ከአንድነት ፓርክ ብዙ ልንማር ይገባል!

13

ኢትዮጵያውያን በአቧራ የተሸፈኑ በርካታ ድንቅ ታሪኮች፣ ባህሎች፣ እሴቶች፣ አንድነቶችና ጀግንነቶች አሉን። ያልተነገረላቸውን ማንነቶቻችንን የምናገኘው፣ የምናየውና የምንረዳው የተሸፈነብንን ግርዶሽ ከላያችን ላይ አሽቀንጥረን ስንጥል ብቻ ነው። ግርዶሹ ብዙ ነገሮችን ይከልላል። ብርሃኑን ያጨልምና ተግባሩን ይደብቃል። ጥቅሙንና ጉዳቱን እንዳንለይ ያደርጋል። የሚያስተሳስሩንን ነገሮች ሳናይ እንድንቀርና ፍቅራችን እንዲቀዛቀዝም ያደርገናል።

ሰሞኑን የተመረቀው የአንድነት ፓርክ ግን ይህንኑ የሰበረ ነበር። አቧራው ተነስቶ ወርቅ አይተንበታልና። የአንድነት ፓርክ በታሪክ ሦስት ትውልዶችን የሚያገናኝ ከ130 ዓመት በላይ የቆየ ታሪክን ሰንዶ የያዘ ነው። ያልተነገረላቸው ኢትዮጵያዊ ጥበብን በእቅፉ ያኖረም። ይሄ ሁሉ ታሪክ፣ ጥበብ፣ ባህል፣ የወቅቱ የሥልጣኔ ደረጃ ግን በአቧራ ተሸፍኖ፤ ሳይነገርለት እና ማንም ሳያውቀው ተደብቆ ኖሯል። ዛሬ ጊዜው ደርሶ ተመልካች፣ አስታዋሽና ፈታሽ አግኝቶ እነሆ ታሪክ፣ ጥበብ፣ ኢትዮጵያዊ አንድነት ሊለን አዲስ ምዕራፍ ላይ ደርሰናል።

የአንድነት ፓርክ የሚያስተምረን በርካታ ነገሮች አሉ። ከእነዚህም አንዱ ኢትዮጵያውያን ጥበበኞች እንደነበርን ታሪካችንን ያየንበት እና የተማርንበት ነው። ሌላው ደግሞ ምንም ነገር እንስራ ብለን ከተነሳን፤ ከተባበርንና አንድ ከሆንን በተባበረ ክንድ ምንም የሚያቆመን ነገር እንደሌለ ሰርተን ለውጤት መብቃት እንደምንችል ያሳየንበት ነው። ዋናው ጉዳይ ግን ዛሬ ይሄንን አይተን ነገን በተሻለ ሁኔታ ለመስራት እንደምንችል አመላካች ነው።

የአንድነት ፓርክን አሁን ባየነው መልክ ለመስራት ዕቅድ ሲታቀድ፣ ለፕሮጀክቱ ግንባታ ዝግጅት ሲደረግ በተያዘለት የጊዜ ገደብ (በስድስት ወር)፣ በታሰበው ልክ አድሶ፣ ገንብቶ፣ ተውቦና ተጠናቆ እውን ይሆናል ብለው ብዙዎቹ አልገመቱም ነበር። ይህን ቢያስቡና ቢገምቱ አይፈረድባቸውም። ምክንያቱም ብዙ ፕሮጀክቶቻችን የሚታወቁት ተጀምረው ሲጠናቀቁ ሳይሆን ረጅም ጊዜ ሲወስድባቸውና ሳያልቁ መፍረስ ሲጀምሩ ጭምር ነው። በተያዘላቸው የፕሮጀክት የጊዜ ገደብ፣ ገንዘብ፣ የጥራት ደረጃ ሳይጠናቀቁና ሀገርና ሕዝብን ለተጨማሪ ወጪ ሲዳርጉ ነው።

