ጫማ ሰቅለው ጓንት ያነሱ፤ ከሩጫም ወደ ኳስ ያቀኑ ኮከቦች

17

 ልምምድን አድምቶ በመስራትና በጥንካሬ በመቆየት የመጨረሻዋን መስመር በቀዳሚነት መርገጥ ዋጋው ከደስታም ይልቃል። ሃገርን ማስጠራት እንዲሁም ክብርን መቀዳጀት ደግሞ የስኬታማነት ክፍያው ነው። እንደ አትሌቶቹ ሁሉ፤ ልምምድን በትጋት መልሶ መላልሶ መስራት የግድ ነው፤ በየትኛውም ስፖርት ከውጤት ማድረሱም እውነት ነው። ባሉበት ስፖርት በታማኝነት ጊዜን፣ ጉልበትንና አቅምን አሟጦ መጠቀምም አስፈላጊ ነው።

ነገር ግን ስኬትን ከተቀዳጁበት አንድ ስፖርት ወደ ሌላ በመሸጋገር በድጋሚ ውጤታማ መሆን ይቻላል? ከተጫዋችነት አሊያም ከአትሌትነት ወደ አሰልጣኝነት እንዲሁም ወደ አማካሪነትና ሌሎች ስራዎች መሸጋገር የተለመደ ነው። ጫማ ሰቅሎ የቦክስ ጓንት ማጥለቅ፣ ከመም ወደ እግር ኳስ ሜዳ መሸጋገር እንዲሁም ጓንት ሰቅሎ የበረዶ ላይ ገና ጨዋታ ዱላን ማንሳት ግን አደናጋሪ ነው። ዋናው ጥያቄም እውን እጅግ በተለያዩ ሁለት ስፖርቶች በቀላሉ ስኬታማነትን ማግኘት ይቻላል? የሚለው ይሆናል። ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ለማግኘት ጥናት ማድረግን ቢጠይቅም፤ ለዛሬ ከአንዱ ወደ ሌላኛው ስፖርት የተሸጋገሩ ስፖርተኞችን እናንሳ።

«በርካታ ዋንጫዎችን አንስቻለሁ፤ አሁን ግን ቀበቶ ማግኘት እፈልጋለሁ» በሚል ነበር የተነሳው። ይህ የሁለት ክብሮች ናፋቂ የእንግሊዝን ብሄራዊ ቡድንን ለ14ዓመታት በተለይ የታወቀበትን ክለብ ማንቸስተር ዩናይትድን ደግሞ ለ12ዓመታት ያገለገለው ሪዮ ጋቪን ፈርዲናንድ ነው። በአራት ክለቦች ሁለት አስርት ዓመታትን በተጫዋችነት ያሳለፈው ፈርዲናንድ፤ በእንግሊዛውያን ዘንድ የምንጊዜም ተወዳጅነትን ካተረፉ ተጫዋቾች መካከል ተጠቃሽ ነው።

ስድስት የፕሪምየር ሊግ፣ አንድ የቻምፒዮንስ ሊግ፣ አንድ የፊፋ የክለቦች እንዲሁም ሌሎች ዋንጫዎችን ጨምሮ በርካታ ክብሮችንም በግሉ እና በቡድን አግኝቷል። በ39ዓመቱ የእግር ኳስ ሜዳን ሲሰናበት ግን የቦክስ መፋለሚያ ሪንግን እያሰበ ነበር። በሰቀለው ጫማ ምትክም ጓንት ማጥለቁ መነጋገሪያ አድርጎታል፡፡ በፕሮፌሽናል ቦክሰኛነት በከባድ ሚዛን ለመሳተፍ በሳምንት ከ4-5 ቀናት ልምምድ እንደሚያደርግም አስታወቀ። ነገር ግን በፕሮፌሽናል የቦክስ ማህበር በኩል «ብቁ ነህ» የሚል ማረጋገጫ ማግኘት ሳይችል ቀረ። በዚህ ምክንያትም ማዘኑን «ቦክስ ሰውነት ብቻም ሳይሆን ጠንካራ ልብ ነው የሚፈልገው» ሲል ነበር የገለጸው። የእግር ኳስ ተንታኝ የሆነው አንጋፋው ተጫዋች እንዲያም ቢሆን ፈቃዱን ለማግኘት ጥረቱን እንደማይተውና ጠንክሮ እንደሚሰራ አረጋግጧል።

