክኒክ ጉድለት የተለዩበትና 102 ሺ የሚሆኑት በተለያየ የጉድለት ደረጃ ተፈርጀዋል። እነዚህም በየክልሉ እንዲቀጡ ተደርጓል።

አዲስ ዘመን፦ አዲስ አበባ ውስጥ ከመናኸሪያዎች በር ላይ ሳይቀር ሕገ ወጥ ስምሪቶች ይደረጋሉ፤ መንገድ ላይ የእናንተ የቁጥጥር ባለሙያዎች ሲገኙ ደግሞ ለማለፍ ወደ ሙስና ውስጥ ይገባልና በዚህስ ዙሪያ ምን ይላሉ?

አቶ አብዲሳ፦ ከፖሊሶችና ከስነ ስርዓት አስከ ባሪዎች ጋር በመቀናጀትና ሰራተኞቻችንን በማነቃቃት 36 ያህል የሕገ ወጥ ስምሪት ቦታዎች በመለየት 13ቱን ማስወገድ ችለናል። ይህ ሁሉ ቢሆንም የቁጥጥር አቅማችንን ከተሰጠን ኃላፊነት አኳያ ሌሎች ስራዎቻችንን ወደጎን ብለን ይህ ሕገ ወጥ አሰራሩን መከላከል የሚቻልበት ህብረተሰቡም እፎይታ የሚያገኝበትን ሁኔታ ለማመቻቸት እንሰራለን ።

ሕገ ወጥነትን ከመከላከል አንጻር በቃሊቲ አሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም ውስጥ ሕገ ወጥነት የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ሙሉ በሙሉም ባይሆን በተወሰነ ደረጃ ለውጥ ለማምጣት የተቻለበት ሁኔታ አለ።

አዲስ ዘመን፦ ሕገ ወጥ የስምሪት ቦታዎችን ከመለየት ባሻገር ግን ባለሙያዎቻችሁስ ለዚህ ሕገ ወጥ ስራ ተባባሪ እንዳይሆኑ ምን ያህል ቁጥጥር ታደርጋላችሁ?

አቶ አብዲሳ፦ የመንገድ ትራንስፖርት ባለስልጣን ሰራተኞች ገቢ ይሰበስባሉ፣ በአሽከ ርካሪዎች ማሰልጠኛ በተሽከርካሪዎች ብቃት ማረጋገጫ ተቋማት ላይ በመሄድም ፍተሻና ቁጥጥር ያደርጋሉ፤ እንዲሁም በተለያየ ከተገልጋይ ጋር ፊት ለፊት በሚያገናኙ የስራ መስኮች ላይ ይሳተፋሉ፣ ከነዚህ ስራቸው ጋር ተያይዞ ግን በሀሜት መልኩ የሚነሱ አንዳንድ ነገሮች እንዳሉ ደግሞ እናውቃለን።

ሆኖም ከሀሜት በዘለለ በሰራተኞቻችን ያለ አግባብ ጥቅም የተጠየቀ ሰው ካለ መረጃ ማቅረብ ይችላል፤ በዚህ መሰረት የሚገኙትንም በሕግ ለመጠየቅ ተቋሙ ዝግጁ ነው። ከዚህ ውጪ ግን በተለይ የስራ ሁኔታቸው ከህዝብ ጋር የሚያገናኛቸውን የስራ ክፍሎች በስነ ምግባር ምክር ቤታችን አማካይነት ስልጠናዎች ይሰ ጣሉ።

አዲስ ዘመን፦ ይህንን ጥያቄ ያነሳሁሎት ከዚሁ ከእናንተ ተቋም ባገኘሁት መረጃ መሠረት አንዳንድ የስምሪት ባለሙያዎች እቁብ እስከ ማስጣል የደረሰ የጥቅም ግንኙነት ይፈጥራሉ የሚል መረጃ ስላለኝ ነው፤

አቶ አብዲሳ፦ እኔ ጋር የደረሰ የለም ካለ ግን ማቅረብ ነው። በተለይ በማስረጃ የተደገፈ ነገር ከሆነ ደግሞ ለእኛም ለፍተሻ ስለሚያመቸን ይዞ መቅረብ ጥሩ ነው። ዘርፉ ህዝቡ ውስጥ እየተሰራ የሚዋልበት ስለሆነ ብዙ ሀሜቶችም አብረው ሊመጡ ይችላሉ። ሆኖም በተጨባጭ በፎቶ፣ በድምጽ አስደግፎ ማስረጃ የሚቀርብ እስከ አሁን የለም።

አዲስ ዘመን፦ አሁን ላይ በተሽከርካሪዎች ላይ ይገጥማሉ እየተባለ ያለው የስፒድ ሊሚትና ሌሎች ቴክኖሎጂዎች ምን ደረጃ ላይ ደረሱ?

