በግጭት ማንም አሸናፊ አይሆንም!

15

በዛሬው ፅሑፌ የእርስ በርስ ጦርነት፣ መፈናቀል፣ ማቁሰልና መግደል እንዲሁም ህዝብንና ወገንን ለረሃብ መዳረግ ለምንም ችግር መፍትሔ እንደማይሆንና ሰላም ለሁሉም ነገር መሰረት መሆኑን ሊያሳዩን የሚችሉትን የተለያዩ ነገሮችን ከየሀገሩ በመንቀስ በምሳሌነት ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡

ሰሞኑን በአልጀሪያ በመካሄድ ላይ ባለው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ተካፋይ የሆነ አልጄሪያዊ በሰልፉ ላይ ለምን ተካፋይ እንደሆነ በጋዜጠኞች ለቀረበለት ጥያቄ ሲመልስ “እኛ የምናደርገውን የምናውቅ የነቃን ህዝቦች ነን! ሰልፍ የወጣሁት መብቴን ለመጠየቅ ነው እንጂ በማንም ተገፍቼና ተመርቼ አይደለም” ብሎ ነበር:: ጥሩ ብሏል። ሕዝብ መብትና ግዴታውን አውቆ ለድጋፍም ሆነ ለተቃውሞ አደባባይ ከወጣ ተገቢውን ምላሽ ማግኘት አለበት፡፡

በማደግ ላይ ያሉ ሀገሮች ህዝቦች ተስማምተው በመኖር በሰላም ሰርተው ለማደግ ጥረት በማድረግ ፈንታ መጤ ፍልስፍናዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ሲሉ እርስ በርስ ለምን ይጨራረሳሉ? ይህ የሁሉም ጥያቄ ነው፡፡ እነርሱ ሲዋጉ ብልጦች ቅኝ ገዢዎች መንግስትን እንረዳለን፣ ለህዝቡ ዲሞክራሲን እናሰፍናለን ብለው በመግባትና መሳሪያ በማቀበል የሀገሪቱን ማዕድን ማጋዛቸውን ይቀጥላሉ።

እያንዳንዱ ሀገር የህዝቡን የውስጥ ችግር ስር ሳይሰድ በቀላሉና በአጭር ጊዜ መፍታት ሲችል ምንም አያመጣም በሚል በቸልታ የሚታለፍ ከሆነ መዘዙ ዛሬ ላለው ትውልድ ብቻ ሳይሆን ለመጪውም እንደሚተርፍ ከወዲሁ መገመት አያዳግትም፡፡

በአንዲት ሀገር በብሄር፣ በፆታና በሃይማኖት የሚነሱ ያለመግባባቶችን በማባባስ ለማይበርድ ጥፋት ሲዳረጉ ማየት የተለመደ ነው፡፡ ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል እንዲሉ የውጭ ኃይሎች በአሁኑ ጊዜ የቅኝ አገዛዝ ዘዴያቸውን በመቀየር በተለያዩ ዘዴዎች ታዳጊ ሀገሮችን እርስ በርስ በማጋጨት ተጠቃሚነታቸውን ለማስቀጠል ተኝተው አያድሩም፡፡

በዛሬው ፅሑፌ የእርስ በርስ ብጥብጥን ካነሳሁኝ ለረጅም ጊዜ ሰላም የራቃትን አፍጋኒስታንን መዘንጋት አይገባም፡፡ ተዋጊዎችስ ለስልጣን ሽሚያና ለነፃነታቸው ሲሉ ነው እንበል! የሚያሳዝነኝ በማያባራና በዚህ ጊዜ ፍፃሜ ያገኛል ብሎ ለመገመት በማይቻል ጦርነት ውስጥ ያለው ሕዝብ ነው፡፡

በአፍጋኒስታን ኩንዱዝ ከተማ በሚገኘው የድንበር የለሽ ሐኪሞች ሆስፒታል ክፍል ውስጥ በቦምብ እሳት የጋየ የአልጋ ፍሬም ተገልብጦ ይታያል፡፡ የክፍሉ ጣሪያ ወደ ከሰልነት ተለውጦና ረግፎ ሰማዩ ወለል ብሎ ይታያል፡፡ ወለሉ ደግሞ በመስተዋቶች ስብርባሪና በአመድ ተሞልቷል፡፡ ግድግዳው በጥላሽነት ጠቁሯል። አሚና ጋዲር የተባለቸው የ12 ዓመት ታዳጊ በጥይት ራሷ ላይ በመመታቷ ሰዎች ተረባርበው ድንበር የለሽ ሀኪሞች ሆስፒታል ስላደረሷት ረጅም ሰአት የወሰደ ቀዶ ጥገና ተደርጎላት ከፍተኛ ጥንቃቄ በሚደረግበት ክፍል (አይ.ሲ.ዩ) ውስጥ ተኝታ በማገገም ላይ ነበረች፡፡

ለአንድ ሰዓት ያህል በተካሄደው ድብደባ 42 ታካሚዎች የሆስፒታል ሰራተኞችና አስታማሚዎች የሞቱ ሲሆን፤ ከደርዘን በላይ የሆኑት ቆስለዋል፡፡ ድብደባውን ያካሄደው ሀገር መንግስት በሆስፒታሉ ላይ የተካሄደው ድብደባ በስህተት መሆኑን በማመን በኩንዱዝ የጦር ሰፈር በተደረገው ስብሰባ ላይ ይቅርታ ጠይቋል ተብሏል፡፡ ለማፅናኛ ይሆናል በሚልም የገንዘብ ስጦታ አበርክቷል፡፡

