የአገልግሎቱ ስኬትና ተግዳሮት

20

የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ መረጃ እንደሚያመለክተው በከተማ አስተዳድሩ በአሁኑ ወቅት የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ረገድ 893 የአንበሳ አውቶቢሶች (408 መደበኛ አዲስ ባሶች፣ 25 ተደራራቢ አዲስ ባሶች፣ 460 ነባር መደበኛ ባሶች) ከእነዚህ ውስጥ 480ዎቹ በየቀኑ ሥምሪት ላይ ይውላሉ፤ 362 ሸገር የከተማ አውቶቢሶች (98 የተማሪዎች ሰርቪስ፣ 240 መደበኛ ባሶች፣ 24 ተደራራቢ ባሶች)፤ 7,500 አካባቢ የሚገመቱ ነጭ እና ሰማያዊ ታኪሲዎች፣ 6,500 ነጭ እና ሰማያዊ እና ቢጫ ላዳ ታክሲዎች፣ ወደ 500 ሃይገር ባሶች እና 4,000 አካባቢ ድጋፍ ሰጪ ነጭ ሚኒ ባሶች ሥራ ላይ ይገኛሉ። በተጨማሪም 410 የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት ሰማያዊ አውቶቢሶች የመንግሥት ሠራተኞች የሥራ መግቢያ እና የመውጫ ስዓት ላይ አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡

የኢፌዴሪ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የመንግሥት ሠራተኞች የትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅትን በመንግሥት የልማት ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር 25/1984 አንቀጽ 21 እና አንቀጽ 42(4) መሠረት በደንብ ቁጥር 362/2008 እንዲቋቋም አድርጓል፡፡ ድርጅቱ ሲቋቋም መነሻ የሚሆን የተፈቀደ 1,572,618,280 ካፒታል የተበጀተለት ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ 1,072,618,280 ካፒታል በመያዝ ወደ ሥራ እንዲገባ ተደርጓል፡፡ ስለዚህ በመንግሥት በተፈቀደለት በጀት 55 አውቶቢሶችን በመያዝ በጨፌ- አያት፣ ጀሞ፣ አቃቂ ቃሊቲ፣ የሺ ደበሌ እና አስኮ መሥመሮች መስከረም 5 ቀን 2007 ዓመተ ምህረት የሙከራ ሥራውን ጀምሯል፡፡

የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት ከመጀመሩ በፊት የመንግሥት ሠራተኛው ሲጠቀም የነበረው በከተማ አውቶቢሶች፣ ሃይገሮች እና ታክሲዎች ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ ሠራተኛው በየፌርማታው ትራንስፖርት እየጠበቀ ሦስት ወይም አራት ታክሲዎችን አቆራርጦ ለመሄድ ይገደድ ነበር፡፡ ስለዚህ የፐብሊክ ሰርቪስ ሠራተኛውን የትራንስፖርት ችግር ለመፍታት ምን መደረግ አለበት የሚል ጥናት በሀገር አቀፍ ደረጃ ተካሄደ፡፡ ቴክኒካል እና ስትሪንግ ኮሚቴ ተቋቁሞ፤ መጀመሪያ የፌዴራል ከዚያም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠራተኞች ላይ ጥናት ከተካሄደ በኋላ ወደ ውሳኔ ተደረሰ፡፡ በጥናቱ መሠረትም የተለያዩ አማራጮች ቀረቡ፡፡ ከአማራጮች አንዱ መንግሥት የራሱ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥ ድርጅት አቋቁሞ አገልግሎት መስጠት አለበት የሚለው አማራጭ አስፈላጊ ሆኖ ተገኘ፡፡ ስለዚህ የፐብሊክ ሰርቪስ ሠራተኞች ትራንስፖርት ድርጅት በመንግሥት የልማት ድርጅትነት ተቋቁሞ አገልግሎት መስጠት እንዲጀምር ተደረገ፡፡

ይህ ድርጅት አገልግሎት ለመጀመር ያለፋቸውን ሂደቶች በፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት የትራንስፖርት ኦፕሬሽን አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ተወካይ አቶ አማኑኤል ተዘራ ያብራራሉ፡፡ የድርጅቱን አጀማመር ሲያስረዱ እንደገለፁት የዛሬ አምስት ዓመት አካባቢ ቢሮ ሳይኖር ውስን ሠራተኞች ተቀጥረው፣ የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን በሰጣቸው አንድ ክፍል ውስጥ ከ10 እስከ 15 ሰው በመሆን እና በረንዳዎችን ጭምር በመጠቀም ወደ ሥራ ተገባ፡፡ ጥናቱ ሲካሄድ በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር እና በፌዴራል ደረጃ ተጠቃሚ ይሆናል ተብሎ የታሰበው የመንግሥት ሠራተኛ ቁጥር ከ35 እስከ 40 ሺህ ነበር፡፡ በወቅቱ አገልግሎቱን ለመጀመር ታሳቢ ተደርጎ የነበረው የመንቀሳቀሻ ቦታ የሚበዛው ሠራተኛ ነዋሪነቱ ከተማዋ ውስጥ ውይም መካከል ነው ተብሎ ነው፡፡ በጥናቱ የተወሰደው መረጃ የት አካባቢ ትኖራላችሁ ተብሎ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ ቦሌ አራብሳ፣ የካ አባዶ፣ የካ አያት ቁጥር አንድ፣ ቂሊንጦ፣ ቱሉ ዲምቱ እና ጀሞም የተወሰነው አካባቢ እና ኃይሌ ጋርመንት በሚባሉ የኮንዶሚኒየም መኖሪያ ሰፈሮች ነዋሪዎች አልገቡባቸውም ነበር፡፡ በመሆኑም በጥናቱ ታሳቢ ለተደረጉት ተጠቃሚ ሠራተኞች 410 አውቶቢሶች ያስፈልጋሉ ተብሎ ድርጅቱ ቢሮ፣ የመሥሪያ ቦታ እና በቂ ሠራተኛም ሳይኖረው ነጭ ወረቀት ላይ ነው ሥራ እንዲጀምር የተደረገው፡፡ ከነጭ ወረቀት የተነሳው ድርጅት በአንድ ወር ከአሥራ አምስት ቀን ወይም ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ የሙከራ አገልግሎቱን በ55 አውቶቢሶች ጀመረ፡፡