አቶ አብዲሳ፦ በአሽከርካሪው ፍጥነት ምክንያት የሚከሰትን የትራፊክ አደጋ ከመከላከል አኳያ ከፍተኛ የሆነ ጠቀሜታ እንደሚኖራቸው ይታመናል። እስከ አሁንም ይህንን ማሽን ተሽከርካሪዎች ላይ ለማሰር የሚረዱ ቅድመ ዝግጅቶችን ስናደርግ ከርመናል። ከቅድመ ዝግጅቱ መካከልም ማሽኑ በአገሪቱ የደረጃ መዳቢ አካል ታይቶ ብቃቱ ተረጋግጦ እንዲጸድቅ የማድረግ ሲሆን ሌላው ለማስፈጸም የሚረዳ መመሪያ ማዘጋጀት ነው። ይህንን ቴክኖሎጂ ከነጻ ገበያው ላይ ገዝተው የሚገጥሙ ሲበላሽም የሚጠግኑ ካምፓኒዎችን አወዳድረን ወደ ስራ እንዲገቡ አድርገናል።

በአሁኑ ወቅትም ከውጭ የሚገቡ አዲስ መኪኖች ይህንን ቴክኖሎጂ ገጥመው እንዲገቡ እያስገደድን ነው። በአገር ውስጥም ከህዝብ ትራንስፖርት ጀምረን ደረጃ በደረጃ ሁሉም ላይ ቴክኖሎጂውን ለመግጠም እየሰራን እንገኛለን።

ምናልባት በዚህ ስራ ላይ አሁን በአገሪቱ አሉ ለሚባሉት አንድ ሚሊየን የሚሆኑ ተሽከርካሪዎች የሚሆኑ እቃዎችን ከውጭ ገዝቶ በማስገባት ሂደት ላይ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እየገጠመን በመሆኑ ይህንን ከሚመለከተው አካል ጋር በመነጋገር ላይ እንገኛለን።

አዲስ ዘመን፦ በህዝብ ላይ ከፍተኛ ምሬትን እያስከተሉ ያሉ እንደ ትርፍ ጭነት፣ ከታሪፍ በላይ መጠየቅ እንዲሁም ሌሎች ህጋዊ ያልሆኑ ተግባራት ህጋዊ እስኪመስሉ ድረስ በከተማም ሆነ ከከተማ ውጭ እየተፈጸሙ ነውና ይህ ድርጊት የእናንተን የቁጥጥር አቅም መላላት አያሳይም ይላሉ?

አቶ አብዲሳ፦ አንድ አሽከርካሪ የትራንስፖርት መኪና ይዞ ሲንቀሳቀስ እንደ ጥፋት ከሚቆጠሩ ነገሮች መካከል ትርፍ መጫን፣ ከታሪፍ በላይ ማስከፈል እንዲሁም መሰል ተግባራት ሲሆኑ እነዚህን ሲፈጽሙ የተገኙ አሽከርካሪዎች ሕጉ በሚያዘው እርከን መሰረት ተጠያቂ ይሆናሉ። ይህንን ሕግ ከማስተግበር አኳያ በየደረጃው ያሉት የትራፊክ ፖሊሶችና የሕግ አስከባሪዎች ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው። የእኛ መስሪያ ቤትም ከትራፊክ ፖሊስ ጋር በመተባበርና ከክልል ትራንስፖርት ቢሮዎች ጋር በመቀናጀት በመንገድ ላይ ቁጥጥር ማድረግ ይጠበቅበታል።

አዲስ ዘመን፦ የእናንተን ተቋም ጨምሮ በየደረጃው ያሉ አካላት ይህንን ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል ለማለት የሚያስችል ስራ አለ?