አሚና በመገደሏ አባቷ ጋዲር ስድስት ሺህ ዶላር የተሰጠው ሲሆን በጥይት ድብደባው ለቆሰሉት ሌሎች ሰዎች ደግሞ ሶስት ሶስት ሺህ ዶላር ተሰጥቷቸዋል። የአሚና አባት ጋዲር በሁኔታው በእጅጉ የተበሳጨና ተስፋ የቆረጠ መሆኑን ከገለፀ በኋላ “ገንዘቡ ከልጄ ሕይወት ጋር ሲነፃፀር እዚህ ግባ የማይባል ነው፡፡ ያም ሆኖ ግን የአሚናን ቀብር ለማስፈፀምና ብዛት ያለው ቤተሰቤን በለቅሶው ወቅት ለማስተናገድ ገንዘብ ተበድሬ ስለነበር ያንን ለመክፈል የተሰጠኝን ከመቀበል በስተቀር አማራጭ የለኝም ነበር” በማለት ምሬቱን ገልጿል፡፡

ቀዶ ጥገናው የተሳካ ስለነበር ዶክተሮች አሚና በአጭር ጊዜ ውስጥ አገግማ ከቤተሰቦቿ ጋር ትቀላቀላለች የሚል ተስፋ ያደረባቸው ሲሆን፤ ትምህርቷን በመቀጠል ዶክተር የመሆን ህልሟን ታሳካዋለች በማለት ያስቡ ነበር፡፡ እንደ ሌሎች የአይ.ሲ.ዩ. ታካሚዎች አልጋዋ ላይ እንደተኛች ወደ ከሰልነትና ወደ አመድነት እንድትለወጥ ተደረገ እንጂ!

አፍጋኒስታን ውስጥ ለተጎጂ ቤተሰቦች ገንዘብ መስጠት በውጭ ሀገር ወታደሮች ዘንድ የተለመደ ነው። ይህን የሚያደርጉት በሲቪሎች ላይ የሚደርሰውን የሞራልና ህጋዊ ኃላፊነት አምነው ሳይቀበሉ ነው፡፡ ለምሳሌ የተባበሩት መንግስታት ሪፖርት እንደሚያመለክተው በ7 ዓመት ብቻ 21.323 አፍጋኒስታውያን ሲገድሉ 37.413 ቆስለዋል፡፡

ከሁሉም የሚገርመው 14 የድንበር የለሽ ሐኪሞች አባላት ከተገደሉ ከ6 ወር በኋላ ነበር የጦሩ አባላት ይቅርታ ለመጠየቅና የማይመጥንና እዚህ ግባ የማይባል ገንዘብ ለመስጠት ተወካዮች የመጡት፡፡ በዚያም ጊዜ ቢሆን በቦታው ተገኝተው ነበር ይባል እንጂ የተጎጂ ቤተሰቦችን አግኝተው አላነጋገሩም:: (ምንጭ ኒውስ ዊክ መፅሔት ነው)፡፡

በእርስ በርስ ጦርነት አሸናፊም ተሸናፊም የለም። ሟችም፣ ገዳይም፣ ቆሳይም፣ አቁሳይም፣ አፈናቃይም፣ ተፈናቃይም ወገን ነው፡፡ ወንድም በወንድሙ ላይ ነው የተነሳው፡፡ የውጭ ኃይሎች ለሀገሬው ሕዝብ ቆም ብሎ የማሰቢያና የመወያያ ጊዜ አይሰጡትም፡፡ በእሳት ላይ ቤንዚን እየጨመሩ የአዳዲስ መሳሪያዎቻቸው መሞከሪያ ያደርጉታል እንጂ ለሰላምና ለእርቅ የሚሰሩት ነገር የለም፡፡

ቀሪው ዓለም ከዚህ ምን ይማራል? ጦርነት በአፍ እንደሚወራውና በፅሑፍ እንደሚነበበው ቀላል አይደለም፡፡ በሰላም መኖር እየተቻለ ጥቃቅን ነገሮችን አንስቶ ያለመግባባትን በመፍጠር መሳሪያ አንግቦ ወደ ጦርነት መግባት ጉዳቱ ይህ ነው የማይባል ነውና በተቻለ መጠን በመወያየትና በመቻቻል ችግሮችን ለመፍታት መጣሩ ብልህነትና ለሀገርና ለወገን አሳቢነትን ነው የሚያመለክተው።

ሀገራችንን በተመለከተ ባለፈው አንድ ዓመት መልካም የሆኑ ነገሮች ተከውነዋል ብንልም የሚቆጠቁጡ አይረሴ የሆኑ ጥፋቶች መፈፀማቸውን አስተውለናል፡፡ መንግስት በሰጠው ይፋዊ መግለጫ በተለያዩ ክልሎች 1229 ሰዎች ሲሞቱ 1393 ሰዎች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ 2.5 ቢሊየን ብር የሚገመት ንብረት የወደመ ሲሆን፤ ከ2.4 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ መፈናቀሉ ታውቋል፡፡ በህዝብና በመንግስት የተባበረ ጥረት የተፈናቀለው ህዝብ ወደቀዬው እንዲመለስ ከመደረጉም በላይ በዚህ አስከፊና ለትዝብት በዳረገ የጥፋት ተግባር ላይ የተሰማሩ ወንጀለኞች በቁጥጥር ስር መዋላቸው በተጨማሪ ተገልጿል፡፡ እሰየው ነው!

ቸር እንሰንብት !

አዲስ ዘመን ጥቅምት 3/2012

 ፋንታሁን ኃይሌ