የእንጨት ቁሳቁስ እርሻ

7

ዛፎች ለማገዶ፣ ለቤት መስሪያ፣ ለቤትና የቤሮ ዕቃዎች ማምረቻ፣ወዘተ እንጠቀምባቸዋለን። ፀሐይ አላለውስ ሲለን ጥላቸው ከሐሩር ያስጥለናል፤ማረፊያችንም ናቸው፡፡ የደን ውጤቶች የተለያዩ የቤት ቁሳቁሶች ይሠራባቸዋል፡፡ ወንበር፣ አልጋ፣ መደርደሪያና የመሳሰሉት ማለት ነው፡፡ እነዚህ ውጤቶች የሚገኙት ግን ዛፎች ተጨፍጭፈው ነው።

ሰሞኑን ከወደ ከእንግሊዝ የሰማነው ዜና ግን ለየት ያለ ነው፡፡ ዛፎች እየተጨፈጨፉ ሳይሆን እንደ ወንበር፣ ጠረጴዛ፣ ወዘተ ያሉት እቃዎች የሚመረቱት ዛፎቹ እየታረቁ ወንበር፣ ጠረጴዛ፣ ወዘተ እንዲወጣቸው ተደርገው እንዲያድጉ በማድረግ ነው። በሀገራችን እንጨት በማረቅ ከዘራ፣ የመጥረቢያ ዛቢያ፣ ሞፈር፣ ወዘተ እንደሚሰራው አይነት ማለት ነው፡፡ የዚህ ልዩነቱ የማረቁ ሥራ የሚፈፀመው ዛፎች ከተቆረጡ በኋላ መሆኑ ላይ ነው፡፡

የዘላቂነት ዘይቤን ከፍተኛ ደረጃ ላይ ለማድረስ ጥረት የሚያደርጉት የእንግላድ ነዋሪዎቹ ጋቪንና አላይስ ሙንሮ የተባሉ ጥንዶች በዚህ አይነቱ የደን ልማት ላይ በመሰማራት የእንጨት እቃዎችን ማምረት ጀምረዋል፡፡ ጥንዶቹ ዛፎቹን ሁሌም ያርቃሉ፡፡ በመጨረሻም የተለያዩ የእንጨት ቁሳቁስ ያመርታሉ፡፡

ጣምራዎቹ ደርቢይሽሬ በተባለው አካባቢ ለእዚህ አገልግሎት የሚውል የቤትና የቤሮ የእንጨት እቃዎች እርሻ አላቸው፡፡ በዚህ እርሻም 250 ወንበሮችን እና 100 የመብራት ፋናዎችና 50 ጠረጴዛዎችን እያረቁ በማሳደግ ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህን በማድረግም ለቁስቁስ ማምረት ሥራ በሚል ግዙፍ ዛፎች ለመቁረጥ የሚደረገውን ሂደት ትክክል እንዳልሆነ ጣምራዎቹ ይተቻሉ፡፡

“ዛፎችን ለ50 ዓመታት በማሳደግ ቀጥሎም ወደ ትናንሽ አካላት በመቆራረጥ ከመጠቀም ይልቅ ሃሳባችን ዛፎችን በቀጥታ በሚፈልጉት ቅርፅ እያረቁ ማሳደግ ነው ”ሲሉ ጋቪን ይናገራል። ወደ እዚህ ሥራ ለመግባት ያነሳሳውን ምክንያት ሲገልጽም የልጅነት ጊዜውን ያስታውሳል፡፡ በልጅነቱ የተመለከተው ወንበር የሚመስለው የቦንሳ ዛፍ በአይነ ህሊናው ከተፍ ይላል፡፡ ጋቪን የተወለደው አከርካሪው ጎብጦ መሆኑን በመጥቀስ፣ በልጅነቱ ለዓመታት ጀርባውን ለማስተካከል የብረት ክፈፍ አድርጎ ይንቀሳቀስ እንደነበር ያስታውሳል።

ህክምናውን ሲያደርግለት የነበረውን የህክምና ቡድን የሚያደንቀው ጋቪን፣ በወቅቱ ሀኪሞቹ፣ ነርሶቹ፣ ወዘተ ያደረጉለት የነበረው እንክብካቤ አሁን በሚሰራው ዛፎችን እያረቁ የተለያዩ የእንጨት ቁሳቁስ ማምረት ሥራ ትልቅ ትምህርት እንደሆነው ይገልፃል፡፡

የ44ዓመቱ ጎልማሳ ሙከራውን የጀመረው እ.ኤ.አ 2006 በመካከለኛው ኢንግላንድ ፒክ ወረዳ ባለው አነስተኛ መሬት ላይ የተከላቸውን ዛፎች ወንበሮች እንዲወጣቸው እያረቀ በማሳደግ ነው። እ.ኤ.አ በ2012 ከአላይስ ሙንሮ ጋር በትዳር ከተጣመረ በኋላ ይህን የእንጨት ቁሳቁስ ዛፎችን እያረቁ በማሳደግ የማምረቱን ሥራ የሙሉ ሰዓት ሥራ ወደ ማድረግ መሸጋገራቸውን ዘገባው ይጠቁማል፡፡

