የምክር ቤቱ የስንብት የቤት ስራዎች

10

ለአምስተኛው የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተያዘው የ2012 በጀት አመት ካለፉት አራት የበጀት አመታት የተለየ ነው። ምክር ቤቱ የበጀት አመቱን ስራውን ትናንት በተከፈተው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ የመጀመሪያ ስብሰባ ጀምሯል። በስብሰባው ላይ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ባስቀመጧቸው የስራ አቅጣጫዎች ላይ በመመስረት ስራውን ማከናወን ይ ጀምራል።

እንደሚታወቀው ሀገሪቱ በኢኮኖሚው እና በፖለቲካው መስኮች በርካታ ተግባራትን ለመስራት አቅዳለች። ህዝቡ በኑሮ ውድነት እና በዋጋ ግሽበት ተቸግሯል፤ ስራ አጥነት ሌላው ትልቅ ችግር ነው።በመንግስት በኩል እነዚህን ችግሮች ለመፍታት በአቅርቦት እና በምርታማነት ላይ በስፋት ለመስራት ታቅዷል። ስንዴ በሀገር ለማምረት በተለይ ለመስኖ ልማት ትኩረት የሚሰጥበት አመት እንደሚሆን ይጠበቃል። በዘይት ላይም ተመሳሳይ እርምጃ ለመውሰድ እየተሰራ ነው። በፕሬዚዳንቷ ንግግር እንደተመለከተውም መንግስት የምግብ ፍጆታዎችን በሰፊው ለማቅረብ ይንቀሳቀሳል።

ስራ አጥነትንም እንዲሁ በበጀት አመቱ ለ3 ሚሊዮን ዜጎች የስራ እድል በመፍጠር ለማስተንፈስ እንደሚሰራ ባለፈው በጀት አመት መጨረሻ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ማስታወቃቸው ይታወቃል። ለዚህም ዘንድሮ የሚከናወኑ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች በጠቅላላ የስኬታቸው መለኪያ እንዲሆን የሚጠበቀውም ምን ያህል የስራ እድል ፈጠሩ የሚለው ይሆናል።

ሀገሪቱ ለልማቷ ማሳለጫ የሚሆን የውጭ ምንዛሬ እጥረት አለባት። የውጭ ምንዛሬ ማግኛ ከሆኑት ምንጮች አንዱ የውጪ ንግድ መሆኑ ይታወቃል። ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን የዚህ ዘርፍ አፈጻጸም በጣም ዝቅተኛ ነው። ሌላው የውጭ ምንዛሬ ምንጭ የውጭ ብድር ነው። እሱም ቢሆን ባለፉት አመታት ከፍተኛ ብድር መወሰዱን ተከትሎ ሀገሪቱን ከፍተኛ ብድር ካላባቸው ሀገሮች ተርታ እንድትሰለፍ ያደረጋት በመሆኑ የሚጠበቀውን ያህል ብድር በማግኘት የውጭ ምንዛሬ ፍላጎቱን ለመመለስ ሳይቻል ቀርቷል። ሀገሪቱ አሁን የውጭ ምንዛሬ ከአበዳሪ ተቋማት ከማግኘት ይልቅ ብድር መክፈል ላይ በትኩረት እየሰራች ትገኛለች።

ከሀገሮች እና ከአንዳንድ ተቋማት ብድር ለማግኘት ፣የውጭ ባለሀብቶች በስፋት ከወትሮውም በተለየ መልኩ ወደ ሀገሪቱ እንዲገቡ በማድረግ እንዲሁም ከሀገሮች ጋር በመነጋገር ወለድ የሚቀንስበትን እንዲሁም የብድር ጊዜ የሚራዘምበትን መንገድ በመፈለግ በውጭ ምንዛሪ በኩል ያለባትን ጫና ለማቃለል በትኩረት እየሰራች ትገኛለች። ይህ ሁሉ የሚያመለክተው የውጭ ምንዛሬ ላይ በትኩረት መስራት ቀጣዩ አብይ ተግባር ሆኖ እንደሚቀጥል ነው።

