የግሉን ክፍለ ኢኮኖሚ ያሰሩ ቋጠሮዎችና መፍትሔዎቻቸው

20

የነጻ ኢኮኖሚ ፍልስፍና የሚከተሉ ሀገራት ያለ ግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ንቁ ተሳትፎ የኢኮኖሚ ብልጽግና ሊያስመዘግቡ እንደማይችሉ የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ ምክንያቱም የግሉ ዘርፍ የኢኮኖሚ ሞተር ነውና። ከደርግ ስርዓት መገርሰስ በኋላ ስልጣን የተቆናጠጠው በኢህአዴግ የሚመራው መንግስት የግሉ ዘርፍ የኢኮኖሚ ሞተር መሆኑን አምኖ በመቀበል የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚ ውስጥ የሚጠበቅበትን እንዲያበረክት ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርግ በፖሊሲው አስፍሯል። ይሁን እንጂ የመንግስት የመድረክ ንግግሮችና ተግባሩ ለየቅል እንደነበር የዘርፉ ምሁራን ይገልጻሉ። የመንግስት ድጋፍ ማነስ እና የቢሮክራሲ ችግሮች የግሉን ዘርፍ ተተብትቦ በመያዙ ዘርፉ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ መጫወት ያለበትን ሚና መጫወት እንዳልቻለ ምሁራኑ ይናገራሉ።

የምስራቅ አፍሪካ የምርምር እና ፖሊሲ ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር አንዳርጌ ታዬ እንደሚሉት፤ በኢትዮጵያ ውስጥ በግሉ ክፍለ ኢኮኖሚና በመንግስት መካከል ያለው ግንኙነት በጣም ደካማ ነው። የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ከመንግስት ሊያገኝ የሚገባውን እገዛ እያገኘ አልነበረም። መንግስት የሚጠበቅበትን አልተወጣም። በዚህም ምክንያት ዘርፉ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ማበርከት የሚጠበቅበትን አላበረከተም። ይህ ችግር አሁንም ቀጥሏል ይላሉ።

መንግስት ተገቢውን ድጋፍ ለግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ እንዳያደርግ ያደረጉ የተለያዩ መንስኤዎች አሉ። ከእነዚህ መንስኤዎች አንዱ መንግስት የሚከተለው የልማታዊ መንግስት ፖሊሲ ነው።

በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት መንግስት በኢኮኖሚ ውስጥ ጣልቃ በመግባት በግሉ ዘርፍ በማይደፈሩ ዘርፎች ላይ ገብቶ ክፍተቱን እንዲሚሞላ ይጠበቃል። ይህ ክፍተት የመሙላት ተግባር ታዲያ ችግሮቹ እስኪቀረፉ በጊዜያዊነት የሚከናወን እንጂ በፍልስፍና ደረጃ እንደ አካሄድ ሊያዝ አይገባም። መንግስት ራሱ ፖሊሲ አውጪ፣ ራሱ ሀብት ፈጣሪ ነኝ ብሎ መነሳት ከመንግስት መሰረታዊ አስፈላጊነት ፍልስፍና ጋር ጭምር የሚጋጭ ነው ይላሉ ዶክተር አንዳርጌ።

የልማትዊ መንግስት ፖሊሲ መንግስትን እንደ ሃብት ፈጣሪ እንዲሁም ስራ ፈጣሪ እንዲሆን የሚፈቅድ ነው። መንግስት የሚያስፈልገው ግን ሀብት እና ስራ ለመፍጠር አይደለም። የመንግስት ዋናው ተግባር ሀብት የሚፈጠርበትን ሁኔታ በማመቻቸትና ድጋፍ ማድረግ እንዲሁም ስራ እንዴት እንደሚፈጠር አቅጣጫ በማሳየት ላይ ሊሆን ይገባ ነበር። ራሱ ግን ሀብትም ሆነ ስራ ፈጠራ ላይ ሊሳተፍ አይገባም ነበር። መንግስት በኢኮኖሚ ላይ ከመጠን በላይ መሳተፉና የግሉን ዘርፍ በዝባዥ አድርጎ መሳሉ የግሉ ዘርፍ መጣብኝ የሚል ማህበረሰብ እንዲፈጠር አድርጓል ሲሉ ያብራራሉ።

በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር ዶክተር ጉቱ ቱፋ የግሉ ዘርፍና በመንግስት መካከል ሊኖር የሚገባው መልካም ግንኙነት አልተፈጠረም የሚለውን የዶክተር አንዳርጌን ሀሳብ ያጠናክራሉ። በግሉ ዘርፍና በመንግስት መካከል መልካም ግንኙነት እንዳይኖር ያደረገው መንግስት ባለሃብቶችን በፍትሃዊነትና በእኩልነት ማስተናገድ ባለመቻሉ ነው ብለዋል። የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ አድሏዊ ነበር። በአንድም በሌላም መንገድ ከመንግስት የስራ ሀላፊዎች ጋር ቅርበት ያላቸው ባለሃብቶች ተገቢውን መስተንግዶ ሲያገኙ ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር ቅርበት የሌላቸው ሲበደሉ እንደነበሩ ያነሳሉ።

