የአደባባይ በዓላቶቻችን ብሔራዊ ሀብትም

9

ኩራትም ናቸው

 “አገሬ ኢትዮጵያ – ተራራሽ አየሩ፤

ፏፏቴሽ ይወርዳል በየሸንተረሩ፤

ልምላሜሽ ማማሩ” … ከሚል የአገርን ውበት ከሚያደንቁ የግጥም ስንኞችና ውብ ዜማ አንስቶ ፡-

‹‹ አገር ማለት ልጄ፣ አገር ማለት፤

እንዳይመስልሽ የተወለድሽበት ቦታ፣ የተወለድሽበት አፈር፤

እትብትሽ የተቀበረበት፣ ቀድመሽ የተነፈሽው አየር፤

ብቻ እንዳይመስልሽ፤

አገር ረቂቅ ነው ቃሉ፤

አገር ውስብስብ ነው ውሉ … ›› እስከሚለው የአገርን ምንነት በጥልቀት እስከሚያስረዳው የዶክተር በድሉ ዋቅጅራ ግጥም ድረስ አገርን በተለያየ መንገድ ለመግለፅ የተኬደው ርቀት ኢትዮጵያውያን የሚወዷትን አገራቸውን ከፍ ከፍ ለማድረግ የተጠቀሙበት የመግለጫ ቃላቸውን ጥንካሬ ያሳያል።

ኢትዮጵያውያን አገራቸው በወራሪ ጠላት ስትደፈር በብሔርና በሃይማኖት ሳይለያዩ አጥንታቸውን ከስክሰው፣ ደማቸውን አፍስሰውና የሕይወት ዋጋ ከፍለው ጠላቶቻቸውን አሳፍረው መመለሳቸው በመላው ዓለም የሚታወቅ አኩሪ ገድላቸው ነው። አገሪቱ ያላትን የዚህን አኩሪ ገድል ያህል በሥልጣኔም ቀደምት ለመሆኗ አመላካች የሆኑ ታሪካዊ ቅርሶች ባለቤት መሆኗ በብዙዎች ዘንድ የተመሰከረ ነው።

ከሚዳሰሱት ታሪካዊ ቅርሶች ባሻገር የዜጎቿ ባህላዊ እሴቶች የሆኑ በማይዳሰስ የታሪክ ቅርስነት የተመዘገቡና እንዲመዘገቡ ጥረት እየተደረገላቸው ያሉ ውብ ክብረ በዓላት ተጠቃሽ ሲሆኑ፤ ክብረ በዓላቱ ደማቅና ተናፋቂ፤ እንዲሁም እጅግ በርካታ ቁጥር ያለው የህብረተሰብ ክፍል የሚሳተፍባቸው መሆናቸው ለተመልካች ማራኪ ሆነው የብዙዎችን ቀልብ ስበዋል። ይህ በመሆኑም የአገሪቱን የክብረ በዓላት ቀናት እየጠበቁ ከመላው ዓለም በኢትዮጵያ ተሰባስበው በበዓል የሚታደሙ በብዙ ሺዎች ይቆጠራሉ።

በተለይም በአሁኑ ወቅት አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል በክብረ በዓላት ላይ በስፋት መካፈሉ ለበዓሉ ድምቀት ከመሆን ባለፈ ከፍተኛ የገቢ ምንጭ እየሆነ ይገኛል። በርካታ የበዓል ተሳታፊዎች መኖራቸው ለገበያ አመቺ መሆኑን የተረዱት ወገኖቻችን ወቅቱ የሚጠይቀውን የገበያና የሰዎች ፍላጎት በመከተል አልባሳትን የእጅና የራስ ላይ ጌጦችን፣ እንዲሁም የአንገት ስካርፎችንና ሰንደቅ ዓላማዎችን በማዘጋጀት የገቢ ምንጫቸውን ሲያዳብሩ ማየት ምንኛ ያስደስታል።

ለረጅም ዘመናት ስናከብር ያሳለፍናቸው በዓላት በቅርብ ዓመታት እንዳሳለፍናቸው በብልህነት የተጠቀምንባቸው እንዳልሆኑ፤ ይልቁንም ለመጪዎቹ ክብረ በዓላት ከወዲሁ እየተዘጋጀን ለራሳችንም ደምቀን፣ አብረውን ሊታደሙ የሚመጡትም እንደ እኛው እንዲደምቁ፣ ገቢያችን እንዲያድግና ብሔራዊ ኩራታችንም ከፍ እንዲል ብሔራዊ ሀብቶቻችንን መጠበቅ የሁላችንም ኃላፊነት ይሁን።

እንደባህልና ቱሪዝም እንዲሁም እንደ የሥራ ዕድል ፈጠራ ማስተባበሪያ ያሉ ተቋማትም ብልህ አስቀድሞ ይዘጋጃል እንደሚባለው በቀጣይ ከሚከበሩ በዓላት አገርና ህዝብ ብዙ እንዲያተርፉና የአደባባይ በዓላቶቻችን ራትም ኩራትም እንዲሆኑ በልዩ ትኩረት ሊሠሩበት ይገባል!

አዲስ ዘመን መስከረም 28/2012