የሀገሪቱን ኢኮኖሚ እድገት ዘላቂነት ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ያሉ የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታዎች በውጭ ምንዛሬ ግኝት፣ በስራ እድል ፈጠራ፣ በቴክኖሎጂና እውቀት ሽግግር ያስገኙት ፋይዳ መቃኘት ይኖርበታል። ግብርናውን በማዘመን እና በተለይም በቆላማ ቦታዎች የመስኖ ስንዴ ለማምረት መታቀዱ አንድ ትልቅ ስራ ሲሆን፣ አየር ላይ እንዳይቀር ክትትል ሊደረግበትና ሊደገፍም ይገባል። ኢኮኖሚው ችግር ውስጥ ያለበት ሁኔታ እንዳለ ሁሉ በግብር አሰባሰብና በመሳሰሉት ዘርፎች የመጡ ለውጦችን እንዲሰፉ ማድረግ ላይም ሊሰራ ይገባል። በግብር አሰባሰብ ላይ የመጣው ለውጥ በእርግጥም ትምህርት ሊቀሰምበት የሚገባ ነው።

በፖለቲካው መስክም እንዲሁ ይህ የበጀት አመት የለውጡን ዘላቂነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባሮች የሚከናወኑበት አመት እንደሚሆን ይጠበቃል። እንደሚታወቀው ለውጡ በርካታ ያልተጠበቁ ድሎች የተመዘገቡበት ነው። ይዟቸው የመጣው የዴሞክራሲ ፣ የፍትህ፣ የሰብአዊ መብት ጥበቃ መሻሻልን የመሳሰሉ ጭላንጭሎች ተቋማዊ መሆንን የሚጠይቁ መሆናቸውን ተከትሎ ባለፈው አንድ አመት ከዚህ አንጻር በርካታ ተግባሮች ተከናውነዋል። ለውጡን የሚሸከሙ እንዲሆኑ በሚል በበርካታ ህጎች ላይ ማሻሻያዎች ተደርገዋል። ለእዚህም የምርጫ ህጉን እና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ህጉን በአብነት መጥቀስ ይቻላል። ሌሎች በመንገድ ላይ የሚገኙ የህግ ማሻሻያዎችም አሉ። በእነዚህ እና በሌሎች ህጎች ላይም በትኩረት መስራት የዚህ በጀት አመት ተግባር ይሆናል።

የተሻሻሉት ህጎች ወደ ስራ መግባት አለመግባታቸውን፣ወደ ስራ ገብተው እያመጡ ያሉትንም ለውጥ መከታተል ያስፈልጋል። የለውጡ ተቋማዊነት አንዱ መገለጫም ይሄው ነውና በዚህ ላይ በመስራት የዜጎችን እና የሀገርን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይገባል።

በሀገራችን የዴሞክራሲ ምህዳር ጥበት ሳቢያ ሀገሪቱ ለተፎካካሪ ፓርቲዎች በሯን ጥርቅም አርጋ ዘግታ መቆየቷ ይታወሳል። ይሁንና ለውጡ ይህን የተከረቸመ በር እንዲከፈት በማድረግ ሀገሪቱ የተለያየ የፖለቲካ ሃሳብ የሚንጸባረቅባት እንድትሆን አድርጓል። ይሁንና የፖለቲካ ብዝሃነት በሀገሪቱ መንጸባረቁ ብቻውን ግብ ግብ አይደለም። በሀገሪቱ በሚደረጉ ምርጫዎች እነዚህ ፓርቲዎች በነጻነትና በዴሞክራሲያዊ አግባብ ተንቀሳቅሰው ህዝቡ የፈለገውን ፓርቲ የሚመርጥበት ሁኔታ እውን ሊሆን ይገባል። ለእዚህ ደግሞ ይህ አመት ታላቅ ስራ ተግባር የሚከናወንበት እንደሚሆን ይጠበቃል።

