«የባቡር ፕሮጀክቱ በጀት የለውም»- አቶ ሙሉቀን አሰፋ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንዚት አገልግሎት የኦፕሬሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ

7

ዘመናዊ የባቡር ትራንስፖርት እ.አ.አ በ1820 ዓ.ም በእንግሊዝ አገር መጀመሩን መረጃዎች ያመላክታሉ። በባቡር ትራንስፖርት ከመቶ ዓመት በላይ ያስቆጠረ ታሪክ ያላት ኢትዮጵያም ባቡሩ ከመጀመሩ በፊት በ18ኛው ክፍለ ዘመን በጅቡቲ ወደብ በኩል ለውጭ ገበያ በየዓመቱ 12 ሺህ ቶን የሚሆን ሸቀጥ ታቀርብ ነበር። ሸቀጡን ወደ ወደብ ለማድረስም 50 ሺህ ግመሎችን ትጠቀም እንደነበርና ከሰባት ወራት በላይ ጉዞ ይፈጅ እንደነበር መዛግብት ያሳያሉ።

ይህንን ችግር ለመቅረፍ በወቅቱ አገሪቱን ያስተዳደሩ የነበሩት አጼ ምኒልክ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎትን ለመጀመር ከሌሎች አገራት ጋር በመደራደር ሥራውን አስጀምረዋል። የመጀመሪያ የሆነው የኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር 784 ኪሎ ሜር ርዝመት የነበረው ሲሆን ከአዲስ አበባ ተነስቶ በሐረር፣ ድሬዳዋን አቋርጦ ጅቡቲ የሚዘልቅ ነበር።

የባቡር መንገዱ ግንባታ 20 ዓመታትን ፈጅቶ በ1911 ዓ.ም ሥራ የጀመረ ሲሆን የኢትዮጵያ የባቡር ቴክኖሎጂም በኢትዮ-ጅቡቲ መስመር ብቻ ተወስኖ ለዘመናት መቆየቱ ይታወቃል። ባቡሩ ለሁለቱ አገራት የኢኮኖሚና የንግድ ትስስር ማደግ አስተዋፅኦ ሲያበረክት የቆየ ቢሆንም አገልግሎት መስጠት ካቆመ ዓመታት ተቆጥረዋል።

ከእነዚህ ረጅም ዓመታት የባቡር ታሪክ በኋላ የአገሪቱን ብሎም የመዲናዋን የትራንስፖርት አገልግሎት ማዘመን የሚያስችል የቀላል ባቡር መሰረተ ልማት ግንባታ በወርሃ ግንቦት 2004 ዓ.ም በአዲስ አበባ በይፋ ተጀምሯል። እስከ አሁንም በርካታ የከተማዋን ነዋሪዎች ከቦታ ቦታ በማንቀሳቀስ የበኩሉን እየተወጣ ይገኛል። እኛም አሁን በሥራ ላይ ያለው የከተማ ቀላል ባቡር የአገልግሎት አሰጣጥ እንዲሁም በሥራው ላይ ያሉ ችግሮችና እነሱን ለመቅረፍ በተወሰዱ እርምጃዎች ዙሪያ ከአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንዚት የኦፕሬሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ ከአቶ ሙሉቀን አሰፋ ጋር ቆይታ አድርገናል።

አዲስ ዘመን ፦ የከተማ ቀላል ባቡር ፕሮጀክቱ አሁን ያለበት ቁመና እንዴት ይገለጻል? በተለይ ከአገልግሎት ሽፋን፣ከተጠቃሚ ቁጥር፣አገልግሎት ጥራት ወዘተ አንጻር)

አቶ ሙሉቀን፦ የባቡር ትራንስፖርት ቁመና መለከያው ደህንነት፣ተደራሽነት፣በሰዓት መድረስ ናቸው። የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት ትራንዚት እስከ አሁን ድረስ በዘርፉ በተፈጠረ ክፍተት የተፈጠረ አደጋ የለም፡፡ በዚህ መሠረትም የደህንነት ስጋት የለበትም ማለት ነው። ሆኖም ባቡሩ ሥራውን ከጀመረ ጊዜ ጀምሮ ግን የሦስት ሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡ ይህም የተፈጠረው አጥር ዘለው በመግባታቸውና የባቡር አሽከርካሪዎቹም ባቡሩን ለማቆም በማይችሉበት ፍጥነት ላይ ስለነበሩ የተከሰተ አደጋ ነው።

