ፕሪሚየር ሊጉ በኅዳር ይጀምራል

8

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የዘንድሮ የውድድር ዓመት በኅዳር ወር አጋማሽ እንደሚጀመር የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታወቀ። ሊጉን የሚመራው ዓብይ ኮሚቴም የመጀመሪያ ስብሰባውን አድርጓል።

የ2012ዓ.ም የውድድር ዘመን ፕሪሚየር ሊግ በሚቋቋመው አክሲዮን ማህበር እንዲመራ መወሰኑ እንዲሁም ዓብይ ኮሚቴዎች መመረጣቸው የሚታወስ ነው። ይህ ኮሚቴም የመጀመሪያ ዙር ስብሰባውን ያደረገ ሲሆን፤ ፕሪሚየር ሊጉ የሚጀመርበትን ቀን ወስኗል። በቀጣዩ ኅዳር ወር የመጀመሪያ ሳምንት ለመጀመር ቢወስንም፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ጨዋታ ከሜዳው ውጪ ከማዳጋስካር ጋር የሚያካሂድ መሆኑን ተከትሎ በአንድ ሳምንት እንዲራዘም መደረጉን ሶከር ኢትዮጵያ አስነብቧል። በዚህም መሠረት በኅዳር 13 እና 14 የውድድር ዓመቱን ለመጀመር ኮሚቴው ከውሳኔ ደርሷል።

ዓብይ ኮሚቴው በስብሰባው ላይ ከተገኙት የፌዴሬሽኑ አመራሮች ጋር በመሆን በዕለቱ በተያዙ አጀንዳዎች ላይ ተነጋግሯል፤ የሰነድ ርክክብም አድርጓል። ከዚህ ባሻገር የሚቋቋሙ ኮሚቴዎች ላይ ሰፊ ውይይት የተደረገ ሲሆን፤ የእግር ኳሱ ችግር የሚመነጨው ከውድድር ኮሚቴ እና ዳኞች ኮሚቴ አባላት በመሆኑ በኮሚቴዎቹ ላይ ጥርት ያለ አቋም በመያዝ ሃቀኛ አመራር መስጠት የሚችሉ ሰዎችን ለመምረጥ ጠንካራ ዕጩዎችን እንዲያቀርቡም ተነጋግረዋል።

ክለቦች ሜዳዎቻቸው ማሟላት የሚገባቸውን እንዲያሟሉ እና ምቹ እንዲሆኑም በስብሰባው መመሪያ ተላልፏል። በተለይ የድሬዳዋ፣ ወላይታ ድቻ፣ አዳማ፣ ሃድያ ሆሳዕና፣ ወልቂጤ፣ ሰበታ ከተማ እንዲሁም ጅማ አባጅፋር ሜዳዎች የጸጥታ ማስጠበቂያ (አጥር)፣ በሚገባ የተዘጋጀ የተጫዋቾች መልበሻ ክፍል እንዲዘጋጅ እንዲሁም በሜዳ ዙሪያ ለተመልካች አደገኛ እና ተወርዋሪ የሆኑ አላስፈላጊ ቁሶች መነሳት ይገባቸዋል። ይህ የማይሆን ከሆነ ግን ውድድሩን ለማድረግ እንደሚቸገው ዓብይ ኮሚቴው አስገንዝቧል።

አዲስ የተዋቀረው ኮሚቴ ደብዳቤዎችን ለመጻፍ የሚያስችል ሕጋዊ መሠረት ባለመያዙ፤ ፌዴሬሽኑ ለስድስቱ ክልሎችና ሁለቱ ከተማ አስተዳደር ክለቦች ተዟዙረው በሚጫወቱበት ወቅት በቂ ጥበቃ እንዲያገኙ፣ ጨዋታውን የሚመሩ ዳኞች በትክክል እንዲዳኙ፣ የክለብ ደጋፊዎች ተገቢው ቦታ ተሰጥቷቸው እንዲደግፉና የሕግ ከለላ እንዲሰጣቸው፣ የክልል አመራሮች እንዲሁም የከተማ ከንቲባዎች የሕግ ከለላ ማረጋገጫ ደብዳቤ እንዲሰጡና ለሚመለከታቸው አካላት ደብዳቤ እንዲጽፍ ተስማምተዋል።

ከዚህ ባሻገር የተነሱ ሌሎች አጀንዳዎች በይደር የቆዩ ሲሆን፤ በቀጣዩ ሳምንት መጨረሻ ውይይት ለማድረግም ቀጠሮ መያዙንም ዘገባው አመላክቷል።

አዲስ ዘመን ጥቅምት 2/2012

 ብርሃን ፈይሳ