የኢሕአዴግ ውህደት ለምን አስፈለገ?

12

ኢሕአዴግ ግንባር ሁኖ 27 ዓመታት ዘለቀ። ይህን ያህል ዓመታት በግንባርነት የዘለቀ ሀገር የመራ በአለም ታሪክ የለም። ኢሕአዴግ ወደ ውሁድ ፓርቲነት እንዲለወጥ ለበርካታ ዓመታት ሲወተወት ቆይቷል። የትልቅ ሀገርና ሕዝብ ባለቤት ሆኖ የሚነገረውን አለመስማት ትልቅ ዋጋ አስከፍሎታል። ዛሬ የምናየው ቅጥ አምባሩ የጠፋ የፖለቲካ ምስቅልቅልና ትርምስ የዚሁ የኢሕአዴግ ፈጥኖ አለመሸከፍ ሁሉን አቀፍና በአንድ ሁኖ አለመቆም ድምር ውጤት ነው።

ትልቋን ሀገር ለማሳነስ ከሚደረግ ሩጫ ውጭ የፈየደው ምንም ነገር የለም የሚሉ በሌላ ወገን ይደመጣሉ። የተሳሳተና የተዛባ የፖለቲካ አካሄድ ፈተናችንን አብዝቶታል። ዛሬ የተያያዝነው ከድህነትና ከኋላቀርነት ጋር ታግለን ሀገርን ወደ ታላቅ ምዕራፍ ማሸጋገር ሳይሆን እርስ በእርስ መናቆር በጥላቻና በሴራ ፖለቲካ መጠላለፍ አንዱ በሌላው ላይ መዝመት ሆኖ ይስተዋላል። ታላቅ ታሪካዊ ስህተት ሆኖም እየተጓዘ ይገኛል። የአንዲት ትልቅና ገናና ሁና የኖረች የተከበረች ሀገር የኢትዮጵያ ልጆች ይሄን ሊሰሩ አይገባም ነበር።

በጋራ ቆሞ ሀገር መጠበቅ ማገልገል ለሀገር መስራት ሲገባ የአንድ እናት ልጆች እንዲህ እየተባሉ ሀገራቸውን ለማጥፋት በእልህና በቂም በቀል ታጅበው ሲራወጡ ማየት በእጅጉ ያሳዝናል። እንደ ሀገርም አንገት ያስደፋል። ሲዘራ የነበረው ልዩነትን የማግዘፍ ፖለቲካ ሀገርን ማጥ ውስጥ ከቷል። ልዩነት ውበትና የጥንካሬ ምንጭ እንጂ ለመጠፋፋት በር የሚከፍት መሆን የለበትም። ያለፈው አልፏል፤ አንበታተንም፤ አንለያይም።

ለጠቀስኳቸውም ሆነ ሌሎች ችግሮችን ይፈታል የተባለው ኢሕአዴግ ወደ አንድ ውሁድ ጠንካራ ብሔራዊ ፓርቲነት ለመለወጥ የጀመረው መንገድ ይደገፋል፤ ይበረታታልም። በአንድ ወጥ ፓርቲ ውስጥ ዜጎች አገራዊ ሆነው በፖለቲካ እምነታቸውና አስተሳሰባቸው የሚደራጁበት፤ የሚሰባሰቡበት፤ ሀገርን ለማልማትም ሆነ ከችግር ለማውጣት በጋራ የሚመክሩበት፤ በብቃትና ችሎታው የሚሰሩበት ክልልና ወሰን የማያግዳቸው በመሆኑ ኢሕአዴግ ወደዚህ ደረጃ መሸጋገሩ እሰየው የሚያሰኝ ነው። ታላቅ ድልና ውጤትም ነው።

የፓርቲው ውሁድ ሁኖ በአንድ ሀሳብ፤ በአንድ ጉልበት፤ በአንድ አስተሳሰብ መቆም ሀገርን ከጥፋት ከቀውስና ችግር ይታደጋል የሚለው ተስፋ የጠነከረ ነው። ሌሎች ተመሳሳይ ሁለትና ሶስት ብሔራዊ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ርእዮተ አለማዊ የመስመር ልዩነታቸውን ይዘው ቢፎካከሩ ለሀገርም ይበጃል። የተለዩ አስተሳሰቦች መኖራቸው የሚደገፍ እንጂ የሚነቀፍ አይሆንም። አንዱ የሀገሪቱን መሰረታዊ ችግር ያባባሰውና ዛሬ ላለንበት አስቸጋሪ የፖለቲካ ሁኔታ ያበቃን የጋራ የምንላቸው የአብሮነት እሴቶቻችን እየተናዱ መሄድ ነበር። አሁን ፈጥኖ ማረቅ ይገባል።