ሌላው ባቡሩ ኃይል በመቆራረጥና መንገድ ላይ ካሉ ተሽከርካሪዎች አጥር ጥሰው በመግባታቸው ምክንያት ወደ 380 ጊዜ የባቡር መሠረተ ልማቱ ላይ አደጋ ተፈጥሯል። ከዚህ በተረፈ ግን ይህ ነው የሚባል አደጋ ስላላደረሰ በደህንነት መመዘኛ የተሻለ ነው።

ከተደራሽነት አንጻር ስናየው ደግሞ መጀመሪያ አገልግሎቱን ስንጀምር በስድስት ደቂቃ በኋላም በ20 ደቂቃ ባቡሮች ይመላለሳሉ ብለን ነበር፤ አሁን ላይ ግን የደረስንበት ወደ 10 ደቂቃ ነው። ይህም የሆነው በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ነው። ይህ ደግሞ ሲጀመር ከተነሳበት አንጻር በጣም ትልቅ ውጤት ነው።

አሁን ላይ ስታዲየም ላይ የተሰቀለ መረጃ ሰጪ ቴሌቪዥን አለ ይህ የሚቀጥለው ባቡር በስንት ደቂቃ ልዩነት እንደሚመጣ የጠራ መረጃን ይሰጣል፤ ሆኖም ሰዎች ተስፋ ስለሚቆርጡና እውነት ስለማይመስላቸው ነው እንጂ ትክክለኛ መረጃ ሰጪ ነው።

አዲስ ዘመን ፦ ግን እኮ መጀመሪያ ላይ ባቡሩ ወደ ሥራ ሲገባ በየስድስት ደቂቃው ይመጣል ነበር የተባለው?

አቶ ሙሉቀን፦ መሰረተ ልማቱ ይህንን ያህል አቅም አለውና ዛሬ ላይ ደግሞ በዚህ ደረጃ እጠቀማለሁ ማለት የተለያዩ ናቸው። መግለጫው በየስድስት ደቂቃው ይመጣል ብሎ ከሆነ መጀመሪያውንም ስህተት ነው። ግን በየስድስት ደቂቃው መሄድ ይችላል ወይ? ከሆነ አዎ ይችላል ይህንንም ባለፉት ስድስት ወራት ሞክረነው አረጋግጠናል።

ስድስት ደቂቃን በትክክል ለመሄድ ግን መሟላት ያለባቸው ነገሮች አሉ፤ አንደኛው ስድስት ደቂቃ ባደረግን መጠን የባቡሮቹ ፍጥነትና በየጣቢያው የሚደርሱበት ደቂቃ እጅግ በጣም ፈጣንና መቆሚያቸውም በጣም የተቀራረበ ነው የሚሆነው ይህ ሲሆን ደግሞ ከመኪናና ከሰዎች ጋር በፍጹም መገናኘት የለባቸውም። አሁን ባለው ሁኔታ በስድስት ደቂቃ ይምጡ ቢባል አንዱ ባቡር መኪና ወይም ሰው ላሳልፍ ብሎ ከቆመ ከኋላው የሚደረደሩት ይበዛሉ፡፡ በዚያን ምክንያት ደግሞ ሰዓቱም ይዛባል ስምሪቱንም መቆጣጠር በጣም ከባድ ነው የሚሆነው።

ሆኖም እነዚህን ስጋቶች በማስወገድና የባቡሮቹን ቁጥር በመጨመር ስድስት ደቂቃን ተግባራዊ ማድረግ ይቻላል።

አዲስ ዘመን ፦ አሁን ላይ የምልልስ ጊዜውን ወደ 10 ደቂቃ ማሻሻል የተቻለው የባቡሮቹን ቁጥር ጨምራችሁ ነው ወይስ ሌላ ምክንያት አለው?

