ጅት ኩን ዶ- የገሃዱ ዓለም ፍልሚያ

9

 ተወዳጅ ከሆኑ የፍልሚያ ስፖርቶች መካከል ጅት ኩን ዶ በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡ በኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተለያዩ የፍልሚያ ስፖርቶች በርካታ ተከታዮችን በተለይም ወጣቶችን ከማፍራት አልፈው በዓለም አቀፍና አገር አቀፍ ደረጃ ውጤት ማስመዝገብ ችለዋል፡፡ ወርልድ ቴኳንዶና ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ በዚህ ረገድ ረጅም ርቀት የተጓዙ የፍልሚያ ስፖርቶች ሆነው ይገኛሉ፡፡ በፍልስፍና እንዲሁም በእንቅስቃሴ ደረጃ የተለየና የገሃዱ ዓለም ፍልሚያን መሬት ማውረድ የቻለው ጅት ኩን ዶ በዝነኛው የማርሻል አርት ንጉስና ተዋናይ ብሩስ ሊ እንደተፈለሰፈ ይነገራል፡፡ ይህ እንቅስቃሴ እንደሌሎቹ የፍልሚያ ስፖርቶች በኢትዮጵያ በስፋት ሲዘወተርና ሲወራለት አይታይም፡፡

ማስተር ኤርሚያስ ገሰሰ ጅት ኩን ዶ ከሌሎች የማርሻል አርት እንቅስቃሴዎች የሚለየው በሳይንሳዊ ፍልስፍናው መሆኑን ይናገራል፡፡ ጅት ኩን ዶ በገሃዱ ዓለም ፍልሚያ ላይ እንደሚያተኩር የሚያብራራው ማስተር ኤርሚያስ፤ ሰዎች ራሳቸውን እንዲሆኑና ራሳቸውን እንዲገልፁ ያስችላቸዋል ይላል፡፡ በስፖርቱ ከሃያ አምስት ዓመታት በላይ ያሳለፈው ማስተር ኤርሚያስ ገርጂና መገናኛ አካባቢ በሁለት ቅርንጫፎች በከፈተው የጅት ኩን ዶ ስፖርት ክለብ በርካታ ወጣቶችን እያፈራ ይገኛል፡፡

በአሁኑ ወቅትም ከሁለት መቶ በላይ ወጣቶችን እያሰለጠነ ይገኛል። ጅት ኩን ዶ እንደሌሎች የፍልሚያ ስፖርቶች በአገራችን እንዳልተሰራበት ይናገራል፡፡ በስፖርቱ ሙያተኞች ቢኖሩም ፍላጎት ከማጣትም ሊሆን ይችላል በሌሎች መሰናክሎች በአገራችን ስፖርቱን ለማስፋፋት ሲሰሩበት አይስተዋልም፡፡ ጥቂት እንደ ማስተር ኤርሚያስ ያሉ ባለሙያዎች ግን ስፖርቱን

 ለማስፋፋት ጠንክረው እየሰሩ መሆኑን መካድ አይቻልም፡፡

ጅት ኩን ዶ እንደሌሎቹ የማርሻል አርት ስፖርቶች ሁሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያንቀሳቅሰው ፌዴሬሽን አለው፡፡ የዚህ ስፖርት መታሰቢያነቱ የማርሻል አርት ንጉሱ ቻይናዊው ብሩስ ሊ መሆኑን ማስተር ኤርሚያስ ይናገራል፡፡ በዚህ እንቅስቃሴ ዋናው ትምህርት ፍልሚያ ላይ የሚያተኩር ሲሆን ሰዎች የሚመዘኑትም በፍልሚያ ነው፡፡ሰዎች ምን ያህል ተጋጣሚያቸውን ማጥቃት ይችላሉ፣ ምን ያህልስ ራሳቸውን መከላከል ይችላሉ? የስፖርቱ ዋና መመዘኛ መሆኑን ማስተር ኤርሚያስ ያብራራል፡፡

በዚህ ስፖርት እንቅስቃሴ ውስጥ የነጠላ ወይም አንድ ለአንድ ፍልሚያ፣ ሁለትና ሦስት ለአንድ ፍልሚያ እንዲሁም የቡድን ፍልሚያ የሚታወቁ ሲሆን እንቅስቃሴዎች በባዶ እጅ፣በመሳሪያና ሌሎችም በገሃዱ ዓለም ያሉ ፍልሚያዎችን ያካተተ ነው፡፡ ፍልስፍናውም በጥልቀት የሚሰራው እዚሁ ላይ ነው፡፡