በዚያው ዓመት በሁለተኛው ዙር 144 አውቶቢሶችን በመረከብ የአውቶቢሶቹን ቁጥር 199 አደረሰ፡፡ በ2008 ዓ.ም ላይ ደግሞ የቀሩትን 211 አውቶቢሶች በመረከብ ሥራውን አጠናክሮ ሲቀጥል የተጠቃሚው ቁጥር እየጨመረ ነበር፡፡ በመሀል ከተማ ላይ ትኩረት አድርጎ አገልግሎት ሲጀምር፤ በከፍተኛ ወጭ ቤት ተከራይቶ ይኖር የነበረው ሠራተኛ ርካሽ ወዳለበት የከተማዋ የዳር አካባቢዎች መውጣት በመጀመሩ የሰርቪስ ፍላጎቱ ጨመረ፡፡ ስለዚህ ይህን ፍላጎት ለማሟላት ተጨማሪ አውቶቢሶች በመጠቀም አዳዲስ መሥመሮችን በመክፈት አገልግሎት መስጠት ቀጠለ። መንግሥት ሠራተኛውን ወጪ እጋራለሁ ብሎ የትንስፖርት አገልግሎት መስጠት ከመጀመሩ ጎን ለጎን ከተሠሩት የጋራ መኖሪያ ቢቶች 20 በመቶውን ለመንግሥት ሠራተኛው በዕጣ ማስተላለፉ፤ አምስት ሺህ ቤቶች በአዳዲስ የኮንዶሚኒየም መኖሪያ መንደሮች ለመምህራን በኪራይ መሰጠቱ እና ዝቅተኛ ደመወዝ ላላቸው ሠራተኞች ከ3 እስከ 4 ሺህ ቤቶች እንዲተላለፉ መደረጉ ከፍተኛ ፍላጎት በመሥመሮቹ ላይ እየጨመረ መጥቷል፡፡ ቢሆንም ይህን ታሳቢ ያደረገ ሥምሪት እንደተደረገ አቶ አማኑኤል ያስረዳሉ፡፡

እንደ አቶ አማኑኤል ገለፃ አገልግሎቱ ከተጀመረበት ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ በየዓመቱ አዳዲስ መዋቅሮች እየተዘረጉ እና አዳዲስ አደረጃጀቶች እየተፈጠሩ ብዛት ያላቸው ሠራተኞች በመንግሥት መዋቅር ውስጥ በመቀጠራቸው፤ የአገልግሎት አድማሱ በዚያው ልክ እየሰፋ መጣ፡፡ በመሆኑም በ2011 ዓ.ም የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚጠቀሙ የፌዴራል መንግሥት እና የአዲስ አበባ መስተዳድር ሠራተኞች ቁጥር 190 ሺህ ደርሷል፡፡ ከዚህ ውስጥ 128 ሺህ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና 65 ሺህ የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች ናቸው፡፡ ድርጅቱ አገልግሎት የሚሰጥባቸው አንዳንዶቹ መሥመሮች በየትኛውም የትራንስፖርት ዘርፍ ከመነሻ እስከ መድረሻ የማይሸፈኑ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ከአቃቂ ዊንጌት፤ ከአቃቂ ሽሮ ሜዳ፤ ከአቃቂ አዲሱ ገበያ፤ ከየካ አባዶ ጦር ኃይሎች፤ ከየካ አባዶ ዊንጌት፤ ከሃያ ኪሎ ሜትር በላይ ነው፡፡ አገልግሎቱ የሚሰጠው በከተማ የብዙኅን ትርንስፖርት መርሕ ነው፡፡ ለአንድ ተቋም ተለይቶ የሚሰጥ መኪና የለም፡፡ በመሥመሩ ላይ የሚገኙ የሁሉም ተቋማት ሠራተኞችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ስትራቴጂ ነው፡፡ ለየተቋማት ሰርቪስ ተለይቶ ይመደብ ቢባል፤ ምናልባት አንድ ሺህ አውቶቢስ ላይበቃ ይችላል፡፡ በጋራ ሲጠቀሙ የታወቀ መነሻ ቦታ፤ የጉዞ አቅጣጫ እና መድረሻ አለ፡፡ ከተማዋ ውስጥ ባሉ ፌርማታዎች የብዙኅን ትራንስፖርት ይሰጥ የነበረው አንበሳ ከተማ አውቶቢስ ብቻ ነበር፡፡ ምክንያቱም አንበሳ አገልግሎት ሲጀምር፣ ዛሬ ከተማዋ ውስጥ የምናገኛቸው የብዙኀን የትራንስፖርት ተቋማት አልነበሩም፡፡ ሌላው ቀርቶ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮም አልነበረም፡፡

ምንም እንኳ የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጠው አገልግሎት የመንግሥት ሠራተኛውን መሠረታዊ ችግር በመቅረፍ ረገድ የተጫወተው ሚና ከፍተኛ ቢሆንም፤ ችግሮች እንዳሉ ደግሞ ተጠቃሚዎች ያነሳሉ፡፡ የአውቶቢሶች መነሻ ቦታ እና ሰዓት አለመከበር፣ በአንዳንድ ቦታዎች የሚንቀሳቀሱ አውቶቢሶች ከልክ በላይ መሙላት፤ አንዳንዶች ደግሞ እምብዛም ሳይሞሉ መንቀሳቀስ፣ የመሥመር መረጣ ችግር፣ የመነሻ እና የመድረሻ ስዓት ችግር፣ የዲፖዎች እና የመለዋወጫ ቁሳቁሶች እጥረት፣ የአውቶቢስ ማቆሚያ ቦታ ችግር፣ በአንዳንድ ተገልጋዮች፣ የድርጅቱ የቁጥጥር ሠራተኞች፣ ሹፌሮች እንዲሁም ከሠራተኞች በተመረጡ አስተባባሪዎች ላይ የሚታይ የሥነ ምግባር ችግር መታየት የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ከሚያነሷቸው ችግሮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ እንዲሁም ድርጅቱ ሥራ በጀመረበት ወቅት ለጊዜው የአንበሳ ፌርማታዎችን ተገልግሎ በቀጣይ ግን በጥናት የራሱን እንደሚያደራጅ ገልፆ ነበር፡፡ ከፐብሊክ ሰርቪስ አገልግሎት አሰጣጥ አንጻር የትራንስፖርት አገልግሎት በራሳቸው የሚሰጡ መሥሪያ ቤቶችን ተሞክሮ በመውሰድ ለምን የራሱን ማዕከል መፍጠር አልቻለም የሚልም ጥያቄ የሚያነሱ ተገልጋዮች አሉ፡፡

