ግጭቶች በሚፈለገው ልክ ለምን መቆም ተሳናቸው?

15

በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚነሱ ግጭቶች መቋጫ ያለማግኘታቸው ጉዳይ ‹‹ያልተመለሱ የህዝብ ጥያቄዎች ስላሉና መንግሥትም ህግ የማስከበር አቅም አጥቶ ነው›› ብለው ለሚገልፁ አንዳንድ ወገኖች ግጭት ከመንግሥት አቅም በላይ ሆኖ በሀገሪቷ ሰላም ጠፍቷል የሚያስብል ደረጃ ላይ የደረሰ ግጭት አለመኖሩን ከግጭት ጋር በተያያዘ ሳይንስና ህግን መሰረት በማድረግ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በሰላም ሚኒስቴር የግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያ ምላሽና ዘላቂ መፍትሄ ዳይሬክቶሬት ጀነራል አቶ ምግባሩ አያሌው እንደሚያስረዱት ግጭትና ሰላም የሚቃረኑ ግን አብረው የሚኖሩ ናቸው።ግጭት ተፈጥሯዊም ነው።ነገር ግን ግጭትን ከሰላም መለየት ያስፈልጋል የሚሉት ዳይሬክተሩ ግጭት እንደሸቀጥ መታየት እንደሚችል በማስረዳት ነው።

ግጭት ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ ቦታ ይመጣል (ኢምፖርት) ይደረጋል የሚሉት አቶ ምግባሩ ከግጭት ትርፍ የሚፈልጉ ወይም እንደ ሥራ የተያያዙት አካላት ‹‹ኢንተርፕሪነር›› ግጭት ፖለቲካዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ሌላም ይዘት እንዲኖረው በማድረግ የሚሳተፉበት መሆኑን አፅንኦት በመስጠት ያስገነዝባሉ።

ግብ የሚያደርጉትም በሚፈጠረው ግጭት በማህበረሰብ ውስጥ አለመግባባት መፍጠር፣ በተለይ ደግሞ የፖለቲካ አክቲቪስቶች መንግሥትን በማጣደፍ፣የተሳሳተ መረጃ በማሰራጨት ስሜታዊ ማድረግ፣ እንዲሁም ጉዳት እንዳለውና ሰላም እንደሌለ አድርጎ ማራገብ፣መገናኛ ብዙሃንም አጀንዳቸው እንዲያደርጉት ማድረግ ከብዙ በጥቂቱ የሚገለፁበት ነው ብለዋል።

አቶ ምግባሩ እንዳብራሩት ሰላም አብሮ ከመኖር፣ከማህበረሰብ ታሪክ እና እሴት ጋር የተያያዘ በመሆኑ ግጭት በተፈጠረበት ፍጥነት እንኳን ማህበረሰቡ ሲገነዘበውና ባቆየው እሴት ትርጉም ባለው መልኩ ይፈታዋል። ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ ውስጥ የሚስተዋለው ግጭት፤ ‹‹ግጭት የሚፈልጉ ኃይሎች ፍላጎት እየተሳካ ነው፤በሀገሪቷ ውስጥ ሰላም የለም›› የሚያስብል ደረጃ ላይ አልደረሱም ሲሉ ይከራከራሉ። ግጭቶቹም ጊዜያዊ እንደሆኑና ማህበረሰቡም እየተከላከላቸው እንደሆነ ያስረዳሉ።በአፍሪካ ባለው ተሞክሮም በሰብአዊ መብት ጥሰት ካልሆነ በሰላም እጦት በዓለም ላይ የደረሰ ወቀሳም እንደሌለ አመልክተዋል።

በፌዴሬሽን ምክርቤት የግጭት አፈታትና የሰላም እሴት ግንባታ ዳይሬክተር አቶ አስቻለው ተክሌ እንደሚያስረዱት ግጭቶች ተፈጥሮአዊ ቢሆኑም ለተለያየ ፍላጎቶች ማራመጃነት እንደሚውል፣ በአግባቡ ተይዞ በወቅቱ ካልተፈታ ደግሞ መልኩን መቀየሩ፣ ሰብአዊ ቀውስ ማስከተሉና ዋጋም ማስከፈሉ አይቀሬ እንደሆነ ይናገራሉ።