ለዚህ የቅርብ ጊዜዎቹን ማንሳቱ ብቻ በቂ ይሆናል። የታላቁን ህዳሴ ግድብ ግንባታ፣ የስኳር ፋብሪካዎች፣ የማዳበሪያ ፋብሪካ እና ሌሎችንም በምሳሌነት መጥቀሱ ብቻ በቂ ነው። ይሄ ለምን ሆነ ብለን ብንጠይቅ በርካታ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ደግሞም አሉ። ሆኖም ግን በዋነኛነት ቆራጥ የሆነ አመራር አለመኖር፣ የቁጥጥርና የክትትል ሥራው ደካማነት፣ በየደረጃው ያለው አካል ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት ባለመቻሉ ነው ብሎ ደፍሮ መናገር ይቻላል። ታዲያ ይህንን መሳዩን ችግር ማሸነፍና ለውጤታማነት መብቃት የሚቻለው ሁሉም በየደረጃው ኃላፊነቱን በብቃት መወጣት ሲችል መሆኑ ግልጽ ነው። በአንድነት ፓርክ ፕሮጀክት ላይ የታየው ርብርብና የተመዘገበው ስኬት የሚያመለክተውም ይሄንኑ ነው።

የአንድነት ፓርክ የኢትዮጵያን የዘመናት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁነቶች ያቀፈ፣ ታሪክ ነጋሪ፣ ለቀጣዩ ትውልድ ብልጽግና የተሻለ አቅጣጫና መሠረት የሚያስቀምጥ፤ በጥቅሉ የኢትዮጵያውያንን የዘመናት አሻራ ከነገው ተስፋ ጋር አስተሳስሮ በአንድ ማዕከል ያገናኘ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እንዳሉት፤ ግቢው የሚያኮራ ታሪክ እንዳለን በደንብ ያሳያል፤ የሚያሳፍር ታሪክ እንዳለንም እንዲሁ ይናገራል፡፡ ትውልድ ከድል ብቻ ሳይሆን ከውድቀትም መማርን፤ እያፈረሱ ሳይሆን ባለው ላይ እየደመሩ መስራት እንደሚገባ፤ ከቆረጡ ሁሉንም ማድረግ እንደሚቻል፤ ኢትዮጵያም ይሄን ለማድረግ ቆራጥ ልጆች እንዳሏት ያሳየም ነው፡፡ አገር ወረትም ውዝፍ ዕዳም አላት፤ ይህንን እንደሚዛኑ መጠቀም ይገባል፡፡ ኢትዮጵያውያን ታሪክ አላቸው፤ ነገር ግን በታሪክ የሚኖሩ ሳይሆን ታሪክ በውስጣቸው የሚኖር ናቸው፡፡ ሥልጣኔም የተከማቸ ጥበብ እንደመሆኑ ከትናንት ወደዛሬ፣ ከዛሬም ወደነገ ይፈስሳል፡፡ እናም በአባቶች ጀግንነት እንደምንኮራው ሁሉ በጥፋቶቻቸውም ሳናፍር የእነርሱን ጥፋት ላለመድገም መስራት ይገባል ብለዋል፡፡

በአንድነት ፓርክ ፕሮጀክቶችን ማቀድና ዕቅድን ሰርቶ ማጠናቀቅ እንደሚቻል አይተናል። በዚህ ፕሮጀክት የተሳተፉ ከአመራር እስከ ፈጻሚ ሰርተውና አሰርተው ለምረቃ አብቅተው አስተምረውናል። ይሄ የሚያሳየው በቆራጥነት ከተነሳን፣ ከተባበርንና አንድነት ከፈጠርን ከጦርነትም ውጪ በማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ጀግኖች መሆን እንደምንችል ነው። ዕቅዶችን ማቀድ ብቻም ሳይሆን መፈጸም የሚያስችል አቅም እንዳለንም ነው። በዚህ ረገድ የአንድነት ፓርክ ላልገባን ዜጎች አስተማሪና መሪ፤ ለገባን ደግሞ የበለጠ መስራት እንደምንችል ፍንጭ ሰጪ ምልክታችን ነው።

አዲስ ዘመን ጥቅምት 2/2012