የአገሪቱን የግንባታ ግብዓት አቅርቦት ሰንሰለት የሚያጠናክር መድረክ

8

አገራችን ባለፉት ዓመታት ፈጣን ዕድገት በማረጋገጥ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት በተደማሪነት የማፋጠን ምህዋር ውስጥ ገብታለች። ይህ መሰረታዊ እውነት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ እጅግ ስኬታማና ዓለምን ካስደመመው የአገሪቱ የዕድገት ሂደት የሚመነጩና ቀጣይ የአገሪቱን ዕድገት ሊፈታተኑ ከሚችሉ ዘርፎች አንዱ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው የሚስተዋለው የቅልጥፍና እና የጥራት መጓደል ነው። ለዚህ ችግር ተጠቃሽ ከሆኑ መሠረታዊ ጉዳዮች አንዱ ደግሞ የተሳለጠ የግብዓት አቅርቦት ሰንሰለት ያለመኖር መሆኑ ግልጽ ነው።

በመሆኑም፤ ኢትኤል ማስታወቂያና ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በአገሪቱ የተሳለጠ የግንባታ ግብዓት አቅርቦት ሰንሰለት እንዲፈጠር በየዓመቱ ዓለም አቀፍ የኮንስትራክሽን ግብዓቶችና መሰረተ ልማት ኤግዚቢሽን የሚያዘጋጅ ሲሆን፤ ዘንድሮም በማህበሩ እና በቱርክ አጋሩ (Ladin Inter¬natinal Fair and Con­gress Organization INC) አዘጋጅነት፤ እንዲሁም በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ትብብር አስረኛው አዲስ ቢዩልድ ዓለም አቀፍ የኮንስትራክሽን ግብዓቶችና መሰረተ ልማት ኤግዚቢሽን ከመስከረም 28 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ እየተካሄደ ይገኛል። ኤግዚቢሽኑም እስከ ጥቅምት 1 ቀን 2012 ዓ.ም የሚቆይ ነው።

በኤግዚቢሽኑ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከቱርክ፣ ከጀርመን፣ ከሳውዲ አረቢያ፣ ከህንድ፣ ከኦማን፣ ከታይላንድ፣ ከኩዌት፣ ከኢራን፣ ከኳታር፣ ከፓኪስታን፣ ከዩክሬንና ከቻይና በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ የግብዓት አቅርቦትና በቴክኖሎጂ ሽግግር ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱ 97 ኩባንያዎች ይሳተፋሉ።

የሲሚንቶና ኮንክሪት ምርቶች፣ ኬብሎች፣ የኢነርጂ ስርዓትና የቴሌኮም ሥራዎች፣ የብረታ ብረት ፍሬሞችና የብረት ሥራ ውጤቶች፣ ቀለም፣ የፊኒሽንግ እቃዎች፣ የውሃ ማስተላለፊያ ቱቦዎች፤ እንዲሁም አዲስ ውጤት የሆነው post-tension and pre-stress steel technology እና ሌሎች ከ22 በላይ የግንባታ ግብዓትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ውጤቶች በኤግዚቢሽኑ ለዕይታ ከመቅረባቸው ባሻገር፤ የኢትዮጵያን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ እየፈተኑ ባሉት የጥራት መጓደል፣ የዋጋ መናርና የማጠናቀቂያ ጊዜ መጓተት ተግዳሮቶች ላይም የፓናል ውይይት ተደርጓል።

ይህ ኤግዚቢሽን ለአገሪቱ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ እና ለዘርፉ ተዋናዮች የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ አስመልክቶ በከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የኮንስትራክሽን ዘርፍ ተወዳዳሪነት ማበልጸጊያ ክፍል ኃላፊው ኢንጅነር አብዱ ጀማል በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በአገራችን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ሲመዘገብ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውም በትይዩ እያደገ ነው። በመሆኑም በመኖሪያ ቤትና በትላልቅ መሠረተ ልማቶች ግንባታ መስፋፋት ምክንያት የኮንስትራክሽን ዕቃዎች ፍላጎት ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ ሄዷል።

የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች ሲከናወኑ 60 በመቶ የሚሆነው የስራቸው ክፍል የግብዓት አቅርቦት ማረጋገጥ በመሆኑ፤ ከአገር ውስጥና ከውጭ የሚቀርቡ የፋብሪካ እና በአካባቢ የሚመረቱ የኮንስትራክሽን ግብዓቶችን አቅርቦት የማረጋገጥ ስራ ዋነኛ ተግባር ነው። ይሁን እንጂ፤ በአገራችን በብዙዎቹ እየተካሄዱ ባሉ የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች የአካባቢና የፋብሪካ ውጤት የሆኑ ግብዓቶች ላይ ከፍተኛ በሚባል ደረጃ እጥረት አለ።