ሥራው ፈታኝ መሆኑንም ጥንዶቹ ይገልፃሉ። የመጀሪመሪያው የደን ልማት ሥራቸው በድርቅ ተመትቶባቸው ልማቱ የእንስሳትና የአይጦች ሲሳይ ሆኖባቸው እንደነበርም ያስታውሳሉ፡፡

ይህን ችግር ለመፍታት የተለያዩ የመውጫ መንገዶችን ያማትራሉ፡፡ ዛፎች ምንም አይነት የእድገት ችግር ሳይገጥማቸው እነሱ ለሚፈልጉት የቁሳቁስ ሥራ እንዲደርሱ ለማድረግ የሚያስችላቸውን ሥራም ይጀምራሉ፡፡ ዛፎቹን ሲያርቁም እነሱ በሚፈልጉት አቅጣጫ ብቻ ሳይሆን ለዛፎቹ የሚመቸውንና የማይጎዱበትን አቅጣጫ በመጠቀምም ማረቃቸውን ይጀምራሉ፡፡ ይህም መንገድ ከቀደመው የተሻለ ሆኖ ያገኙታል፡፡

ይህ ሥራ ግን በቀላል ጊዜ እና ወጪ የሚከናወን አይደለም፡፡ የሥራው አድካሚነት ቁሳቁሱ የሚሸጡበት ዋጋ በቀላሉ የማይቀመስ አይነት እንዲሆን አርጎታል፡፡ በዚህ አይነት ሁኔታ የሚያድጉ ወንበሮች 10 ሺ ፓውንድ ወይም 12 ሺ 480 ዶላር እንደሚያወጡ ዘገባው ያመለክታል፡፡ የመብራት ማስቀመጫው ከ900 እስከ 2ሺ 300 ፓውንድ ወይም ከ1 ነጥብ 120 እስከ 2 ነጥብ 870 ዶላር እንዲሁም ጠረጴዛዎች ደግሞ ከ2ሺ 500 እስከ 12 ሺ 500 ድረስ እንደሚሸጡም ያብራራሉ፡፡

በእዚህ አይነት መንገድ የሚያድገው ወንበር ከስድስት እስከ ዘጠኝ ዓመት ሊወስድበት እንደሚችል ዘገባው ያመለከተ ሲሆን፣ ወንበሩ ደርቆ ለገበያ ለመቅረብ አንድ ዓመት እንደሚወስድበትም ይጠቁማል፡፡ ጥንዶቹ ያቋቋሙት ኩባንያ ከፍተኛ ምርት የሚጠብቀው እ.ኤ.አ በ2030 ነው፡፡

‹‹ በደን ላይ ጉዳት እንደምናደርስ እናውቃለን፤ ይህንንም በሚገባ እየተገነዘብን መጥተናል፡፡ › ያለው ጋቪይን፣ እነሱ ከዚህ በተቃራኒው እየሠሩ መሆናቸውን ይገልፃል፡፡ እኛ እየተጠቀምንበት ያለው መንገድ እንደ ድንጋይ ዘመኑ ያለ ቴክኖሎጂ ነው›› ሲል አብራርቶ፣ በደን ላይ ጉዳት እያስከተሉ አለመሆናቸውን ይጠቁማል፡፡

ጥንታውያን ሮማኖች፣ ቻይናዎች እና ጃፓኖች ዛፎችን በሚፈልጉት መልኩ ለተለያየ አገልግሎት እንዲውሉ ለማድረግ የማረቅ ሥራዎችን ይሠሩ እንደነበር በማስታወስም፣ ጋቪን እና አሊሴ በፈረንጆች እ.ኤ.አ 2022 ጀምሮ በየዓመቱ ማምረት ውስጥ እንደሚገቡ ተስፋ አድርገዋል።

በረጅም ጊዜ ምርምራቸው የሚተገብሩበት የእርሻ ቦታ ለመግዛት ፍላጎቱ አላቸው፡፡ ዕውቀታቸውን በምክር አገልግሎት ማሠራጨትም ይፈልጋሉ። በመካከለኛ ጊዜ እቅዳቸውም አዳዲስ የምግብ ገበታዎችን ለማምረት አቅደዋል፡፡ ዛፍ ተክሎ እነዚህን ቁሳቁስ ለማግኘት ግን ቢያንስ አስር ዓመት ሊወሰድ እንደሚችል ነው የተጠቆመው፡፡

አዲስ ዘመን  መስከረም 27/2012

 ሀይለማርያም ወንድሙ