ማራቶንን ከ2ሰዓት በታች ማጠናቀቅ ተቻለ

9

 ኬንያዊው የማራቶን የዓለም ክብረወሰን ባለቤት ኢሉድ ኪፕቾጌ በናይኪ የተያዘውን ከሁለት ሰዓት በታች የመግባት ሙከራ አሳካ። ትናንት በኦስትሪያዋ ቬና በተካሄደው ሙከራ ላይ ኢሉድ ኪፕቾጌ 1፡59፡40 በሆነ ሰዓት በመግባት ዓላማውን ማሳካት ችሏል። አትሌቱ በታሪክ 42ኪሎ ሜትርን ከሁለት ሰዓት በታች የገባ የመጀመሪያው ሰው ይሁን እንጂ ሰዓቱ በዓለም ክብረወሰንነት አይመዘገብለትም።

የሰው ልጅ አቅም ወሰን የሌለው መሆኑን ለማሳየት በታዋቂው የስፖርት ትጥቅ አምራች ናይኪ የተያዘው ይህ ፕሮጀክት በአትሌቲክስ ስፖርት ረጅሙን ርቀት ከተለመደው ሁለት ሰዓት በታች ለመግባት የሚያስችል ሙከራ ነው። ለዚህም የዓለም ክብረወሰን ባለቤቱ ኪፕቾጌ የተመረጠ ሲሆን፤ ትጥቅ አምራቹ በሚያደርገው በቴክኖሎጂ የታገዘ ድጋፍ 1ሰዓት ከ59 ደቂቃ ለመግባት ነበር የታቀደው። ለዚህ ሙከራ ነፋሻማ የአየር ሁኔታ ያላትና ሰዓቱን ለማሟላት የሚያስችል የቦታ አቀማመጥ ያላት ቬና ስትመረጥ፤ ከ41 በላይ የሆኑ አሯሯጮችም ተዘጋጅተው ነበር።

ትናትን ጠዋት በተካሄደው ሩጫም አትሌቱ የርቀቱን ግማሽ የሸፈነበት ሰዓት አጠራጣሪ ይሁን እንጂ በአሯሯጮቹ ብርታት 1፡59፡40 በሆነ ሰዓት በመፈጸም ግቡን ሊያሳካ ችሏል። ከሩጫው በኋላም «አሯሯጮቹን ላመሰግናቸው እወዳለሁ፤ ይህንን ሙከራ ተቀብለው አብረውኝ በመሮጣቸው ታሪክ ለማስመዝገብ ችለናል። ይህ በርካቶችን የሚያነሳሳ እና የሰው ልጅ አቅም የሚገደብ አለመሆኑንም ያሳያል። በጣም ደስ ብሎኛል ልጆቼ እና ባለቤቴም ሩጫዬን በመመልከታቸው ተደስቻለሁ» ማለቱን ኢንዲፔንደንት በድረገጹ አስነብቧል።

ሙከራው በዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ዕውቅና የሌለው መሆኑን ተከትሎ በዓለም ክብረወሰንነት አይመዘገብም። እ.አ.አ በ2018 የበርሊንን ማራቶን የገባበት 2፡01.39 የሆነ ሰዓት የዓለም ፈጣን ሰዓት ሲሆን፤ ከሁለት ዓመት በፊት አትሌቱ በጣሊያኗ ሞንዛ ከተማ ባደረገው ሙከራ በ26ሰከንዶች ዓላማውን አለመሳካቱ ይታወሳል።

አዲስ ዘመን ጥቅምት 2/2012

 ብርሃን ፈይሳ