እንዲሁም በአካባቢና በፋብሪካ የሚመረቱ ግብዓቶች በሚፈለገው መጠን፤ ጥራትና ጊዜ የማቅረብም ከፍተኛ ችግር ይስተዋላል። የፋብሪካ ምርት ሆነው ከውጭ የሚቀርቡ ግብዓቶችና መሳሪያዎች በሚፈለጉበት ወቅት ተወዳዳሪነትን ባረጋገጠ ዋጋ፤ እንዲሁም የጥራት ደረጃውን በጠበቀ ሁኔታ ለማግኘት ከፍተኛ ፈተና ሆኗል። በዚህ ምክንያት በግንባታው ዘርፍ የግብዓት አቅርቦት ላይ ከፍተኛ የጥራት መጓደልና መቆሚያ የሌለው የዋጋ ንረት እየተስተዋለ ነው፤ ይላሉ።

በግንባታው ዘርፍ ለሚስተዋለው የግብዓት አቅርቦትና የፍላጎት አለመመጣጠን ክፍተት አንዱ ምክንያት በዘርፉ ያሉ ተዋናዮች አቅም ማነስ እንደሆነ የሚናገሩት ኢንጅነሩ፤ የፋብሪካ ውጤት የሆኑ እንደ ብረታ ብረት፣ ሴራሚክስ፣ ፕላስቲክና የኤሌክትሪክ ዕቃዎች የመሳሰሉ የግንባታ ግብዓቶች የአቅርቦትና የፍላጎት አለመመጣጠን ችግርም በአገሪቱ ይስተዋላል።

በተጨማሪም በአገር ውስጥ የሚመረተው የብረታ ብረት ምርት የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ከሚፈልገው 40 በመቶ የማይበልጥ ሲሆን፤ ለግንባታው ዘርፍ ግብዓት የሚሆኑ ምርቶችን ማቅረቢያ ተሽከርካሪዎች እና የግንባታ ስራውን የሚያሳልጡ የአጋዥ ማሽነሪዎች እጥረት በኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች ላይ የዋጋ መናር፤ የጊዜ መጓተትና የጥራት መጓደል እንዲከሰት የበኩሉን አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳረፈ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

እነዚህንና መሰል በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እና የአገር ውስጥ አቅምን ለማሳደግ መንግስት አልሞ እየሰራ መሆኑን የጠቆሙት አቶ አብዱ፤ ኤግዚቢሽኑ የውጭ ኩባንያዎች ወደ አገራችን ገብተው ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂና ጥበብ በአገር ውስጥ ላሉ የዘርፉ ባለሙያዎች ከማስተዋወቃቸው ባሻገር የአገር ውስጥ ድርጅቶች በውጭ ያለውን የቴክኖሎጂ እድገት ተረድተው እራሳቸውን ለዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት የሚያዘጋጁበት ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል።

በሌላ በኩል ከውጭ መጥተው በኤግዚቢሽኑ ላይ የሚሳተፉ ኩባንያዎች በአገሪቱ ያለውን የኢንቨስትመንት አማራጭ በአካል በማየት፣ መንግስት በኢንቨስትመንት ዘርፉ ያመቻቸውን ምቹ ሁኔታ ተጠቅመው ኢንቨስት እንዲያደርጉ እድል ይፈጥራል። በአጠቃላይ ኤግዚቢሽኑ በአገሪቱ ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች በአይነት፣ በጥራትና በዋጋ እንዲበራከቱ ከማድረጉ ባሻገር፤ ቀጣይነት ያለው የግንባታ ግብአቶች የአቅርቦት ሰንሰለት በአገሪቱ እንዲኖር ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተናግረዋል።

ኤግዚቢሽኑ ለውጭና ለአገር ውስጥ የዘርፉ ተዋንያን የልምድ ልውውጥ ማድረጊያና የገበያ ትስስር መፍጠሪያ መድረክ እንደሆነ የሚናገሩት የኢትኤል ማስታወቂያና ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ፕሮግራም ማናጀር የሆኑት ወይዘሪት ዮካቬድ ኑርልኝ ናቸው።

እርሳቸውም እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ13 አገራት የተውጣጡ 97 ኩባንያዎች በኤግዚቢሽኑ ላይ እየተሳተፉ ሲሆን፤ እነዚህ ኩባንያዎች በግንባታው ዘርፉ የደረሱበትን ቴክኖሎጂና ጥበብ እንዲሁም የእነዚህ ውጤት የሆኑትን ግብዓቶችና ማሽኖች በመድረኩ ላይ በማስተዋወቅ ነገ ላይ የገበያ ትስስር በመፍጠር በአገሪቱ የኮንስትራክሽን ግብዓት አቅርቦት የተሳለጠ እንዲሆን ያስችላል።

በአጠቃላይ በኤግዚቢሽኑ አዲሱ ቴክኖሎጂ (post-tension and pre-stress steel technology) እና ሌሎች ከ22 በላይ የግንባታ ግብዓትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ውጤቶች ለዕይታ መቅረባቸውን ጠቁመው፤ መድረኩ እነዚህ ኩባንያዎች በወኪል አከፋፋይ አማካኝነት በአገር ውስጥ ምርታቸውን የሚያቀርቡበትን እድል ከማመቻቸቱም ባሻገር እነዚህን ምርቶች በአገር ውስጥ ማምረት እንዲችሉ እድል የሚፈጥር እንደሆነ ተናግረዋል።

አዲስ ዘመን መስከረም 30/2012

 ሶሎሞን በየነ