በቸልተኛነት ሕግን ማስከበር አይቻልም!

25

 አርቲስት አበበ ተካ ‹‹ ወፊቱ … ጭራ ለቅማ የምታድረው፣ እንዲህ አስናቀችኝ፤ ቀድማኝ ጎጆ ወጥታ – ጎጆ አስተማረችኝ፤

ጎጆ አቤት … ጎጆዬ – ወፍዬ አስቀናችኝ፤

ምነው ባደረገኝ የሷ ጋሻ ጃግሬ፤

እንደምንም ብዬ እኔም ጥሬ ግሬ፤

ያገዳ ጎጆዬን ባቆምኳት ማግሬ፤… ››

ሲል በአንድ ወቅት ወፍ እንኳ ባቅሟ የምትሰራው ቤት ለእርሱ አስቀንቶት የእርስዋ ረዳት መሆን መመኘቱን ከእንጉርጉሮው ማድመጣችን ይታወሳል። ከቀደምት አባቶችና እናቶች አንስቶ እስካሁን ድረስ የወፊቱን ያህል የ‹‹አንገት ማስገቢያ ጎጆ›› አስፈላጊነት አንገብጋቢ መሆኑን የማይገነዘብ ያለ ይኖራል ብሎ ለመገመት ያዳግታል። የቤትን አስፈላጊነት ማንም የሚረዳው ቢሆንም ለአቅመ አዳም የደረሰ የቻለ ራሱ ቤት ገንብቶ፤ ያልቻለ ሌላው የገነባውን ቤት ተከራይቶ፣ ምንም የሌለው ደግሞ ተገን ፈልጎ የትም ጎኑን እያሳረፈ ኑሮውን ለመግፋት ተገድዷል።

በከተማም ይሁን በገጠር የመሬት ጥበት መከሰቱ ለመኖሪያ ቤት እንዳስፈላጊነቱ ያለመገኘት በምክንያትነት ቢጠቀስም፤ ዋናው ግን የህዝብ ቁጥር ያለገደብ እየጨመረ የመሄዱ ጉዳይ ሆኗል። መንግሥት ህብረተሰቡ የመኖሪያ ቤት እጥረቱ እንዲቃለልለት በተለያዩ ወቅቶች በግል፣ በቡድንና የጋራ መኖሪያ ቤት ግንባታ እያከናወነ ለችግሩ መፍትሄ ለመስጠት ጥረት ቢያደርግም ችግሩን ለመቅረፍ እንዳልተቻለ ማስተዋል አይከብድም።

በመንግስት በኩል የቤት እጥረትን ለመቅረፍ ደጋፊ የነበረው የቀድሞ መጠሪያው የኪራይ ቤቶች ኤጀንሲ፤ የአሁኑ ቤቶች ኮርፖሬሽን በአነስተኛ ክፍያ ቤቶችን ሲያከራይ እንደነበር ይታወቃል። የመንግስት የስራ ኃላፊ በመሆናቸው ምክንያት የመንግስት ቤት ከኪራይ ነጻ ወይም በአነስተኛ ኪራይ ተሰጥቷቸው ሳለ የራሳቸውን የግል ቤት አከራይተው የሚኖሩ እንዳሉም ይነገራል። ይህ በመሆኑም ኮርፖሬሽኑ በአንድ ወቅት ያለ አግባብ የመንግስት ቤቶችን የያዙ 156 የስራ ኃላፊዎችን እንዳስለቀቀ መግለጹ ይታወሳል።

በሌላም በኩል ኮርፖሬሽኑ ለመኖሪያነት የሚያከራያቸውን ቤቶች አንዳንዶች በራሳቸው ስም እያዛወሩና ለቤቱ ካርታ እያወጡ የራሳቸው ይዞታ ማድረጋቸው ተደርሶበታል። ይህ ተግባር ህገወጥነት ቢሆንም የመንግሥት ይዞታ እንዴት ለግለሰብ ተዛወረ የሚለው ግን አጠያያቂ ጉዳይ ነው።

ኮርፖሬሽኑ እነዚህን መሰል ህገወጦች ሲያጋጥሙት በዝምታ መመልከቱ ሌሎች ይህንን መሰል ተግባር እንዲፈጽሙ ሊያበረታታ እንደሚችል ግልጽ ማሳያ ነው። መንግሥት የሚያስተዳድረው ሀብት የሕዝብ ሀብት ነው። ይህንን የሕዝብ ንብረት እንዲያስተዳድር ኃላፊነት የተሰጠው ተቋም ንብረቱን ግለሰቦች በስማቸው ሲያዛውሩት አስፈላጊውን ርምጃ ለመውሰድና ለማስወሰድ ችላ ሲል መታየቱ ተገቢ አይደለም።

ዛሬ ከምግብ፣ ከመጠጥ ውሀና ከልብስ በባሰ ሁኔታ ህብረተሰቡን በእጅጉ ያማረረው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣው የቤት ኪራይ ንረት ሲሆን፤ መንግሥት የሚያስተዳድረውን የሕዝብ ንብረት ለግላቸው የሚያድርጉትን፣ መንግሥት በሰጣቸው ቤት እየኖሩ የራሳቸውን ቤት ኪራይ የሚሰበስቡትን በዝምታ ማለፍ መጠለያ አጥተው የሌት ቁር፣ የቀን ሀሩርና የክረምት ዝናብ በሚፈራረቅባቸው ወገኖች ላይ በደል መፈጸም ነው።

በቤት እጦትና በኪራይ ውድነት የሚንገላቱት ወገኖች ከያኒው እንዳለው ባሻት ሥፍራ ቤቷን መገንባት ለምትችለው ወፍ ጋሻ ጃግሬ መሆንን ቢመኙ ቤት የማግኘት ጉጉታቸውን ዕውን ለማድረግ ነው። ይህ ምኞት ዕውን ሊሆን የሚችለው ግን ኃላፊነት የተሰጠው አካል ሕግን ማስከበር በሚችልበት አቅምና ፍጥነት ሥራውን ማከናወን ሲችል በመሆኑ ህገወጦች ህጋዊ መስመርን እንዲከተሉ ኃላፊነት የተሰጠው አካል በአግባቡ ሥራውን ማከናወን ይጠበቅበታል።

አዲስ ዘመን  ጥቅምት 5/2012