አቶ ሙሉቀን፦ ሁለት ምክንያቶች አሉ፤ አንዱ የባቡር ቁጥር መጨመር ሲሆን ሌላው ደግሞ የአሽከርካሪ ቁጥር ነው። የመጀመሪያው ሥራ ስንጀምር ከቻይናውያኑ በቀጥታ ሥልጠና በወሰዱ 136 አሽከርካሪዎች ነበር፤ እነሱን ባለው የፈረቃ አሰራር መሰረት ብናሰራ ኖሮ ቁጥራቸው አይበቃም፣ ዛሬ የደረስንበት መሻሻል ላይም አንደርስም ነበር። ሆኖም ተጨማሪ አሽከርካሪዎች እንደሚያስፈልጉን በማመን ቀጥረን ለአንድ ዓመት ከስምንት ወራት ሥልጠና ወሰዱ፤ ባለፈው ዓመት ታኅሣሥ ወር ላይ የመጀመሪያውን የማሽከርከር ስራ በራሳችን በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች እየታገዙ ጀመሩ ማለት ነው። ይህ ደግሞ የአገልግሎት አሰጣጡንም ለማሻሻል አግዟል።

አዲስ ዘመን ፦ በተደራሽነት በኩልስ ያለውን ሁኔታ እንዴት ይገልጹታል?

አቶ ሙሉቀን፦ በኃይል እጥረት ምክንያት ሊያቆሙ የሚችሉበት ሁኔታዎች አሉ፤ በዚህ ጊዜ በአንድ ጣቢያ ላይ ቆመን በስልክ ልውውጥ ብቻ የባቡር ስምሪቱን ለመቆጣጠር የምንገደድበት ሁኔታም ይፈጠራል። ሌላው ባቡሩ ሙሉ በሙሉ ኃይል ሲያጣ መንቀሳቀስ ስለማይችል በዚህ ጊዜ የሚፈጠር የተደራሽነት ችግር ይስተዋላል። እነዚህን ሁኔታዎች አምናና ካቻምና ድግግሞሹ ቀንሷል ሆኖም አሁንም ውስንነቱ እንዳለ ነው። ይህንን ለማሻሻል ከአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ቢሮ ጋር አንዳንድ ምልክቶችን መትከልና የማሻሻያ ሥራዎችን በባቡር መሠረተ ልማቶች ላይ የመስራት ፣የአደጋ ቦታዎችን የመለየት ተግባራት እየተከናወኑ ነው። በቀጣይም ይህንን ሁኔታ ለማስተካከል በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ከመገናኛ ብዙኃን ጋር በመስራትና ኅብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲኖረው በማድረግ ችግሩን ለማቃለል እየተሰራ ነው።

በሌላ በኩልም ከኃይል አቅራቢው ተቋም ጋር የኃይል አቅርቦቱ እንዳይስተጓጎል እየሰራን ያለነው ነገሮች አሉ፤ በዚህም የተበላሹ ገመዶችን መቀየር የሚቻልበትንና ሌሎችን ሂደቶችን በመሄድ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።

ባቡር ብልሽት ለተደራሽነቱ ያለው ተጽዕኖ ከፍተኛ እንደመሆኑ ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ችግር ሆኖ የቆየው የመለዋወጫ ዕቃ እጥረት ነበር፡፡ ይህንንም በጣም በረጅም ድርድር የ3 ሚሊዮን ዶላር ዕቃዎች አሁን እየገቡ ነው። ቢሆንም በቂ አይደለም። በዘላቂነት ግን የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባም ባደረጉት ጉብኝት ቃል የገቡት ነገር ስላለ እነሱን ማድረግ ከተቻለ ቁመናውን ማስተካከል ይቻላል። ዘርፉን ጠቅለል አድርገን ስናየው ግን ባለፉት ከነበሩት የአገልግሎት አሰጣጥ የተሻለ ሁኔታ አለ ማለት ይቻላል።

አዲስ ዘመን፦ የምክትል ከንቲባውን ጉብኝት ካነሱ አይቀር በጉብኝቱ ወቅት ምን ዓይነት ቃሎች ተገቡላችሁ ምን ያህሎቹስ ተፈጻሚ ሆኑ?

