የሟች እናቱን ቃል ለማክበር፤ ከኑሮ ጋር የተቆራኘ ትግል ልጅነት

14

ለሥራው አዲስ ቢሆንም ቀጣሪዎቹ ግን ፊት አልነሱትም። ሥራም ሰውም ይለመዳል ሲሉ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የሠራተኛ መዝናኛ ክበብን የተከራዩት ግለሰብ ይቀጥሩታል። እርሱም ሥራ ማግኘቱን እንጂ ስለደመወዙም አልተጨነቀም።

ዋናው ውሎ መግባቱ ነበር። በባህሪው ዝምተኛ፣ በአንደበቱ እሺ ማለትን የሚያዘወትር ነው። ሰዎችን አክባሪና ስለነገ አብዝቶ የሚጨነቅ፣ በውጣ ውረዶች ተፈትኖ የመጣ አሁንም ውጣውረዶችን በትዕግስትና በፅናት ለማለፍ የሚታትር ወጣት ነው። ኑሮ እንደ ገብስ ቆሎ ፈትጋ፤ እንዳሻት አመንዥካ ወደምትፈልገው ስፍራ ለመጣል ብትከጅልም እርሱ ግን አልተንበረከከላትም።

በላቸው ድሪባ ይባላል የ22 ዓመት ወጣት ሲሆን በወሎ ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዓመት የኮምፒዩተር ሳይንስ ተማሪ ነው። የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በተወለደበት ገርባ ጉራቻ ከታችኛው የትምህርት እርከን ጀምሮ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም እስከተቀላቀለበት ጊዜ ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ሲወጣ የመጣ የደረጃ ተማሪ ነው።

8ተኛ ክፍል ተፈትኖ 99ነጥብ4 ያስመዘገበ ሲሆን፤ 10ኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተና ሲፈተን 3ነጥብ75 ነው ያመጣው። በአሁኑ ወቅትም ቢሆን በትምህርቱ ታታሪ እና የአንደኛ ዓመት ውጤቱ 3ነጥብ96 አስመዝግቧል። በላቸው የተወለደው በሰሜን ሸዋ ዞን ፍቼ ከተማ ኩዩ ወረዳ ነው።

ከአንደኛ እስከ አራተኛ ክፍል ብርቲ በምትባል ትምህርት ቤት ነው የተማረው። ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱንም በዚያው አካባቢው በሚገኘው ገርባ ጉራቻ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው የቀሰመው።

የበላቸው አባት ቀደም ብለው አግብተው ልጆች ወልደዋል። የበላቸው እናት ለበላቸው አባት ሁለተኛ ሚስት ናቸው ማለት ነው። በላቸው ሁለተኛ ልጅ ሲሆን ታላቅ ወንድምና ሁለት ታናናሽ እህቶች አሉት።

የፈተና ጅማሮ

በላቸው አራተኛ ክፍል ተማሪ ሳለ እናቱ ወርሃ ጥቅምት ላይ አረፉ። በዚህን ጊዜ ነበር ከባዱ ፈተና እና የሕይወት መቃወስ የጀመረው። ትምህርቱን በሚገባ ለመማር አልቻለም። የአባቱ ወገኖች ብዙም እንዲማሩ አያበረታቱትም ነበር። ከስንቅ ማጣት እስከ ጭንቀት ተፈራረቁበት።

ታላቅ ወንድሙም ገርባጉራቻ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቆ ወደ 11ኛ ክፍል ቢዘዋወርም ትምህርቱን ሳይቀጥል ከተወለደበት አካባቢ ኮበለለ። በአሁኑ ወቅት ሐረር አካባቢ እንዳለ በስልክ ለበላቸው አሳውቋል፤ ግን በዓይን ከተያዩ አራት ዓመት ተቆጥረዋል። አባቱም በጤና መታወክ የተነሳ በአንድ ወቅት ከቤት እንደወጡ አልተመለሱም፤ እርሱም የት እንዳሉ ሊያውቅ አልቻለም።

ታናናሽ እህቶቹ ደግሞ ወደ አዲስ አበባ ኮብልው ሰው ቤት መሥራት ጀምረው ነበር። አንደኛዋ እህቱ ሰው ቤት እየሠራች ስምንተኛ ክፍል ደርሳለች። ተቀጥራ የጀበና ቡና እያፈላች ነው የምትተዳደረው። ማርታ የምትባለው ሌላኛዋ እህቱ ደግሞ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የሠራተኞች መዝናኛ ክበብ ውስጥ በእቃ አጣቢነት ተቀጥራ እያደር ምግብ አብሳይ ‹‹ሼፍ›› ሆናለች።

