<>- በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ፋክልቲ መምህር ሙከሚል በድሩ

18

 ሀገር ውስጥ የባንክ ኢንዱስትሪው ከቅርብ አመታት ወዲህ በተደራሽነት፣በካፒታል አቅም፣ በትርፋማነት፣ በቁጠባ እና ብድር አገልግሎት ፈጣን ዕድገት አስመዝግቧል። በአሁኑ ወቅትም የተለያዩ ባንኮች እየተመሰረቱ ናቸው።

አዲስ ዘመን የባንኮቻችንን መበራከት፣ ወቅታዊ አቋማቸውን እንዲሁም ሌሎች መልካም እድሎችንና ስጋቶችን በሚመለከት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ፋክልቲ መምህር እና የሂጅራ ባንክ ፕሮጀክት ሃላፊና አደራጆች ምክትል ሰብሳቢ አቶ ሙከሚል በድሩ ጋር ቆይታ አድርጓል።

አዲስ ዘመን:- የአገሪቱ ባንኮች ወቅታዊ ቁመናና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንዴት? ይገለፃል

አቶ ሙከሚል:- የባንክ ኢንዱስትሪው እያደገ ከፍተኛ መነቃቃት እያሳየ ያለበት ወቅት ላይ ደርሷል። ባንኮቹ ግን በካፒታል ረገድ ብዙም አላደጉም። የሁሉም ባንኮች ካፒታል ሲደመር 85 ቢሊዮን ብር አካባቢ ነው። ኢንዱስትሪው በአጠቃላይ አንድ ትሪሊዮን ሀብት እያንቀሳቀስ ነው።

የእያንዳንዱን ባንክ የትርፍ መጠን ከተመለከትን ለውጡ በጣም ግዙፉ መሆኑንና አስደናቂ እምርታ እያሳየ ስለመሆኑ በቀላሉ መረዳት ይቻላል። ባንኮቹ የሰበሰቡት ተቀማጭ ሀብት /ዲፖዚት ሞቢላይዜሽን/ ከ400 /አራት መቶ / ቢሊዮን ብር ከፍ ማለቱን መገንዘብ ይቻላል። እነዚህን ለአብነት ወስደን ብንመለከት የፋይናንስ ዘርፉ መጠነ ሰፊ እምርታ ማስመዝገቡን መገንዘብ ይቻላል።

በአንድ አገር የባንኮች መበራከት በኢኮኖሚው ላይ የሚኖረው አስተዋፆኦ ከፍተኛ መሆኑ ግልፅ ነው። የባንኮቹ መበራከት ውድድር ይፈጥራል። ባንኮች ምን አይነት አገልግሎት መስጠት ቢንችል ነው ተወዳዳሪ የምንሆነው የሚለውን እንዲያስቡ ያስገድዳቸዋል። ይህ ደግሞ ሰዎች ካፒታላቸውን በቀላሉ እንዲያንቀሳቅሱ በማድረግ የኢኮኖሚውን ምህዋር ዙር ያፋጥነዋል።

የውጭ ምንዛሬን ከማስገኘት አንፃር በተለይ ህገ ወጥ በሆነ መልኩ የሚዘዋወረውን ገንዘብ ወደ ባንክ መደበኛ ፍሰት ለማስገባት እንዲሁም በስራ እድል ፈጠራም ረገድ የሚኖራቸው አበርክቶ ከፍተኛ ነው። በአጠቃላይ በአገሪቱ ኢኮኖሚው መነቃቃት ላይ የሚኖራቸው አስተዋጾኦ ዘርፈ ብዙ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ከቅርብ አመታት ወዲህ በባንክ ኢንዱስትሪው ለታየው መነቃቃት ምክንያቴ ምነድን ነው ይላሉ?

አቶ ሙከሚል፡- ከቅርብ አመታት ወዲህ የባንክ ኢንዱስትሪው እየተነቃቃ በአሁኑ ወቅትም ከሰባትና ስምንት የማያንሱ ባንኮች እየተቋቋሙ ናቸው። በተለይ በአሁኑ ወቅት እየታየ ላለው መነቃቃት በሀገሪቱ የመጣው ለውጥ እንደ ምክንያት ሊወሰድ ይችላል። ምክንያቱም በአንድ አገር ለውጡን ተከትሎ ኢኮኖሚ ይነቃቃል ተብሎ ስለሚታሰብ ባንኮች ይመሰረታሉ።