አቶ ሙሉቀን ፦ እርሳቸው ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በተለይም በከተማው የትራንስፖርት ዘርፍ ላይ እየተሰሩ ያሉ ብዙ ጥሩ ነገሮች አሉ፤ ከዚህ በፊት የነበሩት የሥራ ኃላፊዎች ምናልባትም ለምርቃት ካልሆነ በቀር አይመጡም ነበር። እርሳቸው በአካል ተገኝተው ያሉትን ችግሮች ተረድተው እኛም ለወደፊት ሊሻሻሉ የሚገቡ ነገሮችን አስቀምጠን ነው የተለያየነው።

በእኛ በኩል ከቀረቡ ሀሳቦች መካከል የባቡር ትራንስፖርቱ ቀጣይነት እንዲኖረው ከተፈለገ በተለይም በመለዋወጫ በኩል የሚከሰቱ እጥረቶችን መፍታት፣አቅርቦትን መጨመር፣ባቡሩ አሁን ካለበት የአስር ደቂቃ የምልልስ ጊዜ በታች ለማድረግ ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ጋር መስተካከል ያለባቸው የመኪናና የእግረኛ ማቋረጫዎችን መስራትና ተጨማሪ ባቡሮች እንዲገዙ የሚሉ ናቸው።

አዲስ ዘመን፦ የባቡር ትራንስፖርቱ አገልግሎት መስጠት ከጀመረበት ከ 2008 ዓ.ም ጀምሮ በምን ያህል ደረጃ የትራንስፖርት ችግሩን ፈትቷል ማለት ይቻላል?

አቶ ሙሉቀን፦ ይህ አንጻራዊ ነው ፤ እስከ አሁን ድረስም በምድር ባቡር በኩል የተሰራ ጥናት የለም ፤ ሆኖም ከተቋማችን መረጃ እየወሰዱ አንዳንድ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሚሰሯቸው ጥናቶች አሉ። በዚህ የተገኘው ውጤት በመስመሩ ላይ የትራንስፖርት አቅርቦት እንዲጨምር አድርጓል፤ ሆኖም ግን በቂ አይደለም። ወደፊት ግን የጠራ መረጃ እንዲኖር ለማድረግ ከአዲስ አበባ ትራንስፖርት ማስተባበሪያ ቢሮ ጋር በመሆን መስመሩ ከላይ ያለውን ነገር እንዴት ማጥናት ይቻላል? ለወደፊትስ ከሌሎች የትራንስፖርት አማራጮች ጋር ማስተሳሰር ይቻላል? የሚለውን ለመስራት በዝግጅት ላይ ነው።

አሁን ባለው ሁኔታ ግን አውቶቡሱም፣ታክሲውም ባቡሩም በአንድ መስመር ነው የሚንጋጉት፤ ይህንን ማሻሻል የሚቻለው ደግሞ መጀመሪያ የባቡሩን ቁመና በደንብ ካስተካከልን በኋላ ሌሎቹን የትራንስፖርት አማራጮች ወደሌላ አካባቢዎች እንዲለወጡ ማድረግ ይቻላል።

አሁን ባለው ሁኔታ ግን ባቡሩ በቀን ከ 1 መቶ 20 ሺ ሰው በላይ ያመላልሳል፤ ግን የምንሰጠው አገልግሎት ምን ያህል ለተጠቃሚው ምቹ ነው በምንልበት ጊዜ አሁንም ይቀረናል።

ሌላው በከተማ ውስጥ ያለው የትራፊክ መጨናነቅ ይታወቃል፤ ባቡሮች ግን በተባለው ሰዓት አንድን ሰው ይዘው ወደሚፈለገው ቦታ ማድረስ ይችላሉ። የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከመቶ ሰላሳ ሚሊዮን በላይ ሰው አመላልሰናል፤ ባለፈው ዓመት ብቻ ደግሞ 40 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎችን አገልግሎቱን አግኝተዋል።