ይህን አሰመልክተው አቶ አማኑኤል እንደገለፁት ፐብሊክ ሰርቪስ የትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት እና የሌሎቹ ሰርቪሶች አሠራር አንድ ዓይነት አይደሉም፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከ15 እስከ 20 አውቶቢሶችን አሠማርቶ ለሠራተኞቹ የሰርቪስ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ አየር መንገድን መነሻ (ቤንች ማርክ) ማድረግ እንችላለን ወይ? አገልግሎት በምንሰጠው ሕዝብ ብዛት፣ በምናሠማራው የተሽከርካሪ ብዛት፣ በምንሄድበት አቅጣጫ ብዛት፣ የመነሻ እና መድረሻ ብዛት ሊነፃፀሩ ይችላሉ ወይ? የሚሉ ጥያቄዎች ካነሱ በኋላ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከተለያየ አቅጣጫ ሠራተኞቹን አንስቶ አንድ መዳረሻ ነው የሚወስደው፡፡ በኋላም ከአንድ ግቢ ወደ ተለያየ መዳረሻ ነው የሚያጓጉዘው፡፡ ፐብሊክ ሰርቪስ ግን መነሻው 48 እና መድረሻው 20 ቦታ ነው፡፡ የአየር መንገድ ሠራተኞች የአንድ መሥሪያ ቤት ሠራተኞች ናቸው፡፡ ፐብሊክ ሰርቪስ ሠራተኞች ግን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠራተኞች ብቻ በተቋም ደረጃ እንዲሁም በአንድ ተቋም ሥር የሚገኙ ቅርንጫፎች ቁጥር በጣም ከፍተኛ ነው፡፡ በጽ/ቤት እና በቢሮ ደረጃ ከተቆጠሩ ከ16 ሺህ በላይ ናቸው፡፡ ሁሉም የመንግሥት ሥራ የሚሠሩ ናቸው፡፡ ስለዚህ የትኛው ነው ተመራጭ የሚሆነው? በየፌርማታው የምንቆመው በቦታው አገልግሎት የሚፈልግ ሠራተኛ ስላለ ነው፡፡ አንድ ነገር መታሰብ ያለበት መጨረሻ ላይ የሚሄደው ሰው እሱ የሚደርስበትን ስዓት ነው፡፡ በየፌርማታ ሳይቆም ቢሄድ አገልግሎት የማያገኘው ሠራተኛው ቁጥር በርካታ ነው በማለት ይሞግታሉ፡፡

ይሁን እንጂ በዚህ አሠራር አጭር ርቀት የሚጓዙ አንዳንድ ሠራተኞችን የበለጠ ተጠቃሚ ሲያደርግ፤ ለረጅም ተጓዦች ደግሞ ጊዜ ከመውሰዱም በላይ የሚፍጠር ድካም አለ፡፡ ለምሳሌ አንድ ሠራተኛ የመሄጃ እና የመመለሻ ትራንስፖርት የመምረጥ ዕድል ሲኖረው፤ ከመነሻ መድረሻ የሚሄደው ግን ያን ሁሉ እያስተናገደ በሄደ ቁጥር ጊዜን ይበላል የሚል አስተያየት ከተጠቃሚዎች ይነሳል፡፡

ይህም ከግል ፍላጎት የሚመነጭ አስተያየት መሆኑን ገልፀው፤ እንዳውም በዚህ አሠራር ተጠቃሚ የሚሆነው ከመነሻ የሚይዘው ነው፡፡ ምክንያቱም ከመነሻ የሚነሳ ሠራተኛ ወንበር ያገኛል፤ የመነሻ ስዓቱ አይዛነፍበትም፡፡ በየፌርማታው የሚገለገለው ሠራተኛ ግን ወንበር አያገኝም፤ አውቶቢስ የማግኛ ስዓቱም ወጥ አይደለም፡፡ መንገድ ላይ የትራፊክ መጨናነቅ ካለ አውቶቢሱ ዘገየ ወይም ጥሎኝ ሄደ በሚል ሥጋት ሌላ አማራጭ ለመጠቀም ይገደዳል፡፡ ቋሚ የሆነ መኪና መጠቀም አይችልም፡፡ የመኖሪያ ቦታ ረጅም ርቀት መሆኑ የምርጫ እና የውሳኔ ጉዳይ ነው፡፡ መሀከል ላይ የሚገኘው ሠራተኛ አማራጩ በተገኘው አውቶቢስ መሄድ ስለሆነ፤ በወጪ ወራጅ ይሄዳል፡፡ አገልግሎቱ ፕላን ሲደረግ አውቶቢሶቹ 50 ሰው በወንበር፣ 35 ሰው በመቆም እና 15 ሰው እና ከዚያ በላይ በወጪ ወራጅ እንዲገለገሉ ነው፡፡ የብዙኀን ትራንስፖርት መርሕን ተከትሎ ነው የሚሠራው፡፡ ከመነሻው እስከ መድረሻው ዝም ብሎ በርሮ አይሄድም፡፡ መሥመሮች ከጥናቱ ውጪ በጣም ረጅም ሆነዋል፡፡ ለምሳሌ ሰሜን ሆቴል አካባቢ የነበረው ጉለሌ ክ/ከተማ አዲሱ ገበያ ሲሄድ፤ እንደገና ወረዳዎች ሲጨመሩ፣ ጽ/ቤቶች ሲጨመሩ ረጅም ርቀት የምንሄድበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በዚህ ላይ የወጪ ወረጃ ቁጥር ይበዛል ብለዋል፡፡

በየሩብ ዓመቱ በሚደረገው ቁጥጥር በአንዳንድ መሥመሮች የሚገለገለው ሠራተኛ ቁጥር እስከ 200 እና 221 ሰው ድረስ በወጪ ወራጅ የተቆጠረበት አጋጣሚዎች ነበሩ ያሉት አቶ አማኑኤል፤ ድርጅቱ አውቶቢስ አልጨመረም፡፡ ነገር ግን ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ የመንግሥት ሠራተኞች ቁጥር ጨምሯል፡፡ ስለዚህ ይህን ችግር ለመቅረፍ በሁለት አቅጣጫ እየተሠራ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡

