‹‹ፓራዳይዝ …ሙዚየምና ፓርክ›› ወጣቱን ያማከለ አዲስ ፕሮጀክት

12

በቅርቡ ለስራ ጉዳይ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባው ቢሮ እግሬ ደርሶ ነበር። ከስራ ሰዓቱ ቀደም ብዬ በመድረሴ ለእንግዳ ማረፊያ በተዘጋጁት አግዳሚ ወንበሮች ላይ አረፍ እንዳልኩ በወንበሩ ላይ ተቀምጠን የምክትል ከንቲባውን መምጣት እየጠበቅን ከባለጉዳዮች ጋር ስለጉዳያችን እያነሳን መነጋገር ጀመርን። በዚች ወቅት ከ‹‹ፓራዳይዝ ብሔራዊ የቡና ሙዚየምና ፓርክ›› መስራቾች ጋር ለመተዋወቅ እድል አገኘሁ።

ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር እና ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ላሏቸው መስሪያ ቤቶች ማድረሳቸውን እና እዚህ የመጡት ደግሞ ለምክትል ከንቲባው ለማስገባት መሆኑን አጫወቱኝ። የፕሮጀክቱ ባለቤት አቶ አስቻለው ካሳዬ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ባሌ ዞን ጊኒር ወረዳ በስማቸው የተሰየመ የስንዴና ገብስ መካናይዝድ እርሻ አላቸው። በዚህ ስራም ከአስር ዓመታት በላይ የዳበረ ልምድ እንዳላቸውም በቆይታችን ነግረውኛል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ አዳዲስ አስተሳሰቦችና እይታዎች ስር እየያዙ የመጡ ይመስላል። ወንዞቻችን ከመጥፎ ጠረን፣ ወጣቶቻችንን ደግሞ ከስራ አጥነት ማላቀቅ ካልቻልን ሀገር አያምርባትም። ስለዚህ ‹‹ለአንዲት ሀገራችን አንድ ይሁን ልባችን›› ብለው በተግባር ርብርብ ውስጥ እንደሚገኙ ይታወቃል። በመሆኑም የግል ባለሀብቱ የሀገሪቱን ወጣት በከፍተኛ ደረጃ ስራ ማስያዝ የሚችሉ አዳዲስ ሀሳቦችና እይታዎችን ይዞ መቅረብ መጀምሩን ከአቶ አስቻለው ፕሮጀክት መረዳት አያዳግትም።

‹‹ፓራዳይዝ ብሔራዊ የቡና ሙዚየምና ፓርክ›› አዲስ የኢንቨስትመንት ሐሳብ ያዘለ ፕሮጀክት ነው። ለወጣቶች ከሚያስገኛቸው የሥራ እድሎች ባሻገር ሀገራዊ ፋይዳውም ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም የሚሉት የፕሮጀክቱ ባለቤት አቶ አስቻለው፤ ቡናን በተወለደበት ሀገር ለዜጎቹ እንዲጠቅም ያደርጋል፤ ለቱሪስት መስህብነትም ከፍተኛ ፋይዳ ያበረክታል፤ በመሆኑም መንግስት እየተከተለው ያለውን የአረንጓዴ ልማት ስትራተጂ በመደገፍ በአዲስ አበባ ወንዝና የወንዝ ዳርቻ ተፋሰሶችን በተለያዩ የቡና ዝርያዎች ጫካዎችን ለማስዋብ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ ከሚያቅፋቸው በርካታ ተግባራት መካከል የተለያዩ ዝርያ ያላቸው የቡና ጫካዎች፣ ባህላዊ አዳራሾች፣ የቡና ቤተ መጽሐፍት፣ የቡና ዘር ባንክ፣ የእደ ጥበባት ማምረቻ ማዕከሎች፣ የቡና ታሪክ ሙዚየም፣ ባህላዊ ጎጆዎች፣ የሽያጭ ሱቆች፣ የመኪና ፓርኪንግ፣ ማማዎች እና ፋውንቴኖች ጥቂቶቹ ናቸው። ፕሮጀክቱም በርካታ ማህበራትና እስከ 30 ሺህ ለሚደርሱ ወጣቶች የሥራ እድል የሚፈጥር ሲሆን ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታልም የሚጠይቅ እንደሆነ አቶ አስቻለው ያስረዳሉ።

የፕሮጀክቱ አማካሪ አቶ ሙላት ታዘበው እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ ቡና የተወለደባት ሀገር ብትሆንም በቡና ዙሪያ በሰፊው ተሰርቶበታል፤ ሀገሪቱም ከዘርፉ የሚገባትን ያህል ተጠቃሚ ሆናለች ማለት አይቻልም። በመሆኑም ፕሮጀክቱ ለወጣቶች የስራ እድል ይፈጠርበታል፤ ለቱሪስቶችና ለጎብኝዎች የሀገሪቱን የቡና ሀብት ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ መረጃውን ከማደራጀት አንስቶ ባህላዊ ወግና የክዋኔ ስርዓቱን ጠብቆ የኢኮኖሚና የውጪ ምንዛሪ ምንጭ እንደሚሆን ያስረዳሉ።