‹‹ያልተመለሱ የህዝብ ጥያቄዎች አሉ›› በሚለው ሲመልሱ በቋንቋ የመማር መብት ተፈጥሯዊም ህገመንግሥታዊም ነው።ለእንዲህ አይነት ጥያቄ የአስተዳደር መዋቅሩ ምላሽ መስጠት የሚችል ከሆነ ሳይዘገይ መልስ መስጠት አለበት።በዚህ ረገድ ከታች እስከ ላይ ድረስ ባለው መዋቅር ውስንነት መኖሩን አረጋግጠዋል።

በአቅም ውስንነት አሊያም ሌላ ምክንያት ካለ ደግሞ ግልጽ በማድረግ ምላሽ መስጠት ይጠበቃል።ይህ ካልሆነ እየዋለ ሲያድር ጥያቄው መልኩን ቀይሮ ወደ ግጭትና ሰብአዊ ቀውስ ያመራል ሲሉ አቶ አስቻለው አስረድተዋል። ሆኖም ግን ተፈጠሩ የሚባሉት ግጭቶች ከመንግሥት አቅም በላይ አለመሆናቸውን አመልክተዋል።

በፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የህግ ጥናት ማርቀቅና ማጽደቅ ዳይሬክቶሬት የህግ ጥናት ቡድን አማካሪ አቶ ሳምሶን ተገኔ ጉዳዩን ከህግ አንጻር ይፈትሹታል።ግጭት ገዥ የሆኑ ምክንያቶችን ይዞ የሚነሳና ከኋላም በግፊት የሚታገዝበት ሁኔታ ያለው በመሆኑ ብዙ ሰውን የማሳተፍ ይዘት አለው።አቶ ሳምሶን ‹‹ህግን ጥሶ ከመጠቀም ህግን አክብሮ መጎዳት››የሚለውን አባባል ያሰምሩበታል።በግልም በቡድንም ኢኮኖሚያዊ ወይም የፖለቲካ ጥቅም ለማግኘት ሲንቀሳቀሱ መስተዋላቸውና የግጭት ግፊቱ እያየለ እየመጣ በማስመሰል ‹‹የኢትዮጵያ ህዝብ በውስጡ ተሳትፎ እየተጋጨ ነው›› ወደሚል የተሳሳተ ድምዳሜ የሚወስዱ አለመጥፋታቸውን አስገንዝበዋል።

አቶ አስቻለው እንዳስረዱት በመንግሥት በኩል ግጭትን መከላከልም ሆነ ሰላምን እያረጋገጡ ለመሄድ ህዝብን ያሳተፈ ሥራ እየተከናወነ ነው።የግጭት መንስኤዎችን አስቀድሞ በመለየት ምልሽ ለመስጠት የግጭት መከላከልና ሰላም ግንባታ ስትራቴጂ ተዘጋጅቷልም ብለዋል።

በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈጠሩ ግጭቶች ሰላም ማሳጣት ደረጃ ላይ የደረሰ አለመሆኑን የሚገልፁት አስተያየት ሰጪዎቹ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥና በህዝቦች መካከል የቆየው ማህበራዊ እሴት እንዲጎለብት አሁን እየተሰራ ካለው በበለጠ መጠናከር እንዳለበት ይመክራሉ።የሕዝብን ትክክለኛ ጥያቄ በወቅቱ መመለስ ከተቻለ ግጭትን መቀነስ ይቻላል፤ የህግ የበላይነትንም ማስከበር ከባድ አይሆንም ሲሉ አስተያየት ሰጪዎቹ ጠቁ መዋል።

አዲስ ዘመን ጥቅምት 6/2012

ለምለም መንግሥቱ