አንደኛ በአንዳንድ መሥመሮች እየጨመረ የመጣውን ፍላጎት ለማሟላትም የ50 አውቶቢሶች ግዥ ከብረታ ብረት ኮርፖሬሽን ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ ጋር በመፈራረም አንድ ሶስተኛ /1/3ኛ/ ክፍያ ተከፍሏል። ሌላው ሠራተኛው በሚያደርገው የመኖሪያ ቤት ለውጥ ምክንያት አንዳንድ አካባቢ ተሳፋሪ ሲጨምር፤ አንዳንድ አካባቢ ደግሞ ተሳፋሪ የቀነሰበት ሁኔታ አለ። ይህን ለውጥ መሠረት በማድረግም አውቶቢሶችን ሽፍት የማድረግ ሥራ ተሠርቷል፡፡ በዚህ አሠራር ነው እነ የካ አባዶ፣ ቦሌ አራብሳ፣ ኮዬ ፈጬ፣ ቂሊንጦ፣ ቱሉ ዲምቱ ከ5 እስከ 11 አውቶቢሶች የተመደቡላቸው፡፡ ይኼ ዘላቂ መፍትሔ ሊሆን አይችልም፡፡ የተጨማሪ አውቶቢስ ግዢ ዋናው ምክንያት ተጨማሪ ፍላጎት በመኖሩ፤ ከዓቅም በላይ የሚጭኑ አውቶቢሶች ስላሉ ነው፡፡ በየዓመቱ መጀመሪያ ሁሉም አውቶቢሶች ላይ የተሳፋሪ ቆጠራ በማድረግ የማሸጋሸግ ሥራ ይሠራል። በዚህም አነስተኛ ተሣፋሪ ሆነው ሁለት አውቶቢሶች የነበሩበትን መሥመር ወደ አንድ በማውረድ አንዱን አውቶቢስ እጥረት ወዳለበት አካባቢ በመመደብ መፍትሔ ይሰጣል ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ ከተጠቃሚዎች የሚሰጠው አስተያየት ከተሣፋሪ ቁጥር አንፃር የአንበሳ አውቶቢስ ከሚያሳፍረው መጠን በላይ ነው የሚጭነው፡፡ አንበሳ በማስታወቂያ ደረጃ የሰው ልክ 70 ይላል፡፡ ከዓላማ አንፃር አንበሳ ቢዝነስ መሥራት (ገንዘብ መሰብሰብ) ነው፡፡ በሰበሰበው ገንዘብ መጠን ነው ተጠቃሚነቱ። ፐብሊክ ሰርቪስ ደግሞ አገልግሎት በመስጠት የመንግሥት የሥራ ጊዜን ምቹ በማድረግ ርካታ መፍጠር ነው፡፡ የፐብሊክ ሰርቪስ አውቶቢስ ግን 85 ሰው በመደበኛ፣ 15 ሰው በወጪ ወራጅ በድምር 100 ሰው ይጭናል፡፡ ስለዚህ በተገልጋዩ ላይ መጨናነቅ ከመፍጠሩም በተጨማሪ፣ በመተፋፈግ ለሚመጡ

 የጤና ችግሮች ያጋልጣል የሚል ነው፡፡

ይህን የተጠቃሚዎችን አስተያየት በተመለከተም፤ በመሠረቱ ይህ ድርጅት የመንግሥት የልማት ድርጅት ነው፡፡ ስለዚህ የድርጅቱ ውጤት በእርካታ ብቻ የሚለካ አይደለም፡፡ የልማት ድርጅት ስለሆነ ማትረፍ፤ ለሠራተኛው ደመወዝ መክፈል፤ መለዋወጫ መግዛት፤ ሌሎች አስተዳደራዊ ወጪዎችን መሸፈን አለበት፡፡ ለሚሰጠው አገልግሎት መንግሥት ክፍያ ቢከፍለውም፤ አስተዳደራዊ ወጪዎቹን ራሱ ስለሚሸፍን ገቢ መሰብሰብ ይጠበቅበታል፡፡ እንደ ደንበኛ የፌዴራል መንግሥት ለፌዴራል፤ ለከተማ አስተዳደሩ ሠራተኞች ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይከፍላሉ። ስለዚህ አንበሳም 70 ሰው ሲል በአንድ ጊዜ በመነሻ ላይ እንጂ በወጪ ወራጅ ግን ከዚያ በላይ ይጭናል። ሌላው የፐብሊክ ሰርቪስ እና የአንበሳ አውቶቢሶች በመጫን ዓቅማቸው ይለያያሉ፡፡ የፐብሊክ ሰርቪስ አውቶቢስ ወንበር 50 ሲሆን፤ የአንበሳ 35 ነው፡፡ ስለዚህ የሚበዛው ሰው ወንበር ስለሚያገኝ 100 ሰው የሚጭነው በወጪ ወራጅ ስለሆነ ተጽዕኖው ብዙ አይደለም በማለት አቶ አማኑኤል ያስረዳሉ፡፡