በላቸው በርካታ ፈተናዎችን እያለፈ የመጣውና ቀዳዳዎቹን እየደፈነ ከዛሬ ላይ የደረሰው በእህቶቹ ጥንካሬና እገዛ እንደሆነ ይናገራል። በእርግጥ አንደኛ ደረጃ ተማሪ ሳለ ራሄል አማረ የምትባል አስተማሪው ምክርና የማበረታቻ መንገዶችን ግን መቼም አይዘነጋውም። የአስተማሪዎቹን ገንቢ ምክር ሁሌም ያስታውሳል።

የእናት አደራ «ተማር ልጄ»

እናታቸው በህይወት ሳሉ በተደጋጋሚ ልጆቻቸውን አንድ ነገር ይመክሩ ነበር። በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ‹‹ልጆቼ እኔ ባልማርም እናንተ ተምራችሁ የቀለም ቀንድ እንድትሆኑ እፈልጋለሁ›› ይሏቸው ነበር። ወዲህ ግን የአባቴ ቤተሰቦች መሬት አርሰውና ጎልጉለው ጎበዝ አራሽ ገበሬ እንዲሆኑላቸው፣ የእናት አባታቸውን ደጅ እንዲያስከብሩላቸውና በዚያው አግብተው ወልደው ከብደው ዘመደብዙ እንዲሰኙ ይፈልጋሉ። ታዲያ በላቸው በዚህ ሃሳብ አልተስማማም። የእናቱ ቃል እንደ ብረት ከብዶታል፤ እንደ ማዕበል ደረስ መለስ እያለ ያስቸግረዋል እንደ ተራራ ገዝፎ ታይቶታል። በብረቱ ፈተና ውስጥ ሆኖም ሕይወቱን ሊመራ፤ የእናቱን የአደራ ቃል ሊያከብር ወደደ። የተናገሩት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ ይሉት ብሂል የእናቱን  ቃል ለማክበር ወሰነ። እየተፈተነ ቢሆንም ህይወቱን ሲመራ ቆየ። ምንም እንኳን እናቱ የአራተኛ ክፍል ተማሪ እያለ ቢሞቱም፤ ቃላቸውን ለማክበር የማይወጣው ዳገት የማይወርደው ቁልቁለት አልነበረም።

በላቸው እናቱ ከሞቱ ጀምሮ በርካታ ሥራዎችን ሲሠራ ነበር። እንደ ህፃን ከአንድ ስፍራ ወደሌላ ስፍራ እቃ ሲላላክ ቆይቷል። ለረጅም ዓመታት በ‹‹ሊስትሮ›› ወይንም ጫማ ማፅዳት ሥራ ላይ ጊዜውን አሳልፏል። እንዲሁም ጭቃ ማቡካት፣ እንጨት መፍለጥና ሌሎች የጉልበት ሥራዎችን እየከወነ ሕይወቱን መርቷል። አሁንም ሕይወቱን ለማቃናት ብዙ ይለፋል።

በእርግጥ ዩኒቨርሲቲ ከገባ ጀምሮ ሁለት እህቶቹ እየተደጋገፉ እስከ 400 ብር የሚልኩለት ጊዜ አለ። ያችን ለሻይ እና ለፎቶ ኮፒ እያብቃቃ ይጠቀማል። ‹‹እህቶቼ ሳይኖራቸው ለእኔ ይጨነቃሉ፤ ሳይለብሱ ለእኔ መልበስ ማማር ይጨነቃሉ። የእናቴ ምትክ ናቸው›› ሲል ያመስግናቸዋል። አንዳንድ መልካም ሰዎችም እገዛ ያደርጉለታል። ታዲያ ይህን ሲያይ ደግሞ ብርታቱ ይመጣል፤ ደረቱን ነፋ አድርጎ ስለነገ ያስባል ስለ አገሩ ይጨነቃል።

 ሁሉን በሆዴ

ይህ ሰው እንቶ ፈንቶ የበዛባትን ዓለም አይፈልጋትም። ምንም ችግር ቢገጥመውም ለማንም መናገር አይፈልግም። በርካታ ውጣ ውረዶችን እንዳለፈና አሁንም ፈተናዎች እንደተጋረጡበት ይገነዘባል። ለጓደኞቹ የሚነግረው የተለየ ነገር የለም። በሁሉም መንገድ ከማንም የተለየሁ አይደለሁም ብሎ ለራሱ አሳምኖታል። ለሰው ቢናገር እንኳን የሚጠቋቆሙበት እንጂ

 የቁስሉን የህመም ደረጃ የሚረዳው አላገኘም። ብዙ ጊዜም ዝምታ የሚውጠው ከዚህ የተነሳ እንደሆነ ይናገራል። መቸገሩን አይገልጽም፤ እናቱ በሕይወት እንደሌሉ አባቱም ይሙቱ ይኑሩ ሥፍራቸው ከወደየት እንደሆነ አይገልጽም። ሁሉ ነገር በሆዴ ብሎ የሚኖር ሰው ነው።