አቶ ሙላት እንዳብራሩት፤ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን ባህል፣ ታሪክና አንድነት መሰረት ባደረገ ጥናት ከ300 እስከ 400 ካሬ ሜትር ላይ የሚያርፍ ‹‹ካልዲ ኢትዮ የቡና አለም አቀፍ ባንክ›› ይኖራል። በኢትዮጵያና በአለም አቀፍ ደረጃ በቡና ዙሪያ የታተሙ መጽሐፍቶች፣ ጥናታዊ ምርምሮችና የስልጠና ማንዋሎች፣ በድምጽና በምስል የተዘጋጁ ሙዚቃዎች፣ ፊልሞችና ዶክመንታሪዎች ጭምር በመልክ በመልክ ተሰድረው ለወጣቶች ልምድ መቅሰሚያነት ይውላሉ።

ከ250 እስከ 300 ካሬ ሜትር ላይ የሚሰራው ‹‹ከፋ ብሔራዊ የቡና ዘር ባንክ›› የተለያዩ የቡና ዝርያዎችን፣ የተለያዩ ጣዕም ያላቸው የቡና ፍሬዎችን፣ በምርምር የተደረሰባቸው የተሻሻሉ ምርት ሰጭ የቡና ዝርያዎችን ይይዛል። የቡና ፍሬዎችን ብቻ ሳይሆን ከቡና ታሪክ ባህልና እሴት ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ታሪካዊ ቁሶችንም ያቅፋል።

ከ15 እስከ 20 የሚደርስ ቁጥር ያላቸው የቡና የማምረቻ፣ መኮትኮቻ፣ መጠጫ፣ መልቀሚያ፣ ማጠራቀሚያ፣ ማጠቢያ፣ መቁያ፣ መውቀጫ፣ ማጨሻና ሌሎች ቁሳቁሶች የሚሰሩበት ባህላዊ የእደጥበባት ማምረቻ ማዕከላት የሚኖሩ ሲሆን በጥቃቅንና አነስተኛ ለተደራጁ ወጣቶች ከፍተኛ የገበያ ትስስርን የሚፈጥር ነው።

ባህላዊ ጎጆዎቹ ጥንታዊ የስነ ሕንጻ ጥበቦችን ተከትለው የሚሰሩ ሲሆን በዋና ቡና አብቃይ አካባቢዎች ስያሜ የሚሰጣቸው ይሆናል። በአካባቢያቸው የሚፈጠረው የቡና ጫካ እና በውስጣቸው ባህላዊ ወግና ስርዓቱን ጠብቆ የሚፈላው ቡናም ስያሜውን ከጎጆዎቹ ይወስዳል። ባህላዊ አልባሳቱ የተሰየመበትን አካባቢ ማህበረሰብ ይገልጻል፤ ያስተዋውቃል።

ለወጣቶች የሚኖረው የስራ እድል ሰፊ ነው። የሽያጭ ሱቆች ቡናው በተገኘበት አገር የሚሰየሙ ሲሆን ለአገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ቱሪስት በሚያመች መጠን የተቆላና ጥሬ ቡና ይቀርባል። ሌሎች ባህላዊ የእደ ጥበብ ውጤቶችም፣ ከቡና የሚዘጋጁ ቸኮሌቶች፣ ከረሜላዎች፣ ማስቲካዎች፣ ዳቦዎች፣ ምግቦችና መጠጦች፣ ቅባቶች ወዘተ ይሸጣሉ። የቡና ቴምብሮች፣ ስዕሎች፣ አርማዎች፣ መጽሐፍትና ሌሎችም የሚሸጡባቸው ሲሆን ብዛታቸው በቁጥር ከ15 እስከ 20 እንደሚያደርሱ አቶ ሙላት በዝርዝር ተናግሯል።

በአጠቃላይ ከላይ የተጠቀሰው ፕሮጀክት አዲስ የስራ ባህል የሚያስለምድ ከመሆኑም በላይ ወጣቶችን በሰፊው ማሳተፍን አላማው ያደረገ ነው። በመሆኑም በተለዩት እያንዳንዳቸው ሥራዎችና ፕሮግራሞች ብዙ ቁጥር ያለው ወጣት ስራ ይይዛል። ራሱን፣ ቤተሰቡንና ሀገሩን የሚጠቅም ይሆናል። በሌላ በኩል በግብርናው ዘርፍ በተለይም ቡናችን ከፍተኛ የቱሪዝም ምንጭ የሚሆንበትን ምቹ መሰረት የሚጥልበት ሊሆን እንደሚችል የሚጠበቅ ነው።

አዲስ ዘመን ጥቅምት 6/2012

 ሙሐመድ ሁሴን