በእያንዳንዱ አውቶቢስ ላይ ከሠራተኛው የተወከሉ ሦስት ሦስት አስተባባሪዎች አሉ፡፡ እነዚህ አስተባባሪዎች በተራ ድርጅቱ በየሩብ ዓመቱ በሚያካሂደው ስብሰባ ይሰበሰባሉ፡፡ ስለዚህ አብረው ያቅዳሉ፣ አፈፃፀማችን ይገመግማሉ፡፡ እነዚህን መድረኮች ተጠቅመውም ከተጠቃሚው የሚሰጡ አስተያየቶች እና የሚነሱ ጥያቄዎችን ያነሳሉ፡፡ ድርጅቱም የሚነሱ ጥያቄዎችን ወስዶ፤ መድረክ ላይ ማብራሪያ ወይም ምላሽ የሚያስፈልጋቸውን የሚመለከተው አመራር መልስ ይሰጥበታል፡፡ ወደ ቢሮ በመውሰድ ሊሠሩ የሚገባቸው ሥራዎች ካሉ ደግሞ በቢሮ ደረጃ እንዲታዩ የሚደረግበት አሠራር አለ፡፡ ስለዚህ መረሐ ግብር ተዘጋጅቶላቸው ለየሚመለከታቸው ክፍሎች፣ ቅርንጫፎች፤ የቴክኒክ ክፎሎች ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጡባቸው ይደረጋል፡፡ በዚህ መልኩ ችግሮች ከተፈቱ በኋላ በቀጣይ መድረክ ላይ የተሠራው ለሕዝብ እና ለባለ ድርሻ አካላት እንዲቀርቡ የሚደረጉበት አሠራር አለ፡፡ የድርጅቱ የሕዝብ እና የባለ ድርሻ አካላት መድረክ ከ250 እስከ 300 ሰዎች የሚሳተፉበት ስለሆነ በተገቢው አግባብ ይገመገማል፡፡ ይህ መድረክ ያለፉትን የሚገመግሙበት ብቻ ሳይሆን፤ የወደፊቱንም ለማቀድ የሚጠቀሙበት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ከክትትል እና ቁጥጥር አኳያ ሥራውን የሚመራ ኮማንድ ፖስት አለ ያሉት አቶ አማኑኤል፤ በዚህ ኮማንድ ፖስት ውስጥ የአዲስ አበባ ፐብሊክ ሰርቪስ፣ ፌዴራል ፐብሊክ ሰርቪስ፣ ከተጠቃሚዎች የተወከሉ ሰዎች፣ የፌዴራል ፖሊስ እና የአዲስ አበባ ፖሊሲ ይሳተፋሉ፡፡ እነዚህ አካላት በየወሩ እየተሰበሰቡ የድርጅቱን ዕቅድ እና አፈፃፀም ይገመግማሉ፡፡ ለምሳሌ ከግንዛቤ እጥረት አንፃር የተነሱ ጥያቄዎች ከአዲስ አበባ ፐብሊክ ሰርቪስ ጋር በመሆን የአሥሩንም ክ/ከተሞች እና ጽ/ቤቶች የሰው ሀብት አመራሮችን በማወያየት እና አቅጣጫ በመስጠት በሥራቸው ላሉ ወረዳዎች እና ት/ ቤቶች አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ግንዛቤ እንዲያስይዙ ተደርጓል፡፡ በዚህ አሠራር መሠረት ምሥራቅ ዞን (የካ እና ቦሌ) በምናደርገው የኮማንድ ፖስት ስብሰባ ላይ እንዲገኙ በማድረግ የሚነሱ ጥያቄዎች ተነስተው ማብራሪያ እንዲሰጥባቸው በማድረግ የየራሳችን ሥራዎችን የተካፋፈልንበት ሁኔታ ነበር፡፡ ሌላው የግንዛቤ መፍጠሪያ ዘዴ ሚዲያዎችን መጠቀም እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ በአገልግሎት ሰጪው እና በተገልጋዩ መሀከል ከባህሪይ ጀምሮ መመሪያውን ባለማወቅ ወይም ባለማክበር አልፎ አልፎ የሚፈጠሩ የሥነ ምግባር ክፍተቶች ከሚነሱ ችግሮች አንዱ ነው፡ ፡ አቶ አማኑኤል እንዳሉትም በአንዳንድ አሽከርካሪዎች ፌርማታ የመዝለል ሁኔታ ይታያል፡፡ ከባህሪይ አንፃርም አንዳንድ ሹፌሮች አመናጨቁን ተብሎ የጎን ቁጥር ተጠቅሶ ሪፖርት ይደረጋል፡፡ እነዚህ እና መሰል ችግሮችን ለመፍታት ድርጅቱ ሁሉንም ሠራተኞቹን በ1 ለ 5 አደራጅቷል፡፡ በየሣምንቱ የሥራ አፈፃፀም ይገመገማል፡፡ የቅሬታ ማቅረቢያ መዝገብ አለ፡ ፡ ከግምገማ ነጥብ አንዱ በአገልግሎት አሰጣጣችን ላይ የቀረበ ቅሬታ አለ ወይ? የቀረበ ቅሬታ ካለ ምንን የሚመለከት ነው? በማን ላይ ነው የቀረበው? ምንድን ነው የተፈጠረው? የሚሉት ጥያቄዎች ተነስተው ውይይት ይደረግባቸዋል፡፡ ሹፌሮቹም በተመሳሳይ ሁኔታ ያካሂዳሉ፡፡ መጀመሪያ ለማስተማር፣ ለማረም የሚወሰደው ርምጃ ከቡድኗ ነው የሚጀምረው፡፡ ቡድኗ አስተምራው ሊመለስ ያልቻለ ሰው ካለ፤ በድርጅቱ አደረጃጀት መሠረት የቅርብ ኃላፊው እንዲያርመው፣ እንዲያስተካክለው ይደረጋል፡፡ በዚህ ሂደት አልፎ እስከ መሰናበት የደረሰ ሠራተኛ አለ፡፡

በአገልግሎት ተቀባዩ የሚስተዋሉ የሥነ ምግባር ችግሮች ደግሞ በዋናነት መታወቂያ አለማሳየት በሁሉም አቅጣጫዎች የሚያጋጥም ችግር ነው። ሁል ጊዜ በዚህ ሰርቪስ እጠቀማለሁ፤ ለምንድን ነው መታወቂያ የምጠየቀው? የሚሉ አሉ፡፡ ነገር ግን ሥራ የሚለቁ ወይም የሚቀይሩ ይኖራሉ፡፡ አመሳስሎ የሚሠራም አለ፡፡ ለምን መታወቂያ አሳያለሁ ብሎ ከአስተባባሪዎች እና ከሹፌሮች ጋር የሚጣሉ ሠራተኞች አሉ፡፡ ሌላው የተገልጋዮች የሥነ ምግባር ችግር ቆሻሻ መጣል፣ መኪና ውስጥ ከፍተኛ ድምጽ ማሰማት ነው። ምክንያቱም ሥራ ላይ የዋለ ሠራተኛ አርፎ መሄድ ይፈልጋል፤ ማንበብ የሚፈልግም ሊኖር ይችላል፡፡ ስለዚህ ዘፈንም ይሁን ሬዲዮ በግሉ ለመስማት ከፈለገ በጆሮ ማዳመጫ መስማት እንጂ ሌሎችን በሚረብሽ መልኩ መሆን የለበትም፡፡ መኪናው ውስጥ ጮሆ መደመጥ የሚችለው ከመኪናው የሚከፈት ሬዲዮ ብቻ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት መታወቂያቸው ተይዞ፤ መጥተው አስተባባሪዎች ባሉበት አነጋግረን፤ በራሳቸው ስህተታቸውን አይተው፤ እናስተካክላለን ብለው የሄዱ በርካታ ሠራተኞች አሉ፡፡