እቅድ

በላቸው ሩቅ አሳቢ ነው። ዛሬ በችግርና ከባድ ፈተና ውስጥ ቢሆንም ነገ የተቃኑ መንገዶች እንደሚኖሩ የጸና እምነት አለው። በጥረትና በትጋት ውስጥ የማይለወጥ ነገር የለም የሚል አቋም አለው። ‹‹ፈጣሪ ከረዳኝ ከዩኒቨርሲቲ እስከምወጣ ድረስ አንድ አዲስ አፕሊኬሽን መስራት እፈልጋለሁ›› ይላል። ከዚህ በተረፈ

 በልጅነቱ ለመማር ከሚያስበው የጤና ትምህርት ጋር በቀጥታ መዋሃድ ስላልቻለ ለጤናው የሚያግዙ ‹‹አፕሊኬሽኖችንና ሶፍትዌሮችን›› ማሳደግና መፍጠር ዋንኛ ህልሙ ነው። ለአገሩ ኢትዮጵያ ርባና ያላቸው ተግባራትን ለማከናወንም ከእቅዶቹ ውስጥ በቀዳሚ ሥፍራ አስቀምጧል በላቸው።

መልዕክት

የሰው ልጅ ዓለምን የሚያሸንፈው በብሄሩ ወይንም በጎሳው ሳይሆን በሳይንስ ነው ይላል። እኛን አስተሳሰባችን እንጂ ብሄራችን ወይንም ጎሳችን አንዱን ሰው ከሌላው ሰው አያበላልጠንም። በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ዓለም አቀፍ እውቀት ለመሸመት የገባ ሰው መንደርተኛ ሆኖ አገርን ወደኋላ መጎተት የለበትም።

ዩኒቨርሲቲዎች ከመስጊዶችና ቤተክርስቲያኖች በላይ ሆነው የእምነት ልዩነት የሚሰበክበት ሥፍራ ሆነዋል። ሌላው ቀርቶ የተማሪዎች ህብረት አባላት ወይንም የተማሪዎች ፕሬዚዳንት ምርጫ ሲካሄዱ እምነትና ብሄርን መሠረት እያደረጉ መጥተዋል። ይህ አሳፋሪና ለኢትዮጵያም ዕድገት የማይበጅ የዴሞክራሲ ባህልንም የሚያቀጭጭ ነው። እነዚህ ሊታረሙ ይገባል የሚል ነው ሃሳቤ።

በሌላ ጎኑ ደግሞ በርካታ ከተሞች የሱሰኞችና ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ሆነዋል። ጎዳናው መተላለፊያ ሳይሆን የድሆች መዋያና ማደሪያ ሆኗል። ይህን ለማስቀረት የሥራ ባህል ማጠናከርና ጠንካራ ህግ ያስፈልጋል ይላል።

በተረፈ እዚህ አገር ችግረኞችን ለመርዳትና ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሻገር የግድ ሃብታም መሆን አያስፈልግም። ችግሩ የገንዘብ ብቻ ሳይሆን የአስተሳሰብ አሊያም የሥነ ልቦና መቃወስ ይሆናል። ስለዚህ ሰዎችን ስናግዛቸው ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሻገርና ኢትዮጵያን ለማሳደግ መሆን አለበት። በተረፈ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሠራተኞች ብሎም ክበቡን በኪራይ የያዙት ግለሰቦች ለእኔ ያደረጉት የሞራል ግንባታና የቁሳቁስ ብሎም የገንዘብ ድጋፍ የበለጠ ሞራሌን አነሳስቶታል። ምስጋናዬ ከፍ ያለ ነው።

ክበቡን በኪራይ የያዙት ግለሰብ በየወሩ 300 ብር እንደሚሰጡኝ ነግረውኛል። የመጀመሪያውን አሁን ሰጥተውኛል። ይህ ለእኔ ብዙ ችግሮቼን ይቀርፋል። ችግሬን እኔና ፈጣሪ ብቻ ነን የምናውቀው። ሌላው ቀርቶ ከሁለት እህቶቼ ጋር ሆነን የከረምኩበት ቤት በየወሩ 1ሺ500 ብር መክፈል እንዴት እንደሚቸግር እገነዘባለሁ።

እህቶቼ ለእኔ በማሰባቸው እንድከፍል አይፈልጉም። በትምህርት ወቅት እንዳልቸገር ገንዘብ አታውጣ ይሉኛል። ብቻ የእነዚህን ሰዎች ውለታ መክፈል የምችለውም ለሌሎች አርዓያ ሆኜ ስገኝ ነው። ስለዚህ ምስጋናዬ ከልብ ነው፤ ከልብም አጠናለሁ ከልብም እሠራለሁ። አንድ ቀን የእኔም ታሪክ ተቀይሮ የሌሎች ታሪክ እንዲቀየርም እጥራለሁ። የእናቴን ቃል ለማክበር ስል የማልፈነቅለው ድንጋይ የለም ይላል አይረቴው በላቸው።

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 24/2012

 ክፍለዮሐንስ አንበርብር