የት ሄዱ?

7

ሁሌም ጠዋት ጠዋት ቁርሴን እየበላሁ ትስስራቸው ጠብቆ ፍቅራቸው ሞቆ አብሮነታቸው ጎልቶ የሚታዩኝ ጥንዶች ዘወትር አገኛቸው ከነበረበት ቦታ አጣኋቸውና ብዙ ጠየቅሁ። በነገራችን ላይ እኛ ግቢ የሰው አይን ማረፊያ መሆናቸውን፤ በሁሉም ዘንድ እውቅና የተሰጣቸው ጥንዶች መሆናቸው ጥያቄ የጠየኩት ሁሉ ስለነሱ ሳነሳ በሚመለሰው መልስ አወቅሁ። አዎን! እንደኔ ሌሎችም መድረሻቸው አሳስቦታል። “የት ሄደው ይሆን?” ብዙ መላ ምቶች አሰብኩ። “ተጣልተው ይሆን?” የዘንድሮ ፍቅር የኢንዶሚን አይነት ነው ቶሎ ሞቆ ቶሎ ደርሶ ተፋፍሞ ወዲያው ጣፍጦ በፍጥነት የሚያልቅ።

የእርስ በርስ ቁርኝታችን ላልቶ ማህበራዊ ግንኙነታችን ሻክሮ እንደው ምን ነካን? የሚያስብል ደረጃ ላይ ደርሰናልና መፋቀር፣ ፍቅር ስናይ መገረም፤ መዋደድን ስናስተውል መመሰጥ ተላምደናል። በፍቅር መተሳሰሩ፤ በመውደድ መጣመሩ የሚሰጠውን ልዩ ጣዕም የሚያሳጡን ጉዳዮች በዝተዋልና ደጋግመን ምሬት፤ መስማት መነጣጠል ማየት አዘውትረናል። ፍቅር መገኛው የት ይሆን? ተፋቀሪዎችስ የት ገቡ? ማለታችን በዝቷል። ምን እናድርግ ሰው ከፍቅር ይልቅ ጠብ ቀሎታል። ከአንድነት ይልቅ መነጠል ብቸኝነት ውስጡ ሆኗል።

“ሲሄዱም አንድ ላይ ሲጠጡም አንድ ላይ ለየብቻ እንዳላይ..” ያለው ዘፋኝ፤ ማለቴ የስንኙ ባለቤት እነዚህን ጥንዶች አይቶ ይሆን እንዴ? እንጃ ይመስላል፤ ለየብቻ መሆን ፈፅሞ የማይሆንላቸው እነዚያ ጥንዶች ብቻውን የሆነ ሰው ሲያዩ ምን ይሉ ይሆን? አሁን ላይ ብቸኝነት በርክቷልና ተላምደውት እያለፉን ይሆናል እንጂ አስቁመው ለምን ብለው ሁላ የሚጠይቁን ይመስለኛል።

በዚህ ፍቅር የኑሮን ያህል በተወደደበት ዘመን ላይ ተገኝተን የእርስ በርስ ግንኙነታችንን አለዘብነው። ከአብሮነት ይልቅ ብቻነት ቀለለን። ሁኔታችን የሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህንን ግጥም “ፈራን ፍቅርን ፈራን” ደጋግሞ ያስነበንባል። አዎን ፈርተናል። መተሳሰርን አብሮነትን ንቀናል። እኔ ምለው? ለብቻ መሆንን የመረጥነው በአብሮነት መኖሩ ሰልችቶን ይሆን እንዴ? በእርግጥ መቀራረባችን አንድ ላይ መሆናችን እኮ አሁንም አለ። ችግሩ ውስጣዊ ጥምረት ነው ከኛ የነጠፈው። እንጂማ “ውዴ፣ ማሬ፣ ከረሜላዬ” መባባሉን በጣም ተክነንበታል።

ማፍቀር ቢያቅተን እንዴት የፍቅር ተጓዦችን ማድነቅ ያቅተናል። ፍቅረኞችን ማየት ናፍቃችሁ ታውቃላችሁ? እውነተኛ ጥምረት ማርኳችሁስ ያውቃል? በበጎ ነገር መማረክ በጎነትን ያላምዳል። ፍቅርን መናፈቅ ወደ ፍቅር ጉዞ ሚያደርጉትን መንገድ ያሰምራል።

