«የአምቦ ከተማና አካባቢው ዴሞክራሲ እንዲጎለብት የትግል ማዕከል ሆኖ  አገልግሏል» -ዶክተር አብይ አህመድ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር

17

አዲስ አበባ፡- ‹‹የአምቦ ከተማና አካባቢው እውነተኛ እኩልነትና ትክክለኛ ዴሞክራሲ እንዲጎለብት የትግል ማዕከል ሆኖ አገልግሏል›› ሲሉ  ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አስታወቁ፡፡  ተማሪዎች ለትምህርታቸው ልዩ ትኩረት በመስጠት መማር እንዳለባቸውም አስገነዘቡ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትናንት በአምቦ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት ተገኝተው ለተማሪዎች ንግግር ባደረጉበት ወቅት እንደገለጹት፤ የከተማዋና አካባቢው ህዝብ ጨቋኙን ሥርዓት ለመለወጥ  በተደረገው ትግል ውስጥ የማይተካ ሚና  ተጫውቷል፡፡ አካባቢውም የሰላም ቀጣና መሆን ችሏል፡፡

‹‹አባቶቻችን የጀመሩትን ትግል  ቄሮና ቀሬ በሁሉም አካባቢዎች መስዋዕትነትን ከፍለው ዛሬ ለኦሮሞ ህዝብ ነጻነትን አጎናጽፈዋል፡፡  ህዝባችን ሰላማዊና ተስፋ ያለው አየር እንዲተነፍስ ትልቅ ዕድል ሰጥተዋል›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹መስዋዕትነት ለከፈለው ህዝባችን በሙሉ ትልቅ ክብር እንዳለን ለመግለጽ እውዳለሁ›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለፃ፤ የጀግኖችን አደራ ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ ይገባል፡፡ የሚጠቅመውንና የማይጠቅመውን በመለየትና በመገንዘብ ከዓለም እኩል ለመራመድ ደግሞ የእነ ጀነራል ታደሰ ብሩን ትግልና መልዕክት ማስቀጠል ያስፈልጋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለተማሪዎች ባስተላለፉት መልእክት ‹‹ከዚህ በኋላ ህዝባችን ለነጻነት መስዋዕትነት መክፈል የለበትም፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ነጻነቱን ተጎናፅፏል፡፡ ከአሁን በኋላ ለምተንና ተለውጠን ለእኛም ብቻ ሳይሆን ለጎረቤቶቻችን መትረፍ እንድንችል ለትምህርታችሁ ልዩ ትኩረት በመስጠት መማር አለባችሁ›› ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡

‹‹ከነጻነት በኋላ ለኦሮሞ ህዝብ ፣ ለኢትዮጵያ  እና ለአፍሪካ አንድነት የትምህርት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ጀግናው ጀኔራል ታደሰ ብሩ አስተምሮናል›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹አሁን ባለንበት ዘመን ለትምህርት ልዩ ትኩረት ሰጥተን አዲስ ነገር ፈጥረን ለመሥራት የማንዘጋጅ ከሆነ ባለንበት ሁኔታ ለመቆየት ያስቸግራል›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡ የሚያዛልቁ ነገሮችን በመለየት መሥራት እንደሚገባና ይህ ደግሞ በምሁራኑና ባሉት መልካም እሴቶች ተሞክሮ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አስታውቀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አሁን የሚያስፈልገን መስዋዕትነት ሌት ተቀን በማጥናትና ነገሮችን በመገንዘብ ሃሳብ ማካፈል እንዲሁም አዲስ ነገር ለመፍጠር ጥረት ማድረግ መሆን እንዳለበት አስታውቀዋል፡፡ ይህ ከሆነ የዛሬው ድል ሊቀጥል እንደሚችል መጠቆማቸውን የኦሮሞ ብሮድካስት ኔትዎርክ ዘገባ አመልክቷል፡፡  ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወደ አምቦ ያቀኑት ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑ ታውቋል፡፡

አዲስ ዘመን ታህሳስ 16/2011

በአስቴር ኤልያስ