ሌላም መጥቀስ ይቻላል። እንደሚታወቀው፣ አሁን ላይ በሀገሪቱ የሚገኙት 16 ባንኮች ያላቸውን አፈፃጸምና ጥቅል ትርፋቸውን ብንመለከት በዚህ አመት ብቻ 32 ቢሊዮን ብር ማትረፍ ችለዋል። ይህን ከፍተኛ የትርፍ መጠን የሚመለከቱም ኢንዱስትሪው ውስጥ ተቀላቅለው ከትርፋማቱ ለመጋራት ፍላጎት ሊያድርባቸው ይችላል። ከመንግስት በውጪ የሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች በተለይ በባንክ ኢንዱስትሪው በመሳተፍ መዋእለ ነዋያቸውን ስራ ላይ እንዲያውሉ ፈቃድ መሰጠቱም ሌላው በምክንያትነት የሚጠቀስ ነው።

አዲስ ዘመን ፡- ባንኮቹ ከተደራሽነት አንጻር ያሉበትን ቁመናስ እንዴት ይመለከቱታል?

አቶ ሙከሚል፦ከጥናቶቹ መረዳት እንደሚቻለው በአማካይ የባንክ አገልግሎት ማግኘት የቻለው የማህበረሰብ ክፍል ሰላሳ በመቶው ብቻ ነው። ይህም ባንክ ለመጠቀም አቅም ያለው የማህበረሰብ ክፍል ታሳቢ ያደረገ ነው። ከዚህም የባንኮቻችን ተደራሽነት በጣም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ስለመሆኑ በቀላሉ ያመለክታል። ሌሎች አገራት 60 እና 70 በመቶ ደርሰዋል። ኬንያን ለዚህ በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል።

በመሆኑም በተደራሽነት ረገድ ባንኮቻችን መስራት የሚኖርባቸው በርካታ ስራዎች እንዳሉ መገንዘብ ግድ ይላል። አብዛኞቹ ባንኮች ቅርንጫፎቻቸውን ለመክፈት ቅድሚያ ትኩረት የሚሰጡት ትላልቅ ከተሞች ላይ ነው። አዲስ አበባ ላይ ደግሞ ይበልጥ ያበረክታሉ። የገጠሩን ማህበረሰብ አሁንም ቢሆን ተደራሽ የማድረግ ውስንነት ይታይባቸዋል።

በእርግጥ ባንኮች ተደራሽነታቸውን ለማስፋት የግድ ተጨማሪ ቅርንጫፎችን መክፈት አለባቸው ማለት አይደለም። በተለያዩ ቴክኖሎጂዎች ተደራሽ መሆን ይችላሉ። ይህም ቢሆን ብዙ የሚቀረውና የራሱ የሆነ ውስንነት የሚስተዋልበት ነው። በተለይ ተደራሽነትን በማስፋት ረገድ በመሰረተ ልማት አቅራቢ ተቋማት መካከል በተለይ የኢንተርኔት አገልግሎቶችና የኤሌክትሪክ አቅራቢ ተቋማት ከባንኮች ጋር አብሮ መጓዝ ሳይሆን መቅደም ይኖርባቸዋል። ፡

ተደራሽነት ለህዝብ ከመቅረብ ባለፈ በአገልግሎትም ይገለፃል። ይህም በብዛትና በጥራት ሊቃኝ ይችላል። በተለይ ባንኮቻችን በሚሰጡት አገልግሎት ስንመለከተው ብዙ እንደሚቀራቸው መገንዘብ እንችላለን።

አዲስ ዘመን፦ ባንኮቻችን ከዘመናዊነት ጋር ምን ያህል ተቀራርበዋል ይላሉ ?

አቶ ሙከሚል፦ የአገራችን ባንኮች ሌላኛው ትልቅ ክፍተት ዘመናዊ አለመሆን ላይ ይስተዋላል። የባንኮቻችን ዘመናዊ አሰራር እጅግ ደካማ ነው። ከዘመናዊነት መገለጫ አንዱ የሰዎች የአኗኗር ዘይቤ በተቀየረ ቁጥር ይህን ታሳቢ ያደረገና አብሮ የሚጓዝ የፋይናንስ አገልግሎት ማቅረብ ነው።

አገሪቱ ያለባት ከኢንተርኔት ጋር የተያያዘ መሰረተ ልማት ችግር እንደተጠበቀ ሆኖ ባንኮች ባላቸው አቅም በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት ለመስጠት መትጋት ሲገባቸው ወደኋላ የመጓዝ አዝማሚያ ይታይባቸዋል። አዲስ ዘመን፦ ባንኮቻችን የሚንቀሳቀሱትስ በብቁ ባለሙያዎች ነው ብለው ይገምታሉ?