እንዳለፉት የምርጫ ዘመናት አይነት የይስሙላ የፖለቲካ ምህዳር ለሀገሪቱ አያስፈልግም። በመሆኑም ህዝቡ ይመራኛል የሚለውን ፓርቲ መምረጥ እንዲችል አስፈላጊው ሁሉ መደረግ ይኖርበታል። ተአማኒ የሆነ የምርጫ ቦርድ ፣ የፍትህ አካል አለመኖር ያለፉት ምርጫዎች ሁሉ መሰረታዊ ችግር እንደነበር ይታወቃል። መንግስት ከዚህ አኳያ የምርጫ ቦርዱን እና ጠቅላይ ፍርድ ቤቱን በአዲስ መልክ በማዋቀር ይህን ችግር የሚፈታ ስራ ከኃላፊዎች ምድባ አንስቶ በህዝብ አመኔታ የሚጣልባቸውን ኃላፊዎች በመመደብ ሰርቷል። እነዚህ ተቋማት በነጻነት ይንቀሳቀሳሉ ተብሎ ይጠበቃል። ይህም ስራ አያያዙ መልካም ቢሆንም ውጤቱ የሚታየው አንድም በዚህ በጀት አመት በሚደረገው አጠቃላይ ምርጫ ነውና በትኩረት መከታተልን ይጠይቃል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች በነጻነት ተንቀሳቅሰው ምርጫው በዴሞክራሲ መንገድ ተፈጽሞ ሀገሪቱ በፖለቲካ ምህዳር ጥበት ስትማቅቅ ከነበረበት ሁኔታ በምትወጣበት ሁኔታ ላይ መስራትም ትኩረትን የሚሻ ተግባር ነው። ባለፉት አመታት ብቅ ብቅ ብለው የደረቁ የዴሞክራሲ ምህዳር የመስፋት ምልክቶች ዘንድሮ እንዳይደገሙ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል።

ይህ በጀት አመት ከ2008 አንስቶ ሲተገበር የቆየው ሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ትግበራ የሚጠናቀቅበት መሆኑ ይታወቃል። ትልሙ በአብዛኛው የእቅዱን ያህል እየተፈጸመ ላለመሆኑ በግዙፍ ፕሮጀክቶች እና በውጪ ንግድ በኩል የሚታዩ አፈጻጸሞች ያመለክታሉ። በጣም በተወሰኑ ዘርፎች ካልሆነ በቀር ብዙ ርቀት የተሄደበት ሁኔታ እንደሌለ በተለያዩ ወቅቶች የቀርቡ ሪፖርቶችም ያመለክታሉ። ለእቅድ ዘመኑ የተያዙ ግቦች ከአሁን አንስቶ እየተፈተሹ በቀሪ ጊዜያት ጠንክሮ በመስራት ለውጥ በሚመጣባቸው ላይ ለውጥ ማምጣት ይጠበቃል። ለውጥ ያልመጣባቸውንም ገምግሞ ለቀጣይ ስራ ምቹ ሁኔታ መፍጠርም ይጠበቃል።

በ2007 ዓ.ም በተካሄደ አጠቃላይ ምርጫ ወደ ፓርላማው የመጡት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የአምስት ዓመት የስራ ዘመን የሚያበቃውም በዚሁ አመት መጨረሻ መሆኑ ይታወቃል። ፓርላማው በዚህ አምስተኛ አመት አምስተኛ የስራ ዘመኑ ብዙ ማከናወን የሚጠበቅበት ተግባር አለ።

እንደሚታወቀው ሀገሪቱ ለውጥ ውስጥ ትገኛለች። ለውጡ ደግሞ ፓርላማውን ጭምር እውነተኛውን ዴሞክራሲ ያጎናጸፈ ነው። የምክር ቤቱ አባላት በለውጡ ዋዜማና ከለውጡ ወዲህ ኃላፊነታቸውን በመወጣት በኩል በትኩረት እየሰሩ ናቸው። አንዳንድ ውሳኔዎቻቸው ፣ የድምጽ አሰጣጣቸው ፣ በውይይት ወቅት የሚያነሷቸው ሃሳቦች በእርግጥም በለውጡ ፓርላማው ከጥርስ ከሌለው አንበሳ ጥርስ ወዳለው እንደተሸጋገረ ያስመሰከረ ነው። ገና ከለውጡ ዋዜማ አንስቶ እንደቀድሞው ሁሉንም ነገር አሜን አሜን ብሎ መቀበሉን ወደ ማቆም ተሸጋግሯል።

