ምርጫው በጊዜው ይካሄዳል!

7

 የዘንድሮው ምርጫ አይቀሬ ነው። በሕጉም መሠረት ተቀባይነት አለው። እንዴት ተደርጎ አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት በሌለበት ሁኔታ ይካሄዳል? በዚህ መልኩ ብሔራዊ ምርጫ እንዴት ይደረጋል የሚሉ እልፍ ናቸው። ግራና ቀኝ እየተዋቃ ያለው ሃሳብ አያባራም። ምርጫው ግን አይቀሬ ሆኖ ይካሄዳል። በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ መካሄዱ የሕግና የሥርዓት መከበር ጉዳይ ነው።

በዚህም መሠረት ተቃዋሚዎች በብዙ መልኩ ራሳቸውን ለውጠው ለሀገርና ለሕዝብ ሰላም እንደሚቆሙ ይጠበቃል። የትናንቱ ጉዞ አልጠቀመም ትውልድን ዋጋ አስከፍሏልና ዛሬ የተሻለ ለውጥ ይመጣል ብለን እንጠብቅ። ከመናቆር ከጥላቻ ከእርስ በእርስ መጠላለፍ ከሴራ ፖለቲካ በመውጣት በመከባበር በመቻቻል በመከባበር በመደማመጥ እንዲያም ሲል ለጋራ ሀገር በጋራ የመቆም ፖለቲካን ማራመድ ጊዜው ይጠይቃል። ተስፋ ባለመቁረጥ አዲሱን ትውልድ እንጠብቅ። ጥላቻ የበቀል መንፈስና የሴራ ፖለቲካ ቁልቁል ሀገሪቷን ይዞ ሄደ እንጂ ከፍ አሊያም እልፍ አላደረጋትም።

በሰላም ሀገርቤት ገብታችሁ አብረን እንስራ ሲባል የበለጠ ለሰላምና ለሀገር እድገት መትጋት የተገባ ነበር። ሀገር ማመስ ለማንም አይበጅም። የምር ተኳሹን እኛ ስናውቀው ዝናር በእቅፌን ምን ደባለቀው ይላሉ አባቶች። ዛሬ ሁሉም ጀግና፤ ሁሉም ተንታኝ፤ ሁሉም ፖለቲከኛ ሆኖ ሀገር ጠቧቸው ሲያምሱን ውለው የሚያድሩትም ወደ ሰላሙ፤ መረጋጋቱ ለሀገርና ለሕዝብ ወደ ማሰቡ መመለስ ይጠበቅባቸዋል። ያም ሆነ ይሄ ግን ምርጫው በተቀመጠለት የጊዜ ገድብ መካሄዱ እርግጥ ነው።

ሁሉም ፓርቲዎች ምርጫው ሰላማዊ ፍትሀዊ ተአማኒ እንዲሆን በጋራ ሊሰሩ ይገባል። ምርጫው በተቀመጠለት ጊዜ ገደብ ካልተካሄደ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ሕጋዊ ሆኖ የመቀጠሉ ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ይወድቃል። ስለዚህ ምርጫ መካሄዱ ተፎካካሪዎችም መፎካከራቸው ውጤቱ ምንም ይሁን ምን መገለጹ ግድና አይቀሬ ነው።

ከሀገራዊ ምስቅልቅልና ረብ የለሽ የፖለቲካ ሁኔታ በመነሳት ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ሆኑ መንግሥት ምን ያህል ለምርጫ ውድድሩ ተዘጋጅተዋል የሚለው ጥያቄ ይነሳል። የምርጫ ቦርዱ መዋቅር አዲስ አደረጃጀት ስለሆነ መዋቅሩ በብሔራዊ ደረጃ እየተዘረጋ ይገኛል። አስፈጻሚዎች አልተመለመሉም አልሰለጠኑም የሚሉ ጥያቄዎች ይደመጣሉ። በየቦታው የሚታየው የሰላም መደፍረስና መታወክ ምርጫውን የትና እንዴት ማድረግ እንደሚቻል አስቸጋሪና አደናጋሪ መሆናቸውን ያነሳሉ። አያሳስብም አይባልም። ምክንያቱም በየቦታው አክራሪና ጽንፈኛ ኃይሎች በአሰፈሰፉበት፤ ክብሪት እየጫሩ ሁከትና ብጥብጥ እንዲነሳ በሚያደርጉበት ሁኔታ ውስጥ ምርጫውን በሰላማዊ መንገድ ለማካሄድ አይቻልም የሚሉት ይበዛሉ።

እርግጥ ነው። ግን ደግሞ ምርጫውን ማካሄድ ይቻላል። እንቅፋት ለመፍጠር እየጣሩ ያሉትን ክፍሎች ሴራ ማምከን የሚቻለው ሕዝብና መንግሥት በጋራ ሲቆሙ ብቻ ነው። ሆኖም ሕዝቡ በበቂ ሁኔታ ተደራጅቶ ሥራውን እየከወነ መታገል እንቅፋቶቹንም ማንሳት ምርጫውንም ማሳካት ይችላል። አሁን ተመዝግበው ካሉት 134 ፓርቲዎች ውስጥ ምን ያህሉ ለውድድር ይቀርባሉ፤ ባይቀርቡስ የሚፈጠረው ስሜት ምንድነው የሚለውም ጥያቄ አለ።

አብዛኛዎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ልዩነታቸውን እያጠበቡ ሕብር ወይም ውሕደት መፍጠር ይችላሉ። ተፎካካሪ ፓርቲዎችን በተመለከተ አንዳንዶቹ እየጠየቁ ያሉት የምርጫው ይራዘም ጉዳይ ውሃ አይቋጥርም። ሁኔታዎችን ተረድተው ለምርጫው መዘጋጀቱ ነው የሚጠቅማቸው። ፓርቲዎቹ የእኔ ከሚሉት የኅብረተሰብ ክፍል ጋር መወያየት መምከር ሀሳባቸውን ማንሸራሸር አዳዲስ ሃሳቦችን መቀበል ይጠቅማቸዋል።

አንድ ፓርቲ መሠረቱን በሕዝብ ውስጥ ካላደረገ፤ ሰፊ የታች ግንኙነት ካልፈጠረ፤ አላማውን ከዳር ሊያደርሱ የሚችሉ አባላት ከሌሉት፤ ድርጅታዊ መርሆዎቹ አላማና ግቡ የሚከተለው ርዕዮተ ዓለማዊ መስመር በጠራ ሁኔታ የተቀመጠ ካልሆነ ሕዝብን ማንቀሳቀስ አይችልም። ብቁ ተፎካካሪና ተገዳዳሪ የሚሆነውም በዚህ መልኩ ነው።

ምርጫው በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ ውስጥ መካሄዱ በግልጽ ታውቋል። በዚሁ መሠረት ራሳቸውን ማብቃት ከሁሉም በላይ ምርጫው ፍጹም ሰላማዊ እንዲሆን የሀሳብና የመንፈስ ዝግጅት ማድረግ አባላቶቻቸውን ለውድድሩ ማዘጋጀት ከመንግሥት ጋር ባላቸውም መድረክ በሰላም መምከር መወያየት የሀሳብ ክርክር ለማድረግ ዝግጁ መሆን ይገባል። ጊዜው ምክንያታዊነትንና የሀሳብ የበላይነትን ይጠይቃል። ልክ እንደ ገዢው ፓርቲ ሁሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ራሳቸውን ለሰላማዊ ውድድር ማብቃት መዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል። አይቀሬው ምርጫ ይካሄዳል፡፡

 አዲስ ዘመን  መስከረም 29/2012

 ወንድወሰን መኮንን