በውህደትም በጥምረትም

23

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እየተዋሀዱ እና በጋራ ለመሥራት እየተስማሙ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ውጤታማ ለማድረግ እንደ ፓርቲዎቹ ባህርይ መዋሀድ ወይም መጣመሩ ይበጃል ሲሉ የፖለቲካ ምሁራን ይገልጻሉ ።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፖለቲካል ሳይንስ መምህሩ ዶክተር የሺጥላ ወንድሜነህ ‹‹ውህደትም ሆነ ጥምረት አሁን ባለው ሁኔታ አወዛጋቢ ናቸው›› ይላሉ፣ ምክንያቱም የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ውህደት ወይም ጥምረት  ሲፈጥሩ መጀመሪያ የተነሱበት መሰረታዊ የርዕዮተ ዓለም(አይዲዮሎጂ)፣ መስመር ወይም አቅጣጫ ያላቸው መሆኑን እንዲሁም ‹‹እወክለዋለሁ›› የሚሉት  የህብረተሰብ ክፍል መኖሩን ነው ።

ውህደትም ሆነ ጥምረት ይፈጠር ሲባል፤ በምን አግባብ ነው የሚዋሀዱት ወይም የሚጣመሩት? የርዕዮተዓለም መጣጣማቸውስ እንዴት ነው? በፖሊሲና ፕሮግራማቸው አፈጻጸም ላይ ምን ያህል ይግባባሉ? የሚሉት መመለስ የሚገባቸው መሰረታዊ ጥያቄዎች መሆናቸውን ዶክተር የሺጥላ ይናገራሉ።

እንደ ዶክተር የሺጥላ ገለጻ፣ አሁን እየታየ ያለው አንዳንዶቹ የያዙትን አይዲዮሎጂ  የፖሊሲና ማስፈጻሚያ ስትራቴጂያቸውን ሳይለቁ ጥምረት ይላሉ፤ ወደ ውህደትም እንምጣ በሚሉበት ወቅትም ምንም ዓይነት ግልጽነት የላቸውም። በመሆኑም ይህ ሁኔታ ትልቅ አደጋ ስለሆነ ሁለቱም አማራጮች በእኛ አገር ላይ ከጥቅማቸው ጉዳታቸው ያመዝናል ሲሉ ያስገነዝባሉ።

ለእኛ አገር  ምርጫው  ዴሞክራሲያዊ  ሽግግሩም ውጤታማ እንዲሆን የሚያስፈልገን ጠንካራ  የሆኑና ቁጥራቸውም ከአራት ያልበለጠ ፓርቲዎች ቢኖሩን ነው የሚሉት ዶከተር የሺጥላ፣ በፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና በልሂቃን መካከል ግልጽ ወይይት ተካሂዶ የአይዲዮሎጂ ውህደት ፈጥረው  ግልጽ የፓርቲ ፕሮግራምና አቅጣጫ ነድፈው የሚወክሉትን የህብረተሰብ ክፍል ለይተው አውቀው ወደ ውህደት ቢመጡ መልካም መሆኑን ይናገራሉ።

የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አባተ  ጌታሁን በበኩላቸው፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ብሔር ተኮር መሆናቸውን እና ብዛታቸውም እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ይናገራሉ፡፡  በአደጉት አገራት እንደዚህ አይነት ሁኔታ እንደሌለ፣ የሚከተሉት ርዕዮተ ዓለም እንዳላቸውና ይህንን የሚደግፉ በሥራቸው እንደሚሰባሰቡ ያብራራሉ፡፡ ‹‹እኛ ደግሞ ብሔር ተኮር ነን»፤ በመሆኑም  ውህደትም  ሆነ ጥምረት  ለእኛ አገር ፖለቲካ የሚያስኬዱ ናቸው ይላሉ።

ዶክተር አባተ በመዋሃድ የሚኖረው አንድ ፕሮግራም መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ አንድ ፕሮግራም ሲኖር በምርጫ ቅስቀሳም ከዚያ በኋላም በሚኖረው ሥልጣን ላይ ተዋህዶ መሥራት ይቻላል ይላሉ።

‹‹ይህ ምናልባት ፈተና የሚሆነው የብሔር ፖለቲካ ይዘው ለሚመጡ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ነው›› የሚሉት ዶክተር አባተ፣ከብሔር ወጥተው ወደ አንድ ርዕዮተ ዓለም ከመጡ ግን ውህደቱ ዘላቂ እንደሚሆን ይጠቁማሉ፡፡ የእነሱን ርዕዮትና አመለካከታቸውን  የሚፈልግ ማንኛውም ሰው እንደሚቀላቀላቸው፣ በዚህ ደግሞ ብዙ ድምጽ ማግኘት እንደሚችሉ ያብራራሉ፡፡

ጥምረት በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ የተለያየ ብሔርና ጎጥ ይዘው የተነሱ ፓርቲዎች የርዕዮተ ዓለም መመሳሰል እንኳን ባይኖራቸው አንድ የጋራ ስያሜ በመያዝ መንቀሳቀስ እንደሚችሉ ዶክተር አባተ ይጠቁማሉ። ይህ አካሄድ ቁጥራቸውን በመቀነስ እንወክለዋለን ከሚሉት ህዝብ ድምጽ የማግኘት ዕድላቸውን እንዲሁም ተወዳዳሪነታቸውን ከፍ እንደሚያደርገውም ነው የሚያመለክቱት።