ለባለሃብቶች እጅግ አስፈላጊ ከሆኑት ነገሮች አንዱ የሆነውን የውጭ ምንዛሬ እንኳ በፍትሃዊ መንገድ አያገኙም ነበር። በተለይም በውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ረገድ የነበረው ቅጥ ያጣ አሰራር በመንግስትና በግሉ ዘርፍ መካከል አለመተማመን እንዲሰፍን አድርጎ መቆየቱን ያወሳሉ። ይህም ሁሉም ባለሃብቶች እኩል የሚሳተፉበት የተስተካከለ ምህዳር እንዳይኖር ተግዳሮት መሆኑን ዶክተር ጉቱ ያብራራሉ።

ዶክተር ጉቱ እንደሚሉት፤ ለግል ባለሃብቶች የሚደረገው ድጋፍ የፖለቲካ አስተሳሰባቸውን መሰረት ያደረገ ነበር። የመንግስትን የፖለቲካ አስተሳሰብ የሚቃረን አቋም ያላቸውን ስራቸውን እንዳይሰሩ የማዋከብና ከሀገር እንዲወጡ ጫና ሲደረግ ነበር። በሌላ በኩል የመንግስትን አስተሳሰብ ይደግፋሉ ተብለው የሚታሰቡት ከተገቢ በላይ ድጋፍ ሲደረግላቸው ነበር። ይህም መተማመን እንዲሸረሸር ብሎም ዘርፉ እንዲዳከም ካደረጉት አንዱ ነው።

መንግስት ከነጻ ገበያ ፍልስፍና በሚቃረን መልኩ ኢኮኖሚ ውስጥ ሲሳተፍ ነበር የሚለውን የዶክተር አንዳርጌን ሀሳብ የሚያጠናክሩት ዶክተር ጉቱ መንግስት በኢኮኖሚው ላይ ከሚገባው በላይ መሳተፉ የግሉ ዘርፍ እንዳይፋፋ የራሱን አሉታዊ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ይናገራሉ። መንግስት የግሉ ዘርፍ መያዝ ያለባቸውን ዘርፎችን ተቆጣጥሮ ቆይቷል። ለአብነት ከውጭ እቃ በማስገባት ረገድ መንግስት ሊሳተፍ አይገባም ነበር። ሆኖም ሲያስገባ ነበር። መንግስት ከግሉ ዘርፍ ጋር እኩል ተወዳድሮ ከውጭ እቃ ለማስገባት መነሳት ማለት የግሉን ዘርፍ ማቀጨጭ እንደማለት ነው። ምክንያቱም መንግስትና የግል ባለሃብት እኩል ሊወዳደሩ አይችሉም። ይህ የመንግስት አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነት ባለሃብቶች በሙሉ አቅማቸው ወደ ስራ እንዳይገቡም አድርጎ መቆየቱን ያነሳሉ።

የገንዘብ ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ እንደሚሉት መንግስት በፖሊሲና በቃል የግሉ ዘርፍ የኢኮኖሚው ሞተር እንደሆነ አስቀምጧል። ተግባርና ቃል ግን ለየቅል ነበር። የግሉ ዘርፍ ያለውን ሙሉ ሀይል አውጥቶ እንዲሰራ የሚያበረታታ አልነበረም። የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ በርካታ ተግዳሮቶች ገጥመውት ነበር። በግልጽ በግሉ ዘርፍና በመንግስት መካከል ከፍተኛ የሆነ የመጠራጠር ስሜት ነው የነበረው። የመንግስት ቢሮክራሲ ከማበረታታትና ከመደገፍ ይልቅ መቆጣጠር ላይ ያተኮረ ነበር። በዚህ ምክንያት አጠቃላይ የቢዝነስ ድባቡ ለቢዝነስ የማያመች ሆኖ ቆይቷል። በኢትዮጵያ ውስጥ ቢዝነስ መስራት ከባድ ነው የሚል እሳቤ ተፈጥሯል።

ወደ ስራ ሊገባ ያሰበ ወጣት ፈቃድ ለማውጣት እና ለማሳደስ ወራትና ዓመታት የሚፈጅበት፣ ሊበደር የፈለገ ባለሃብት በፈለገበት ወቅት ብድር የማያገኝበት፤ በሀይል አቅርቦት ችግር ሳቢያ አምራቾች በአቅማቸው ልክ የማያመርቱበት፤ በውጭ ምንዛሬ እጥረት ሳቢያ ባለሃብቶች ማምረት ከሚችሉት ከ20 ወይም ከ30 በመቶ በላይ ማምረት የማይችሉበት አስቸጋሪ ሁኔታ ተፈጥሮ እንደነበር ያነሳሉ።