ይህንን ስናደርግ የተጠቀምነው አንድ ሊትር ነዳጅ የለም፤ በውሃ በመነጨ የኤሌክትሪክ ኃይል እንጂ፤ ይህ ደግሞ ልቀት፣የሚበክል ድምጽም የለውም፤ ይህንን ሁሉ ሰው ስናመላለስ የተፈጠረውን አደጋም ቀደም ብዬ ጠቅሸዋለሁ። ሌላውና ትልቁ ጥቅም ሰጠ የምንለው ደግሞ ከከተማው ራቅ ያለ ቦታ ላይ ያሉ ሰዎችን ሳይቆራርጥ በአንድ መስመር ወደ ከተማ ማስገባቱ ነው። ከዚህ አንጻር የታለመለትን ግብ መትቷል።

አዲስ ዘመን ፦ አሁን ላይ የተለያየ የነበረው የአገልግሎት ታሪፍ አንድ ወጥ ተደርጓል፤ ይህ ለምን አስፈለገ? ያመጣው ለውጥስ እንዴት ይታያል?

አቶ ሙሉቀን፦ ቀድሞ ባለሁለት ብር ሆነው አጫጭር መስመር የሚሄዱ ባቡሮች ስለነበሩ አብዛኛውን ሰው በር ላይ ወይም መውረድ የሚያመቻቸው ቦታ ላይ በመቆም ባቡሩ ባይጨናነቅ እንኳን ወደ ውስጥ ለመግባት በጣም አስቸጋሪ ነበር፤ ይህንን አጭር ትኬት ካስወገደን በኋላ ሁኔታው በጣም ተቀይሯል።

በሌላ በኩል ትኬቱ ወጥ መሆኑ ተሳፋሪዎች በየጣቢያው እየወረዱ ተደጋጋሚ ትኬት ከመግዛት ያድናል፤ ሌላው ለአንድ ትኬት ሻጭ ስድስት ዓይነት ትኬት የምንሰጥበትን አሰራር ከማስቀረቱም በላይ ተቋሙም በዚህ ምክንያት ወረፋ እንዳይኖር በማለት በአንድ ትኬት መሸጫ ውስጥ ብዙ ሠራተኞችን በማስቀመጥ ለአላስፈላጊ ወጪ የመዳረግ ሁኔታው ተወግዷል፤ ከዚህ ባለፈም በቁጥጥር ሥራው ላይም መሻሻል እንዲኖር አድርጓል።

ከተጠቃሚ አንጻር ደግሞ ባለ ስድስት ብር ትኬት መግዛት የነበረበት ሰው አሁን የአራት ብር ትኬት ገዝቶ ነው የሚሄደው፤ባለ አራት ብር ትኬት ገዝቶ 14 ጣቢያዎችን ብቻ ይሄድ የነበረው አሁን 22 ጣቢያዎችን መሄድ ችሏል፤ ባለ ሁለት ብሩ ላይ ብቻ ነው አሁን ልዩነት የተፈጠረው፤ እኛ እነሱን የምናበረታታው የተለያዩ አማራጮችን እንዲጠቀሙ በእግራቸው እንዲራመዱ እንዲሁም በጣም ረጅም የሆነ ርቀትን ለሚጓዙ ሰዎች ቦታ እንዲለቁ ነው።

ብዙ ጊዜ በባቡር ውስጥ በተሳፋሪና በተቆጣጣሪ መካከል አለመግባባቶች ይነሳሉ፤ ይህ ደግሞ ሁሉም አጭበርባሪ ሆነው ሳይሆን አንዳንዶቹ ማንበብና መጻፍ ባለመቻላቸው፣በዕድሜ የገፉ በመሆናቸው፣ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በመምጣት ለከተማው እንግዳ በመሆናቸውና የትኬት ቁጥራቸውን ባለማወቅ በሁለት ብር ቆርጠው ጣቢያዎችን መቁጠር ስለማይችሉ ከተቆጣጣሪዎች ጋር ጸብ ይፈጠራል።

አዲስ ዘመን፦ እዚህ ላይ ተቋሙ ትኬቶች ሁሉ በተመሳሳይ ዋጋ ይሸጡ ከማለት ባለፈ ዘመናዊ አሠራሮችን ለመጀመር የያዘው ዕቅድ የለም?