ኢሕአዴግ በውስጡ አራት በብሔር የተደራጁ ድርጅቶች እንዲሁም አምስት አጋር ፓርቲዎች ይዞ 27 ዓመታት መጓዙ ይታመናል። ለምን ሌሎቹ አጋር የተባሉት ‹‹በእህት ፓርቲነት›› አልተደራጁም? የሚለው ጥያቄ ‹‹የፖለቲካዊ ሴራና ደባ አይነተኛ መገለጫ ነው›› የሚሉ በርከት ይላሉ።

በዚህ ጉዳይ ዝርዝር መረጃ ስለሌለ ብዙም አልገፋበትም። ነገር ግን ዋናው ቁም ነገር አጋር ፓርቲዎቹ ፍጹም ኢትዮጵያዊ ሁነው ሳለ በሀገራቸው ጉዳይ ‹‹አጋዥ ወይም ተባባሪ እንጂ፤ ባለቤት አይደላችሁም፤ አይመለከታችሁም›› የሚል አካሄድ እንደነበረ በግልፅ ያሳያል። በመሆኑም ይሕ ዛሬ የሚፈለገው ውህደት ይሕን ችግር አስቀርቶ አጋሩንም እህት ፓርቲውንም እኩል መብት ያጎናፅፋል፤ እኩል አገራዊ ግንባታንም ተካፋይ ያደርጋል።

አጋር ፓርቲዎቹ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን እንዲሁም ሰፊ የጂኦፖለቲካዊ መልክአ ምድርን ቢይዙም በሀገራቸው ጉዳይ ባይተዋርና ገለልተኛ መደረጋቸው የዛኑም ያህል የተፈጥሮ ሀብታቸውን ሌሎች ሲቀራመቱና ሲከብሩበት መኖሩ ይህ ‹‹የግንባር ፖለቲካዊ ካባ›› ሊወድቅ እንደሚገባው በግልፅ ያሣያል። አምናና ካቻምና ያየነው ሀቅ ነው። ይህ አካሄድም ከፋፍሎ ለመያዝ የተቀየሰ አካሄድ እንደነበር አይካድም።

27 ዓመት በዚህ መልክ በዋነኛ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ባለቤቶች ሆነው ሳለ አጋር ናችሁ እየተባሉ በገለልተኝነት ይታዩ የነበሩትን ወደ ውህዱ ፓርቲነት መቀላቀል ታላቅ ውጤት ነው። እነሱም ‹‹በሀገራችን ጉዳይ ሙሉ የመወሰን መብት አለን›› የሚል ፅኑ አቋም ይዘው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ። ነገ ከእነሱም ውስጥ የሀገር መሪ ሊወጣ እንደሚችልም ተስፋ ሰንቀዋል።

በኢትዮጵያ መልክአ ምድራዊ ክልል ያሉ ዜጎች ሁሉ የሀገራቸው ጉዳይ ባለቤቶች ናቸው። ይመለከታቸዋል። ይህ ሁኔታ እንዲሻሻል እንዲቀየር አጋር ድርጅቶች በሀገራቸው ጉዳይ ወሳኝ ኃይልና ጉልበት ሁነው እንዲሳተፉና እንዲሰሩ በተደጋጋሚ በኢህአዴግ ጉባኤዎች ሲጠየቅ የከረመ ጉዳይ ነው። ዛሬ ጊዜ እየፈታው ይመስላል። በአምስተኛውና ከዚያም በኋላ በነበሩ ጉባኤዎች መነሳቱን አጋር ድርጅቶቹ ሳይቀሩ ያስታውሳሉ።

ኢሕአዴግ ከግንባርነት ወደ ውህደት አምርቶ አንድ ብቁና ጠንካራ ብሔራዊ ፓርቲ ሁኖ እንዲሰራ ለበርካታ ዓመታት ሲወተወት ሲነገርም ቆይቷል። በተለይ መቀሌ በተካሄደው አስረኛው የድርጅቱ ጉባኤ ላይ በስፋት ተነስቷል። ‹‹ግዜው ገና ነው›› በሚል የተቃወሙም ነበሩ። ኢህአዴግ ወደ ውሁድ ፓርቲነት ለመለወጥ በጣም ዘግይቷል። ጥቅሙ ሁሉም በእኩልነት በብቃቱና በችሎታው የሚመዘንበት ከጎሳ ኃላቀር አስተሳሰብ የሚወጣበት በጋራ ለሀገሩ የሚያስብበት፤ ልዩነቱን አቻችሎ ተጋግዞ ተከባብሮ የሚኖርበትን ሁኔታ ይፈጥራል የሚል ትልቅ ተስፋ ተጥሎበታል። ይህን ተምሳሌታዊ ተግባር በአገር ውስጥ ያሉ ከ100 በላይ ፓርቲዎች ሊጋሩት ይገባል። ተሰብሰቡ፡፡ አትበተኑ፡፡

አዲስ ዘመን ጥቅምት 6/2012

ወንድወሰን መኮንን