ከተጠቀሱት ችግሮች አልፈው ለመደባደብ ሞክረው (ቃትተው) በፖሊስ ተይዘው የተጠየቁ ሰዎችም አሉ፡፡ በዚህ መልኩ ችግር የፈጠሩ ሠራተኞችን ለመ/ቤታቸው ደብዳቤ ተጽፎ የዲሲፕሊን ርምጃ የተወሰደባቸው ሠራተኞች አሉ፡፡ ይህ ሁሉ የሚደረገው የአገልግሎት አሰጣጡ ሠላማዊ እንዲሆን ነው፡፡ ምክንያቱም ተልዕኳቸው ቢለያይም ሁሉም የመንግሥት ሠራተኞች ናቸው፡፡ ድርጅታችን ከሚሰጠው አገልግሎት ጋር የተያያዙ ጥቄዎችንም ሆነ አስተያየቶች ሚዲያው ባያሳየን ሁል ጊዜ ትክክል ነን ብለን ተጨማሪ ስህተቶችን ልንሠራ እንችል ነበር፡፡ ስለዚህ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ተባብረን ነው የምንሠራው፡፡ እንደዚህ መረዳዳት ከሌለ ሥራ አይሠራም፡፡ አንዳንድ ጊዜ የሚፈጠሩ መንገራገጮች ግን ይኖራሉ ብለዋል፡፡

ከአገልግሎት አሰጣጥ አኳያ የድርጅቱ ሹፌሮች ለሠራተኛው የሰርቪስ አገልግሎት ከሰጡ በኋላ መልሰው ሰርቪስ ይጠቀማሉ፡፡ ስለዚህ ከጊዜ አንፃር በአብዛኛው እስከ 2፡00 ስዓት ሠርቪስ እየሰጡ ያመሻሉ፡፡ በየመንገዱ በሚፈጠር መጨናነቅ ወደ ዲፖ በተመሳሳይ ስዓት አይደርሱም፡፡ ተጠባብቀው ነው በሰርቪስ የሚሄዱት፡፡ በዚህ ምክንያት ለአንዳንድ ሹፌሮች እስከ አምስት ስዓት ለማምሸት ይገደዳሉ፡፡ በተጨማሪም ጧት የ12፡30 ሰዓት ሰርቪስ ለመስጠት 11፡00 ሰዓት የመሰባሰብ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ይህ መሆኑ ሹፌሮች በቂ እረፍት እንዳይኖራቸው ስለሚያደርግ ችግር የሚሉ አስተያየቶች ይሰጣሉ፡፡

ለዚህ አስተያየት አቶ አማኑኤል ሲመልሱም እንዳስቀመጡት የአዲስ አበባ የትራንስፖርት አገልግሎት በአጠቃላይ ሕዝቡን እያሥቸገረ ነው ያለው፡፡ በአዲስ አበባ ውስጥ ያለውን የትራፊክ መጨናነቅ ለማቃለል በሚመለከተው አካል የተለያዩ ስትራቴጂዎች ተነድፈው እየተሠሩ ነው፡፡ እንደ አገልግሎት ሰጪ ተቋም አመራር የመፍትሔ ሀሳብ ለመስጠት በተለይ በዋና ዋና መንገዶች እና ከፍተኛ የሆነ የትራፊክ መጨናነቅ ባለባቸው መሥመሮች ላይ ጠዋት እስከ 3፡00 ስዓት እና ማታ ከ10፡00 ሰዓት እስከ 1፡00 ስዓት ድረስ በመንገዶች ግራ እና ቀኝ ምንም ዓይነት ተሽከርካሪ እንዳይቆም በማድረግ መንገዱን ለትራፊክ ፍሰት ጤናማ ማድረግ ይቻላል ይላሉ፡፡ ይህ አሠራር ቦሌ መንገድ ላይ፤ ቀደም ሲልም ፒያሳ መንገድ ላይ በ1998/99 ተሞክሮ ውጤታማ ሆኗል፡፡

አሁን ደግሞ ከሐምሌ 1 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ የጭነት ተሽከርካሪዎች ቀን ላይ ከጠዋቱ ከ12፡ 30 ሰዓት እስከ ምሽት 2፡00 ስዓት ወደ ከተማ እንዳይገቡ እና እንዳይወጡ በመደረጉ ምክንያት ሰሞኑን የተፈጠረው እፎይታ ቀላል አይደለም፡፡ የትራፊክ መጨናነቅ የሚያስከትለው ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ ችግር፣ የአየር ብክለትም ጭምር ከተረዳን መፍትሔው ለመጨናነቅ ምክንያት የሆኑ ችግሮችን ማስወገድ ነው፡፡ ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ ባለበት ስዓት ሁሉም ተሽከርካሪዎች በዝቅተኛ የፍጥነት ደረጃ (ሚኒሞ) እየሠሩ ጭስ ያመነጫሉ፡፡ መኪኖቹ ግን አይንቀሳቀሱም፤ ነዳጅ ግን ይበላሉ፡፡ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የገባው ነዳጅ ይባክናል፡፡ ግለሰብ ቢገዛውም በሀገር ሀብት ነው የሚገዛው፡፡

በተለይ በጣም ረጅም መንገድ የሚሄዱ መኪኖች አምሽተው ይገባሉ፡፡ ነገር ግን አምሽተው ገብተው ወደ ቤታቸው ሲመለሱ አምስት ስዓት ይገባሉ የተባለው የተጋነነ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ይህንንም ሀሳባቸውን ምሳሌ በመጥቀስ ነበር ያብራሩት፡፡ ማታ ሁለት ስዓት ላይ አቃቂ ዲፖ የደረሰ ሹፌር ሰርቪሱ ቡልቡላ ወይም ሃና ማርያም የሚያደርሰው ከሆነ፤ አንድ ስዓት ቢፈጅበት ሦስት ስዓት ቤቱ ይደርሳል፡፡ የፐብሊክ ሰርቪስ የሹፌሮች ሰርቪስ 2፡00 ሰዓት ላይ ነው የሚወጣው፡፡ ያም ሆኖ በቂ የእረፍት ጊዜ አላቸው፡፡ ምክንያቱም ጠዋት አገልግሎት ከሰጡ በኋላ አርፈው ነው የሚውሉት፡፡ ከሰርቪስ በኋላ የመኪናውን ጽዳት ይጠብቃል፣ መኪናውን ይጠብቃል በዚያውም

 መኪናው ላይ ያርፋል፡፡ ከዚያ በኋላ የማታ ሥራውን ይቀጥላል፡፡ ከመንገድ ሥራ ጋር የተያያዘ ችግር አለ፡፡ ለምሳሌ የቃሊቲ- አቃቂ መንገድ በግንባታ ላይ ነው። ቢሆንም የመንገድ ግንባታው በግንባታ ላይ እያለ የመንገዱ ግማሽ ክፍል ለትራንስፖርት ክፍት በመሆኑ ምክንያት የሚፈጠሩ የትራፊክ መጨናነቆች አሉ፡፡ ጊዜያዊ ችግሮች ናቸው፡፡ ስለዚህ የአቃቂ እና የቃሊቲ መንገድ ሲጠናቀቅ በዚያ ቅርንጫፍ ላይ ላሉ ሠራተኞች ችግር ይቀረፋል ማለት ነው፡፡ ሩቅ የሚባለው ቅርንጫፍ የደቡቡ ስለሆነ፡፡