አቶ ሙሉቀን፦ አለው፤ ወደፊት የባቡር ትራንስፖርቱ የተጠናከረ ደረጃ ላይ ሲደርስ ከከተማው ትራንስፖርት አገልግሎቶች ጋር በማጣጣም የክፍያ ሥርዓቱን ለማዘመን በከተማ አስተዳደሩ የተያዘ እቅድ አለ። በዚህም የትኬት ዓይነቶችን ለአዛውንት፣ለተማሪዎች እንዲሁም በተለያየ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች እያልን እንለያያለን፤ ከዚያም በተጨማሪ የ24 ሰዓት ትኬት የማዘጋጀት ሀሳብ አለን።

አሁን በተወሰደው የታሪፍ ማሻሻያ እንኳን ከጠዋትና ማታ በስተቀር በባቡሩ ውስጥ የነበረው መጨናነቅ በጣም ቀንሷል። ይህንንም ለማቃለል አሁን የገቡልንን መለዋወጫዎች በመጠቀም ባቡሮችን በመጠገን ወደ ሥራ የምናስገባበት ሁኔታ ይኖራል።

አዲስ ዘመን፦ እዚህ ላይ ግን ባቡሩ የጭነት ልክ አለው? ምናልባት ሁላችንም መረጃው ስለሌለን ግልጽ ቢደረግ?

አቶ ሙሉቀን፦ የጭነት ልክ አለው፤ በዚህም ከሥራ ሰዓት ውጪ 285 በሥራ መግቢያና መውጪያ ሰዓት 317 ሰዎችን ነው የሚጭነው። ባቡሮቻችን ውስጥም ይህንን ልክ የሚያመላክት መሣሪያ አለ። ባቡሩ ከተባለው ሰው በላይ በሚጭንበት ወቅት ለአሽከርካሪው ምልክት ስለሚታይ ባቡሩን አያንቀሳቅስም፤ ይህ 317 ሰው በነጠላዋ ባቡር ነው ሁለቱ አንድ ላይ ታስረው ሲመጡ ቁጥሩ ወደ 634 ከፍ ይላል፤ እነዚህ ሰዎች ደግሞ በአንድ ጊዜ ሲወርዱ መንገድ ላይ ምን ያህል መጨናነቅ እንደሚያመጣ እንረዳለን ከዚህ አንጻርም ሰው ባቡሩ ልክ የሌለው ሊመስላቸው ይችላል።

አዲስ ዘመን፦ የባቡር ትራንስፖርቱ ምን ያህል በጀት ተመድቦለት ነበር ወደ ሥራ የገባው? አሁን ያጋጠመው የበጀት እጥረት መነሻው ምንድን ነው?

አቶ ሙሉቀን፦ ባቡሩ ሥራ ከጀመረ ጀምሮ ምንም ግልጽ የሆነ በጀት የለውም። የምድር ባቡር ከፌዴራል መንግሥት ከሚያገኘው በጀት ላይ ቀንሶ ይሰጠዋል እንጂ እራሱን የሚያስተዳድርበት በጀት የለውም። አሁን ላይ ግን የበጀት መጠየቂያ ሰነድ አዘጋጅተን አስገብተናል ይጸድቃል ብለን እናስባለን።

የትኛውም ዓይነት የከተማ ትራንስፖርት አንደኛ መሠረተ ልማቱ የሚሰራው በፌዴራል መንግሥትና በከተማ መስተዳድሩ በጋራ ወጪ ነው፤ በሌላ በኩል ግን ስናየው የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጠው በሁለትና አራት ብር ነው፤ እነዚህን ለቅሞ ደግሞ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚገቡትን መለዋወጫዎች መግዛትም ሆነ በጀት አድርጎ መጠቀም አይቻልም። በመሆኑም ሥራው አትራፊ አይደለም ማለት ነው። ግን የከተማው ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንዲሳለጥና ሰዎች ወደሚፈልጉት ቦታ እንዲንቀሳቀሱ 16 ሰዓት ይሰራል። የበጀት እጥረት አለብን፣ ሌላው የውጭ ምንዛሪ ችግርም አለ። ይህንን ማስተካከል ቢቻል ጥሩ ነገር ይመጣል ብዬ አስባለሁ።