በግሉ ዘርፍና በመንግስት መካከል ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ የተለያዩ ስራዎች ሊሰሩ እንደሚገባ ምሁራን ያብራራሉ። ዶክተር አንዳርጌ እንደሚሉት፤ በግሉ ዘርፍና በመንግስት መካከል ያለውን ችግር ለመቅረፍ በቅድሚያ መንግስት የፖሊሲ አቅጣጫውን ዳግም መቃኘት አለበት። የፍልስፍና ለውጥም ያስፈልጋል። የፖሊሲ አቅጣጫውን ከቃኘ በኋላ መንግስት ሚናውን መለየት አለበት። ሚናውን መለየት ብቻውን ውጤታማ ሊያደርገው አይችልም። እጁን ማውጣት ካለባቸው አካባቢዎችም እጁን ማውጣት አለበት። ሚናውን ለመወጣት የሚያስችል አቅም መገንባትም ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። የቢሮክራሲውን አሰራርና አቅም ማዘመን እና ማሳደግም አለበት።

መንግስት ፖሊሲውን በመቃኘት በኢኮኖሚው ውስጥ የሚገባውን ሚና በመለየት የሚጠበቅበትን ሚና መጫወት ከቻለ በማይሆን ቦታ እየፈሰሰ ያለውን ሃብት፣ ጉልበትና እውቀት ማዳን ይቻላል የሚሉት ዶክተር አንዳርጌ፤ መንግስት አስተሳሰብና የፍልስፍና ለውጥ ማምጣት ከቻለ የግሉ ዘርፍ ከፍተኛ ሚና ሊጫወት ይችላል ብለዋል።

ዶክተር ጉቱ እንደሚያብራሩት፤ የግሉን ዘርፍ ለማጠናከር መንግስት የተሸረሸረውን መተማመን ወደ ቦታው የመመለስ ስራውን በትኩረት ሊሰራ ይገባል። ባለሃብቶች በፖለቲካ አቋማቸው ሊመዘኑ አይገባም። መንግስት ባለሃብቶችን በፖለቲካ አቋማቸው ከመመዘን አባዜ ከወጣ መተማመን ያድጋል። የግሉ ዘርፍ ለኢኮኖሚው ማበርከት ያለበትን አስተዋጽኦ ማበርከትም ይችላል።

ባለሃብቶችን ለማበረታታት መንግስት በአሁኑ ወቅት በርካታ አዋጆችን የማሻሻል ስራ እየሰራ ነው። ይህም ከማምረት አንስቶ ወደ ውጭ እስከመላክ ያሉትን መሰናክሎች ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት የሚጠበቅ ነው። እነዚህ የአዋጅ ማሻሻያ ስራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም ዶክተር ጉቱ አብራርተዋል።

ከለውጡ ወዲህ በተለያዩ ዘርፎች ላይ የግል ባለሃብቶች በስፋት እንዲሳተፍ አበረታች ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውንም ያብራሩት ዶክተር ጉቱ ይህ ስራም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተናግረዋል። ለግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ሌላኛው ማነቆ የመሰረተ ልማት እጦት ነው። ይህንንም ለመቅረፍ ትኩረት ተሰጥቷል። ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው። የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ስራዎችም ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል።

የገንዘብ ሚኒስትር ዲኤታው ዶክተር እዮብ እንደሚሉት እየተካሄደ ያለው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው በግሉ ዘርፍ ያሉ ችግሮችን በማቃለል የግሉን ዘርፍ እምቅ አቅም አሟጦ መጠቀምን አንዱ ግቡ አድርጓል። የሚነግደውም ሆነ የሚያመርተው በስራው መክበር እንዲችል ያንን አስተሳሰብ ለማምጣት ነው የተጀመረው። ሰዎች ወደ ስራ ፈጠራ እንዲገቡ፣ ያላቸውን እውቀት አጠራቅመው ትልቅ አቅም መፍጠር እንዲችሉ ማድረግ ላይ ያተኮረ ነው።

ኢትዮጵያ ቢዝነስ የሚሰራባት፣ ሰዎች ሰርተው የሚከብሩባት ሀገር መሆን አለባት፣ ቢዝነስ መስራት ሀጢያት አይደለም የሚል የተለየ እይታ አለው። ከዚህ አንጻር የቢዝነስ ድባቡን ከስር መሰረቱ ለመቀየርና ለኢንቨስትመንትና ለስራ ፈጠራ አመቺ እንዲሆን የማድረግ አስተሳሰብ አለው። አምራች ወይም ነጋዴ ያለውን አጠቃላይ አቅም አሟጦ እንዲያወጣና ውጤታማ እንዲሆን በየቦታው የተቀመጡ ጉቶዎችን መንቀልና መዋቅሩን ማስተካከል እና የቢሮክራሲውን እሳቤ መቀየር አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት ለማስተካከል ግብ ተቀምጦ እየተሰራ ነው።

አዲስ ዘመን መስከረም 22/2012

መላኩ ኤሮሴ