በአገራችን ጅት ኩን ዶ በፌዴሬሽን ደረጃ በጥምር ማርሻል አርት ፌዴሬሽኖች ውስጥ ተካቶ ውድድሮችንም እያካሄደ ይገኛል፡፡ ጅት ኩን ዶ በአገራችን ከጥምር ማርሻል አርት ፌዴሬሽን ተነጥሎ ራሱን ችሎ ለመቋቋም የሰዎች አለማግባባትና የአሰልጣኞች አለመትጋትና የሚጠየቁ መስፈርቶች ውስብስብ መሆን እንቅፋት እንደሆነ ማስተር ኤርሚያስ ያስረዳል፡፡ ጅት ኩን ዶ ራሱን ችሎ በፌዴሬሽን ደረጃ ለመውጣት በተለይም የሚጠየቀው መስፈርት ከባድ መሆኑን ይናገራል፡፡

በአንድ ክፍለ ከተማ ሦስትና ከዚያ በላይ ክለቦችን የሚጠይቅ መስፈርት ከባለሙያ እጥረት ጋር ትልቁ ችግር መሆኑንም ያስቀምጣል፡፡ የስፖርቱ ባህሪ በራሱ አስቸጋሪና ውስጡ መቆየትን የሚጠይቅ መሆኑን የሚያስቀምጠው ማስተር ኤርሚያስ የኑሮ ውጣውረድና ሌሎችም ፈተናዎች ወጣቱን በሚፈለገው መጠን በስፖርቱ እንዲያልፍ አላስቻለውም ባይ ነው፡፡ ይህም ስፖርቱን እንዳይስፋፋ አድርጎታል፡፡

ወርልድ ቴኳንዶን በመሳሰሉ ስፖርቶች በርካታ ወጣቶች በዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ውድድሮች አገራቸውን ወክለው ትልቅ ውጤት ከማስመዝገብ ባሻገር ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን መጥቀም እየቻሉ ነው፡፡ ጅት ኩን ዶ ለሚያዘወትሩት ወጣቶች እንደ ወርልድ ቴኳንዶ ሁሉ አገርን በመወከልና ጥቅም በማግኘት ረገድ ያለውን ተስፋ ማስተር ኤርሚያስ ሲናገሩ ‹‹በፊት ለፊት የሚታይ ነገር የለም፣ነገር ግን የእኛ ጥረት ይሄን ይለውጠዋል፣ አሁን በአገራችን ጥሩ መነሳሳት አለ፤በተለይ በከተማችንና በክፍለ ከተሞች ደረጃ በስፖርቱ ተነሳሽነት አለ፤ ማንኛውንም ስፖርት ለማስፋፋት ባለሙያዎች እየተጠሩና እያወያዩ ነው፣ ይሄን ማሳደግና በፌዴሬሽን ደረጃ ራሱን እንዲችል ማድረግ ከተቻለ ዓለም አቀፍ ግንኙነቶችንም መፍጠር ይቻላል፣ይህም ወጣቶች በዓለም አቀፍ ውድድሮች ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል›› በማለት ስፖርቱ ያለውን ተስፋ ያብራራል፡፡

ኤርሚያስ ገሰሰ ጂምና ማርሻል አርት ማዕከል ወጣቶችን በጅት ኩን ዶ እንቅስቃሴ ከማብቃት ጎንለጎን የበጎ አድራጎት ስራዎችን እንደሚሰራም ማዕከላቱ በሚገኙበት አካባቢ ይታወቃል፡፡ የበጎ አድራጎት ስራ ከማርሻል አርት ስፖርት ጋር አብሮ እንደሚሄድ የሚናገረው ማስተር ኤርሚያስ፤ ወጣቶች ማርሻል አርትን ሲማሩ የስነምግባር ትምህርትም አብሮ እንደሚሰጣቸው ያብራራል፡፡ ይህ የስነ ምግባር ትምህርት መገለጫው በጎ ተግባር ነው፡፡

1995 ዓ.ም አካባቢ የተማሪ ቤተሰቦች፣በጎ ፍቃደኞችና ሌሎችም በጋራ ሆነው የስፖርቱን እንቅስቃሴ ሲጀምሩ ገንዘብ በማዋጣት ጎዳና ላይ ያሉ ወገኖችን በምግብ፣በአልባሳት ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር በዘላቂነት በማቋቋም መደበኛ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ እየተደረገ ይገኛል፡፡ የበጎ አድራጎት ስራውን ከስፖርቱ ባሻገር ለማስፋት በቅርቡ ‹‹ጳጉሜን 5 የበጎ አድራጎት ድርጅት›› በሚል ስያሜ በማሳደግ እውቅና አግኝቶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ በየዓመቱም የትንሳዔን በዓል ምክንያት በማድረግ በጎዳና ላይ ያሉ ወገኖችን የመመገብ፣አልባሳትንና ገንዘብ የመስጠት መርሃግብሮችን ያካሂዳል፡፡

መማር የሚችሉ እንዲማሩ፣መስራት የሚችሉ እንዲሰሩ ማድረግም አንዱ ተግባር ነው፡፡ በዚህም የበርካታ ወጣቶችን ሕይወት መለወጥ ተችሏል፡፡

አዲስ ዘመን ጥቅምት 3/2012

 ቦጋለ አበበ