አዲስ ዘመን፦ ከዚህ አንጻር ግን እየተሰጠው ያለው ትኩረት በቂ አይደለም ለማለት ነው?

አቶ ሙሉቀን፦ በእኛም በኩል ያለው ክፍተት አንዳለ ሆኖ፤ ኅብረተሰቡና የሥራ ኃላፊዎች ላይ ስለ ጥቅሙ ያላቸው ግንዛቤ አናሳ ነው፤ በእርግጥ እኛም እንዲገባቸው የሰራነው ሥራ ብዙ አይደለም ።

ሌላው ከበፊቱም ጀምሮ በባቡሩ ላይ የተጋነኑ ዘገባዎች ለምሳሌ በቀን በአንድ መስመር 60ሺ ሰዎችን እናጓጉዛለን፣በየስድስት ደቂቃው እንመላለሳለን እንዲሁም ሌሎች ብዙ መረጃዎች ነበርና እነዚህ ነገሮች ኅብረተሰቡ ከፍ ያለ አገልግሎት እንዲጠብቅ አድርገዋል። እዚህ ላይ ግን ለሁሉም ግልጽ እንዲሆን የምፈልገው በባቡር ታሪክ ከ15 ደቂቃ ወደ 10 ደቂቃ የምልልስ ጊዜን ማሳጠር ማለት እጅግ በጣም ትልቅ ውጤት ነው።

አዲስ ዘመን፦ የባቡር መሠረተ ልማቱ ከወጣበት የገንዘብ ኢንቨስትመንት አንጻር በተገቢው ሁኔታ ጥቅም ሰጥቷል፤የወጣበትንም ወጪ መልሷል ማለት ይቻላል?

አቶ ሙሉቀን፦ መንግሥት የባቡር መሰረተ ልማትን የሚገነባው 30 እና 40 ዓመት ከዚያም በላይ ለመጠቀም ነው፤ ሌላው ባቡር ልዩ ባህሪው በተወሰነች ቦታ ብዙ ሰዎችን ማመላለስ መቻሉ ነው። ባለፈው ዓመት 40 ሚሊዮን ሰዎችን ስናጓጉዝ ከነዳጅ አንጻር ለአገሪቱ የወጣ ምንም ወጪ የለም። ግን የዘርፉ መጥፎ ጎን መለዋወጫዎችን ከውጭ መግዛት በመሆኑ አሁን መፍትሔው የባቡር ቴክኖሎጂን አገራዊ ማድረግ ነው። ይህንን ለማድረግ የሚያስችል 1ሺ 3 መቶ የሰለጠነ የሰው ኃይል አለን። ከዚህ በፊት የኦፕሬሽን ኮንትራት እንፈርም ነበር፤ አሁን ግን በአገር ውስጥ ባለሙያዎች ተክተናል። ግንባታና ማማከር ላይም በተደራጀ መልክ ካምፓኒዎች ባይወስዱም የተበታተነ የሰው ኃይል አለን። እኔ እነዚህን እንደ መልካም ዕድል ነውና የማያቸው ባቡሩም ተገቢውን ጥቅም ሰጥቷል የወጣበትንም ወጪ መልሷል እላለሁ። እዚህ ላይ ግን ጥያቄው ያወጣችሁትን ገንዘብ በብር እየመለሳችሁ ነወይ? ከሆነ በፍጹም አይመለስም ።

አዲስ ዘመን፦ አገልግሎቱ ሲጀመር የባቡሩን እንቅስቃሴ የመምራት ሥራ ያከናውኑ የነበሩ የውጭ አገር ባለሙያዎችን በኢትዮጵያውያን የመተካት ሥራ ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