ሌላው የሚጨናነቀው መሥመር በተለይ ወደ ቱሉ ዲምቱ፣ ኮዬ ፈጬ፣ ቂሊንጦ፣ ጎሮ እና ወደ አያት የሚሄዱ መኪኖች የሚያልፉበት በተለምዶ ከአንበሳ ጋራዥ እስከ ጎሮ ያለው መንገድ ነው፡፡ በተጠቀሰው ቦታ ላይ በርካታ የንግድ ተቋማት አሉ፡፡ ስለዚህ መንገድ ላይ ደርቦም ጭምር ፓርክ ይደረጋል፡፡ ስለዚህ አካባቢው የትራፊክ ትኩረትን ይሻል፡፡ በዚያ መሥመር ጠዋት ወደ መሀል ከተማ እና ማታ ከመሀል ከተማ ወደ ዳር ለመሄድ እሰከ ጎሮ አደባባይ ድረስ መንገዱ ይዘጋል፡፡ እንደዚህ ዓይነት መንገዶች እየተመረጡ እንደመንገዱ ሁኔታ የሚስማማ የትራፊክ ማኔጅመንት መፍትሔ ሊቀመጥላቸው ይገባል፡፡ ይህ ሲደረግ ፐብሊክ ሰርቪስ ብቻ ሳይሆን፤ ሌላውም ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ አንቡላንስም ማለፊያ አጥቶ የሚቸገርበት ስዓትም አለ፡፡ ስለዚህ በ2012 እንደ ባለድርሻ አካል ከሚመለከታቸው ጋር አብሮ ለመሥራት ዝግጅት እያደረግን ነው ብለዋል፡፡

ድርጅቱ ለሚሰጣቸው አገልግሎቶች ውጤታማነት የላቀ ሚና ያላቸው ዲፖዎች፣ የነዳጅ መቅጃዎች እና የመለዋወጫ ዕቃዎች አቅርቦት እጥረት እንዳለ ይነገራል፡፡ ነገር ግን ይህን አስተያየት አቶ አማኑኤል አይቀበሉትም፡፡ ምክንያታቸውን ሲገልፁም፤ መንግሥት አስቦበት ድርጅቱ ከመቋቋሙ በፊት ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በተሰጠ ትዕዛዝ የአዲስ አበባ አስተዳድር ለዲፖ የሚሆኑ ቦታዎች በአራቱም አቅጣጫዎች እንዲያዘጋጅ አድርጓል፡፡ አውቶቢሶቹ የሚያድሩባቸው ቦታዎች (አባ ኪሮስ አደባባይ፣ ዊንጌት፣ ዩኒሳ እና የሲ.ኤም.ሲ) የድርጅቱ ቦታዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ ቦታ አለ፤ የቀረው የግንባታ ሥራ ነው። የዲዛይን ሥራ አልቋል፡፡ ለግንባታው የሚሆነውን ገንዘብ መንግሥት መመደብ ስላለበት ጥያቄው ቀርቧል፡፡ ግንባታውን የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር እንዲያከናውን ተሰጥቷል፡፡ በዚህ መሠረት የግንባታ ፈቃድ ባገኙ ሁለት ዲፖዎች ላይ የአስተዳደር ሕንፃ ሥራ ለመጀመር እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

ሌላው የተነሳው መሠረታዊ ችግር በአራቱም ቅርንጫፎች (ዲፖዎች) የነዳጅ ማደያ አለመኖሩ ነው። ይህንንም አስመልክተው ሲመልሱ፤ አገልግሎቱ ከነበረው ችግር አኳያ አውቶቢስ ተረክቦ ዲፖ እስከሚሠራ፣ የነዳጅ ማደያ እስከሚሠራ እና የአስተዳደር ሕንፃ አስከሚሠራ አውቶቢሶቹ ይቁሙ ተብሎ የሚታለፍ አልነበረም፡፡ ከእነ ችግሩ አገልግሎት ወደ መስጠት ነው የተገባው፡፡ ስለዚህ መንግሥት የገንዘብ አቅሙ ፈቅዶለት በጀት ሲመድብ ግንባታቸው ይካሄዳል፡፡ የነዳጅ ዲፖ ለማቋቋም የታንከር ቀበራ ለመሥራት አንዳንድ እንቅስቃሴዎች እንደተጀመሩ ገልፀው፤ የማደያዎቹ መገንባት የአውቶቢሶቹን እንቅስቃሴ እና የነዳጅ ፍጆታን ይቀንሳል፡፡ ያለው ችግር እየታወቀ ነው ከግል ማደያዎች ነዳጅ እየተገዛ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው ብለዋል፡፡ ምክንያቱን ሲያስረዱም ይህን አሠራር ካልተከተለ መኪናው ያለ ነዳጅ ስለማይሄድ አገልግሎቱን መስጠት አይችልም ነበር፡፡ የትራንስፖርት ችግሩ በመንግሥት ሠራተኛው ላይ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ሕዝቡ ሲደርስ የነበረ ችግር ስለሆነ፤ ጊዜ የሚሰጥ አልነበረም፡፡ እስኪሟላ አገልግሎት አይስጥ ቢባል ኖሮ በአማካይ በቀን ከ120 እስከ 130 ሺህ ሰው የፐብሊክ ሰርቪስ እና የከተማ ትራንስፖርት አገልግሎት ሳያገኝ ይውል ነበር ማለት ነው፡፡ ስለዚህ መጀመሩ የተሻለ አማራጭ ነበር፡፡ ነገር ግን ከወጪ አንፃር ሲታይ እንደ ልማት ድርጅት አዋጪ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ከሥራ በኋላ ነዳጅ ለመቅዳት ነዳጅ ያባክናል፡፡ ስለዚህ ነዳጅ ለመሙላት የሚያባክነው ጊዜ እና ነዳጅ ይቀራል፡፡ የነበረው አማራጭ ዋጋ ተከፍሎ አገልግሎት መስጠት ወይስ እስኪሟላ መጠበቅ የሚለው ነበር፡፡ በፌዴራል እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚሠሩ የመንግሥት ሠራተኛ በትራንስፖርት እጥረት መንገላታታቸው ሳያንሳቸው፤ በሥራ የመግቢያ ስዓት ሠራተኛው ባለመግባቱ ከመንግሥት አገልግሎት ለማግኘት የሚጠብቀው ሕዝብ ይደረስበት የነበረውን መጉላላት መቅረፍ አልቻሉም፡፡ ስለዚህ የነበረው አማራጭ ገንዘብ አውጥቶ ወደ 200 ሺህ የሚደርስ ሠራተኛን ችግር መፍታት ነበር፡፡ እስከዚያው ግን ጥንቃቄ ተደርጎ መኪኖች በሣምንት አንድ ቀን ነዳጅ የሚቀዱበት ሁኔታ በመፍጠር እየተሠራ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

