ከጀግናው አትሌት ለሕዝብ የተበረከተ ታሪካዊ ሜዳሊያ

8

እኤአ 2016 በሪዮ ኦሊምፒክ የመዝጊያ ውድድር በነበረው የወንዶች ማራቶን ላይ አንድ ክስተት ተፈጠረ። አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ ቀለማት ያለውን የመሮጫ ልብስ ያጠለቀ አትሌት ታላቁን ውድድር በሁለተኛነት ለመፈፀም ሲቃረብ እጆቹን በማጣመር ያሳየው የተቃውሞ ምልክት የዓለም መነጋገሪያ ሆነ።

አትሌቱ ከድርጊቱ በኃላ በወቅቱ የዓለም ህዝብ በኢትዮጵያ መንግስት እየተፈጸመ ያለውን ኢ ሰብዓዊ ድርጊት ለማመልከት እንደሆነ ለመገናኛ ብዙሃን አስታወቀ። አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ በኦሊምፒክ መድረክ ላይ ፖለቲካን ማንጸባረቁ ዋጋ እንደሚያስከፍለው ቢረዳም ከማድረግ ወደ ኋላ አላለም። ፈይሳ ድርጊቱን በመፈጸሙ አገር ቤት የሚገኙት ሚስትና ልጁ እንዲሁም ቤተሰቦቹ ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚገቡ ቢያውቅም ህዝብን ነጻ ለማውጣት በሚችለው ነገር ተቃውሞ በማሰማት ከፊት ለፊቱ የሚጠብቀው አደጋን መጋፈጡ በብዙዎች ዘንድ ጀግና አሰኝቶታል።

ፈይሳ የዓለም ህዝብ አይንና ጆሮውን ባደረገበት የኦሊምፒክ መድረክ ላይ በአገሪቱ በነበረው ፖለቲካ ላይ ተቃውሞ ማሰማቱ ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጠው ያደረገ ነበር። ፈይሳ ከድሉ ማግስትም ቢሆን የህዝብ ድምጽ መሆኑን አላቆመም ነበር። በተለያዩ አለም አቀፍ መድረኮች ላይ በመገኘት በወቅቱ በኢትዮጵያ መንግስት እየተፈጸሙ የሚገኙ ኢሰባዊ ድርጊቶችን ለማጋለጥ ተንቀሳቅሷል።

በተለይ በካፒታል ሂል ዋሽንግተን ዲሲ በሰጣቸው መግለጫዎች ላይ ሪፐብሊካን የሆኑት ሴናተር ክሪስ ስሚዝ ጎኑ ቆመው አሜሪካ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ አቋም እንድትወሰድ መጠየቁ ትልቅ መነጋገሪያ አድርጎት ነበር። ሴናተር ክሪስ ስሚዝ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር በአፍሪካ የዓለም ጤና መጠበቅ እና ሰብዓዊ መብት መከበር ጉዳዮች ላይ የሚሰሩ ዓለም አቀፍ ተቋማትን የሚከታተል ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሲሆኑ፤ የቴክሳሱ የሪፐብሊካን ሴናተር አለን ግሪን እና የኮላራዶው የሪፐብሊካን ሴናተር ማይ ኮፍማን አጋሮች በማድረግ ያደረግ የነበረው እንቅስቃሴ የዓለምን ትኩረት በመሳብ ደረጃ ትልቅ ሚና ነበረው።

በኢትዮጵያ ምድር አለም ለምስክርነት የቆመለትን ፖለቲካዊ ለውጥ በስተመጨረሻ ለማምጣት በቅቷል። በኢትዮጵያ ከመጣው ለውጥ ፊት ለፊት በመሆን እንደ አትሌት ፈይሳ ለሊሳ ሁሉ በተለያዩ አለም አገራት የተበታተኑ ኢትዮጵያዊያን፤ እንዲሁም በአገር ውስጥ በአራቱም አቅጣጫ የነበሩት ለውጥ ፈላጊዎቸ ራሳቸውን ለመስዋዕትነት ያቀረቡበት ነበር።

የለውጡን ፍሬ ተከትሎም አርበኛው አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ ወደ እናት አገሩ ኢትዮጵያ ለመምጣት በቅቷል። የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም ፈይሳን ቤተመንግስት ድረስ በመጋበዝ እውቅናን ሰጥተውታል። ፈይሳ እኤአ በ2016 በሪዮ ኦሊምፒክ የማራቶን ውድድር ሁለተኛ ሆኖ ያጠናቀቀበትን የብር ሜዳሊያ በኢትዮጵያ ለውጥ ለማምጣት ለተሰዉ ሰማዓታት መታሰቢያነት እንደሚሰጥ ቃል መግባቱ ይታወሳል። አርበኛው አትሌት ቃል በገባው መሰረትም መስከረም 22 ቀን 2012 ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ በተዘጋጀው ርክክብ ስነ ስርዓት ላይ በመገኘት ታሪካዊውን ሜዳሊያ አስረክቧል። የህዝብን ለውጥ በመሻት ግንባራቸውንና ደረታቸውን ለመስጠት ሳይሰስቱ ለታገሉት ሁሉ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ሜዳሊያውን በክበር ለአትሌት ታሪኩ በቀለና እጅጋየሁ ዲባባ አስረክቧል። ከእነርሱም ለኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በክብር አበርክተዋል።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ታሪካዊ በሆነው ሜዳሊያ ርክክብ መድረክ ላይ «አትሌት ፈይሳ ችግራችንን በአለም አቀፍ ህዝብ ዘንድ ለማድረስ የታገለ ጀግና ነው» ሲሉም ታላቅ አርበኛ መሆኑን መስክረውለታል። የተረከቡት ሜዳሊያና ሌሎች መታሰቢያዎች፣ ጥናት የሚከናወንበት ማዕከል እንደሚገነባም ምክትል ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በበኩላቸው «በኦሊምፒክ ሜዳ ላይ ሌሎች ደስታቸውን ሲገልፁ አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ የኢትዮጵያን ህዝብ ችግርና ሀዘን ሲገልጽ ቆይቷል። አትሌቱ በአለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ ድምፃችን እንዲሰማ አድርጓል። በዚህም ትግሉ በመፋፋም በሀገሪቱ ለውጥ መጥቷል» ሲሉም ፈይሳ ከለውጡ መምጣት ጀርባ ያለውን ሚና ተናገረዋል። «አትሌት ፈይሳን ብናመሰግነው ቢያንስበት እንጂ አይበዛበትም» በማለት ኢንጂነር ታከለ ለወጣቱ አርበኛ አክብሮትና ምስጋናቸውንም ቸረውታል።

አዲስ ዘመን ቅዳሜ መስከረም 24/2012

ዳንኤል ዘነበ