አቶ ሙሉቀን፦ ከዛሬ ዓመት በፊት ጀምሮ የባቡሩን ሥራ ሙሉ በሙሉ የሚያንቀሳቅሱት ኢትዮጵያውያን ነበሩ። ይህ ማለት ግን ከፍተኛ የሆነ እውቀትን የሚጠይቁ እንዲሁም በአምራቹ ኩባንያ ብቻ ሊመለሱ የሚችሉ ችግሮችን በእነሱ ቴክኒሻኖች አናሰራም ማለት አይደለም። ምክንያቱም ለእኛ የማይፈቀድልን የባለቤትነት ጥያቄዎች ስላሉ ።

አዲስ ዘመን፦ ከዚህ ቀደም በሠራተኞች የጥቅማ ጥቅም ጥያቄ ምክንያት የተቋሙ ስም ይነሳ ነበርና በምን ደረጃ ተፈታ? አሁን ያለበት ሁኔታስ ምን ይመስላል?

አቶ ሙሉቀን፦ ከዚህ በፊት የነበረው ችግር ሠራተኞቹ ሠራተኛ ተብለው የተቀጠሩ ቢሆንም ተማሪዎች ነበሩ፤ እናም ሠራተኛ ተብለን ስለተቀጠርን ብዙ ጥቅማ ጥቅም እናግኝ የሚል ጥያቄ ነበራቸው ሆኖም ተቋሙ ይህንን ማድረግ አልቻለም። ከዚያም በኋላ ስልጠናቸውን አጠናቀው ወደ ሥራ ሲገቡም በወቅቱ እኛ ጋር በተፈጠረ ችግር ከተማሪነታቸው የተለየ ጥቅም ልንሰጣቸው አልቻልንም፤ በዚያም ቅሬታ አነሱ፤ በሂደት ተቋሙ ከመሠረታዊ የሠራተኛ ማህበር ጋር ረጅም ውይይት በማድረግ ስምምነት ላይ በመድረሱ የጥቅማ ጥቅም ጥያቄውም ተመልሷል። አሁን ሰላማዊ የሥራ አካባቢ ተፈጥሯል።

አዲስ ዘመን፦ በቀጣዮቹ ጊዜያት ከባቡር ትራንስፖርት ዘርፉ ምን አዲስ ነገር ይጠበቃል?

አቶ ሙሉቀን፦ በቀጣይ ሊረዱን ከሚገባ አካላት ጋር ረጅም ውይይትና ምክክር በማድረግ ቀላል ባቡሩን ቀጣይነት እንዲኖረው ማድረግ ተቀዳሚ እቅዳችን ሲሆን የተገዙትን ባቡሮች በትክክል ለመጠቀም የሚያስችለንን መለዋወጫ አግኝተን በመሠረተ ልማቱ ላይም ችግር ሳይኖር መቀጠል እንፈልጋለን ።

ሌላው የቀላል ባቡሩ ያለውን አቅም መጨመር ነው፤ ይህ ማለት የተሰራውን የሀዲድ አቅም በማሳደግና አንዳንድ ማሻሻያዎችን በማድረግ የባቡር ቁጥሮችን በመጨመር መጠቀም ነው። በዚህም ለተገልጋዮቻችን የምንመኘውን ዓይነት ምቾት ለመስጠት ጥረት ማድረግም ሌላው እቅዳችን ነው።

መንግሥት ደግሞ ሊያስብበት የሚገባው ነገር ቢኖር ከዚህ በፊት የታቀዱ የባቡር መስመሮችን በደንብ በማስጠናት ለኅብረተሰቡ የተሻለ የትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ማስፋፋት ያስፈልጋል። ለጊዜው ግን በምድር ባቡር የተያዘ እቅድ የለም፤ ምክንያቱም በጀት ስለሌለው።

አዲስ ዘመን ፦ በጣም አመሰግናለሁ።

አቶ ሙሉቀን ፦ እኔም አመሰግናለሁ።

አዲስ ዘመን  መስከረም 28/2012

 እፀገነት አክሊሉ