የፌዴራል መንግሥት ለአዲስ አበባ ባቡር አገልግሎት 6 ቢሊዮን ብር ደጉሟል

71

አዲስ አበባ፡- የፌዴራል መንግሥት ለአዲስ አበባ ቀላል ባቡር አገልግሎት በአራት ዓመታት ስድስት ቢሊዮን ብር መደጎሙን አስታወቀ ።

በኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚና የባቡር ኔትወርክ ዘርፍ ኃላፊ አቶ የኋላሸት ጀመረ፣ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፣ ለአዲስ አበባ ባቡር ፕሮጀክት የፌዴራል መንግሥት 475 ሚሊዮን ዶላር ተበድሮ ሰርቷል። አሁን ላይ ከግንባታው በተጨማሪ በየዓመቱ አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር እየደጎመ ይገኛል።

ሥራው ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ባለፉት አራት ዓመት ስድስት ቢሊዮን ብር ደጉሟል። ኮርፖሬሽኑ የፌዴራል ተቋም እንደመሆኑ የኢትዮጵያ ህዝብ ያዋጣውን ገንዘብ ለአንድ ከተማ አስተዳደር መደጎም ትክክል አይደለም።

ኃላፊው ‹‹ የከተማ አስተዳደሩ ድጎማውን እንዲሞላ ለመንግሥትም ቀርቦ በመወሰን በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል ለከተማው አስተዳደሩ ደብዳቤ ተጽፏል።የከተማ አስተዳደሩም ጉዳዩን አጥንቷል።

እስካሁን ግን በጽሁፍ የተሰጠን መልስ የለም። ጥያቄ ከቀረበ ረጅም ጊዜ ቢሆንም የከተማ አስተዳደሩ በመደጎም ደረጃ ዳተኝነት አሳይቷል። የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት መነሻው የከተማው አስተዳደር ነው። ፕሮጀክቱ ሲሰራም እያንዳንዱ ሥራ የተወሰነው በከተማ አስተዳደሩ ነው። ኮርፖሬሽኑ የሰራው ቴክኒካልና የአስተዳደር

 ሥራውን ነው።አሁንም አገልግሎት እየሰጠ ያለው ለከተማ አስተዳደሩ በመሆኑ ድጎማ ማድረግ አለበት ›› ብለዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ኢንጅነር ሰለሞን ኪዳኔ ምላሽ እንዲሰጡን ጠይቀናቸው በሰጡት ምላሽ ጉዳዩ በካቢኔው ውሳኔ መወሰኑንና የካቢኔውን ውሳኔ ከከንቲባ ጽሕፈት ቤት እንድንወስድ ነግረውን ነበር፡፡

የጽሕፈት ቤት ኃላፊው ከአገር ውጭ በመሆናቸው ምክትል ጽሕፈት ቤት ኃላፊው ግን መረጃውን እንደማያውቁና ቢሮ ሲገቡ ስለጉዳዩ ምላሽ እንደሚሰጡን ቃል ቢገቡም ደጋግመን ብንደውልላቸውም ስልካቸውን አንስተው ምላሽ ሊሰጡን አልቻሉም። በጉዳዩ ላይ የከተማ አስተዳደሩ ምላሽ ሲሰጡን የምናስተናግድ ይሆናል።  

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 5/2012

አጎናፍር ገዛኸኝ