መጋቢት 24 ቀን 2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው ትንሽ ቀደም ብሎ የፓርላማው አባላት መጠየቅ ፣ ያልመሰላቸውን የውሳኔ ሃሳብ በድምጻቸው መቃወም መጀመራቸው ይታወሳል። ይህንን ዘንድሮም አጠናክሮ በመቀጠል በህግ ማውጣት፣በክትትልና ግምገማ በኩል በትኩረት ሊሰራ ይገባል።

እንደማንኛውም የመጨረሻ ዘመኑ እንደሆነ ፓርላማ የሚያከናውናቸው በርካታ ተግባሮች እንዳሉ ሆነው፣ የዚህን በጀት አመት ስራውን ብቻ ሳይሆን የአምስት አመት የስራ ዘመኑን ሂሳብ የሚያወራርድበት አመት እንደመሆኑ ይህ የበጀት አመት ልዩ ስፍራ የሚሰጠው እንደሚሆን ይታመናል። በስራ ዘመኑ ሊሰሩ የታቀዱ ምን ያህል እንደተፈጸሙ እየተመለከተ መስሪያ ቤቶች በእቅዱ ትግበራ ያላቸው የመጨረሻ አመት ይሄ አመት ነውና በቀሪ ጊዜያት ማከናወን ያለባቸውን በትኩረት እንዲያከናውኑ ማድረግ ይኖርበታል። ፓርላማው እንደ ፓርላማ በኢኮኖሚው እና በፖለቲካው መስክ የሚጠበቁ ታላላቅ ተግባሮች መፈጸማቸውን መከታተል እና መገምገም ይጠበቅበታል።

የፓርላማው አባላት ባለፈው ክረምት እንዳለፉት ዓመታት ሙሉ የእረፍት ጊዜያቸውን በመረጣቸው ህዝብ አካባቢ ያሳለፉ አይመስለኝም። ሀገሪቱ እያራመደች ካለችው ለውጥ ጋር በተያያዘ መጽደቅ ያለባቸው አዋጆች በመኖራቸው ሳቢያ ወደ ሶስት ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ ስብሰባዎችን እየተጠሩ አዋጆችን አጽድቀዋል። አዋጆቹ በይደር የሚቀመጡ ስላልነበሩ ነው ይህ የሆነው። ከእነዚህም አንዱ አዋጅ የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ መሆኑ ይታወቃል።

ሀገሪቱ በለውጥ ጎዳና ላይ መሆኗን ተከትሎ በሁሉም መስክ የእነርሱን የነቃ ተሳትፎ የሚጠይቁ በርካታ ተግባሮች እንደመኖራቸው የምክር ቤቱ አባላት ዘንድሮም ብዙ የቤት ስራ ይጠብቃቸዋል። በተለይ በየአምስት ዓመቱ የሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫ ዘንድሮ የሚካሄድ እንደመሆኑ ስራቸው የገዘፈ ነው። መንግስት የዴሞክራሲ ምህዳርን ለማስፋት ፣ በሀገሪቱ የመድበለ ፓርቲ ስርአት እውን እንዲሆን እውነተኛ ምርጫ ለማካሄድ ከያዘው ቁርጠኛነት አኳያ ሲታይ የምክር ቤቱ አባላትም ኃላፊነት የዚያኑ ያህል ግዙፍ ነው። በአጠቃላይ ፓርላማው በዚህ ታሪክ ሊሰራበት በታቀደ ወሳኝ ዘመን ላይ ይገኛል። ስለሆነም ታሪክ ሰርቶ ቦታውን ለማስረከብ በትጋት መስራት ይኖርበታል እላለሁ። መልካም የስራ ዘመን !!

አዲስ ዘመን  መስከረም 27/2012

 ኃይሉ ሣህለድንግል