አቶ አብዲሳ፦ በመላው አገሪቱ በተጠናቀቀው ዓመት ባደረግነው የተቀናጀ ስራ 120 ተሽከርካሪዎች ላይ ለአንድ ወር በተደረገው ክትትልና ጠበቅ ያለ ቁጥጥር 102 ሺ የሚደርሱት ጥፋተኛ መሆናቸው ተረጋግጧል። ከተገኙበት የጥፋት ዓይነቶች ውስጥም ትርፍ መጫን፣ ጠጥቶና ያለ መንጃ ፈቃድ ማሽከርከር ይገኙበታል።

ለዚህ ችግር ግን ዘላቂው መፍትሔ የተጀመረውን የፍጥነት መገደቢያ (ስፒድ ሊሚተር) ና ሌሎችንም ቴክኖሎጂዎች በመላ አገሪቱ ማዳረስ ነው፤ በረጅም ጊዜ ደግሞ የኦን ላይ አገልግሎት በመጀመር የትራንስፖርት አገልግሎቱ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሊጂ ታግዞ ቁጥጥር የሚደረግበትን ስርዓት ማምጣት ነው። ለዚህም ከአለም ባንክ ጋር ስምምነት ላይ ተደርሶ ከሁለትና ሶስት ዓመት በፊት የተጀመረ ስራ አለ፤ ይህንን ማስቀጠል በቀጣይ ትኩረት ተደርጎ ይሰራል።

ይህ የቴክኖሎጂ ዓይነት ተግባር ላይ ዋለ ማለት ደግሞ በተለይም ተሽከርካሪዎች ባሉበት ሆነው ቁጥጥር ለማድረግ፣ መንጃ ፍቃዶች ሲሰጡ እንዳይሰረቁ ለመከላከል አስቻይ ሁኔታዎች ይፈጥራል። አሁን ላይ ግን የጀመርነውን የቁጥጥርና የክትትል ስራ አጠናክሮ መቀጠል ነው መፍትሔው።

አዲስ ዘመን፦ አንድንድ ጊዜ የቁጥጥር ስራዎች የወረት የሚመስሉበት ሁኔታ አለ፤ ለምሳሌ የምሽት ጉዞ ተከልክሎ አንድ ሰሞን ቁጥጥሩም ጠበቅ ብሎ ነበር፤ አሁን ደግሞ ተመልሶ ተጀምሯል፤ በዚህ ላይ ምን አስተያየት አልዎት?

አቶ አብዲሳ፦ የትራፊክ አደጋን እያባባሰና የሕገ ወጦች መደበቂያ እየሆኑ ካሉ ሂደቶች መካከል አንዱ የምሽት ጉዞ ነው፤ በእኛ በኩል ያደረግነው ይህ የምሽት ጉዞ ጥንካሬ ድክመቱና ፈተናው በሚል ጥናት እንዲጠና ማድረግ ነው፤ ውጤቱም መጥቷል ግን ውሳኔ ላይ አልተደረሰም።

በሌላ በኩልም ህብረተሰቡ ጋር ምንድን ነው ያለው? የሌሎች አገሮች ተሞክሮ ምንድን ነው የሚያሳየው? የሚለውንም በሂደት በማጥናትና ጥቅምና ጉዳቱን በመለየት መቀጠል ነው መቆም ያለበት የሚለውን ወደፊት የምንወስን ይሆናል።

አዲስ ዘመን፦ በአዲሱ ዓመት ከዘርፉ ምን ዓይነት ለውጥ እንጠብቅ?

አቶ አብዲሳ፦ ዋናው ዓላማችን ትራንስፖርቱን ተደራሽ ማድረግ ነው፤ ይህ እንዲኖር ደግም የአገልጋይነት ስሜታችንን አሳድገን የሕግ የበላይነትን በማስከበር የቁጥጥር አቅማችንን በማሳደግ አገልግሎቱ በተሻለና ቀጣይነት ባለው ሁኔታ እንዲሰጥ ማድረግ ነው። ህብረተሰቡ በዘርፉ ላይ የሚያሰማውን ሮሮ እንዲቀንስ በማድረግ በከተማም በገጠርም ፍትሀዊ የሆነ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲያገኝ ማድረግ ነው።

ለመንግስት ያቀረብነውን የተቋም ማሻሻያ አዋጅ ማጸደቅና መስሪያ ቤቱ አገልግሎቱን በአዲስ መልክ አደራጅተን የመፈጸም ብቃቱን የህዝብ ተዓማኝነቱን ወደላቀ ደረጃ ማሸጋገርና የተጀማመሩ የመሰረተ ልምት ስራዎችን ማጠናቀቅ ከብዙ ጥቂቶቹ ናቸው።

አዲስ ዘመን፦ አመሰግናለሁ።

አቶ አብዲሳ፦ እኔም አመሰግናለሁ

አዲስ ዘመን መስከረም 21/2012

እፀገነት አክሊሉ