ጃማይካዊው የዓለም ፈጣኑ ሰው ደግሞ ከመም በቀጥታ ወደ እግር ኳስ ማንከባለል የገባ ስፖርተኛ ነው። የሰው ልጅ በዚህን ልክ ይፈጥናል ተብሎ ባይጠበቅም በአጭር ርቀት አትሌቲክስ አዲስ ታሪክ ያስመዘገበው ቁመተ መለሎውና ቀልደኛው ዩሲያን ቦልት ስምንት የኦሊምፒክ ሜዳሊያዎችን ጠራርጎ በመውሰድ ስኬታማ ነው። ቦልት 100 ሜትርን በ9ሰከንድ ከ58 ማይክሮ ሰከንድ፣ 200ሜትርን ደግሞ 19ሰከንድ ከ19ማይክሮ ሰከንድ በሆነ ሰዓት በመግባት የዓለምን ክብረወሰን አርቆ የሰቀለ አስደናቂ አትሌት ነው።

ቦልት ከታወቀበት አትሌቲክስ ባሻገር እግር ኳስን እጅግ የሚወድ እንዲሁም የሚመኘውም ስፖርት ነው። የእንግሊዙ ማንቺስተር ዩናይትድ ክለብ ደጋፊ የሆነው አትሌቱ የቀያዮቹ ሴጣን ተጫዋች የመሆን ህልም እንዳለውም ይናገር ነገር። እአአ ከ2017ቱ የለንደን የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና በኋላም ከአትሌቲክስ ስፖርት ወጥቶ ወደ እግር ኳስ መግባቱን አሳወቀ። የእግር ኳስ ልምምዱን በቅድሚያ የጀመረው በኖርዌይ ክለብ ሲሆን፤ የዓለምን ክብረወሰን ያስመዘገበበትን 9.58 የሚያስታውስ ማሊያ ይለብስ ነበር። ከቆይታ በኋላም የአውስትራሊያውን ሴንትራል ኮስት ማሬነርስ የተባለውን ክለብ ተቀላቀለ፤ በመጀመሪያው የወዳጅነት ጨዋታም ሁለት ግቦችን ማስቆጠር ቻለ። ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ ከስፖርት ህይወት ሙሉ ለሙሉ ወጥቶ ወደ ንግድ መግባቱን ይፋ አደረገ።

ለበርካታ ጊዜያት ጾታዊ ጥርጣሬ ውስጥ በመግባት አስቸጋሪ ጊዜን መግፋት የግድ የሆነባት ደቡብ አፍሪካዊቷ አትሌት ካስተር ሰመኒያም በቅርቡ ከአትሌቲክስ ስፖርት እግር ኳስን እንደመረጠች አስታውቃለች። በተክለ ቁመናዋ ምክንያት በርካታ ፈተናዎችን ለመጋፈጥ የተገደደችው የ800 ሜትር የኦሊምፒክ ቻምፒዮናዋ ሰመኒያ ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ያወጣውን ደንብ ተከትሎ በክስ ሂደት መቆየቷ ይታወሳል። ነገር ግን እሰጣ አገባው እንዳሰበችው ሆኖ ባለመጠናቀቁ፤ በልጅነቷ ታንከባልል እንደነበር ወደ ገለጸችው ኳስ ገብታለች። በሃገሯ የሚገኝን ክለብ የተቀላቀለችው ተጫዋቿ አዲሱ የጨዋታ ዘመን እስኪጀመር በልምምድ ላይ የምትቆይ መሆኗን ተከትሎ «ይሻላል» ባለችው እግር ኳስ ያላትን ብቃት ማስመስከር አልቻለችም።

ከሰሞኑ በተሰማ ሌላ ዜና ደግሞ የቀድሞው ግብ ጠባቂ ፒተር ቼክ በጓንቱ ፋንታ የበረዶ ላይ ገና ጨዋታ ዱላ ወደ ማንሳት መሸጋገሩን አስታውቋል። በተለይ በሰማያዊዎቹ እና በመድፈኞቹ ቤት ቆይታው የሚታወቀው ግብ ጠባቂው ጓንቱን ከሰቀለ በኋላ በቀድሞ ክለቡ ቼልሲ የቴክኒክ አማካሪ በመሆን እያገለገለ ይገኛል። ከዚህ ስራው ጎን ለጎንም በልጅነቱ የተጫወተውንና የሚወደውን ይህንን ስፖርት ተቀላቅሏል። እንደ ግብ ደጀንነቱ ሁሉ በዚህ ስፖርትም ስኬታማ መሆን አለመሆኑም ጊዜ ምላሽ ይሰጥበታል።

አዲስ ዘመን ጥቅምት 3/2012

ብርሃን ፈይሳ