አቶ ሙከሚል፦ አንድ መታወቅ የሚኖርበት ነገር ቢኖር የትኛውም ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀላሉ ገንዘብ የሚሰራ ከሆነ የሰው ሃይል ለማብቃትና ወደ ፊት አንድ እርምጃ ሄዶ ለማሰብ የራሱ የሆነ ፈተና አለው። የእኛ አገር ባንኮች የሰው ሃይልን በደንብ አብቅቶ ለቀጣይ ውጤታማነት መሰረት በመጣል ረገድ ውስንነት ይስተዋልባቸዋል።

ይህን ለመቀየር ብሄራዊ ባንክ በአመት እያንዳንዱ ባንክ ካለው የስራ ማስኬጃ በጀት ውስጥ ሁለት በመቶ ለሰው ሃይል ስልጠና እና አቅም ማጎልበቻ እንዲመድቡ ያስገድዳል። ይሁንና ባንኮቹ ውድድር ያለበት ኢንዱስትሪ ማድረግ የሚጠበቅበትን ያህል የሰው ሃይላቸውን ለማብቃት ጥረት ሲያደርጉ አይስተዋሉም።

የሚሰጡ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችም በተጠና እና ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ዘርፉ ምን አይነት ስልጠና ፣ ክህሎትና የአመለካከት ለውጥ ያስፈልገዋል የሚለውን በአግባቡ በመቃኘት የሚፈጸም አይደለም። ይህ በመሆኑም በተለይ በጣም ወሳኝ በምንላቸው የስራ ዘርፎች ላይ የሰው ሃይል ክፍተቱ እንደሚስተዋል በማጤን የሚከናወነው የማብቃት ስራ ደካማ መሆኑን መመልከት ይቻላል።

አዲስ ዘመን፦ ባንኮች ከተናጥል ጉዞ ይልቅ ውህደት ቢፈጥሩ ጠንካራ መሆን እንደሚቻላቸው የሚጠቁሙ አሉ፤ እርሶዎ ይህን እሳቤ እንዴት ይመለከቱታል ?

አቶ ሙከሚል፦ ይህ ትክክለኛ አስተያየት ነው። በተለይ በካፒታል መጠን፣ በደንበኛ ብዛት ዝቅ ያሉ ባንኮች ከተናጥል ይልቅ በትብብር መስራታቸው የሚያስገኝላቸው ብዙ ትሩፋት አለ። ካፒታላቸውን ከፋ ያደርግላቸዋል፤አቅምና የደንበኞቻቸውን ብዛትም ያሳድግላቸዋል፤ ይህ ደግሞ ለባንኩ እድገት ቁልፍ ነው።

የባንኮቹ መጣመር ለወጪ ቅነሳም ጉልህ ፋይዳ አለው። እንደሚታወቀው አሁን ላይ ሁለት የተለያዩ ባንኮች አንድ ሕንፃ ላይ ተከፍተው እንመለከታለን። ምናልባትም ጎን ለጎን ሊሆኑም ይችላሉ። ባንኮች ውህደት ቢፈፅሙ ግን አንድ ላይ አገልግሎት መስጠት ይቻላቸዋል። ይህ ደግሞ ከኪራይና ከሰው ሃይል ጀምሮ አጠቃላይ የስራ ማስኬጃ ወጪያቸውን በእጅጉ ይቀንስላቸዋል።

ይሁንና እንዲሁ ዝም ተብሎ አንድ ላይ ለመጣመር የሚል አካሄድም አግባብ አይደለም። በጋራ መጓዝ ያለባቸው በፍልስፍና፣ በቢዝነስ ሞዴል፣በስትራቴጂ የሚዛመዱ ባንኮች ናቸው። የተለያየ አሰራር የሚከተሉ ባንኮችን ጥምረት ፍጠሩ ማለትም ሁለቱም እንዲወድቁ ማድረግ ሊሆን ይችላል።

አዲስ ዘመን፡- ባንኮቻችን ከስያሜአቸው አንስቶ ብሔርና ሃይማኖት ዘመም እየሆኑ መጥተዋል የሚባለውንስ እንዴት ይመለከቱታል?

አቶ ሙከሚል፦ ባንክ ካፒታል ነው ፤እኔ እስከሚገኝ ካፒታል ብሄርም እምነትም የለውም። ይሁንና አንዳንድ ጊዜ እነዚህ ባንኮች ለምንድነው የብሄርን መስመር ይዘው የመጡት? ብሄር ተኮርስ ናቸው ወይ? የሚለውን መጠየቅ ያስፈልጋል። ባንኮች ብሄር ተኮር ለመሆናቸው መገለጫው ምንና እንዴት ነው? ስያሜአቸው ነው ብሄር ተኮር ያስባላቸው ወይንስ ባለሀብቶቹ? የሚሉት በሙሉ በአግባቡ መቃኘት ይኖርባቸዋል።