ለዚህም ከኦሮሚያ ክልል ኦነግን፣ ከአማራ ክልል ደግሞ አብን፣ ከትግራይ አረናን ለአብነት በመጥቀስ፣  እነዚህ ፓርቲዎች የጋራ ስያሜ በመያዝ መጣመር ቢችሉ ሁሉም ከሚወክሉት ብሔር ድምጽ የማግኘት ዕድላቸው ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል እንዲሁም ፓርቲዎች እንዲሰባሰቡ በማድረግ ብዛታቸው እንዲቀነስ እንደሚያስችሉ ያብራራሉ።

ለኢትዮጵያ አሁን ባለው ሁኔታ የሚሻላት ርዕዮተ ዓለምን መሰረት ያደረገ ፓርቲ መመስረት መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህ ሲሆን ቢዋሀድም  ቢጣመሩም የመግባባት  ደረጃቸው ከፍተኛ ነው ይላሉ፡፡

ወደ ውህደት ለመምጣት ብዙ ወጪን እንደማይጠይቅ ጠቅሰው፣ በህዝቡ መካከል የፖለቲካ መረጋጋት ለመፍጠርና  ምርጫን ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ ግን እንደሚያግዝ ይጠቁማሉ። አሁን ባለው ሁኔታ በአገሪቱ የጥምር ፓርቲ መመስረት በጣም እንደሚከብድ ይጠቁማሉ።

ዶክተር የሺጥላ እንደ ጣሊያንና ሌሎች የአውሮፓ አገራት በርካታ ፓርቲዎችን በምርጫ በማሳተፍ የጥምር መንግሥት ሥርዓት ይመሠርታሉ፡፡ የእነሱ ዴሞክራሲ በጣም ጠንካራ በመሆኑ  ነው ይህንን ማድረግ የቻሉት፤ በእኛ አገር ግን እንደዛ ለማድረግ አንችልም። በመሆኑም  የሚበጀው  መዋሀዱ ነው ይላሉ።

በውህደት ተጨምቀው የሚወጡ ፓርቲዎች ዘውግ/ብሔር ከሆነ ደግሞ ማስታረቁ ሌላ ፈተና  እንደሚሆን በመጥቀስ፣ ይህም ፖለቲካውን  ከብሔር/ዘውግ በማውጣት ወደ መደበኛ የፖለቲካል ሥርዓት  ለማስገባት የሚረዱ ሥራዎችንም ጎን ለጎን  መሥራትን እንደሚጠይቅ ይጠቁማሉ።

በተለይም ወደ ውህደት ለመሄድ ሁለት ዓይነት ምርጫዎች እንዳሉ ዶክተር አባተ ጠቅሰው፣አንዱ አገራዊ  ሌላው ደግሞ ክልላዊ ውህደት መሆናቸውን ያመለክታሉ፡፡ ለአገራዊው ለምሳሌ አብንና አዴፓ ከአማራ ክልል፣ ኦነግና ኦዴፓ ከኦሮሚያ እንዲሁም ሌሎቹም በዚህ መልኩ አገራዊ ውህደትን ቢያደርጉ እንደሚቀል ይጠቁማሉ፡፡ ለዚህም ምክንያት ብለው የሚጠቅሱት ሁሉም ያን ያህል እርስ በእርስ የተራራቀ ሀሳብ የሌላቸው መሆኑን ነው፡፡

ዶክተር አባተ፣ መከፋፈል የትም እንደማያደርስ በመጠቆም፣ ከዚህ ሁኔታ መውጣትና ፓርቲዎቹም አገራዊውን ለውጥ ማስቀጠል እንዳለባቸው ይመክራሉ።

በኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት የመጣውን ለውጥ ተከትሎ ከ70 በላይ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እየተንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች በ2012 በሚካሄደው ምርጫ ጠንካራ ተፎካካሪ ለመሆን በመዋሀድ፣ በመጣመር፣ ወዘተ ቁጥራቸውን ቢያንስ ወደ አራት ማውረድ እንዳለበቸው መንግሥትም እያስገነዘበ ይገኛል፡፡

ፓርቲዎቹም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መዋሀድ የጀመሩ ሲሆን፣ አንዳንዶቹም አብረው ለመሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነት እየፈረሙ ይገኛሉ፡፡ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ከኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ)፣ እንዲሁም የአማራ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (አዴፓ) ከአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች  ንቅናቄ (አዴኃን) ጋር መዋሀዳቸውን ለእዚህ በአብነት መጥቀስ ይቻላል። አርበኞች ግንቦት ሰባት፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ)፣ አንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ እንዲሁም ሰማያዊ ፓርቲ ጥምረት ለመፍጠር በዝግጅት ላይ መሆናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

አሁን ባለው የአገራችን የለወጥ እንቅስቃሴ ላይ የሚያስፈልጉን የፖለቲካ ፓርቲዎች ከአራት መብለጥ እንደሌለበት በርካቶች ይስማሙበታል። ፓርቲዎች በርዕዮተ ዓለም እና በመሳሰለው ከሚመስላቸው ጋር መሰባሰባቸው ይፈለጋል፡፡ ለእዚህ ደግሞ ውህደት፣ ጥምረት፣ ወዘተ ያስኬዳሉ፡፡ የፓርቲዎቹ መሰባሰብ መንግሥት በመጪው 2012 የሚደረገው ምርጫ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማድረግ ለያዘው ቁርጠኛ አቋም ተስፋ የሚጣልበት ነው፡፡ ፓርቲዎቹ አሁን በያዙት ፍጥነት መዋሀዳቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉና ስለምርጫው ዝግጅት ሊያደርጉ ይጠበቃል፡፡

አዲስ ዘመን ታህሳስ 16/2011

እፀገነት አክሊሉ