የቴርሼሪ ህክምና አገልግሎትን ለመተግበር የሚያስችል ኘሮጀክት ይፋ ሆነ

12

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በሀገሪቱ የሚታየውን ሁሉ አቀፍ የቴርሸሪ ህክምና አገልግሎት ችግር ለማቃለልና በዘርፉ የህክምና ማዕከላትን ለማልማት የሚያስችል የሜዲካል ሃብ ዴቨሎፕመንት ኘሮጀክት ህዳር 13 ቀን 2011 ዓ.ም በይፋ አበሰረ፡፡

በኘሮጀክቱ ማብሠሪያ ሥነስርአት ላይ 3 የተመረጡ የዩኒቨርስቲ ሆሰፒታሎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡

ፕሮጀክቱ በዋናነት የቴሪሸሪ ህክምና ማዕከላትን(Medical Hubs) በማልማት ደረጃውን የጠበቀ እና ተወዳዳሪ የሆነ የቴሪሸሪ ህክምና አገልግሎትን ለመስጠት የሚያስችል ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ያለመ መሆኑ ተገልጧል፡፡

በሚኒስቴሩ የክሊኒካል ዳይሬክቶሬት የስፔሻሊቲ ኬዝ ቲም አስተባባሪ የሆኑት ዶ/ር የኔነህ ጌታቸው በዘርፉ ያለውን አለም አቀፍ ተሞክሮ መሠረት በማድረግ ሆስፒታሎቹ ከአለማቀፍ ስታንዳርድ አንፃር የሚገኙበትን ደረጃ የሚያመላክት የመነሻ ነጥብ ግምገማ በማካሄድ ሆስፒታሎቹ አለማቀፍ እውቅና (አክሪዲቴሽን) እንዲያገኙ የሚያስችላቸውን ፍኖተካርታ የሚስቀምጥ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ፕሮጀክቱ የቴርሼሪ የጤና ማዕከላትን በመንግስት እና የግል አጋርነት ማልማትና አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ ሁኔታዎችን የሚያመቻች እና እንዲሁም ለቴርሼሪ ህክምና ማዕከላቱ በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመለዋወጥ የሚያግዙ ቀጣይ አሰራሮችን ለመተግበር የሚያግዝ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የቴሪሸሪ ህክምና ማዕከላት ልማት ከፍተኛ ወጪ እያወጡ ወደ ሌላ አገር ለህክምና የሚጓዙ አገልግሎት ፈላጊዎችን እንግልት ለመቀነስ እና በዚህም ምክንያት የሚወጣውን የውጪ ምንዛሪ የሚያስቀር መሆኑ ተገልጿል፡፡

ኘሮጀክቱ በቀጣዮቹ አስር ዓመታት የሚተገበርና በመጀመሪያው ምዕራፍ ለአስራ ስምንት ወራት የሚዘልቁ ተግባራትን መቅረጹን ያወሱት ዶ/ር የኔነህ በቅድሚያ በሶስት የተመረጡ የዩኒቨርስቲ ሆስፒታሎች ላይ ትኩረት በማድረግና ዕውቅና ሰጪ አለም አቀፍ ተቋማትን በመጋበዝ አሠራሩ እንዲተገበር ሁኔታዎችን ያመቻቻል ብለዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ከአውሮፓህብረት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ እና በገንዘብ ሚ/ር የቅርብ ክትትል በተመረጡ 3 የዩንቨርሲቲ ሆስፒታሎች በቀጣይ 18 ወራት ግዜ ውስጥ የሚተገበር መሆኑን እና ከዚህ ፕሮጀክት የሚገኝን ልምድ መሠረት በማድረግ በቀጣይ አስር ዓመታት ወደ ተቀሩት የዩኒቨርስቲ ሆስፒታሎች በማስፋት ለቴርሼሪ ህክምና አገልግሎት ብቁ ለማድረግና ወደ ውጪ ለአገልግሎቱ የሚሄዱትን በአገር ውስጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከማስቻል ባለፈ የጎረቤት አገራትም እንዲገለገሉበት መታቀዱን ዶ/ር የኔነህ ተናግረዋል፡፡

የፕሮጀክቱን አላማዎች እና አተገባበር በተመለከተ ከዎርክሾፑ ተሳታፊዎች ጥያቄዎች እና አስተያየቶች የቀረቡ ሲሆን በጤና ጥበቃ ሚ/ር የህክምና አገልግሎት ጀነራል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ዳንኤል ገ/ሚካኤል እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የገንዘብ ሚ/ር የሥራ ኃላፊዎች ለተነሱት ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በመጨረሻም ፕሮጀክቱ እንዲሳካ የባለድርሻ አካላትን የነቃ ተሳትፎ የሚጠይቅ በመሆኑ በተለይም ፕሮጀክቱ የሚተገበርባቸው ሆስፒታል ኃላፊዎች በቁርጠኝነት እንዲሠሩ ዶ/ር ዳንኤል ገ/ሚካኤል አሳስበዋል ሺል መረጃውን ያደረሰን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ነው፡፡