ይሁንና በእኔ አመለካከት ባንኮቹ ነፃ ሆነው መስራት ቢችሉ መልካም ነው። ምክንያቱም ተጠቃሚ የሚያደርጋቸው ራሳቸውን ነው። ለአብነት አንድ ባንክ የብሄር አባላትን ታሳቢ በማድረግ ቢከፈት ደንበኞቹ የተወሰኑ ሊሆኑ ይችላሉ። ይህ መሆኑ መጠቀም የሚቻልበትን ሰፊ አቅም የሚያሳጣበት ሁኔታ ይኖራል።

ከእምነት ጋር ተያይዘዋል የሚባለውም የአመለካከት ውስንነት የሚፈጥረው እንዳይሆን እሰጋለሁ። እነዚህ ባንኮች ለአንድ እምነት አገልግሎት ለመስጠት የተቋቋሙ ናቸው ወይ? እኔ ሲገባኝ ፣ዘርፉ ውስጥ እንዳለም ሰው እንዲህ አይነት አስተሳሰብ የለም፤ትክክልም አይደለም። የትኛውም የእምነት ተከታይ እነዚህን ባንኮች ማደራጀት ይችላል፤ መጠቀምም ሆነ ባለቤት መሆንም ይችላል። ምንም የሚከለክለው የለም። ይሁንና የአመለካከት ክፍተት ስላለ ከወለድ ነፃ ባንክ ሲባል የሙስሊም ብቻ አድርጎ የመመለከት ሁኔታ አለ። ይህ ግን ፈፅሞ የተሳሳተ አመለካከትና መታረም የሚገባው አመለካከት ነው።

አዲስ ዘመን:- የባንኮቻችን ስጋቶች ናቸው የሚሏቸው ካሉ ቢጠቅሱልን ?

አቶ ሙከሚል፦ የባንኮች ቁጥር እየጨመረ በመጣ ቁጥር ውድድሩም አብሮ ይጨምራል። የውድድሩ መጨመር ለማህበረሰቡ የሚሰጠው ጥቅም እንዳለ ሆኖ በባንኮች መካከል ተገቢ ያልሆነና ስርአት አልባ ፉክክር እንዲፈጠር ሊያደርግ ይችላል። ይህም ወደ አልሆነ መስመር ገብቶ ከፍተኛ ኪሳራ እንዳያስከትል ጥንቃቄ መደረግ አለበት።

ለአብነት ብድር ከመስጠት ጋር በተያያዘ ሊኖር የሚችለውን ስጋት እና አደጋ ከፍ ሊደርገው እንዲሁም የተበላሸ ብድር እንዲበዛ ሊያስገድድ ይችላል። ውድድር ውስጥ ሲገባ የብድር ማስያዣዎች የሚገመቱበት መንገድ እና የፕሮጀክቶች አዋጭነት ጥናት በማካሄድ ረገድ ሊደረጉ በሚገባቸው ጥንቃቄ የተሞላባቸው ስራዎች ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ሊያሳርፍ ይችላል። ይህ ደግሞ የህዝቡን ገንዘብ አደጋ ውስጥ መጣል ነው። በመሆኑንም የባንኮቹ የአደጋ ቅነሳ አሰራር በጣም በጥንቃቄ ሊከናወን ግድ ይላል።

በአሁኑ ወቅትም ከፕሬዚዳንት አንስቶ እስከ ታች ድረስ ከአንድ ባንክ ወደ ሌላ ባንክ የመዘዋወር ሁኔታ አለ። ባንኮቹ በተበራከቱ ቁጥር ባለሙያዎችን መቀማማት ሁኔታ ይፈጠራል። ይህም አንዳንድ ባንኮችን ሊያዳክምና ሊጎዳ እንዲሁም የአንደኛውን ባንክ መረጃ ለሌላኛው የመስጠት አዝማሚያም ሊፈጠር ይችላል። ይህም አጠቃላይ ዘርፉና ገበያው ላይ ጤናማ ያልሆነ ከባቢ እንዲፈጠር ያደርጋል።

ከዚህ ባሻገር አንድ ሕንፃ ላይ አገልግሎት የሚሰጡ ምናልባትም ጎን ለጎን ሃያ ከዚያ በላይ የባንክ ቅርንጫፎችን እንድንመለከትና ባልተገባ መልኩ ሃብት እንዲባክን ሊያደርግ ይችላል። በመሆኑም እነዚህን ስጋቶች መከላከል የባንኮቹ ሃላፊነት ብቻ ሳይሆን፣ እንደ አንድ አስተዳዳሪ አካል የብሄራዊ ባንክ ሚና መሆን አለበት።

አዲስ ዘመን ፡- ለቃለ ምልልሱ ላደረጉልን ትብብር በጣም እናመሰግናለን።

አቶ ሙከሚል፡- እኔም አመሰግናለሁ።

አዲስ ዘመን  መስከረም 27/2012

 ታምራት ተስፋዬ