እንደ ድርጅት ከመለዋወጫ ጋር የተያያዘ ችግር የለም ያሉት አማኑኤል የአውቶቢሶቹ ግዥ ሲፈፀም የሚያስፈልጋቸውን የመለዋወጫ ዕቃ ሜይቴክ (የብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን) ለ15 ዓመት እንዲያቀርብ ውል መገባቱን ይገልፃሉ፡፡ በውሉ መሠረት በርካታ መለዋወጫዎች ተገዝተዋል፡፡ ስለዚህ ድርጅቱ ውስጥ በብልሽት ወይም በመለዋወጫ ዕጥረት የቆመ መኪና የለም፡፡ 410ሩም መኪናዎች ሥራ ላይ ነው ያሉት ብለዋል፡፡

የደርጅቱ ሠራተኛም ሆነ ሰርቪስ ተጠቃሚው ሊያውቀው የሚገባው፤ የፐብሊክ ሰርቪስ አውቶቢስ ሹፌር፣ መካኒክ፣ የኦፕሬሽን ሠራተኛ እና የአስተዳደር ሠራተኛ በሚሠራው ሥራ የመንግሥትን ተልዕኮ ነው የሚፈጽመው፡፡ ዋናው ተልዕኮውም የፌዴራልም ሆነ የአዲስ አበባ አስተዳደር ሠራተኞች በሥራ ስዓታቸው ደህንነታቸው ተጠብቆ በሥራ ቦታቸው እንዲገኙ ማድረግ ነው፡፡ አገልግሎት ሲሰጡ ተመልሰው ተገልጋዮች መሆናቸውን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ አውቶቢሱን ከመንከባከብ ጀምሮ ለደንበኛው በደንበኛ የአገልግሎት አሰጣጥ መርሕ መሠረት አገልግሎት መስጠት አለባቸው፡፡

ምክንያቱም አገልግሎት የሚሰጡትን ሠራተኛ በሠላም እና በስዓቱ ሥራ ቦታው ላይ ሲያደርሱ፤ ለሀገር ልማት የሚበጅ ተግባር ለመሥራት የሚሄድ ሠራዊት እያጓጓዙ እንደሆኑ፤ ከዚያም ሠራተኛው በሚሰጠው አገልግሎት ተመልሰው ተጠቃሚዎቹ ራሳቸው እንደሆኑ መረዳት አለባቸው፡፡ ሐኪም ወደ ሆስፒታል ሲያደርሱ የታመሙ ወገኖቻቸው እንደሚታከሙ፤ መምሕራንን በስዓታቸው በት/ቤቶቻቸው ሲያደርሱ ልጆቻቸው እንደሚማሩ፤ በሌሎች ሙያዎችም ኅብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኝ የራሳቸውን ድርሻ እየተወጡ እንደሆኑ በመገንዘብ በኃላፊነት ማገልገል አለባቸው፡፡ ስለዚህ ሹፌሮች የተሽካሪውን ደህንነት ከመጠበቅ ጀምሮ (ንጽህናውን፣ የቴክኒክ አቋሙን) ሲያሽከረክሩ አደጋ እንዳያደርሱ ተጠንቅቀው ማሽከርከር ይጠበቅባቸዋል፡፡ የአደጋ መንስዔ መሆን ብቻ ሳይሆን፤ የአደጋ መንስዔ የሚሆን ሦስተኛ ወገን ቢኖር እንኳ ያ አደጋ እንዳይደርስ የሚቻላቸውን ሁሉ ጥረት አድርገው ጉዳት መቀነስ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ስለዚህ የትራፊክ ሕግ እና ደንብ አክብረው ብቻ አይደለም አደጋን ተከላክለውም ጭምር የማሽከርከር ኃላፊነት አለባቸው በማለት የድርጅቱ ሠራተኞች ያለባቸውን ኃላፊነት አብራርተዋል፡፡

አያይዘውም የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት ድርጅት ተጠቃሚ ሠራተኞች ደግሞ መታወቂያቸውን አሳይተው፤ የአውቶቢሱን ንጽሕና ጠብቀው፤ የሌሎች ተገልጋዮችን ሠላምና ደህንነት ጠብቀው፣ ከድርጅቱ አሽከርካሪዎች ጋር ተግባብተው እና ተረዳድተው እንዲገለገሉ፤ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚፈጠሩ ችግሮች እና እንከኖች ቢኖሩ ቅሬታዎቻቸውን በተገቢው መንገድ በማሳወቅ በአጠቃላይ በተገልጋይ ሥነ ምግባር ሊገለገሉ ይገባል በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በመጨረሻም ወደ ሥራ ሲገባ ድርጅቱ በሂደት እየተማረ የሚያድግ ድርጅት ይሆናል በሚል እምነት ነው፡፡ በተለይ በየአውቶቢሱ ያሉ አስተባባሪዎች አገልግሎቱ ውጤታማ እንዲሆን እያደረጉት ያለው አስተዋጽፆ በቃላት ለመግለፅ፤ በገንዘብ ለመተመንም የሚከብድ ነው፡፡ መታወቂያ ተቆጣጥረው፤ የአውቶቢስ የመነሻ ስዓት ተቆጣጥረው፤ የሚፈጠሩ ችግሮችን ከሹፌሩ ጋር ተነጋግረው በመፍታት ሠላማዊ የሆነ አገልግሎት እንዲሰጥ በማድረግ በኩል እያደረጉት ያለው አስተዋፆ ከፍተኛ ነው፡፡ ይኼንን ድጋፋቸውን እና አስተዋፆአቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አደራ በማለት እና በአንዳንድ መሥመሮች እየተነሱ ያሉ የተጨማሪ አገልግሎት ጥያቄዎች ስለሚፈቱ ደንበኞች በትዕግሥት እንዲጠብቁ በማሳሰብ ሀሳባቸውን አጠናቅቀዋል፡፡

ዘመን መፅሄት መስከረም 2012

አባይ ፈለቀ