እኔ ግን በእነዚህ ጥንዶች ተጠልፌያለው። አብሮነታቸው ሰምሮ፤ አንድነታቸው ቀጥሎ፤ መተሳሰራቸው ጎልብቶ ማየት ተመኘሁ። “ፍቅር ግን አለ?” ብለው ለሚጠይቁ ሰዎች “አዎን በደንብ ነዋ!” የሚያስብሉ የመውደድና የፍቅር ጥግ የሚያስኮመኩሙ፤ ፍቅርን ከማሳየት በላይ የሚኖሩት አሉ። “ይሄው እዚህ ዘንድ ተመልከቱ!” የሚያስብሉ አንዳንድ የፍቅር መልዕክተኞች አልፎ አልፎ ይገጥሙናል። እኔም አንድ መዝናኛ ውስጥ የሱስ ያህል አብሬ ካላየኋቸው ቅር የሚለኝ፤ ጥምረትና አንድነታቸው የሚያስገርመኝ ፍቅረኛሞች ገጥመውኛል። እንዲያው ጥብቅብቅ ብለው ሲበሉ፤ ሲያወሩ፤ ሲጓዙ አዎን ፍቅር ያስውባል፤ ያሳምራል የሚያሰኙ ጥንዶች ከእይታዬ ሳጣቸው ናፈቁኝ።

የመዝናኛው ተጠቃሚ መነጋገሪያ፤ የቤቱ ደንበኛ ሁሉ አይን ማሪፊያ የነበሩት ጥንዶች የት ሄዱ? ስለናፈቁኝ ፍቅረኛሞች፤ ከአይኔ ስለራቁት ጥንዶች ደጋግሜ ማሰቤ ብሎም መጠየቄን አጠናከርኩ። በእርግጥ የጠፉበትን ምክንያት ባውቅም ጥፉ የተባሉበት መንገድ ቅር አሰኘኝ።

ትናንት ከአንዱ ባልደረባዬ ጋር ስናወጋ ማዕቀብ ተጥሎባቸው ከቤቱ መጥፋታቸው ተነገረኝ። እርግጥ ነው አንዳንዴ ይሳሳሙ ነበር። መሳሳማቸው ግን በፍቅር ስለሆነ በጠብ ከምንናከሰው ከብዙዎቻችን የነርሱ የተሻለ ነው። እርግጥ ነው አብረው የሆኑ ሳይሆን አንድ የሆኑ ያህል ይጠባበቁ ነበር። ግን ከኛ መገፋፋት የነእርሱ መጣበቅ ይሻላል።

እርግጥ ነው በተቀመጡበት ሁሉ በፍቅር አፍ ላፍ ገጥመው ያወሩ ነበር። ግን ከኛ ተደብቆ ከመተማማት እሱ ይልቃል። በማውራታቸው መሀል ከተራ ግንኙነት ያለፈ ጥምረት የሚፈጥር መግነጢሳዊ ሃይል አለ። ሲያወሩ፣ ሲሳሳሙም ሰው አያዩም። ምክንያቱም ፍቅር እውነት እንጂ ሌላ አይታየውም። ፍቅር አይፈራም። በእርግጥ ጨዋነት በሚያጎድል መልኩ፣ ባህልን በማያፋልስ መልኩ ቢያደርጉት መልካም ነበር። ሲሳሳሙ ግን ሁሉም አፍጥጦ ያይ፣ ይመለከታቸው ነበር። መሳሳማቸውን እየተቃወመም ቢሆን እንዳያቋርጡት ይመኝ ነበር።

እነሱም ባስተሳሰራቸው ፍቅር ተጠልለው ሌላውን አያዩትም ነበር። ፍቅር እኮ መሸሸጊያ፤ መከለያ ነው። እሱ ውስጥ ተሁኖ ሌላ አይታይም። ፍቅር ያሉበትን አስረሳቸው። እና እነዚህ ጥንዶች ሁሌ ከሚቀመጡበት ቦታ ሳጣቸው ጠየቅሁ። ሁሌም ከሚጓዙበት መንገድ ሳጣቸው የትነታቸውን ለማወቅ ወተወትኩ። “አትምጡ!” ተብለው እንደሆነ ስሰማ ተገረምኩ።

“መፋቀራችሁ፣ መጣመራችሁ፣ መዋሃዳችሁ ትክክል ነው። አንዳንዴ ሳታውቁት የምትሳሳሙትን ቢያንስ አቁሙ” ማለት ሲገባ፤ “እዚህ ቤት መሳሳማችሁ ያስከፋቸው ሰዎች ስላሉ ወደዚህ ድርሽ ባትሉ መልካም ነው” መባሉ ግን ተገቢ አይደለም። እናም ተፋቃሪዎቹን ያባረረው መዝናኛ ጠበኞችን ሰብስቦ ሊያውል ማሰቡ ይሆን እንዴ? የት ይሆኑ ግን? ያያቸው አለ? አበቃሁ! ቸር ይግጠመን።

አዲስ ዘመን መስከረም 30/2012